Monday, 13 May 2019 09:43

እንቅርትና ማረጥ (Thyroid እና Menopouse)

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)


             በአማርኛው እንቅርት በመባል የተለመደው Thyroid ታይሮይድ በተለይም ሴቶችን በስነተዋልዶ ጤናቸው ዙሪያ ከሚያደርስባቸው ችግር የወር አበባ መዛባት፤ እርግዝና እንዳይኖር ማድረግ፤የጽንስ ማቋረጥ፤ ቀኑ ሳይደርስ ልጅ መውለድ፤ የሞተ ልጅ መውለድ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡እንቅርት በአብዛኛው በምግብ ውስጥ በአዮዲን እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን ሕመም የሚወ ክል ስያሜ ሲሆን በሌላም ምክንያት ሕመሙ ሊከሰት እንደሚችል አንዳንድ ጽሁፎች ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌም  Thyroiditis ታይሮይድ እጢ በተለያዩ ምክንያቶች ሕመም ወይንም ቁስለት ሲደ ርስበት የሚከሰት ሕመም ነው፡፡ ሌላው Thyroid cancer: ነው፡፡ ይህ የካንሰር ሕመም ብዙም ያልተለመደ ነገር ግን በጊዜ ከታከመ ሊድን የሚችል ሕመም ነው:: በቀዶ ሕክምና ወይንም በጨረር ወይንም የሆርሞን ሕክምና ከተደረገ የታይሮይድ ካንሰር እንደሚድን መረጃ ዎች ይጠ ቁማሉ፡፡ ሌሎችም  እንደ Hyperthyroidism: ማለትም ከልክ በላይ ንጥረ ነገር የሚያመነጭ ሕመም ሲሆን ሌላው Hypothyroidism ማለትም ንጥረ ነገርን ባነሰ መልኩ እንዲመረት የሚያደርገው ነው፡፡
ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ማእረግ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ትምህርት አስተማሪ ስለእንቅርት ባለፈው እትም በጽሁፍ ከቀረበው በተጨማሪ ከስነተዋልዶ ጤና  ጋር በተያያዘ በዚህ እትም ያብራሩትን ለንባብ እነሆ ብለናል፡፡
ዶ/ር ማህሌት እንደሚሉት ሴቶች በታይሮይድ ተገቢ ስራ አለመስራት ምክንያት በሚፈጠረው የንጥረ ነገር መብዛትም ይሁን ማነስ በእርግዝናና ልጅ በመውለድ ምክንያት ከሚከሰ ትባቸው ችግሮች በተጨማሪ በእለት ተእለት ማህበራዊ ኑሮአቸው ላይ ተጽእኖ ያሳድርባቸዋል:: ሴቶች በታይሮክሲን መብዛት ምክንያት የልብ ሕመም፤ የአጥንት መሳሳት፤ የፀጉር መርገፍ ይደርስባ ቸዋል፡፡ የሰውነት ቅርጽ ያበላሻል፡፡ ባጠቃላይም ስብእናን የሚነካና እንዲህ ነው ተብሎ የማይ ገለጽ የጤና ችግር ያስከላል፡፡ ሕመሙ ምልክቱም ሆነ ጉዳቱ እንዲህ ነው ብሎ ለመግለጽ የሚያስቸግርበት ምክንያትም የሚሰሙት የህመም ምልክቶች የሌላም ሕመም ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ በቀጥታ ከታይሮይድ ወይንም እንቅርት ጋር የተያያዘ ነው ብሎ መገመት ስለሚያ ስቸግር  ነው፡፡
