Print this page
Monday, 13 May 2019 00:00

“ስለ ልብ ስትሉ ልብ ብላችሁ አድምጡን”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 - ዋና ትኩረቶቻችን ህፃናት ታካሚዎቻችን ናቸው
          - ለአንድ የልብ ቀዶ ጥገና ከ15-18 ሺ ዶላር ያስፈልጋል
          - በወር እስከ 30 ህፃናትን ማከም እየቻልን፣ በችግሩ ምክንያት 8 ብቻ ነው የምንሰራው
          - “ወላጆች፤ ልጆቻቸው ቶንሲልና ሌላ የመተንፈሻ አካል ችግር ሲኖርባቸው በደንብ ማሳከም አለባቸው”
          - የሚድኑትን ልጅ በማሰብ እኛ ብንጐዳና ብንታመም ምንም አይደም


              በዶ/ር በላይ አበጋዝ መስራችነት በ “1 ብር ለ1 ልብ” ዘመቻ፣ በህብረተሰቡና ባለሀብት ድጋፍ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የልብ ህክምና ማዕከል፤ ባለፉት ዓመታት ወደ 5 ሺህ የሚጠጉ ህፃናትን ልብ በቀዶ ህክምና አድኗል፡፡ ቀደም ሲል በውጭ አገር ዶክተሮች ብቻ ይከናወን የነበረው የልብ ቀዶ ህክምናው፤ ዛሬ በዘርፉ በሰለጠኑ በ11 ኢትዮጵያውያን የልብ ህሙማን ስፔሻሊስቶች እየተሰጠ ነው፡፡ ሆኖም ማዕከሉ የራሱ ቋሚ ገቢ ስለሌለው ከአቅሙ በታች እየሰራ መሆኑን የልብ ህክምና ስፔሻሊስቷና የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሄለን በፍቃዱ ይናገራሉ፡፡ “በወር እስከ 30 ህፃናትን ኦፕራሲዮን የማድረግ አቅም ቢኖረንም በችግሩ ምክንያት በወር 8 ህፃናትን ብቻ ነው የምናክመው” ያሉት ሃኪሟ፤ ህፃናቱን የምናድንበትን መንገድ በጋራ እንፈልግ ሲሉ ለመላው ኢትዮጵያውያን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በልብ ህክምና ማዕከሉ ተግዳሮቶችና በልብ ህመም ዙሪያ ዶ/ር ሄለን በፍቃዱን አነጋግራለች፡፡  


            መቼ ነው ወደ ልብ ህክምና ማዕከሉ የመጡት? ከዚያ በፊትስ?  
ያው በሙያዬ የልብ ፅኑ ህሙማን ስፔሻሊስት ነኝ፡፡ በልብ ህሙማን ሆስፒታሉ በሜዲካል ዳይሬክተርነትም በማገልገል ላይ እገኛለሁ፡፡ ብዙ ጊዜዬን ያሳለፍኩት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በትምህርት ላይ ነው፡፡ የልብ ህክምና ሆስፒታሉን የተቀላቀልኩት ከሶስት ዓመት ወዲህ ነው፡፡ ይህን ሆስፒታል በተቀላቀልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለትምህርት ወደ ውጭ ተልኬ በግብጽ፣ በእንግሊዝና በካናዳ ሶስት ቦታዎች ትምህርት ስከታተል ቆይቼ፣ ከተመለስኩኝ ቢበዛ አራት ወር ቢሆነኝ ነው፡፡
የልብ ህክምና ላይ ለመስራት ፍላጐት ያደረብሽ እንዴት ነው? የተለየ ምክንያት አለሽ?
እውነት ለመናገር ይህንን ማዕከል የተቀላቀልኩት ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ነው፡፡ ያኔ ከቤተሰብም ከሚዲያም ስለዚህ ማዕከል እንሰማ ነበር:: የፋውንዴሽኑና የልብ ህክምና ማዕከሉ መስራች ሁላችንም የምናውቃቸው ዶ/ር በላይ አበጋዝ፣ ያን ጊዜ እያለቀሱ ህዝቡን ሲለምኑ፣ ማዕከሉ እንዲገነባና የህፃናቱ ህይወት እንዲተርፍ ሲማፀኑ እንሰማ ነበር:: ቤተሰብም አንድ አንድ ብር አዋጡ እየተባለ ነው ብለው ሲያወሩ፣ ለትራንስፖርት ከሚሰጠን፣ ለሻይም ከምናገኘው እያሰባሰብን የምናደርጋት ነገር ሳላስበው ልቤ ውስጥ የቀረ ይመስለኛል፡፡ እናም ሀይስኩል እያለን “ምን መሆን ትፈልጊያለሽ?” ስባል፤ ሌላው ዶክተር ወይም ኢንጂነር ነው የሚለው፤ እኔ ግን የልብ ሀኪም መሆን እፈልጋለሁ ነበር የምለው:: ዓላማዬም የልብ ሀኪም መሆን ብቻ ሳይሆን አንድ ቀን እዚህ ቤት ገብቼ አገለግላለሁ የሚል ነበር:: የፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ እዚህ እንድገኝ አድርጐኛል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያው የበኩሌን አስተዋጽኦ አበርክቼ ለማለፍ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡
ይህንን ሆስፒታል ስትቀላቀይ በዋናነት የሆስፒታሉ ፈተና ምን ነበር?
