Saturday, 18 May 2019 00:00

ቃለ ምልልስ “እኔ ከፕ/ር ብርሃኑ ጋር የሚያጣላኝ ግላዊ ምክንያት የለኝም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  • በግንቦት 7 ጣልቃ ገብነት ነው ፓርቲያችን ፈርሷል እየተባለ ያለው
            • ሚዲያዎች ኢዴፓ ፈርሷል የሚለውን ማረም አለባቸው፤አልፈረሰም
            • የሸር ፖለቲካን ለአዲሱ ትውልድ ማውረስ የለብንም

       የኢዴፓ መስራችና የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው “ኢዴፓ አልፈረሰም” ይላሉ፡፡ መገናኛ ብዙኃንም ሳያጣሩ “ኢዴፓ ፈርሷል” እያሉ መዘገባቸው ስህተት ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ አቶ ልደቱ፤ ፓርቲያችን በህገ-ወጥ መንገድ ፈርሷል እየተባለ ያለው በ”ግንቦት 7” ጣልቃ-ገብነትና ተሳታፊነት ነው በማለት የከሰመውን ንቅናቄ ይከስሳሉ፡፡
እሳቸው ኢዴፓ አልፈረሰም ይበሉ እንጂ የፓርቲው ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ “ኢዴፓን በህጋዊ መንገድ አፍርሰናል” ብለዋል፡፡ ለመሆኑ አቶ ልደቱ፤ ኢዴፓ አልፈረሰም ሲሉ በምን መነሻ ነው? ኢዴፓ ዳግም የመቀጠል ህጋዊ ዕድል ይኖረው ይሆን? እንዴት? እነ አቶ ልደቱና ቡድናቸው የሚፈልጉት ምንድን ነው? አቶ ልደቱ የፖለቲካ ተሳትፎአቸውን በተመለከተ ምን ዕቅድ አላቸው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ  አነጋግሯቸዋል፡፡


              ፓርቲው ባለፈው አንድ ዓመት የነበረበትን ሁኔታ በማስረዳት ይጀምራሉ - አቶ ልደቱ፡፡
ፓርቲያችን ባለፈው አንድ አመት ችግር ውስጥ ነው የነበረው፡፡ ይሄ ይታወቃል፡፡ በፓርቲያችን ውስጥ የተፈጠረውን ችግርም ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች አድርገናል፡፡ በእርቅና ሽምግልናም ለመስማማት ሞክረናል፤ ሆኖም አልተሳካም፡፡ በኋላ የተረዳነው ፓርቲያችንን ለማፍረስ የሚንቀሳቀስ ሌላ ሶስተኛ ሃይል እንዳለ ነው፡፡ ይሄን ስናውቅ በፓርቲው ደንብ መሠረት፣ የብሔራዊ ም/ቤት ስብሰባ ጠርተን ችግሩን እየፈጠሩ ያሉ አመራሮችን ቀየርን፡፡ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ ተጠናክሮ እንዲወጣ ባለመፈለጋቸውና ከኢህአዴግ ጋር በሚደረገው ድርድር የፓርቲውን ጥቅም የሚጐዱ እርምጃዎች ውስጥ ገብተው በመገኘታቸው የመረጣቸው የኢዴፓ ብሔራዊ ም/ቤት ከኃላፊነታቸው  አወረዳቸው፡፡ የአመራር ለውጥ መደረጉንም ለምርጫ ቦርድ አሳወቀ፡፡ ነገር ግን ምርጫ ቦርድ፣ ይሄን የፓርቲውን የብሔራዊ ም/ቤት ውሳኔ አልቀበልም አለ፡፡ የም/ቤቱ እርምጃ ህጋዊ አይደለም በማለት፣ አምስት ነጥቦችን ሊሟሉ ይገባል ብሎ ላከ፡፡ እኛም በዚያ መሠረት በድጋሚ ነጥቦችን አሟላን፤ ነገር ግን ምርጫ ቦርድ አሁንም ሊቀበለን አልፈለገም፡፡
