Monday, 13 May 2019 00:00

‹‹ሐኪም›› - ሪ ሚክስ! (ሰላሣ ሺህ አሣ አጥማጆች ህመማቸውን ያዋዩት ሐኪም እና ...)

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)


                ምድሩ - ላብራዶር፡ በአትላንቲክ ውቅያኖስና በሀድሰን ባህረ ሰላጤ መካከል የምትገኝ የምስራቃዊ ካናዳ አዋሳኝ ምድር ናት፡፡ ለብዙ ዘመናት ከአለም ተነጥላ በኖረችው በውኃ የተከበበች ቀዝቃዛ ሀገር ውስጥ፤ ከሰው ልጆች ማህበራዊ ዑደት ተገልለው በአሣ ማጥመድ ኑሯቸውን በስቃይ የሚገፉት ሕዝቦች እ.ኤ.አ ከ986 ዓ.ም ጀምሮ ይኖሩባት እንደነበር ይገመታል፡፡ በጥቅጥቅ ደኖች በተቸመቸመው መልክአ ምድሯ መካከል ‹‹የገነት ዥረት›› (Paradise river) ብለው የሚጠሩት ወንዝ ይገማሸራል፡፡ በተለያዩ ዘመናት አሳሾች፣ ታሪክ አጥኚዎችና ወንጌላዊያን ርቃ የምትገኘውን በበረዶ ተሸፈነች ምድር ጎብኝተው መመለስ የቻሉቱ ብዙ አይነት አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፤ አንዳንዶቹም የውኃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል፡፡
‹‹ተስፋ ቢስ ምድር!›› ላብራዶርን ለመጀመሪያ ጊዜ በሺ534 ዓ.ም አይቷታል የሚባለው ፈረንሳዊው አሳሽ ጃክዩስ ካርቲየር የተናገረው ነበር፡፡ ‹‹በዚያ ለመኖር የሚችሉት ግዙፋን አውሬዎች ብቻ ናቸው፤ ምናልባትም እግዚአብሔር ለቃየን የሰጠው ምድር ይቺን ይሆናል፡፡” ብሏል - አሳሹ፡፡
በላብራዶር የሚገኙ አእዋፍን ለማጥናት በ1833 ዓ.ም የሄደው አሜሪካዊው ጆን ጀምስ ደሞ ‹‹በህይወት ዘመኔ አይቼው የማላውቀው እጅግ ሰፋፊና አስፈሪ ጫካዎች ነው ያላት!››ብሏል፡፡
በመርከብ ከሚጓዙ አጥኚዎች መካከል አንዱ ፊቱን ብቅ አድርጎ የላብራዶር የክረምት ውርጭ ገርፎት ሲመለስ መርከቡ ውስጥ ያለው ባልደረባው በርቀት እያሳየው ‹‹ኦ! ገነት ወንዝ ደረስን!›› ብሎ ጮኸ፡፡ ፊቱን ውርጭ የገረፈው ዞር ብሎ ‹‹ገነት እንዲህ በብርድ ካንዘፈዘፈ፣ ወደ ሲኦል እሳት ብጣል እመኛለሁ!›› ሲል ቀልዷል፡፡ በሌላ የመርከብ ጉዞ ተስፋ የቆረጠች ሴት ደግሞ ‹‹እንዲህ በብርድ ተቆራምጄ ለመሞት ረዥም ጊዜ ከማጣጥር ምናለ በአንዲት ጥይት ገላግላችሁኝ እየሞቀኝ ህይወቴ ቢያልፍ?!›› ብላለች፡፡ የሰሜን አሜሪካ ህይወት ዘጋቢ ዶሪስ ሳንደርስም ‹‹ላብራዶር ደርሶ የተመለሰ ሰው የነፍሱ ስልጣን በገዛ እጁ እንዳለች ተቆጥሮ ታሪኩ ሊጻፍለት ይገባል!›› ነበር ያለው፡፡
ሰውየው - እንዲህ በሚያንገፈግፉ አስከፊ ገለፃዎች ወደታወቀችው ምድር ለመሄድ ብዙዎች ቅንጣት ታህል ድፍረት ሲያጡ፡ ከሄዱትም ከፊሉ ሳይመለሱ ሲቀሩ፣ የምድሪቱን  እጣ ፈንታ በድፍረት ተጋፍጦ፣ እስከ ህይወቱ መጨረሻ ለእነዚያ የላብራዶር አሣ አጥማጅ ድሀ ሕዝቦች ታላቅ የህክምና ተግባር ሲያከናውን የኖረ አንድ ልዕለ-ሰብእ ነበር፡፡ ዶክተር ዌልፍሬድ ግሪንፊልድ፡፡ መከራና ሰቆቃ ሳይበግረው 40 አመታትን ላብራዶር ውስጥ የኖረ ድንቅ ሐኪም!
