Monday, 13 May 2019 00:00

“…ይህ ፍቅር መልክ አጣ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 “እኔ የምለው…“ድርጅቱን ከምስራቅ አፍሪካ ምናምነኛ እናደርገዋለን…”፣ “ከተማዋን ከአፍሪካ ምናምነኛ እናደርጋታለን…” ከማለት ለምን ዝም ተብሎ ሥራ አይሠራም! ሥራው ከተሠራ በኋላ... “ይኸውላችሁ፣ ከአፍሪካ ምርጡ ምናምን….” ማለት ይቻላል፡፡ እኔ የምለው…
ቆዩኝማ፣ እኛ ከአፍሪካ ‘አንደኛ፣ ምናምነኛ’ እስከምንሆን ሌላው አፍሪካ ቁጭ ብሎ ይጠብቀናል?! --”
                
           እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ያዋከቡት ነገር ምእራፍ አያገኝም
ፍቅሬ ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም
ወደድኩህ አበዛች ስገባ ስወጣ
ሊናድ ነው መሰለኝ ይህ ፍቅር መልክ አጣ
የምትል ዘፈን አለች፡፡ እናላችሁ… ብልጥነት በዛ፣ የጉልበት አራድነት በዛ፡፡ ለምን መሰላችሁ…ሁላችንም መታየት የምንፈልግ ሆነናል:: ሁላችንም በቴሌቪዥን መታየት፣ በሬድዮ መደመጥ የምንፈልግ ሆነናል፡፡ ሁላችንም መታወቅ ፈላጊ ሆነናል፡፡ ‘ሴሌብሪቲ’ ምናምን ከመሆን ጋር ፍቅር ወድቀናል … ወከባ የበዛበት ፍቅር! “እኔ ለመታየት እንዲህ መከራዬን ሳይ እናንተ አታዩኝም እንዴ!” ለማሰኘት ምንም የማይቀረው ወከባ፡፡
እኔ የምለው… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…“ጥግ የደረስኩ አራዳ ነኝ”፤ “ገዳም ሰፈርን በአውራ ጣቷ ያቆምኩ ነኝ”፤ “ነፋስ ስልከ ለእኔ ሀውልት ልትሠራልኝ ይገባት ነበር!” ምናምን ብሎ በድሮ አራድነት መሸለል እየበቃ ነዋ! አሀ… አራድነት በራሱ ‘ታድሷላ፡፡’ የሆነስ ሆነና ‘የትናንት አራድነት’ እና ‘የዛሬ አራድነት’ ቅብብሎሽ ሳናውቀው ተካሂዷል እንዴ! በቀደም የተበጫጨቀ ጂንስ ለብሰሽ ‘ዳውንታውን’ ስትሸልይ የነበርሽው ልጅ… ‘የኦሪጂናል ሱሪው መልክ’ እስኪጠፋ ድረስ ይህን ያህል ከምትበጫጭቂው አንደኛውን እኮ በብጥሌዋ ነገር መሄድ ይቻላል፡፡ እዚች ከተማ እንደሁ “ሊሆን አይችልም” የሚባል ነገር የለም፡፡ (እኛ ደግም አንድ ትንሽዬ ምልክት ትበቃናለች!)
“ሊናድ ነው መሰለኝ ይህ ፍቅር መልክ አጣ…” የሚያሰኝ… ‘አራድነት’ በዝቷል፡፡ (ዘንድሮ ቀሺም ብልጥነትም ‘አራድነት’ ሆኖ ተቸግረናል፡፡)
ስሙኝማ…‘አራድነት’ ከ‘ቃሪያ ሱሪ’ ወደተበጫጨቀ ጂንስ ሲሸጋገር፣ አእምሮ ከምን ወደ ምን ‘እንደተሸጋገረ’ ይጠናልንማ፡፡ ልክ ነዋ…ምናቸውም የማይጥሙ ነገሮች በዝተዋላ! እናላችሁ… ከተማችን ውስጥ የምናየው ‘የአራድነት እሽቅድድም’ ኮሜዲ ነገርም እየሆነ ነው፡፡ እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል … ለእኩል ሰዓት ያህል ሜኑውን እንደ ምናምነኛ ክፍል ባዮሎጂ መጽሀፍ ሲሸመድድ ቆይቶ በመጨረሻ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ለሁለት አንድ ተጋሚኖና አንድ አምቦ ውሀ አምጪልን…” እናላችሁ… የአንዳንዶቻችን ሽለላ እኮ ትንሽ ቀሸም ያለ ነው፡፡ እሷዬዋን ለምን ያሳቅቃታል! ደግሞላችሁ…ለሁለት አንድ ተጋሚኖ ለማዘዝ ሜኑውን ለማንበብ (የእውነት ‘ካነበበው’ ማለት ነው) እኩል ሰዓት የወሰደበት፣ ለሦስት አንድ ምንቸት አብሽ ለማዘዝ እኮ “የሆስፒታል ቀጠሮ አለብኝ…” ብሎ ፈቃድ መውሰድ ሊኖርበት ነው ማለት ነው፡፡