የእንቅርት በሽታ በኢትዮጵያና እንደኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት በሕመም መልክ የሚከሰተው በአዮ ዲን እጥረት ነው ተብሎ ቢታመንም ችግሩ ግን አዮዲን እጥረት በማይገለጽባቸው የአለም ክፍሎችም ይስተዋላል:: የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሰውነት በሰውነት ላይ ሲቆጣ ነው የሚል እምነት አለ፡፡ ሰውነት ያቺን እጢ የሚያጠቃ ሴል በሚያዘጋጅበት ጊዜ እየተጎዳች ስለምትሄድ እድሜ ሲጨምር ታይሮክሲን የተባለው ንጥረ ነገር ማነስ የብዙ ሴቶች ችግር ይሆናል፡፡
ሴቶች እድሜያቸው የወር አበባ ከሚቋረጥበት Menopause ሲደርስ ከዚያ ጋር በተያያዘ ያሉትን መልእክቶች በሙሉ ያባብሳቸዋል፡፡ ምክንያቱም የታይሮይድ ስራ እየወረደ እየቀነሰ ይሄድና በማረጫው እድሜ የሚደርሱ አንድ ሶስተኛ የሆኑ ሴቶች የንጥረ ነገሩ እጥረት ይኖርባቸዋል፡፡ ስለሆነም ከወር አበባ መቋረጥ ጋር ያሉትን ሕመሞች ለምሳሌም እንደስብራት እንደልብ ሕመም ኮለስትሮል የመሳሰሉት መጠናቸው ከፍ እንዲል ያደርጋል፡፡ በተለይም የልብ ሕመምን በሚመለከት አንዳድ ጊዜ በፍጥነት እንዲመታ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እጅግ እንዲዘገይ ሊያደ ርገው እና የልብ ጡንቻ መድከም እንዲከተል ሊያደርግ ይችላል፡፡
የታይሮይድ ወይንም የእንቅርት ሕመም አንገት ላይ ከሚወጣው እባጭ በስተቀር ሌላው በላቦራቶሪ ካልታየ አካላዊ ሆኖ የሚታወቅ አይደለም፡፡ እድሜ አንዱና ትልቁ ተጽእኖ ፈጣሪ ነው፡፡ ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ ሕመሙ ጎልቶ የሚታይበት ምክንያት  ሴቶች እድሜያቸው ሲጨምር ኢስትሮጂን የተባለው ንጥረ ነገር መመረቱ እያነሰ ስለሚሄድ ወደ ማረጥ ሲደረስ የታይሮይድ ማነስና የኢስትሮጂን ማነስ የሚመሳሰሉበት ሁኔታ አለ፡፡ በሌላ በኩል ግን ሁለቱም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ የታይሮይድ ሕመም እድሜ የማይወስነው ሲሆን የወር አበባ መቋረጥ ወይንም ሜኖፖዝ ግን የተወሰነ የእድሜ ክልል ያለው መሆኑ እሙን ነው፡፡ ዶ/ር ማህሌት እንደገለጹት፡፡
በእርግዝና ወቅት የታይሮይድ እጢ የሚያመነጨው ንጥረ ነገር በእርግዝናው ሆርሞን ስለሚነ ቃቃ ከፍ ሊል ቢችልም ያ ግን ሐመም ነው ማለት አይደለም፡፡ እርግዝና ግን በባህርይው የሚ ቆጡ ሴሎችን እንዲመጡ ስለሚያደርግ ከወለዱ በሁዋላ ሰውነት እንደ እንቅርት ያሉ እጢዎች ላይ ቁጣ እንዲያመጡ ያደርጋል፡፡ በተለይም ከወለዱ በሁዋላ ሴቶች ባህሪያቸው ሲለወጥ፤እንቅ ልፍ ማጣት ሲደርስባቸው፤ቆጣ ቆጣ ማለት፤ልጁንም ጣል ጣል ማድረግ ፤ኃይለኛ መሆን የመ ሰሉት ነገሮች ሲስተዋሉባቸው ምናልባት የታይሮይድ ችግር ሊሆን ስለሚችል ምርመራ ማድ ረግ ይጠቅማል፡፡
