Monday, 13 May 2019 00:00

ሃሳብና መሻት፤ በገጣሚው መነጽር

Written by  በስንታየሁ አለማየሁ
Rate this item
(5 votes)

 ህይወትን በህቡዕ ከሚኖሩ ብዙኃን ይልቅ በይፋ የተገለጠ ሃሳብና ሊታይ የሚችል ራዕይ ያነገቡ ጥቂቶች የሚሻሉ ይመስለኛል፡፡ ሰውን ከእንስሳው ነገድ የሚለየው ማሰብ መቻሉ ነው ይባላል፡፡ እኔ ግን በዚህ አልስማማም:: ምክንያቱም ወፎች ከሳርና ከእሾህ ጥንግ አስገራሚ ጎጆ የሚቀልሱት ሳያስቡ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በብዙ እንስሳት ላይ የሚታየው የእናትነት ባህርይም ከሰው ቢልቅ እንጂ የሚያንስ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ በማሰቡ ብቻ ሳይሆን የተሻለ በማሰቡና ዕጣ ፈንታውንም የሚያውቅና የሚከተል ፍጡር በመሆኑ፣ ከእንስሳ የተለየ ነው ብንል ሳይሻል አይቀርም፡፡
ከዚህ በታች የተዳሰሱት፣ በዕውቀት የተፃፉ፣ የበዕውቀቱ ሁለት ግጥሞችን የመረጥኩት፣ የሰው ልጅ፣ የተሻለ ብርታትና ተሰጥኦ ባለቤትነቱን የሚያሳዩ እንዲሁም ጥረትና ልፋትንም አጥብቀው የሚሽቱ በመሆናቸው  ነው፡፡
በዕውቀቱ እንግዲህ እንደምናውቀው ነው፤ የተለየ እይታ ይወዳል፣ ፍልስፍናው ድንቅ ነው፤ ሲሻው ህይወትን እየኮረኮረ እንድንስቅ ማድረግ ይችልበታል፤ ከሳቁ መለስ ስንል ደግሞ ከንጥፍ ሰማዩ በታች አግጦ ያፈጠጠውን እውነታ በልቦናችን ውስጥ ይሸጉጥብናል፤ አሊያም ደግሞ ዛሬን በውል በማስቃኘት ነገን በአይነ ህሊና ተመልክተን እንድንደነግጥ፣ አንዳንዴም እንድንናፍቅ ያደርገናል፡፡
“ከሥነ-ፅሁፍ ሁሉ ትልቁ ፈጠራ ግጥም ነው” የሚል አቋም ያለው ገጣሚው፤ በእርግጥም ግጥም የተሻለ ክህሎትና ፈጠራ እንዲሁም የምናብ ጥልቀትና ምጥቀት እንደሚያሻው በራሱ ግጥሞች ያሳየን ይመስለኛል፡፡ ከብዙ ድንቅ ግጥሞቹ መካከል ከተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ጋር የሚጣጣሙ የመሰሉኝን ሁለቱን ለመቃኘት  እሞክራለሁ፡፡
“ነጠብጣብ ሀሳቦች” በሚል ርዕስ የተጻፈችው ግጥም ያዘለችውን ድንቅ ሃሳብ እንመልከት፡-
ሸክም ጸጋ ኾኗል ጸጋህን አትግፋ
በጠባብ ዓለም ውስጥ ትከሻህን አስፋ።
ተኝቶ መነሣት አቤት ሲያቅለሸልሽ
ጌታ ሆይ አትንሳት ነፍሴን እንቆቅልሽ።
ሸክምን እንዳንሸከም የሚፈቅድ ወይም የሚደነግግ አለማዊም ሆነ የሰማየ ሰማያቱ ህግ በሌለበት ሁኔታ፣ ሸክምን እንደ ፀጋ ከመቀበል ውጭ ምን ትሩፋት ይኖራል?! ቅዱስ መፅሐፉም፤ “ጥረግ ግረህ በላብህ ወዝ ኑር” ነው የሚለው፡፡ እርግማን መሳይ ምርቃት ወይስ ምርቃት መሳይ እርግማን እንበለው? መልሱን ለእግዜሩ ብንተወው ይሻላል፡፡ ሸክም ለመሸከም መፍቀድ፣ ከሸክሙ ክብደት ላይ  የተወሰነ ኪሎ እንደ መቀነስ ያህል የሚቆጠር ይመስለኛል:: ምክንያቱም ፈቃድ ወይም አስቀድሞ አምኖ መቀበል ከሁሉ ይበልጣልና፡፡ ነገረ ፍጥረታችንን ብናውቅ ኖሮ፣ ሸክሞችን ሁሉ በፀጋ አምነን ከመቀበልና እሰዬው ብለን ከማለፍ ውጭ ባላማረርን ነበር፡፡ በእርግጥ በዚህ ስንኝ ውስጥ ተራኪው፣ ሸክምን በፀጋ ስለመቀበል ብቻ አይደለም ሊነግረን የፈለገው፡፡ ሸክምን በፀጋ የምንቀበለው አማራጭ ስለሌለን እንደሆነም ይጠቁማል…..