እንዲያውም የብሔራዊ ም/ቤቱን ሳይሆን የዶ/ር ጫኔን የስብሰባ ጥሪ ነው የምቀበለው ብሎ፣ ቦርዱ በእኛ ላይ እገዳ ጣለብን፡፡ እኛም ለፓርቲው ደህንነት ስንል ምንም እንኳ የቦርዱ ውሣኔ ህገወጥ ቢሆንም፣ ዶ/ር ጫኔ ስብሰባውን እንዲጠሩት ፍቃደኛ ሆንን:: ነገር ግን ቦርዱ ዶ/ር ጫኔ ስብሰባውን እንዲጠሩ አላደረገም፡፡ በዚህ ሳያበቃ ለዶ/ር ጫኔና ለሌሎች አራት አመራሮች እውቅና በመስጠት፣ አብላጫውን የብሔራዊ ም/ቤት፣ እውቅና አልሰጥም አለን፡፡ ይሄ ማለት ፓርቲው ብሔራዊ ም/ቤት የለውም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ፓርቲ በተግባር የለም ማለት ነው፡፡ ፈርሷል ማለት ነው፡፡ ስራ አስፈፃሚ ያለ ብሔራዊ ም/ቤት ሊኖር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ስራ አስፈፃሚ ዋነኛ ተግባሩ፣ ብሔራዊ ም/ቤቱ የሚወስነውን ማስፈፀም ነው፡፡ ብሔራዊ ም/ቤት የሌለው ፓርቲ ህልውና የለውም ማለት ነው፡፡ ይሄን ጉዳይ ይዘን ለቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ለሁለት ጊዜያት አቤቱታ ብናቀርብም ምላሽ አላገኘንም፡፡ ቀጥሎ ለመጡት ዶ/ር ዐቢይም አቤቱታችንን አቀረብን፡፡ እሣቸውም ጠርተው እኛን አነጋገሩን፡፡ በጉዳዩ ላይም ምርጫ ቦርድ መፍትሔ እንዲያበጅ አስቸኳይ መመሪያ ሰጡ፡፡ በዚህ መሠረት የምርጫ ቦርድ አመራሮች እንደገና ጉዳዩን ማጣራት ጀመሩ፡፡ ማጣራቱ ከመጠናቀቁ በፊት ግን የቀድሞዋ ኃላፊ ከቦርዱ ሰብሳቢነት ወርደው፣ ወ/ት ብርቱካን ወደ ኃላፊነት መጡ፡፡  
ጉዳያችን በዚህ የሽግግር ሂደት ተራዘመ፤ በኋላም ለማስታወስ በድጋሚ ጉዳያችን ከምን ደረሰ ስንል ጠየቅን፡፡ በዚህም ወ/ት ብርቱካን የማጣራት ሂደቱን ቀጠሉ፡፡ የማጣራት ሂደቱም ተጠናቀቀ፡፡ በተጠናቀቀው ማጣራት ላይ የምርጫ ቦርድ ውሣኔ መስጠት ነበረበት፡፡ ነገር ግን ምርጫ ቦርዱ ገና አልተቋቋመም፡፡ ወ/ት ብርቱካን ደግሞ ብቻቸውን መስራት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ቦርዱ እስኪቋቋም ታገሱኝ፤ ቦርዱ እንደተቋቋመ በመጀመሪያ ጉዳያችሁን ለቦርዱ አቅርቤ ችግሩ ይፈታል የሚል ቃል ተገባልን፡፡ እኛ  አሁን እየጠበቅን ያለነው ቦርድ ተቋቁሞ ውሣኔ የሚሰጥበትን ቀን ነው፡፡ በዚህ ላይ እያለን ነው እንግዲህ እነ ዶ/ር ጫኔ፣ ኢዴፓ ህልውናው ፈርሶ ከእነ ፕ/ር ብርሃኑ አዲስ ፓርቲ ጋር እንደተዋሃደ መግለጽ የጀመሩት፡፡ ይሄ ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡
የተሰሩት ስህተቶች ምንድን ናቸው? ግልጽ ቢያደርጓቸው----
ስህተት ነው የምንለው አንደኛ፣ የኢዴፓ ጉዳይ ገና በምርጫ ቦርድ ተይዞ ነው ያለው፤ ውጤቱ አልታወቀም፡፡ ሁለተኛ፣ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት ማድረግ፣ በህብረት መስራትና መዋሃድ ሊወሰን የሚችለው በፓርቲው ብሔራዊ ም/ቤት ብቻ ነው፤ ሌላ የሚወስን አካል የለም፡፡ ብሔራዊ ም/ቤቱ ከወሰነ በኋላ ለጠቅላላ ጉባኤ አቅርቦ ነው የሚያፀድቀው፡፡ ብሔራዊ ም/ቤቱ ደግሞ ታግዶ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የተሠራው ስህተት ይሄ ነው:: የፓርቲው ብሔራዊ ም/ቤት ሳይወስን ኢዴፓ ፈርሷል ማለት ስህተት ነው፡፡ ኢዴፓ አልከሰመም፡፡
እርስዎ ኢዴፓ ከእነ አርበኞች ግንቦት 7 ጋር በመዋሃዱ ደስተኛ ባለመሆንዎ ይሆን ይሄን ጥያቄ ያነሳችሁት?
