Print this page
Saturday, 18 May 2019 00:00

“በጋዜጠኛው ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የፈፀሙትን ለህግ አቀርባለሁ” - የኮንሶ ዞን አስተዳደር

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በደቡብ ክልል የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳደር ጽ/ቤት፤ ዳዊት ዋሲይሁን በተባለ ጋዜጠኛ ላይ በግለሰቦች  የተፈፀመውን ድብደባና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በጽኑ አውግዞ፣ ጥቃቱን የፈጸሙትን ወገኖች አድኖ ለህግ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡  
በህጋዊ መንገድ ለሥራ ጉዳይ ሚያዚያ 25 ቀን 2011 ዓ.ም በኮንሶ ከተማ ተገኝቶ ለዘገባ ስራ ሲንቀሳቀስ በነበረው የ”አክያ ሚዲያ ኢንተርቴይመንት” ጋዜጠኛ ዳዊት ዋሲይሁን ላይ በቡድን በተሰባሰቡ ግለሰቦች የተፈፀመበት ጥቃትና ክብረ ነክ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት፣ በቸልታ የሚታይ እንዳልሆነ  የዞኑ አስተዳደር ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ ጠቁሟል፡፡  
ጥቃቱን የፈፀሙት የተደራጁ ሃይሎች መሆናቸውን የጠቀሰው የዞኑ አስተዳደር፤ ጋዜጠኛውን ከታገተበትና ሲፈጸምበት  ከነበረው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ለማስጣል የሞከሩ የዞኑ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችም በጥቃት ፈፃሚዎቹ ዘረፋና ድብደባ እንደተፈፀመባቸው አመልክቷል - በመግለጫው፡፡   
በጋዜጠኛው ላይ የተፈፀመው ግልጽ ወንጀል ነው ያለው  የዞኑ አስተዳደር መግለጫ፤ ድርጊቱ የኮንሶን ህዝብ የማይወክል መሆኑንና  አጥፊዎችን በአስቸኳይ አድኖ ለህግ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
ጋዜጠኛው በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ስለ ጉዳዩ ባሰፈረው ማስታወሻ፤ ከዞኑ ሃላፊዎች ፈቃድ አግኝቶ በኮንሶ ከተማ  ለስራ ሲንቀሳቀስ፣ በተቧደኑ ግለሰቦች  መደብደቡን፣ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶም ፀጉሩን በግዳጅ መላጨቱንና ሌሎች ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እንደተፈፀመበት በዝርዝር ገልጾ ነበር፡፡

Read 7942 times