Monday, 13 May 2019 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)


                    “--ዋናው ነገር እያንዳንዱ ግለሰብ አእምሮ ውስጥ አገር መኖሩና የአገር “አእምሮ” ውስጥም እያንዳንዱ ዜጋ መኖሩ ተፈጥሯዊ፣ መሆኑን ማወቅ ነው፡፡ ማንም በአገሩ ባዕድ መሆን አይችልም፡፡ ቀስታችንንና ድህነታችንን አራግፈን በስልጣኔ መንገድ ስንገሰግስ ደግሞ አለም አቀፋዊ አእምሮ እንገነባለን፡፡--”
        

            ሞትና ዲያብሎስ ቀጠሮ ነበራቸው፡፡ አንዳንዴ እየተገናኙ ሰውንም፣ ፈጣሪያቸውንም ያማሉ፣ ስለ ስራቸውና ስለ ሌሎች አለማትም ያወራሉ፡፡
“ምነው ከሳህ?” አለው ዲያብሎስ፤ ሞትን ሲያገኘው፡፡  
“ሥራ የለም” ሞት መለሰ፡፡
“ኧረ ተመስገን በል፣ ምን ጎደለህ? ... ይኸ ሁሉ ሰው በየሆስፒታሉ፣ በየጎጆው፣ በየ …”
“ገብቶኛል፡፡ ጊዜውን የጠበቀ የተፈጥሮ ስርዓትን የተከተለ፣ በእርጅና የሚመጣ ሞት ለኔ ትርፍ የለውም፡፡ እንደውም ‹የመጣበትን ጉዳይ ጨርሶ ወደመጣበት ተመለሰ› እንጂ ‹ሞተ› አይባልም፡፡ እኔ የማተርፈው ከሰው ስህተት ነው፡፡ ሰው በገዛ እጁ ከሚፈጥረው ሞት--”
“ማለት?”
“ከህክምና ስህተት፣ ከፖለቲካ ስህተት፣ ከትራፊክ አደጋ፣ ከችግርና ድህነት ከመሳሰሉት… በአስተሳሰብ እንከኖች ሳቢያ ከሚፈጠሩ ቀውሶች…”
“ሰው እያወቀ፣ እየተማረ፣ እየሰለጠነ መጣ፤ ስህተት ቀነሰ እያልከኝ ነው?”
“በሰለጠኑ አገሮች አዎ፡፡ በሌሎቹ ቦታዎች ግን የአንተ ቸልተኝነት ነው ያስጠቃኝ…”
“ምን አጠፋሁ?”
“ማሳሳት ቀንሰሃል!”
“ከአብሮ አደግህ አትሰደድ የሚባለው‘ኮ እንደ አንተ ዓይነት ጓደኛ ሲያጋጥም ነው፡። እኔ አሳሳች አይደለሁም፣ ተቃዋሚ መልዓክ ነኝ እንጂ፡፡ አንተም የተሳሳትክ ህይወት መሆንህን አትርሳ፡፡”
“ታዲያ የስህተት ምንጩ የት ነው? … ማነው?”
ሁለቱ መንፈሶች “አንተ እንዲህ ነህ፣ አንተ እንዲያ ነህ” እየተባባሉ ሊግባቡ ባለመቻላቸው፣ ለዳኝነት ከፈጣሪያቸው ዙፋን ቀረቡ፡፡ ከፊት ለፊቱም ተንበርክከው …
“እኛ ማን ነን? … እርግጥ ያንተ ስህተቶች ነን?” በማለት ጠየቁት፡፡
“በጭራሽ! … እናንተ ድንቅ ፀጋዎች ናችሁ፡፡ እናንተ ባትኖሩ እኔ አልኖርም ነበር” አላቸው፤ ፈገግ ብሎ፡፡
“እንግዲያው ስህተት ምንድነው? … ሰው ለምን ይሳሳታል?” አሉት፡፡
“አጭር ከሌለ ረዥም፣ ጥቁር ከሌለ ነጭ፣ ውሸት ከሌለበት እውነት፣ ንፁህ ባልታወቀበት ቆሻሻ ይኖራልን?... ስህተትም የእውነተኛው ወይም የትክክለኛው መንገድ ተቃራኒ ነው፡፡ እውነተኛው መንገድ ደግሞ በኔ በኩል ነው፡፡ ሰውን የወለድኩት እኔ ነኝ፤ የእኔ ስህተት የሰው ስህተት ይሆናል እንጂ ሰው በራሱ ስህተት አይደለም፡፡ … ስህተተኛ የሚያደርገው ተፈጥሮው ሳይሆን ድንቁርናው ነው:: ይልቁንስ የኔ ትልቁ ጥፋት …” አለና አምላካቸው ማሰብ ጀመረ፡፡ አንድ ወሳኝ ነገር ሊነግራቸው ፈልጓል፡፡ …
ሁለቱ መንፈሶች ያንሾካሹካሉ፡-
“እሱም ያስባል እንዴ?” ሲል አንደኛው፤ “ማሰብ ብቻ?... እሱ ራሱ ሃሳብ‘ኮ ነው… በዚህ ላይ በግማሽ ሰው መሆኑን ተናግሯል … እንደ ጊልጋሜሽ፡፡”
“ማሰብ ወሳኝ ነገር ነው ለካ?”
