Print this page
Saturday, 11 May 2019 14:15

የሱዳን ተቃዋሚዎች ወታደራዊውን መንግስት አስጠነቀቁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


             ፕሬዚዳንት አልበሽርን ከስልጣን አውርዶ መንበሩን የተቆናጠጠው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን ለሲቪል መንግስት የሚያስረክብበትን ጊዜ ካላፋጠነ በመላው ሱዳን አዲስ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚጠሩ የአገሪቱ የተቃውሞ መሪዎች ማስጠንቀቃቸው ተዘግቧል፡፡
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፤ ወታደራዊ መንግስቱ በአፋጣኝ ስልጣኑን የማያስረክብ ከሆነ አገሪቱን ወደ ከፋ እልቂት ሊያስገባ የሚችል ቀውስ እንደሚፈጠር ከተቃውሞው መሪዎች አንዱ የሆነው ካሊድ ኦማር ዮሴፍ ባለፈው ረቡዕ አስታውቋል፡፡
ተቃውሞውን ያስተባበረው ዲክላሬሽን ኦፍ ፍሪደም ኤንድ ቼንጅ ፎርስስ የተባለው ቡድን መሪ የሆኑት ማዳኒ አባስ ማዳኒ በበኩላቸው ካርቱም ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በመላ ሱዳን ወታደራዊውን መንግስት የሚቃወም እጅግ ከፍተኛ ተቃውሞ ለማድረግ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን በመግለጽ፣ ወታደሩ በአፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ አስጠንቅቀዋል፡፡  
ስልጣኑን የያዘው የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት፣ ምርጫ ከመደረጉ በፊት የሲቪል ወታደራዊ ጥምረት ምክር ቤት ለማቋቋም ከተቃዋሚዎች ጋር ስምምነት ላይ በደረሰው መሰረት፣ አዲስ ህገ መንግስት በማርቀቅ ላይ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ያም ሆኖ ግን ወታደሩ ስልጣኑን ለማራዘም እየተጋ ነው በሚል ተቃውሞው ተባብሶ መቀጠሉን አመልክቷል፡፡
ለሶስት አስርት አመታት ያህል አገሪቱን የገዙትን ኦማር አልበሽርን በአደባባይ ተቃውሞ ከስልጣን ያወረዱት የሱዳን ተቃዋሚዎች፣ ወታደራዊው መንግስት ስልጣኑን ለሲቪሉ እስካላስረከበ ድረስ እረፍት የለንም በሚል ጽኑ አቋም፣ የአገሪቱን ጎዳናዎች በተቃውሞ ማጥለቅለቃቸውን እንደቀጠሉ ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የአገሪቱን መንገዶችና የባቡር መስመሮች በመዝጋት የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ገድበው የሚገኙት የሱዳን ተቃዋሚዎች፣ በወታደራዊው መንግስት ላይ ሊከፍቱት ያሰቡት አዲስ የተጠናከረ ተቃውሞ ምን አይነት እንቅስቃሴዎችን እንደሚያካትትና መቼ እንደሚጀመር በግልጽ አለማስታወቃቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1501 times
Administrator

Latest from Administrator