እዚህ ማዕከል ስገባ፣ የአላቂ እቃና የመድሀኒት እጥረት ችግር ይስተዋል ነበር፡፡ አሁንም ያ እጥረት እየተባባሰ እዚህ ደርሷል፡፡ ይህ እንግዲህ የታካሚው ቁጥር እየበዛ ሲሄድ በዛው ልክ የመድሃኒቱና የአላቂ እቃው ቁጥር ካልጨመረ፣ ያው ችግሩ በስፋት እንደሚከሰት ግልጽ ነው፡፡ ህሙማኑ በአንድም በሌላም መንገድ ስለ አገልግሎቱ ሲሰሙ በርካታ ታካሚዎችን ማስተናገድ ስንጀምር እቃው መድሀኒቱ እያነሳ እየመጣ ነው አሁን ላይ የደረሰው፡፡ ይሄ እንግዲህ ማዕከሉ የራሱ ቋሚ ገቢ የሌለው በመሆኑ የመጣ ችግር ነው፡፡ ያኔም ገና እዚህ ማዕከል እንደመጣሁ፣ ማዕከሉ የቀጣዩን ወር ደሞዝ ለሰራተኛ እንዴት አድርገን ነው መክፈል የምንችለው እየተባለ የአስተዳደር ሰራተኞቹ ሲጨነቁ እሰማ ነበር፡፡
እንደነገርኩሽ ገና ከመቀላቀሌ ወዲያው ለትምህርት ብላክም፣ የቤቱን ህመምና ችግር በልቤ ይዤው ነበር የሄድኩት፡፡ ለእረፍት ስንመጣም ባለችን አጭር ቀናት አገልግሎት እንሰጥ ነበር:: ብቻ ያለፉትን ሶስት አራት አመታት በትምህርት ስላሳለፍኩ፣ እዚህ በቅርበት ሆኜ ተቸግሬያለሁ ማለት አልችልም፡፡ ባለፈው ዲሰምበር ወር ነው ሁሉንም አጠናቅቄ ጨርሼ እንደገና ወደዚህ የተመለስኩት፡፡ ሜዲካል ዳይሬክተር ሆኜም ማገልገል ከጀመርኩ ገና ሶስት ወር ከምናምን ገደማ ቢሆነኝ ነው፡፡
ያለ ደሞዝ  ነው የምትሰሪው የሚባለው እውነት ነው?
እንደዚያ አይደለም፡፡ አንዳንዴ መልዕክቶች ሲተላለፉ ሰዎች በሀዘኔታና በስሜት ውስጥ ሆነው ሲያዳምጡ የመልዕክቶቹ አደራረስ ትንሽ ይለያያሉ:: ምናልባትም ሰሞኑን ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባደረግነው ውይይት ያነሳሁት ምንድነው፣ ልብ ማዕከል የሚሰራው ሰራተኛ የሚጠይቀው ስለደሞዝ ጭማሪ አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ በዲዩቲ (የማታ ተረኛ ስራው) ታክስ ይቆረጥበታል አይደለም፡፡ እኔ ደሞዝ የማይከፈለው የጤና ባለሙያ ነው ያለው ስል… ምን ማለት ነው?
ለምንሰራው ሥራ ተመጣጣኝ ደሞዝ አይከፈለንም ለማለት ይሆን?
ከራስ ጋር የሚመጣጠን ደሞዝ የእኛ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ያለ ችግር በመሆኑ ያኔ የትኛውም ሀኪም ጥያቄውን በሚያነሳ ጊዜ እኛም እንጠይቃለን:: አሁን ላይ እውነት ለመናገር የእኛ ዋነኛ ችግርና ቅድሚያ የምንሰጠው ለታካሚ ልጆቻችን ነው አንገብጋቢ ችግራችን የልጆቻችን ጉዳይ ነው ነው ያልኩት፡፡ አሁንም እንዲታወቅልኝ የምፈልገው እርግጥ ነው ለሰራተኞች ዋና ዋና መሰረታዊ ነገር መሟላት አለበት፡፡
ለምሳሌ ምን ምን?