“ታሞ ከመማቀቅ … ሲባል አልሰማህም?”
“ሞት ከምሆን ሃሳብ ብሆን ይሻለኝ ነበር፡፡”
“እኔም!” አለ ዲያብሎስ፤ በሆዱ እየሳቀ፡፡
ጨዋታቸውን ሳይጨርሱ እግዜር ከሃሳቡ ተመለሰና፤ “የኔ ጥፋት…” በማለት ሊነግራቸው የፈለገውን ነገር እንደገና ሲጀምር … መንፈሶቹ ከመጓጓታቸው የተነሳ አቋረጡትና፡-
“ጥፋትህ ምንድነው የኛ ጌታ?” በማለት ጠየቁት:: ነገራቸው፡፡ በዚህች ቅጽበት ምድርና ሌሎች ዓለማት ሁሉ ተነቃነቁ፡፡ “አንተ ታላቅ ነህ፤ እንደገና እንሰግድሃለን!” አሉ፤ፍጥረታት ሁሉ፡፡
ሁለቱ መንፈሶችም፤ “ባሪያዎችህ በመሆናችን ዕድለኞች ነን” እያሉ ፈነጠዙ፡፡
 … ምን ብሏቸው ይሆን?
***
 ቀደም ባለው ጊዜ ፍልስፍናና እምነት፣ እዚህ ጋ ተጋብተው ወዲያ የሚፋቱ፣ እንደገና ሲገናኙ መልሰው የሚፋቀሩና አፍታም ሳይቆዩ የሚጣሉ፣ አንዳንዴም በወረት ጎን ለጎን የሚጓዙ ነበሩ፤ ተሰለቻችተው “ዓይንህ ላፈር” እስከተባባሉበት ጊዜ ድረስ፡፡ ስልጣኔ ሲስፋፋ፣ ዕውቀት ሲበለፅግ እምነት ለፍልስፍና ቦታውን እየለቀቀ በመምጣቱ ወዳጅነታቸው “በታሪክ ጉርብትናነት” ብቻ እየተጠቀሰ ቀረ የሚሉ ሊቃውንት ብዙ ናቸው፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው ፍልስፍና፣ የእምነት ምክንያታዊነትን ሙልጭ አድርጎ በመጠራረግ ራቁቱን በማስቀረቱ እንደሆነ  ይገልፃሉ፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ሰውን ወደ አለማመን የሚመራው ጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ነው፣ ፍልስፍና በጥልቀት ሲረዱት የሰዎች አእምሮ እምነትን እንዳይቀበል አያደርግም በማለት የሚከራከሩ አሉ:: የነዚህን ሀሳብ ፍራንሲስ ቤከን፡-
“A little philosophy inclineth a man’s mind to atheism; But depth in philosophy bringth men’s minds about to religion” በማለት ሲያጠናክረው፣ ኢማኑኤል ካንትም “Religion cannot be proved by theoretical reason” በማለት ፅፏል፡፡
ወዳጄ፡- አንድ ላይ እየኖሩ በተለያየ መንገድ ማሰብ ወይም በተለያየ መንገድ እያሰቡ አንድ ላይ መኖር፣ ቢሸሹት የማይርቁት ተፈጥሯዊ ህልውና ብቻ ሳይሆን የሆሞጄኒስና የሄትሮጄኒስ አሃዳዊና ማህበራዊ ስነ እሳቤዎች መሰረት ነው፡፡ ህብረተሰብዓዊ ወይም ማህበራዊ ስነ ልቦና (social mind) የግለሰብ አስተሳሰብን ሊፈጥር ወይም ተፅዕኖ ሊያደርግበት እንደሚችል አያጠራጥርም:: በግልባጩ ማህበራዊ አስተሳሰብ የሚገነባው ደግሞ የተለያየ ሃሳብ ባላቸው ግለሰቦች ነው፡፡ ግለሰብዓዊነት ከሌለ ማህበረሰባዊነት የለም፡፡ ማህበረሰባዊነት ቅርፅ የሚይዘው ግለሰብ አእምሮ ውስጥ ሲሆን ማህበራዊ ‹አእምሮ› ውስጥም ግለሰብ ዋነኛው ተዋናይ ነው፡፡