አይደለም፡፡ እኛ በፓርቲዎቹ መዋሃድ ተቃውሞ የለንም፡፡ በነገራችን ላይ እነ ፕ/ር ብርሃኑ ለምርጫ ቦርድ ባስገቡት ፍቃድ መጠየቂያ ላይ፣ አዲስ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለማቋቋም፣ ፊርማ ለማሰባሰብ ትብብር ይደረግልን የሚል ማመልከቻ ነው ያስገቡት:: ምርጫ ቦርድ የሚያውቀው፣ እነ ፕ/ር ብርሃኑ፣ አዲስ ፓርቲ እንደሚያቋቁሙ እንጂ ፓርቲዎችን እንደሚያዋህዱ አይደለም፡፡ ይሄ በሆነበት ሁኔታ ኢዴፓ እንደከሰመ ተደርጐ የሚሰጠው መግለጫ ህገ-ወጥ ነው፤ ትክክለኛ አይደለም፡፡ በተለይ ሚዲያዎች ይሄን ነገር ሳያጣሩ፣ ኢዴፓ ከስሟል ማለታቸው ስህተት ነው:: እኛ ውህደትን እንደግፋለን፤ ነገር ግን ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ኢዴፓን የሚያጠፋ እርምጃ መውሰድ አይችሉም፡፡ ይሄን በመቃወም፣ እኛ አሁን፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ በግንቦት 7 ጣልቃ ገብነትና ተሳታፊነት ነው ፓርቲያችን በህገ-ወጥ መንገድ ፈርሷል እየተባለ ያለው እንጂ ጠቅላላ ጉባኤም ሆነ የብሔራዊ ም/ቤት ስብሰባ አልተጠራም፡፡ ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠራ የሚችለው ብሔራዊ ም/ቤቱ ደግሞ ታግዶ ነው ያለው፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች ጠቅላላ  ጉባኤ እንዴት ጠሩ? ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡  
ፓርቲያችሁ እዚህ ችግር ውስጥ ለመግባቱ ዋና ተጠያቂ ማን ነው?
ዋና ተጠያቂው የቀድሞ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ አሁን ግን አዲሱ አመራር ተገቢውን ስራ እየሰራ ነበር፡፡ ዝም ብለው ቁጭ አላሉም:: የማጣራት ሥራ አጠናቀዋል፤ ነገር ግን ቦርዱ እስኪደራጅና ውሳኔ እስኪሰጥ ነበር የሚጠበቀው፡፡ በወ/ት ብርቱካን የሚመራው ምርጫ ቦርድ፣ መስራት የሚገባውን ተገቢ ስራ ሲሰራ ነው የቆየው፡፡ ውሳኔ እየተጠበቀ ሳለ ነው ኢዴፓ ፈርሷል የሚል አጀንዳ የመጣው፡፡ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ኢዴፓን ከሌላ ፓርቲ ጋር ማዋሃድ የሚቻልበት ምንም መንገድ የለም፡፡ ምክንያቱም የማዋሃድ ውሳኔ በብቸኛነት ሊወስን የሚችለው የኢዴፓ ብሔራዊ ም/ቤት ነው፡፡ ስለዚህ ሚዲያዎች ኢዴፓ ፈርሷል የሚለውን ማረም አለባቸው፡፡ ኢዴፓ አልፈረሰም፡፡
በእናንተ በኩል ኢዴፓን ይዞ የመቀጠል ፍላጎት አላችሁ?