ለምሳሌ ደሞዝን በሚመለከት መንግስት በሚከፍልበት ስኬል መሰረት ባልወረደ መልኩ እንዲሟላ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን አሁንም እኛ ትኩረታችንና ጥረታችን ማዕከሉ የሚሻሻልበትንና አቅሙ የሚችለውን ያህል ማከም የሚችልበትን መንገድ ማግኘት ነው፡፡ ማዕከሉ ሲሻሻልና ሲለወጥ ሰራተኛውም የተሻለ ነገር ይኖረዋል:: ማዕከሉ በመድሀኒት እጥረትና በአላቂ እቃ እጥረት ችግር ውስጥ ሆኖ ህፃናት ህሙማን በጊዜ ህክምና እንዳያገኙ ተግዳሮት እየገጠመን ባለበት በዚህ ወቅት አስቀድመን ስለደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ብናነሳ እንዴት ነው ጥሩ ስሜት አይሰጥም፡፡ ለምን ደሞዛችን ተጨምሮ እኛ ደልቶን ግን ከአቅም በታች ስናክም በወቅቱ መታከም ያለባቸው ልጆች ሳይታከሙ ለሌላ ተጨማሪ ህመም እየተዳረጉ ማን ደስተኛ ይሆናል? ለተጨመረልን ደሞዝ የሚመጥን ሥራ ለመስራት እንቅፋት እያለ የደሞዝ ጭማሪ አያስደስትም፡፡ ስለዚህ ይህን በመሰለ ጥሩ መድረክ ዋናውን የልጆቻችንን ጉዳይ ዘንግተን የራሳችንን ጥቅም መልዕክት አስተላልፎ መውረድ አግባብ አይደለም፡፡ ዋና ጉዳዮቻችን ዋና ትኩረቶቻችን ህፃናት ታካሚዎቻችን ናቸው፡፡ በታካሚዎቻችን ምንም ድርድር የለም፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ግን ማዕከሉ ቋሚ ገቢ ስለሌላው ከሚያገኛት ትንንሽ ገንዘብ እየቀነሰ ደሞዝ ይከፍላል ይሄ በቂ ባለመሆኑ ቀጣይ ጥያቄያችን ይሄው ይሆናል ማለት ነው፡፡
ታዲያ አሁንስ ማዕከሉ የሚንቀሳቀስበት ገቢ ከየት ነው የሚመጣው?
እንደሚታወቀው ይሄ የልብ ህክምና ማዕከል ህዝባዊ ተቋም እንጂ መንግስታዊ ተቋም ስላልሆነ ቋሚ በጀት የለውም፡፡ ከአመሰራረቱ ጀምሮ ብንመለከት፣ በህዝብና በግለሰብ ጥረት ነው የተመሰረተው፡፡ ህዝብ አምጦ ህዝብ የወለደው ጤናማ ተቋም ነው፡፡ በህዝቡና በአንዳንድ ለጋሾች በሚገኝ ገንዘብ እየተደገፈ ላለፉት 10 ዓመታት ለኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል:: ወደ 5ሺህ የሚጠጉ ህፃናት ያለ አንድ ብር ክፍያ ታክመው ድነው ሲቦርቁ እንደማየት የህሊና እርካታ ከየት ይገኛል፡፡ ለዛም እኛ የህፃናቱ ችግር ቀድሞ ሲገለጽና መፍትሔ ሲመጣ እርካታችን ስለሚጨምር እንድንበረታና ይበልጥ እንድንሰራ ያግዘናል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ደሞ ወደ ሌላው የግል ጥያቄ እናመራለን፡፡
የማዕከሉ መሰረታዊ ተግዳሮት የሆኑት መድሃኒቶችና አላቂ እቃዎች ምን ምን ናቸው? ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ አገልግሎቱን ለመስጠትና ጥሩ ህክምና ለማቅረብስ በዓመት ምን ያህል ገንዘብ ያስፈልገዋል?