ለምሳሌ፡- ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጎቿ  አገር ናት፡፡ ዜጎቿ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይኖራሉ፡፡ በሁሉም ቦታ፣ ሰፈሮችና መንደሮች አሉ፤ በየሰፈሮቹ ውስጥ ትንንሽ እድሮች፣ የቡና፣ የጠላ፣ የቦርዴ ወዘተ-- አጣጭ ጎረቤቶች አሉ፡፡ እያንዳንዱ ቤተሰብ ሲደክመው የሚያርፍበት፣ ሲመሽ የሚተኛበት፣ ገመናውን፣ እርቃኑን ማጀቱን የሚከልልበት የየራሱ ጎጆ አለው፡፡ በጎጆው ውስጥ የሚኖሩ የቤተሰብ አባላት ደግሞ የተለያየ አስተሳሰብ፣ ዝንባሌ፣ እምነትና ዕውቀት ይኖራቸዋል፡፡ የደም ዓይነታቸው ሳይቀር ይለያያል፡፡ በዘመናችን ቋንቋ ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ሰፈር፣ ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ክ/ከተማ፣ አስተዳደራዊ ክልልና አገር መሆኑ ነው፡፡ ፍሬ ነገሩ፡- እያንዳንዱ ግለሰብ አእምሮ ውስጥ አገር መኖሩንና የአገር “አእምሮ” ውስጥም እያንዳንዱ ዜጋ መኖሩ ተፈጥሯዊ ፣ መሆኑን ማወቅ ነው፡፡ ማንም በአገሩ ባዕድ መሆን አይችልም፡፡ ቀስታችንንና ድህነታችንን አራግፈን በስልጣኔ መንገድ ስንገሰግስ ደግሞ አለም አቀፋዊ አእምሮ እንገነባለን፡፡ በታሪክ ከመጀመሪያው ቤተሰብ ከአቤልና ከቃየል ወርሰን እስከ ዛሬ የዘለቅንበትን ስህተት እየደገምን ‹ኖረናል› የምንል ከሆነ ተሳስተናል ሳይሆን ‹ስህተት› ራሱን ሆነናል፡፡
To bear all naked truths,
And to envisage circumstance, all clams:
That is the top of sovereignty.
--የሚለን ባለቅኔው ኪትስ ነው፡፡ ልቡና ግዙ ዓይነት፡፡
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፤ ሁለቱ መንፈሶች እግዜር፣ አጥፍቻለሁ ሲል፣ “ስህተትህ ምንድነው?” ብለው እንደጠየቁት አውርተናል፡፡ “ራሴን በራሴ መፍጠሬ ነው” በማለት ነበር የመለሰላቸው፡፡ ይህን ሲሰሙ ነው ዓለማት የተነቃነቁት፣ ፍጡራን ዕልል! ያሉት፡፡ ምክንያቱም እግዜርን ‹እግዜር› ያደረገው፣ ራሱን በራሱ መፍጠሩ ነው፡፡ ጣልቃ ገብ መመሪያ ሰጪ፣ አለቃ የለበትማ!!
ታላቁ ሰዓሊና ባለቅኔ ዊሊያም ብሌክ፡- “Tigers of wrath are better than horses of instruction” ይለናል፡፡
ሠላም!!

Read 447 times