በሚገባ አለን፡፡ የምርጫ ቦርድ፣ በብሔራዊ ም/ቤቱ ላይ የጣለውን ህገ ወጥ ማዕቀብ ካነሳ፣ እኛ ኢዴፓን ይዘን የመቀጠል ፍላጎት አለን፡፡ ከዚያ በኋላ ከኛ ጋር ለመዋሃድ፣ አብሮ ለመስራት የሚፈልግ ፓርቲ ካለ፣ ግንቦት 7ን ጨምሮ ደስታውን አንችለውም፡፡ ግልፅ መተማመንና የህግ መስመርን ተከትለን የምንዋሃድ እስከሆነ ድረስ፣ እኛ ከማንም የፖለቲካ ፕሮግራማችን ከሚስማማ ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ ዝግጁ ነን፡፡ ችግሩ ግን አሁንም ከሴራ ፖለቲካ አለመውጣታችን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች አሁንም ከሴራ ፖለቲካ አለመውጣታቸው ያሳዝናል:: አዲስ ፓርቲ የመፍጠር ጥያቄ አቅርበው፣ ፓርቲዎች ማዋሃድ በሚል ህዝብን እያወናበዱ ነው፡፡ በዋናነት ግን ኢዴፓን የማጥፋት ፍላጎት ነው ያላቸው፤ ይሄ የፖለቲካ ሴራ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም እርስዎም በተገኙበት መግለጫ፤ ኢዴፓ ህልውናውንም ቢሆን አክስሞ ከሌሎች ጋር ለመዋሃድ ዝግጁ ነው ተብሎ ነበር ….
አዎ፤ አሁንም የኛ ፍላጎት እንደዚያው ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ችግሩን ቢፈታልን፣ራሳችንንም ቢሆን አክስመን ከሌሎች ጋር ለመዋሃድ ፍላጎት አለን:: አንድ የማረጋግጠው ነገር ቢኖር፣ እኛ መዋሃድን አልጠላንም፤ እንፈልገዋለን፡፡ ነገር ግን ውህደት ሲፈጠር በሴራ መሆን የለበትም፤ በሃቅና በህጋዊ አሰራር ነው መሆን ያለበት፡፡ እነ ፕ/ር ብርሃኑ፣ በ97 ምርጫ ላይ የሰሩት ስህተት እኮ ተመሳሳይ ነው:: ኢዴፓን በሴራ እጁን ጠምዝዘው ከህዝብ ልብ ለማጥፋት መሞከራቸው ነው ብዙ ዋጋ ያስከፈለው:: አሁንም ያንን ስህተት ለመስራት ነው እየሞከሩ ያሉት፡፡ ይሄ ካለፈው ስህተት አለመማር ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የሃገራችን የፖለቲካ ተሃድሶ ከተፈለገ፣ ከዚህ አይነቱ ሴራ መላቀቅ ያስፈልጋል፡፡  
አሁን በአጠቃላይ ተንኮል የሚሰራው መንግስትም ሆን ብሎ ኢዴፓን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ አግልሎታል፡፡ በመታገዱ የተነሳ በመንግስት ውይይቶች መሳተፍ እንኳ አልቻለም፡፡ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጪ እንድንሆን ነው የተደረግነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ፖለቲካ ውስጥ ከማንም በላይ ተሳታፊ መሆን ይገባው የነበረው ኢዴፓ ነው፡፡ የመቻቻል የድርድር፣ የምርጫ ፖለቲካ እንዲመጣና ስር እንዲሰድ የታገልነው እኛ ነን፡፡ ከማንም በላይ ይሄ እንዲመጣ በተግባር አሳይተናል፡። ከዚያ የተነሳም ብዙ መከራ አሳልፈናል፡፡ የኢህአዴግ ተለጣፊ እየተባልን መከራ አይተናል፡፡ ፅንፈኛ ፖለቲካ እንዲቀር ከማንም