ተኝቶ መነሣት አቤት ሲያቅለሸልሽ
ጌታ ሆይ አትንሳት ነፍሴን እንቆቅልሽ።
….. ይላል፡፡ ተኝቶ መነሳት የሚያቅለሸልሸው ዳግም ለሸክም መንጋቱን ስለሚያውቅ ነው …. ሸክሙ እንደማይቀርለት ያወቀው የሰው ልጅ ታዲያ ….. የሸክሞች ሁሉ አቅላይና ባለቤት ነው ብሎ ወዳሰበው ወደ ፈጣሪው ይማፀን ጀምሯል ……… ጌታ ሆይ አትንሳት ነፍሴን እንቆቅልሽ በማለት ይፀልያል:: (ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣እኔም ሸክማችሁን አቀልላችኋለሁ እንዲል መፅሀፉ):: እንቆቅልሽ አንድም መዝናኛ ነው፤ ሁለትም አስገራሚ ድንቃድንቅ ገጠመኝ ሊሆን ይችላል፡፡ በእንቆቅልሽ የታጀበና የተቃኘ ህይወት ባይኖረን ኖሮ፣ እንደ ሸክማችን ብዛት በጠፋን ነበር፡፡ እንደ ተራኪው ስሜት ከሆነ፤ እንቆቅልሹ እራሱ ሸክሙ ሊሆንም ይችላል ….. የኑሮ ፈተና በሙሉ ሸክም እኮ ነው፤ የሚያጋጥሙን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅፋቶች፣ ሸክም አይደሉም እንዴ? ….. እናም ከዚህ ሁሉ አተካራዎች በቀላሉ እንደማንወጣ ሲያስብ ይሆን እራሱን ፈተናውን የሻተው? ሊሆን ይችላል:: እራሱ ፈተናውና እንዲያ ያለው ግጥምጥሞሽ እንቆቅልሽ ነው ……. እንቆቅልሹ ደግሞ አይቀሬ በመሆኑ ከላይ ከሚጫንበት ይልቅ አስቀድሞ እራሱ በፀሎት እንደ መና ለምኖ ቢቀበለው፣ ከራሱ ጋር አዋህዶና አስማምቶ ለመቀጠል ይበጃልና ነው፡፡
ከሸክማችን ብዛት የአለምን ጥበትና እንሰት ደግሞ ይነግረናል …… በጠባብ አለም ውስጥ ትከሻህን አስፋ በማለት፡፡ ለምሳሌ “ሆደ-ሰፊ ሁን”፣ “ሆድ ከሀገር ይሰፋል” የሚሉ ዘወትሯዊ  ብሂሎች አሉን፡፡ በዚያ ውስጥ መቻልና ህልቆ መሳፍርት ትዕግስትን እንማራለን፡፡ ጭራሽ “ሆድ ካገር ይሰፋል” በማለት የሃገርን እንቶ ፈንቶ ሁሉ ሆድ ውስጥ ከተን ለመኖር እንዳዳለን፡፡ በዚህ የሰፊ ትከሻና የጠባብ አለም ንፅፅር ውስጥ የምናገኘው ድንቅ ምልከታ፤ ከቻልንና ለመሸከም ከበረታን፣ እኛ ከሰፊው አለም እንደምንበልጥ ወይም አለም ጠብባ እኛ እንደምንሰፋ ነው፡፡  በሌላ ምልከታ ደግሞ አለም አማራጭ አልባ፣ በክልክል የተሞላች በመሆኑ፣ ከኛ ህልቆ መሳፍርት መሻትና ከየትየለሌ ሸክማችን አንፃር፣ ጠባብ አለም ላይ መስፈራችንን ነው የሚያትተው፡፡  
ገጣሚው በሌላኛው ድንቅ ግጥሙ፤ የፍልስፍናን ውሃ ልክ ሊያሳየን ይሞክራል፡-