ቀለል አድርገን ለመግለጽና ህዝቡም እንዲረዳው ለማድረግ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በማዕከሉ ከ4ሺህ 800 በላይ አብዛኞቹ ህፃናትና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው አዋቂዎች ታክመዋል፡፡ ይህንን ሥናይ ከውጭ በሚሽን በሚመጡና በአገር ውስጥ የህክምና ቡድን ታክመው የዳኑ ናቸው፡፡ ማዕከሉ በአማካኝ በዓመት ውስጥ ከ300-450 ቀዶ ህክምና ማድረግ ይችላል:: እርግጥ ከዛም በላይ የመስራት አቅም አለው፤ ነገር ግን ያለውን ሁኔታ በመገንዘብ በትክክልና በጥራትም መስራት ስለሚያስፈልግ ቁጥር ብቻ መደርደርም ተገቢ ስላልሆነ፣ በትክክል ከላይ የገለጽኩትን ያህል ታካሚ የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ ምናልባትም በወር ብናካፍለው ከ30-40 ሰው ያስተናግዳል:: በወር አራት ሳምንት አለ፤ በአማካኝ በሳምንት ሰባት ሰው ኦፕሬሽን ቢሰራ ይሄ ትክክለኛ አቅሙ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ህክምና በሌላ በአገር ውስጥ የግል ተቋምም ስለማይሰራ፣ በህንድ አገር በተወሰደ ጥናት ያልኩት፣ ሰው አገር ውስጥ የማይፈታ ችግር ሲገጥመው አቅም ያለውም ሆነ አቅም የሌለውም ተበድሮ ሄዶ የሚታከመው ህንድ ነው፡፡ በተመጣጣኝ ክፍያ የህክምና አገልግሎት የሚገኘው ህንድ ስለሆነ ማለቴ ነው፡፡ እነ ባንኮክና እነ ዱባይን አንጠቅስም፤ በጣም ውድ ናቸው፡፡ ስለዚህ ህንድ አንድ የልብ ቀዶ ጥገና ለማድረግ ከ15-18 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል፤ ይሄ ዝቅተኛው ነው፡፡ የአውሮፕላን ትኬት፣ የሆቴል ወጪና ሌላውም ወጪ እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡ ይህንን ከ15-28 ሺህ ዶላር አሁን ባለው ምንዛሬ ማባዛት ነው፡፡ አሁን በባንክ ምንዛሬ እንኳን ከ28 ነጥብ ምናምን በላይ ነው፤ ይሄን አስይው፡፡ ለአንድ ህመምተኛ ከ15-18 ሺህ ዶላር ያስፈልጋል:: እኛ በዓመት ከ300-450 ኦፕሬሽን የመስራት አቅም አለን፡፡ ይሄንን ስናባዛው የሚመጣውን ገንዘብ ማስላት ነው። አንድ ተቋም ወይም ግለሰብ “እኔ እስኪ ለአንድ ዓመት ለሚታከሙ 300 ህፃናት ልሸፍን” ቢል ሂሳቡና ስሌቱ አሁን የገለፅኩልሽ ነው:: የታከሙት ልጆችም ገና ወደ እኛ ሲመጡ ጀምሮ ተሰርቶላቸው፣ ክትትል እየተደረገላቸው፣ በግልፅ የተቀመጠ ተአማኒነት ያለው ዶክሜንት ስላላቸው ያንን ማቅረብ የምንችልበት ፕሮፌሽናል አሰራር አለን፡፡ ማቅረብ እንችላለን፡፡ ድጋፍ ለማድረግ ለሚፈልግ ሰው ለመንገር የሚቀለውም ይሄ መንገድ እንጂ የተወሳሰበ ሲሆን ትልቅ መስሎ ይታይና ያ ሰው እንዴት ይሄን ሁሉ እችላለሁ ብሎ የመሸሽና ያለመበረታታት ስሜት ውስጥ ይገባል፡፡
ስለ አላቂ እቃና መድሃኒቶቹ ጉዳይ እናውራ?
የልብ ህክምና በባህሪው መድሃኒቱ ውድ ነው:: እንዳለመታደል ሆኖ አገር ውስጥም አይገኝም:: አሁን አሁን እንደውም ትንሽ ይሻላል፡፡ ከ80 በመቶው በላይ ከውጭ ነው የሚመጣው፡፡ መድኀኒቱንና እቃዎቹን ከውጭ ለማምጣት ደግሞ ዶላር ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ምንዛሬ እጥረትም በግልጽ የሚታይ ችግር ነው፡፡ እስከዛሬ ከውጭ አገር ረጅም ጊዜ ከቆዩ አጋሮች ነው መሳሪያዎቹም አላቂ እቃዎችም የምናገኘው፡፡ ዋናው ችግራችንም አሁን የመድኃኒትና የአለቂ እቃ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህን እቃዎች በራሳችን አቅም አለማስመጣት ትልቁ ፈተናችን ነው፡፡
ታዲያ መፍትሄው ምንድነው?
ዋናው መፍትሄ ማዕከሉ የራሱን ቋሚ ገቢ የሚያገኝበትን መንገድ መፈለግ ነው፡፡ አገልግሎቱን ለማስፋት የባለሙያውን አቅምና መጠን ለመጨመር የራሱ ቋሚ ገቢ ያስፈልገዋል፡፡
በገጠማችሁ የአላቂ እቃና የመድኃኒት ችግር ምክንያት መስራት ከምትችሉት በምን ያህል ቀንሳችሁ እየሰራችሁ ነው?