ሕክምና በባህርይው መነሻውን ማወቅ ግድ ይላል:: ለምሳሌ ሴቶች አለአግባብ ወፍረው ቢታዩ ወይንም ኮለስትሮል ቢኖር ምክንያቱ ወይንም መነሻው ምንድነው የሚለውን ለማወቅ የላቦራቶሪ ምር መራ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱ ሳይታወቅ ፊት ለፊት ለታየው ሕመም መድሀኒት ቢወሰ ድም ሕመሙ ለውጥ አያመጣም፡፡ ስለዚህ ማከም የሚገባው ምልክቱን ሳይሆን መነሻውን መሆን አለበት፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገራችን የአዮዲን እጥረት አለ የሚያሰኝ ነገር አለ ለማለት ያስቸግራል ዶ/ር ማህሌት እንዳሉት፡፡ ምክንያቱም ምግቦች አዮዲን እንዲኖራቸው ለማድረግ የተቻለውን ያህል ጥረት የተደረገ በመሆኑ ችግሩ የተቀረፈ ይመስላል፡፡ ነገር ግን የአጠቃቀም ችግር እየተስተዋለ ነው ፡፡ አዮዲን ያለው ጨውን ለመጠቀም ሲያስፈልግ ጨው ከምግቡ ጋር እንዲንተከተክ ማድ ረግ ትክክል አይደለም፡፡ በመንተክተክ ወቅት አዮዲን ከውስጡ ሊጠፋ ይችላል፡፡
ምግቡ በስሎ ከወጣ በሁዋላ ጠረጴዛ ላይ ጨው ነስንሶ መመገብ አዮዲን እንዳይባክን ለማድረግ ትክክለኛው ዘዴ ነው፡፡
የሰው ልጆችን የሚያጠቁ ብዙ አይነት ኢንፌክሽኖች አሉ፡፡ የቫይረስ ኢንፌክ ሽን፤የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ስላሉ እነዚህ ነገሮች ደግሞ እንቅርት እንዲቆጣ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ሲፈጠር ደግሞ የታይሮይድ ሕመም ይጨምራል፡፡
የታይሮይድ ሕመም በባህርይው ከስኩዋር ሕመም ጋር ስለሚመስል የስኩዋር ሕመምን የሚጨምሩ ነገሮች የታይሮይድ ሕመምንም ሊጨምሩ ይችላሉ::
ረዥም እድሜ በተኖረ ቁጥር የታይሮይድ ሕመም ይጨምራል፡፡
ስለዚህም በተቻለ መጠን አመጋገብን እንዲሁም የሰውነትን ጤንነት መጠበቅ ጠቃሚ ነው፡፡ ዶ/ር (ረዳት ፕሮፌሰር) ማህሌት ይገረሙ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት እንዳብራሩት፡
በስተመጨረሻም ከሕመሙ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ምክሮችን ለግሰዋል፡፡
ጭንቀትን ለማስወገድ  የሚያስችሉ የአኑዋዋር ስልቶችን መቀየስ ተቀዳሚው ነው፡፡
ጤናማና ለሰውነት ጠቃሚ የሆነ ምግብን መመገብ፤
ቫይታሚን የመሳሰሉትን ጠቃሚ ነገሮች ለመመገብ አመቺ የሆኑ ዘዴዎችን መጠቀም፤
እንቅልፍን በደንብ ለመተኛት የሚያስችሉ ነገሮችን ማድረግ፤
መዝናናት መቻል…ወዘተ የመሳሰሉት ነገሮች ጠቃሚዎች ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የሰውነት መገጣጠሚያዎችን አስፈላጊ የሆኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች በማድረግ መጠበቅ ይገባል፡፡ እንዲሁም ጡንቻዎች እንዳይላሉ ተገቢውን እስፖርት ወይንም በኑሮ የእለት ተእለት ተግባራትን በማከናወን ሰውነትን ማጠንከር ተገቢ ይሆናል፡፡

Read 14675 times