በቀደም ከፍስኩ በፊት አምስት የሚሆኑ አቅመ አዳም መሀል ላይ ያሉ የሚመስሉ ሰዎች፣ በሆነ ምግብ ቤት ሜኑዎች ይሰጧቸዋል:: እናላችሁ… ሜኑው ላይ የተመሰጡትን ያህል ሥራቸው ላይ የሚመሰጡ ከሆነ ‘ኮከብ ሠራተኛ’ ማለት ብቻ ሊገልጻቸው አይችልም፡፡
ታዲያላችሁ… አሳላፊዋ ከስንት ምልልስ በኋላ ትእዛዝ ይሰጣታል… “አንድ በየአይነቱና አንድ ተጋሚኖ… አንድ ትልቁን ውሀ…” በቃ፡፡ ‘ቁጠባ’ም ከሆነ አሪፍ ነው፡፡ ልጄ … ታጋሚኖ እንኳን በአቅሟ ዋጋዋ በፊት ሁለትና ሦስት ስፔሻል ክትፎ ይበላባት የነበረውን ሆናለች:: (የአሳላፊዋን ፈገግታ ብታዩት ራሱን የቻለ መጽሀፍ ይወጣው ነበር፡፡ “ሁለት የጾም ምግብ ለአራት እየበሉ ነው ይሄን ሁሉ ቦርጭ ያወጡት!” ምናምን ሳትል አልቀረችም! የምግብ ቤቱ ባለቤት የሆነ ‘ወይራ’ ነገር ቢሆን እኮ… አለ አይደል… “ምግብ ሳያዙ መቀመጥ ክልክል ነው…” ብሎ ሁለቱን ሊቀንሳቸው ይችል ነበር!)
እኔ የምለው… ይቺን ነገር ከዚህ በፊት አውርተናት ነበር … ሰውየው የሆነ ምግብ ቤት በራፍ ላይ ይለምናል፡፡ የምግብ ቤቱ ባለቤት… 
“ይሄኔ ትንሽ እንጨት ብትፈልጥ ኖሮ ለምግብ ገንዘብ ታገኝ ነበር” ይለዋል፡፡
የእኔ ቢጤው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“መጀመሪያ የምግብ ዝርዝራችሁን ልየውና እፈልጣለሁ” አለና አረፈው፡፡
“ሊናድ ነው መሰለኝ ይህ ፍቅር መልክ አጣ…” የሚያሰኝ… ‘አራድነት’ በዝቷል፡፡ (ዘንድሮ ቀሺም ብልጥነትም ‘አራድነት’ ሆኖ ተቸግረናል፡፡)
ደግሞላችሁ… ይሄ የፈረደበት ዩቲዩብ ምናምን እየለቀቀብን… አለ አይደል… የፊልም ተዋናይቷ እከሊትን፣ ራፐሩን እንትናን ለመሆን መከራውን የሚበላ መአት ነው፡፡ እናላችሁ… ስለ ውጪ ነገር ካነሳን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… በቃ “ከአሜሪካ በመጡ መምህራን”፣ “ከህንድ በመጡ ሀኪሞች”፣ “ከጀርመን በተገኘ ልምድ” የሚሉ ነገሮች ደረት የሚያስነፉ ነገሮች ሊሆኑ ነው! አሀ...ሌላ ጊዜ “ከአሜሪካን በመጡ…” ምናምን አይነት ማለሳለሻ የምትነግሩን … አለ አይደል… ይህን ያህል ቀና አትበሉማ! ቢያንስ፣ ቢያንስ አንገታችሁን በትንሹ ሰበር አድርጉልንማ! የምር ግን…‘የውጪ ሰዎች’ አምልኳችን ልኩን አልፎ፣ መስመሩን አልፎ፣ የሚያልፈውን ነገር ሁሉ አልፎ … “እግዚኦ!” የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው፡፡
እኔ የምለው…“ድርጅቱን ከምስራቅ አፍሪካ ምናምነኛ እናደርገዋለን…”፣ “ከተማዋን ከአፍሪካ ምናምነኛ እናደርጋታለን…” ከማለት ለምን ዝም ተብሎ ሥራ አይሠራም! ሥራው ከተሠራ በኋላ... “ይኸውላችሁ፣ ከአፍሪካ ምርጡ ምናምን….” ማለት ይቻላል፡፡ እኔ የምለው…ቆዩኝማ፣ እኛ ከአፍሪካ ‘አንደኛ፣ ምናምነኛ’ እስከምንሆን ሌላው አፍሪካ ቁጭ ብሎ ይጠብቀናል!