መስራት ከምንችለው አንድ ሶስተኛ በታች ቀንሰን እየሰራን ነው፣ ቅድም እንደተባባልነው በወር ከ28-30 መስራት እየቻልን፣ በችግሩ ምክንያት፣ በሳምንት ሁለት ህፃናትን ብቻ ነው የልብ ቀዶ ጥገና የምንሰራው:: ሌላ “ካቴተራይዜሽን” የሚባል ህክምና አለ፡፡ የልብ ቱቦዎችን ማስፋትና በተፈጥሮ የተከፈቱ የልብ ቀዳዳዎችን ዘግቶ መውጣት የመሳሰሉ ህክምናዎች… እነዚህን ደግሞ በሳምንት ከ3-6 ሰው እንሰራለን፡፡ ዋናውን ወጪ የሚወስደው ቀዶ ህክምናው ቢሆንም ይሄኛውም ቀላል አይደለም:: በሳምንት ሁለት ቀዶ ጥገና ማለት በወር 8 ህፃናት ብቻ ናቸው የልብ ቀዶ ጥገና የሚደረግላቸው፡፡ አሁን ወረፋ የሚጠብቁ ብዙ ህሙማን አሉ፤ ግን ቶሎ ቶሎ ለማዳረስ ችግር ገጥመን ተጨንቀናል፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት፤ ህዝቡ ግንዛቤው እየጨመረና ስለ አገልግሎቱ እየሰማ ሲመጣ ታካሚው እየበዛ፡፡ ችግሩም በዚያው መጠን እየሰፋ ነው የመጣው፡፡
በፊት በራሳችን ሀኪሞች አልነበረም ህክምናው የሚሰጠው፡፡ ፈረንጆቹ እስኪመጡ ጠብቁ ይባላሉ:: ታካሚዎቹ ቁርጣቸውን አውቀው ይሄዳሉ:: አሁን የራሳችን ሀኪሞች ኖረውን በማቴሪያል እጥረት ታካሚ ሲጉላላ ማየት ያሳዝናል፡፡ በእርግጥ መቶ ፐርሰንት የልብ ቀዶ ጥገና እዚህ ብቻ ወይም በእኛ ሀኪሞች ብቻ ይሰራል ማለት አይደለም:: በጣም ከባድና ውስብስብ ህክምና ሲገጥመን የውጭዎቹ እስኪመጡ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ ያን ጊዜ ሲመጡ ለእኛም እውቀት አጋርተውን፣ ህክምናውንም ሰጥተው ይሄዳሉ፡፡ በእኛ አቅም ሊሰራ የሚችል ህክምና የሚፈልጉ፣ ብዙ ወረፋ የሚጠብቁ አሉ፡፡ በአላቂ እቃና በመድኃኒት እጥረት ምክንያት፡፡ ዛሬ መታከም የሚችል ልጅ፤ የዛሬ ዓመት ተመልሰህና ስትይው፣ ሌላ ውስብስብ ችግር ውስጥ ገብቶ ይመጣል፡፡ ይሄ ከባድ ነገር ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ አሁንም አልረፈደም፤ ተስፋ አስቆራጭ አይደለም፤ በሳምንት አንድም ሁለትም ልጅ እያከምን ነው፡፡ ማዕከሉ በአቅሙ ልክ ሰርቶ፣ ህፃናትን የምንታደግበትን መንገድ በጋራ እንፈልግ ነው እያልን ያለነው፡፡ ማዕከሉ የህዝብ ነው፤ በህዝብ ነው የተገነባው በህዝብ ድጋፍ መቀጠል ይችላል፡፡ እስከ ዛሬም ችግሩን ባለማሳወቃችን የመጣ ክፍተት ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ግን ተናግረናል፡፡ ህብረተሰቡ ደግሞ ለግንባታው እንደተረባረበው ለዘላቂ አገልግሎቱም መረባረብ፣ ሌላውን ማስተባበር የውጭው ማህበረሰብም ጥሪ ማድረግ ይችላል:: ግለሰቦችና ተቋማት በምክር፣ በገንዘብ በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ሊያግዙን ይችላሉ፡፡ አሁን እናንተ የመጣችሁት የበኩላችሁን ለማድረግ ነው፡፡ ይሄ ቀላል አይደለም፡፡ በፊት ስራችን ይናገር ብለን ህክምናው ላይ አተኩረን ብዙ ተጎድተናል፤ አሁን ግን እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡
ቀደም ሲል በጤና ፖሊሲው ሰፊ ትኩረት የሚሰጠው ለተላላፊ በሽታዎች ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የልብ ህመምን ጨምሮ የአገራችን ፈተና ሆኗል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