በእርጅና ዘመኑ መላ ጠጉሩ ሸብቶ፣ አይኖቹ ሞጭሙጨው፤ የአርክቲክ  ውርጭና አመዳይ ሲገርፋቸው የኖሩ መዳፎቹ ቆርፍደው፤ በአለም ዙሪያ ‹‹በህይወታቸው ደስተኛ›› ተብለው ከሚታወቁ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ሆኖ፣ ስሙ በክብር ለመጠቀስ በቃ፡፡ ይኸው ‹‹ሰላሣ ሺህ አሣ አጥማጆች ህመማቸውን ያዋዩት ሐኪም›› በተደጋጋሚ ጀልባው ከግግር በረዶ ጋር ተላትሞ እየተንኮታኮተበት፣ ሌሊቱን ሙሉ ውኃ ላይ እየተንሳፈፈ ውኃ ላይ ሲዋልል አድሯል፡፡ አቅጣጫ ጠፍቶበት በጥቅጥቁ የላብራዶር አስፈሪ ዱር ውስጥ እንደ በድን እስኪቀዘቅዝ ከሞት ጋር ተፋጥጧል፡፡ የደረሰበትን ከፍተኛ ረሀብ ለመቋቋም ከባህር እንስሳ ቆዳ የተሰራ ጫማውን በልቷል፡፡
ሲሞት የ70 አመት አዛውንት ነበር፤ ምናምኒት ሀብት አልነበረውም፡፡ ያም ሆኖ ለራሳችን እንጂ ለላብራዶሩ ሐኪም እናዝንለት ዘንድ አንችልም፤ እርሱ በአለም ላይ ለመኖር በጣም አስፈላጊው የነበሩትና ጥቂቶች ብቻ የሚታደሏቸው ደስታና እርካታ ነበሩትና፡፡
ዶክተር ግሪንፊልድ ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በህክምና ከተመረቀ በኋላ ለንደን ውስጥ በሚገኝ ትልቅ የህክምና ተቋም ውስጥ ስልጠና ጀመረ:: ባስመዘገበው የላቀ ውጤት በከፍተኛ ኃላፊነት እንግሊዝ ውስጥ እንዲሰራ ሹመት ተሰጠው፡፡ እርሱ ግን እረፍት ፈለገ፡፡ እናም የበጋውን ወር ከላብራዶር አሣ አጥማጆች ጋር ለማሳለፍ ወሰነ፡፡
ሕዝቡ - በዚያች አሳዛኝ ምድር፤ በስተደቡብ ከምስራቅ ካናዳ ኒውፋውንድላንድ ጠረፍ 1500 ማይሎች ርቀትና በሀድሰን ባህረ ሰላጤ በምትገኘው በጣም ቀዝቃዛዋና ለኑሮ እማትመቸው የባህር ዳርቻ ሀገር፤ ከአመቱ ዘጠኙ ወራት በበረዶ ተሸፍኖ ዙሪያ ገባዋ በሚያንዘፈዝፍ ቁርና ብርድ የሚቀስፍ ሆኖ ይዘልቃል፡፡ አፈሯ እህል የማያበቅል በመሆኑ በአሣ አጥማጅነት መሰማራት ግድ የሆነባቸው ሕዝቦቿ ለሚያረቧቸውም ከብቶቻቸው እንዲሁ ጨዋማ ስጋ ያላቸውን ትልልቅ የባህር አሦችና የአሣ ነባሪ ጅራቶችንም ይመግቧቸዋል፡፡ ዶክተር ግሪንፊልድ ህይወታቸውን በመከራ ለሚገፉት ሰላሣ ሺ አሣ አጥማጆች አንድም ሐኪም እንደሌላቸው ሲያይ በሀዘን ተነካ፡፡
ግብሩ - በእረፍት ጊዜው አቅሙ የሚፈቅደውን ሲያደርግላቸው ሰንብቶ ከተመለሰ በኋላ፤ በለንደን ከተማ ዘመናዊ ሆስፒታል ውስጥ ለባለ ፀጋ ታማሚዎች የህክምና ውጤትና መድኃኒት ማዘዣ በመፃፍ መኖር ሊቀጥል እንደማይችል ተረዳ፡፡ የሰሜኑ ምድር አላስቀምጥ አለው፡፡ እናም ጓዜን ጨርቄን ሳይል ተነስቶ ወደ ላብራዶር ምድር ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገብቶ ለ42 አመታት ያህል ወዲያ ወዲህ ለማለት በማይተማመኑበት የላብራዶር ባህር ዳርቻ ላይ ጀልባውን ሲቀዝፍ ኖረ፡፡ ለዚህም ታላቅ ግብሩ ከእንግሊዝ መንግሥት ታላቅ ግብር ለፈጸሙ ዜጎች የሚሰጠው Knight ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