ደግሞላችሁ…“እንዲህ፣ እንዲህ ለማድረግ በቁርጠኝነት ተነስተናል…” የሚባል ነገር አለ፡፡ የምን “በቁርጠኝነት መነሳት”፣ የምን “መታጠቅ” ምናምን ነው፡፡ አሀ…. ሁሉም ደሞዝ የሚነጭበትን ሥራ ይሥራ! የምር ግን…የሆነ ነገር ላይ ቅጽል፣ ተውሳከ ምናምን ሲበዛ “ይቺ ነገር፣ ቲራቲር ነች…” ያሰኛል፡፡ ‘ቲራቲር’ ሆነው የቀሩ ብዙ ነገሮች አሉዋ!
እኔ የምለው… በሀርሞኒካ በቀላሉ በአውላላ ሜዳ ላይ ያልቅ የነበረ ሁሉ አሁን ጊዜ ተለወጠና በአራጣ ብድርም ላይሳካ ይችላላ፡፡ “ዝቅተኛው የመኪና ዋጋ ሚሊዮን በገባና እንትናዬዎቻችንን ባየን!” ምናምን ስትል የነበርከው ወዳጃችን… ከጊዜው ጋር ሂድ እንጂ! ለአንተ ሚሊዮን ማለት አሁንም  የህንድ ህዝብ ቁጥር የሆነ እንደሁ፣ ለሌላው ሚሊዮን እኮ ለሰው አበድሮት የሚረሳው ነው፡፡
“ስማ… ያ ወዳጃችን ቅልጥ ያለ ሀብታም ሆነ አይደል?”
“ማንን ነው ምትለው?”
“ያ የኤን.ጂ.ኦው ወዳጃችን…”
“እና አሱ ምን ሆነ?”
“ምን ሆነ ትለኛለህ! ቅልጥ ያለ ሀብታም ሆኗል ነው እኮ የምልህ! አንድ ሚሊየን ብር አያጣም ነው የሚባለው፡፡”
“(ሳቅ) ሚሊየን! ሚሊየን ነው ያልከው? በአንዲት ሚሊየን ብር ነው ሀብታም የሚሆነው!”
“አንድ ሚሊየን ትንሽ ነው ልትል ነው?!”
“አንድ ሚሊየን እኮ ጓደኞች ሰብሰብ ብለው የሚጥሉት የሳምንት እቁብ ነው፡፡”
እናላችሁ… ሚሊየን እንዲህ የቀለለችበት ዘመን ሆኖላችኋል፡፡ ስሙኝማ… ይሄ በየሁለትና በየሶስት ቀኑ “ሊሾልክ ሲል ተያዘ…” ስለሚባለው የኮንትሮባንድ እቃ ብዛት ስትሰሙ… አለ አይደል… ሳይነቃበት ስለሚያልፈው ብዛት አስባችሁ አታውቁም!  የምር ግን… አለ አይደል…ፍራንክን በተመለከተ ሚሊየን እንዲህ ትንሽዬ ቁጥር ትሁን! (እንትና…ምናልባት ለ‘አክቲቪስትነት’ እንደ አጀንዳ የሚጠቅምህ ከሆነ… ‘ክላስ ሪቮሊሽን’ ምናምን ያሰጋን ይሆን እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…)
“ሊናድ ነው መሰለኝ ይህ ፍቅር መልክ አጣ…” የሚያሰኝ… ‘አራድነት’ በዝቷል፡፡ (ዘንድሮ ቀሺም ብልጥነትም ‘አራድነት’ ሆኖ ተቸግረናል፡፡)
እኔ የምለው… አዲስ አበባ ለኖህ ዘመኖቹ ሶዶምና ገሞራ ‘እህት ከተማ’ ሆናለች እንዴ! እኛም ግራ ገባን፤ እሷም እንደ እነሱው ልትሆን ምንም አልቀራት፡፡ እንደ ፍጥነታችን እኮ… አለ አይደል … አምስተኛ ማርሽ የመጨረሻው ቀርፋፋ ይሆናል፡፡ ብልጥነቱንና ‘አራድነቱን’ ቀንሶልን ብስለቱንና ብልህነቱን ያብዛልንማ!
 ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1945 times