እውነት ነው፡፡ የቀደመው የጤና ፖሊሲ ትኩረት የሚያደርገው ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች ላይ ነበር:: ምክንያቱም ተላላፊ በሽታዎች በባህሪያቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችን የማዳረስና የመውረር ባህሪ አላቸው፡፡ ያ የሚሆነው በኑሮ ዘይቤያቸው ስለሚመሳሰሉ ማለት ነው፤ ብዙ ሞትም ያስከትላሉ፡፡ እንደገናም በቀላሉ ለመቆጣጠርም አመቺ ናቸው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ብዙውን ትኩረት ይዘውት ቆይተው ነበር፡፡  
አሁን አሁን የአኗኗ ዘይቤያችን እየተቀየረ፣ ተፈጥሯዊ ከሆኑ ምግቦች ይልቅ ወደታሸጉ ምግቦች ማዘውተር አበዛን፡፡ ይሄ በስራ ውጥረት ይሁን በዘመናዊነት ምክንያት ብዙም ግልጽ ባይሆንም ብቻ አሁን ላይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መጠን 52 በመቶ ደረሰ፤ ከተላላፊዎቹ በልጧል፡፡ በሌላ በኩል፤ ሰው የሰውነት እንቅስቃሴ እንደ ባህል አልተወሰደም፡፡ የስራ ባህሪዎች በብዛት ቁጭ አድርገው የሚያውሉ ናቸው፡፡ ፎቅ በሊፍት እንወጣለን፤ መንገድ ላይ በእግር ትንሽ መጓዝ ጥቅሙ ግምት ውስጥ አይገባም፤ ስለዚህ በአሁን ሰዓት ሁለቱም ተላላፊዎቹም ሆነ ተላላፊ ያልሆኑት አስጊ ናቸው፡፡ እኩል በእኩል እየሆኑ ነው፡፡ ይሄ ከፍተኛ የግንዛቤ ስራ የሚያስፈልገው ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ህዝባዊ ተቋማትን ማጠናከርና ማስፋፋትም የግድ ያስፈልጋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የተጠና ጥናት ካለ የልብ ህመም በምን ሁኔታና ደረጃ ላይ ይገኛል?
በ2016 ዓ.ም አካባቢ የተጠኑ ጥናቶች አሉ፤ ነገር ግን ጥናቶቹ የሚያስቸግሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምን? ህፃናቱንም አካትቶ ምርመራ ለማድረግ ኤቲካል ክሊራንስ ማግኘት ስለሚያስፈልግ ጥናቱ የሁሉንም የእድሜ ገደብ ያካተተ አይደለም፡፡ ጥናቶቹ በአብዛኛው ከ8 ዓመት በላይ ያሉትን የሚያካትት ነው፡፡ በዚያ መሰረት ጥናቶችን ስንመለከት፤ ለልብ ህመም ዋነኛው ከቶንሲል ጋር ተያይዞ የሚመጣ “ሪማቲክ ኸርት ዲዚዝ” የሚባለው፣ ቶንሲልን ከልጅነት ጀምሮ በአግባቡ ካለመታከም የሚመጣ የልብ ህመም አይነት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ቶንሲል በባህላዊ መንገድ ይታከምና ሲታገስ ዝም ይባላል፡፡
ሀኪም ቤት ሄዶ ለ7 ቀን የታዘዘን መድሃኒት 3 ቀን ወስዶ ከተሻለው ያቆመዋል፡፡ ሌላ ጊዜ ሲታመም መድሃኒት ሲወስድ፣ ህመሙ መድሃኒቱን ይቋቋመዋል፡፡ በአጠቃላይ ቶንሲል ጊዜያዊ የከፋ ችግር ስለማያመጣ በህብረተሰቡ ዘንድ ብዙ ትኩረት አይሰጠውም፤ ለልብ ህመም እንደሚዳርግም አይታወቅም፡፡ በዚህም ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡ 15 እና 16 ዓመት ሲሞላቸው ልጆቹ ከቶንሲል አልፎ ልባቸው ተጐድቶ ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ቶንሲልና ሌላ የመተንፈሻ አካል ችግር ሲኖርባቸው በአግባቡ ማሳከም ይኖርባቸዋል፡፡ ሚዲያውም ግንዛቤ በመፍጠር ሊያግዝ ይገባል:: ጤናማ ዜጋ ለመፍጠር ቅድመ መከላከል ላይ መስራቱ ርካሽ ነው ለማለት ነው፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር የጤና ባለሙያው ያደረገው ውይይት እንዴት ነበር? የጤና ባለሙያው ላነሳው በርካታ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ተሰጥቷል ብለሽስ ታምኚያለሽ?