በኃይማኖታቸው ምክንያት ማደንዘዣ ለመውሰድ ፈቃደኛ ያልነበሩ አሮጊትን ለማዳን ግድ ሆኖበት በልጆቻቸው ፊት ያለማደንዘዣ የታመመ እግራቸውን ሲቆርጥ የተሰማው ከባድ ሀዘን ከውስጡ አልወጣ ብሎት ተሰቃይቷል:: ከከተማ ሰዎች የሚላኩለት የሳሎን እልፍኝ ምንጣፎችና የጥጥ ጫማዎች ክምር ሲያናድደው ኖሯል፡፡ የተላኩትን መጻህፍት የላብራዶር ሰዎች ለብርድ መከለያነት ቀዳድደው ግርግዳቸው ላይ ከመለጠፍ ውጪ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ሲያይ በጥልቅ አዝኗል፡፡ አሣ አጥማጆቹ ከበርካታ አምልኮዎቻቸው ጎን ክርስቲያንም ነበሩና ለእምነታቸው ሲሉ ሲባዝኑ አይቷል፡፡ አሳሞች እያሏቸው ዱቄት በውኃ በጥብጠው በመጠጣት ለምን እንደሚሰቃዩ ሲጠይቃቸው የመለሱለትም፤ አሳሞቹ ቤተ ክርስቲያን ጥሰው ገብተው ቅዱሳን መጻሕፍት ስለበሉ አንበላቸውም የሚል ነበርና በጣም ተገርሟል፡፡ የአንዲት በጠና የታመመች ሴትን ህይወት ለማትረፍ በውሾች በሚጎተት ጋሪው ሲከንፍ፣ የበረዶው ግግር እየተጠረማመሰ ቁልቁል ሰርጎ፤ ውሾቹን ነፃ እንዲሆኑ ፈትቶ ለቅቆ አብሯቸው እየዋኙ ወደ ዳርቻ ከወጡ በኋላ በቆፈን ሊሞት ደረስ:: ያለው አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነበር:: ውሾቹን ገድሎ ቆዳቸውን ተጀቡኖ ስጋቸውን ተጠልሎ አድሮ፤ ጠዋት ደግሞ በአጥንታቸው ቀጣጥሎ ጋሪ ሰርቶ መጓዝ፡፡
‹‹ምን አይነት አስደናቂ ህይወት ነው ያሳለፍከው! አንተ በጣም ልዩ ሰው ነህ!›› ሲሉት ታዲያ፤ ዶክተር ግሪንፊል ምላሹ እንዲህ የሚል ብቻ ነበር ‹‹ይኼ ለኔ ብዙ የሚካበድ ነገር አይደለም፤ በሙያዬ የሚጠበቅብኝን ነው ያደረግኩት፡፡ እናም አጋጣሚዎቼንም ሁሉ በቃ ልክ እንደ ጨዋታ ያክል ነበር እምቆጥራቸው፡፡››
ሐኪሙ በህይወት ዘመኑ በፍፁም ቁርጠኝነትና ፈቃደኝነት ህዝብን ሳይሰስት ላገለገለበት የላቀ ሙያዊ ግብሩ በሀገሩ መንግሥት ከተሰጠው የክብር ሽልማቱ በተጨማሪ ለመታሰቢያው በስሙ የሚጠራ ‹‹ዶክተር ግሪንፌል ሆስፒታል›› ቆሞለታል፡፡ መልካም ስም ከመቃብር በላይ ነው እንዲሉ፡፡
ምርቃት  -  ሐኪም ወ እብነ ሐኪም(ማስታወሻ . . .የጽሑፉ ምንጭ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹የላብራዶሩ ሐኪም ድንቅ ገድል›› በሚል አርእስት ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በሜዲካል ጋዜጣ ‹‹እናስተውል›› አምድ ለንባብ ካበቃው ትርጉም የቀነጨበው ነው:: ጸሐፊው በዚህ አጋጣሚ የተቆለሉ አሮጌ ወረቀትና ጋዜጦችን አቧራ በማራገፍ ነፍስ እንዲዘሩ ለተጉ ወዳጆች ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ እነሆ የጽሑፉን አስረኛ አመት ዋዜማ ለመዘከር በሐኪም ወ እብነ ሐኪም አውድና ፍቺ ምርቃት ጥበብ ጥለት re-mix ‹‹ያስጌጠው››ም ዘንድ ወደደ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንጀምር፡፡ እነሆ . . .)
