Sunday, 12 May 2019 00:00

በ2017 ብቻ በአለማችን 35 ቢ. ሊትር አልኮል ተጠጥቷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአልኮል ተጠቃሚነት በ27 አመታት 70 በመቶ ጨምሯል

            የአልኮል ተጠቃሚነት በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ እንደሚገኝና ባለፉት 27 አመታት ጊዜ ውስጥ የአልኮል ተጠቃሚነት በ70 በመቶ ያህል መጨመሩን አንድ አለማቀፍ ጥናት አመለከተ፡፡
አንድ የጀርመን ተቋም በአለማችን 189 አገራት ላይ የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ በፈረንጆች አመት 2017 ብቻ በመላው አለም 35 ሺህ 676 ቢሊዮን ሊትር አልኮል ተጠጥቷል፡፡ ባለፉት 27 አመታት የአልኮል ተጠቃሚነት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው በእስያ አገራት እንደሆነ የጠቆመው ጥናቱ፤ አነስተኛ አልኮል የሚጠቀሙት ደግሞ አውሮፓውያን መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
የአልኮል መጠጥ ተጠቃሚነት በመላው አለም በርካታ ሰዎችን ለተለያዩ የጤና ችግሮች በመዳረግ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ መሆኑንና ከ200 በላይ በሽታዎችን ሊያስከትል እንደሚችል ያመለከተው ዘገባው፤  የአለም የጤና ድርጅት በበኩሉ በፈረንጆች አመት 2016 ብቻ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አልኮል አብዝተው በመጠጣታቸው ሳቢያ ለሞት እንደተዳረጉ ማስታወቁን አስታውሷል፡፡
የአልኮል ተጠቃሚነት በተለይ በወጣቶች ዘንድ እየተስፋፋ እንደሚገኝና በመጪዎቹ አስር አመታት ጊዜ ውስጥ ከአለማችን ወጣቶች መካከል ግማሹ አልኮል ጠጪዎች ይሆናሉ ተብሎ እንደሚገመትም ጥናቱ አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2086 times