የውይይት መድረኩ መፈጠሩ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ አንድ እርምጃም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ መተንፈስ በራሱ አንድ እፎይታ ነው፡፡ ሰው ችግሩን ካልተናገረ መፍትሔ አያገኝም፡፡ ብዙ ችግር ባለበት ሥርዓትና አገር እየኖርን፣ ችግሩ በቃ ግልጽ ነው ይታወቃል ብሎ እጅ አጣጥፎ መቀመጥ ተገቢ አይደለም፡፡ በተገኘው አጋጣሚና መድረክ ችግርን ለሚመለከተው አካል አሳውቆ በሚገባው መልኩ ምላሹን መከታተል የእኛ ሃላፊነት ነው፡፡ መድረኩ ለሁሉም የጤና ባለሙያ እንደ አጠቃላይ የጤናው ሴክተር ትልቅ እርምጃ ነው ብዬ ነው የማምነው:: በመድረኩ ላይ በጤና ባለሙያው አጠቃላይ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ለነዚያ ጥያቄዎች የተሰጡ ምላሾች አሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ገልፀው፣ በዚያ መሰረት ነው ምላሽ ሲሰጡ የነበረው፡፡ እንደኔ የተወሰኑት ጥያቄዎች ተመልሰዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ያንን ለማየት ትንሽ መታገስ አለብን፡፡ ምላሾቹ በምን ያህል ፍጥነት ተሰጡ ለሚለው፣ ቅዳሜ ውይይቱ ከተካሄደ በኋላ ሰኞና ማክሰኞ የጤና ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ነበር፡፡ እነዚህ እነዚህ ማሻሻያ ተደርጐባቸዋል ተብሎ ባልሳሳት 12 እና 13 ነጥቦች አካባቢ ተገልፀዋል:: ሙሉ ለሙሉ የባለሙያው ድምጽ አልተሰማም፤ ምላሽ ተነፍጐታል ለማለት ጊዜው አጭር ስለሆነ ትንሽ መታገስ አይከፋም፡፡ መቼም እስከ ዛሬም ታግሰን ቆይተናል፡፡ አይነ ስውር “ነገ ጠዋት አይንህ ይበራል ሲባል ዛሬን እንዴት አድሬ” እንዳለው መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ የጤና ባለሙያው ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሴክተር ችግር አለ፣ ግን ጤናው ይቀድማል:: ጤናማ ማህበረሰብ በሌለበት ምንም ማሳካት ስለማይቻል፡፡ ተገቢውን ቅንጦት ያልሆነውንና መሰረታዊ የሆነውን ነገር መመለስ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል የተባሉትን እየተከታተሉ ማስፈፀም፣ ባልተመለሱት ላይ ደግሞ እንደገና መድረክ ሲገኝ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በጣም አኩራፊም መሆን የለብንም፡፡ ቅድም እንዳልኩት የሚድኑትን ልጆች በማሰብ እኛ ብንጐዳና ብንታመም ምንም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ብዙዎች ታመው ነው እዚህ ያደረሱን፡፡ ይህንን የምናገረው እንደ ሄለን እንጂ እንደ ማዕከሉም ሆነ ሌላውን የጤና ባለሙያ ወክዬ አይደም፡፡ ሁሉም በራሱ የሚያስበው ነገር ትክክል ነው፡፡ አስተሳሰብ ይለያያልና፡፡
ግን እንደ ማዕከል የጠየቅሽው ጥያቄ በአግባቡ ተመልሶልኛል ብለሽ ታምኛለሽ?
በወቅቱ በተወሰነም መንገድ ቢሆን አድሬስ ተደርጓል ብዬ አምናለሁ፡፡ በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሌላው ታዳሚ፣ ያንን መድረኩን የሚከታተለው ሁሉ ስለ ማዕከሉ እንዲያውቅ ማድረግ ነበር፡፡ የማዕከሉን ስኬትና ያሉበትን ተግዳሮቶች ማሳየት ነበር ዋናው አላማ እንጂ ከመንግስት የሆነ ተዓምር ጠብቄ አልነበረም ያንን የተናገርኩት፡፡ ይሄ ሙሉ በሙሉ በመንግስት የሚሰራም ስራ አይደለም:: እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ማዕከሉም አያስፈልግም ነበር፡፡
ስለ ልብ ስትሉ ልብ ብላችሁ አድምጡን እያልኩ በተደጋጋሚ የምናገረውም ትኩረት እንዲሰጠው ነው፡፡ ያው መድረኩ ግንዛቤ ለመፍጠርም ሌላውንም ማህበረሰብ ለመድረስ በጣም ጠቃሚ ስለነበር፣ የምንፈልገውን አስተላልፌያለሁ ብዬ አምናለሁ:: አሁን አጋዥ ድርጅቶችና ግለሰቦችም ችግሩን ተረድተውት የበኩላቸውን እንዲያደርጉ፣ የችግሩን አሳሳቢነት ማሳየት መፍትሔ ያመጣል በሚል ነው:: የዛሬ 10 ዓመት ደግመን ስንገናኝ ደግሞ ከዚህ ስለተሻለ አገልግሎት መወያየት እንጂ እዚሁ ችግር ላይ መገናኘት የለብንም፡፡
በቅርቡ አንድ ያሰባችሁት ዝግጅት እንዳለ ሰምቻለሁ?  