ሐኪም - በብሉይ ኪዳን - ‹‹በገለዓድ የሚቀባ መድኃኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም የለምን? የወገኔ ሴት ልጅ ፈውስ ስለ ምን አልሆነም?›› (ኤር 8 ፡ 22)
ሐኪሙን ፍለጋ - የሳባም ንግሥት በእግዚአብሔር ስም የወጣለትን የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። (መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 10፡1)
ክብረ ነገሥት  - ‹‹ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ . . .‹‹እሷም ሄደች፡፡ ከእሱ ከተሰናበተች ከዘጠኝ ወራትና አምስት ቀናት በኋላ ዲሳሪያ ውስጥ ባላ ከተባለ ሃገር ደረሰች፡፡ ህመምም ያዛት፡፡ በብዙ ክብርና ተድላም ወንድ ልጅን ወለደች፡፡ ለሞግዚትም ሰጠችው፡፡›› (በምእራፍ ፴፪ ቁጥር ፭) ስለ ንግሥት ሳባ ያሰፈረው ምእራፍ ፭ ደግሞ ስለ ልጇ ግዕዝ እና አማርኛ መሳ  ... ‹‹ህፃኑም አደገ፡፡ ስሙንም ‹‹በይነ ለህለም›› ብላ ጠራችው፡፡›› . . . ‹‹ወልሕቀ ውእቱ ሕፃን፡፡ ወሰመየቶ ስም በይነ ልሕከም/ኢብነ እልሐኪም፡፡›› ገጽ 24/25::
(ክብረ ነገሥት  የመጀመሪያው ድርሣን በሁለቱም ቋንቋዎች በአረብኛ እንደተጻፈ ይታመናል፡፡‹‹ኢትዮጵያዊያን ተጨማሪ መጻሕፍት አገናዝበው ለራሳቸው እንዲሆን አድርገው አክሱም ላይ በግዕዝ ጻፉት››፡፡ ይላሉ አበው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች ‹‹ቅዱስ ቁርኣን›› ከአረብኛ ሲተረጎም ‹‹ከዐረብኛ ግሥ መሰረት የሌላቸው ሃያ ስድስት ያክል የሚሆኑ የኢትዮጵያ ቃላት እንዳሉበትም ያስረዳል፡፡›› -  ‹‹ቅዱስ ቁርኣን››  የአማርኛ ትርጉም ሐምሌ 18 ቀን 1958 ዓ.ም መቅድም ፡፡ (ረመዳን ከሪም፡፡)
ሐኪም - በታሪክ ድርሣናት . . . (ጥንታዊ ኢትዮጵያ) ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹...ንግሥት ሳባም የነዚሁ ከደቡብ አረቢያ ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ ምድር የመጡት የነገደ ዮቅጣን/አግአዚያን 52ኛ ንግሥት ናት፡፡››. . .ንግስት ሳባም ከንጉሥ ሰለሞን ወንድ ልጅ ፀንሳ የተመለሰች ሲሆን ስሙም  እብነ ሐኪም ተብሎ ተሰየመ፤ ትርጉሙም የ‹‹ጠይብ›› ልጅ ማለት ነው፡፡
መዝገበ ቃላት -ጠይብ - በደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላት ፍቺ - ጠይብ - ባለጅ፡ ቀጥቃጭ፡ብረት ሰሪ፡ሸክለኛ፡አንጥረኛ፡ሸማኔ፡ ፋቂ፡ዐራቢ፡አናጢ፤ትርጓሜው ብልህ፡ ፈላስፋ፡ስራን ሁሉ አዋቂ ማለት ነው፡፡...ባረብኛም ጠይብ “ይ”ን አጥብቆ ደግ ማለፊያ ማለት ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ እናሳርግ
...ሐኪም - በአዲስ ኪዳን  -   ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ -
ከእናንተ የሆነ የክርስቶስ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል። ስለ እናንተ በሎዶቅያም በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ እንዲቀና እመሰክርለታለሁ፡፡ የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። (ቆላስያሰ 4 ፡ 14)
 መልካም የነርሶች ሳምንት!!
ፈጣሪ ሀገራችንን ይባርክ!!
‹‹አሜን፡፡››


Read 1980 times