የሥልጣኔ መዝሙር
ማንጋጠጥ እንድችል
“ደመናው የ’ኔ ነው!” እንድል
ተራሮችን እንድነድል
ከጥልቅ ሸለቆዎች ጥግ
የምንጭ ዱካ እንድፈልግ
ከሀኖስ እስከ ውቅያኖስ መንገዴን እንድዘረጋት
ልቤን እርካታ የለሽ፣
ሕይወቴንም ጥም አድርጋት።
… ይለናል፡፡ መፈለግ ፣ መመርመር ፣ ማወቅ ፣ መጠየቅ …… የሚሉ ሃሳቦች በሙሉ የሚወለዱበትን መንገድ፣ በዚያም፣ ትልሙንና ልኬታውን ይጠቁመናል፡፡ ፍልስፍና ማለት ማቆሚያ የሌለው በጥያቄ የታጨቀ ጉዞ ነው ይላሉ - ፈላስፎቹ:: መፈለግ … መመርመርና … መጠየቅ መቻል፣ የእውቀትና የዕጣ ፈንታ ሁሉ መሰረት ይመስለኛል:: እፎይ ደረስኩ፣ በቃኝ፣ ተገላገልኩ፣ ጨረስኩ … የሚሉ እርካታ መሰል የህይወት ጅምር ሀረጎች ደግሞ የኑሮ መሰናክሎች:: ማንጋጠጥ እንድችል ….. ሲለን ምን ማለቱ ነው? ማንጋጠጥ መቻል ምን ያደርጋል? ባናንጋጥጥስ ምን ይቀርብናል? ስናንጋጥጥ የምናየው ሰማይ ነው …… ሰማይ ምንድን ነው ብለን መጠየቅ እንጀምራለን፤ ማን ፈጠረው፣ ለምን ተፈጠረ፣ እንዴት ተፈጠረ፣ መቼ ተፈጠረ ብለን እንጠይቃለን፡፡ በእያንዳንዱ ጥያቄ ስር እልፍ አእላፍ መልሶች ይዘረገፋሉ …. ከዝርግፉም እንጠግባለን እንጂ አንረካም …. እናም  ወደ ሌላ ጥያቄ እንነጉዳለን፡፡
ከጥልቅ ሸለቆዎች ጥግ
የምንጭ ዱካ እንድፈልግ
ደግሞ ወደተቀመጥንበት መሬት እናያለን …. ከመሬት በታችስ ምን አለ? እንላለን …. መሬት ምን አይነት ካስማ ላይ አረፈ? እንላለን ….. ሌላ  ዱካ ፍለጋ እናስሳለን፡፡ በጥያቄ ብዛት በብርሃን ፍጥነት … ካሁን በፊት ወደ ማናውቀው አለም እንነጠቃለን ….. የምንጭን ዱካ ለማወቅ እንጥራለን … ደግሞም ከፍ ሲል … ከሃኖስ እስከ ውቅያኖስ መንገዴን እንድዘረጋት … በማለት ከሚታየው ከምንሄድበት ተረጋጭና ተጨባጭ መሬት ይልቅ በእዝነ-ልቦና ወደሻትነው አለምና እውቀት እንድንስፈነጠር፣ ተራኪው በመሻት፡-
ልቤን እርካታ የለሽ፣
ሕይወቴንም ጥም አድርጋት
በማለት ይፀልያል …. ፈጣሪውን ይለምናል፤ ይማፀናል፡፡  
ሰው የተፈጠረው በእንዲህ ያለው ጥልቅ መሻትና የእርካታ እጦት፣ የፈጣሪንም የራሱንም  የመፈጠር ሰበብና ሚስጥር መርምሮ እንዲገነዘብ ነው፤ ፍጥረታትን ሁሉ በጥልቀት አውቆ፣ የራሱን አሻራም አኑሮ፣ የህይወቱን ምዕራፍ እንዲያሳርግ፡፡ ቸር እንሰንብት!

Read 1921 times