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፤ ከሆስፒታሉ በፊት የተመሰረተው ፋውንዴሽኑ ነው፤ 30 ዓመት ሞልቶታል፤ የተመሰረተበትን 30ኛ ዓመት በተለያየ ዝግጅት ለማክበር፣ እየተዘጋጀን ነው፡፡ ሆስፒታሉ ለመቋቋሙ ፋውንዴሽኑ ነው ዋናው፡፡ ስለዚህ በዚህ 30ኛ ዓመት ዋነኛ አላማው፤ ፋውንዴሽኑ ያስመዘገበውን ስኬት ውጣ ውረዶቹን፣ አላማና ራዕዩን ለማህበረሰቡ ማሳወቅ ነው፡፡ ከ10 ዓመት በኋላ 40ኛ የምስረታ በዓሉን ለማክበር ብንገናኝ ምንድነው ለተተኪው የምናስረክበው? እነዚሁኑ ባለሙያዎች? ይህቺኑ ህንፃ? ይህንን አሁኑ የምንሰጠውን አገልግሎት? ብቻ መሆን የለበትም:: እንደ ፈጣሪ ፈቃድ፣ ማዕከሉ ትልቅ አላማና ግብ አለው በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ የልብ ምርምር ተቋም መክፈት፣ መከላከል ላይ ያተኮረ የምርምር ማዕከል የማቋቋም አላማ አለው፡፡ ተተኪ ሀኪሞችንና ተጓዳኝ የጤና ባለሙያዎችን የሚያፈራበት የስልጠና ማዕከል መክፈት ያስፈልጋል፡፡ የግድ እንደ እኛ ወደ ውጭ ሄደው መማር የለባቸውም፡፡ እዚሁ ይሰለጥናሉ:: እኛ 11ዱ ሀኪሞች በተለያየ ጊዜና ቦታ ወጥተን፣ ከፍተኛውን የልብ ህክምና ትምህርት ስንማርና ስንሰለጥን ከ800 ሚ.ዶላር በላይ ወጪ ወጥቶብናል:: ያንን ማስረቀት እንችላለን፡፡ እዚህ ያለውም ባለሙያ ያክማል፤ ይመራመራል፤ ተተኪ ባለሙያ ይሰለጥናል፡፡ ስለዚህ የፋውንዴሽኑ ምስረታ በዓል ላይ ገቢ ማሰባሰብ፣ የተቋሙ ቁመና ያለበትን ሁኔታ ማሳየት፣ አጋሮችንና አባሎችን አጠናክሮ ማሰባሰብ ይሆናል፡፡
መቼና የት ነው የምስረታ በዓሉ ዝግጅት የሚካሄደው?
ከሰኔ 6-8 ቀን 2011 ዓ.ም ነው የሚካሄደው፡፡ በ6 እና በ7 በዚሁ በማዕከሉ ከጋዜጣዊ መግለጫ ጀምሮ ህሙማን፤ ሀኪሞች ወላጆች፣ በጐ ፈቃደኞችና ሌሎችም የሚገናኙበት ኤግዚቢሽንም ጭምር ይካሄዳል፡፡ በ8 ማለትም በመዝጊያው ቀን ትልልቅ የመንግስት ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላትና ለጋሾች በተገኙበት በአንድ ሆቴል ውስጥ በትልቅ ምክክርና ውጤት ይዘጋል፡፡ ቦታውን ጊዜው ሲደርስ እናሳውቃለን፡፡ እዚህ ድረስ መጥታችሁ፣ ያገባናል ብላችሁ ይህን ሁሉ ሰዓት ጠብቃችሁ፣ አጋርነታችሁን ለማሳየት ላደረጋችሁት ነገር በእኔም በማዕከሉና በታካሚ ልጆቻችንም ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

Read 2988 times
Administrator

Latest from Administrator