በላይ የታገልነው እኛ ነን፡፡ ነገር ግን አሁን እኛ ከፖለቲካ መድረኩ በስልት እንድንገለል ተደርገናል፡፡ ይሄ የኢህአፓ/ መኢሶን የሸፍጥ ፖለቲካ መቆም አለበት፡፡ ይሄ ካልቆመ የወቅቱ ለውጥም የውሸት ነው፤ ማታለያ ነው ማለት ነው፡፡ እኔ ከፕ/ር ብርሃኑ ጋር ያለንን ልዩነት ተነጋግረን እንድንፈታ ጠይቄያለሁ፡፡ በአምስት ስድስት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፊት ለፊት እንድንገናኝ ጠይቄያቸው፣ እምቢ ብለዋል፡፡ አሁንም ቢሆን እነዚህ ሰዎች ከእኛ ጋ በመድረክ ለመነጋገር ከፈለጉ ዝግጁ ነን፡፡ ነገር ግን በይፋ መድረክን እየሸሹ፣ የተንኮል ፖለቲካ ማካሄድ ከወቅቱ ጋር አይመጥንም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም ይህ አይነቱ ፖለቲካ ሰልችቶታል፡፡ ሁላችንም ወይ ጤናማ ፖለቲካ ማድረግ አለብን ወይ መተው አለብን፡፡ የሸር ፖለቲካን ለአዲሱ ትውልድ ማውረስ የለብንም፡፡
ሁሉም እኛን ለማጥፋት ነው የሚፈልገው ብለዋል፡፡ ይሄ ፍላጎት ከምን የመጣ ነው ብለው ያስባሉ?
በዋናነት ይሄን ጥያቄ መመለስ ያለባቸው ድርጊቱን የሚፈፅሙት ናቸው፡፡ ነገር ግን የኔ ግምት አንደኛ፣ እንደምናስታውሰው፣ ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ነኝ ብሎ አንዳንድ የአቋም ለውጦች እየወሰደ ነበር፡፡ ከሚወስዳቸው የአቋም ለውጦች አንደኛው፣ ወደ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲነት መቀየር እንዲሁም ወደ ሊበራል አስተሳሰብ የመምጣት አዝማሚያ ነው፡፡ ኢህአዴግ ወደዚህ ሲመጣ ኢዴፓ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ያን አጀንዳ የሚሻማው አካል በኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ማየት አልፈለገም:: አጀንዳችንን ብቻ አይደለም፤ ስማችንን ጭምር እየወሰዱ ነው፡፡ ለምሣሌ ኦዴፓ፣ አዴፓ እያሉ በቀጣይ ሲዋሃዱ ምን ሊሉት ነው? ኢህአዴግ ቢዋሃዱ ኢዴፓ ነው ሊሆን የሚችለው፤በፕሮግራምም በስያሜም፡፡ ኢህአዴግ ወደኛ መስመር መምጣት ሲፈልግ ከኛ ጋር መተባበርን ወይም ለኛ እውቅና መስጠትን አይደለም የፈለገው፤ እኛን አጥፍቶ የኛን አጀንዳ ወርሶ ነው ለመምጣት ያለመው፡፡  
ይሄ መንግስት የተለወጠ መንግስት ከሆነ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ማጣራት አድርጐ እርምት መውሰድ አለበት፡፡ በተቃዋሚዎች በተለይ በእነ ፕ/ር ብርሃኑ በኩል የአቋም ጉዳይ ነው፡፡ ኢዴፓ ባለበት የፖለቲካ መድረክ ተቀባይነት ማግኘት አንችልም፤ እነሱን ማጥፋት ስንችል ነው ተቀባይነት ማግኘት የምንችለው ብለው ደምድመዋል፡፡ ኢዴፓን እስከ መጨረሻው ለማጥፋት ነው ጥረታቸው:: ኢዴፓ እያለ እኛ በኢትዮጵያ ፖለቲካ መድመቅ አንችልም ከሚል ፍርሃት ነው እነ ፕ/ር ብርሃኑ እየሰሩ ያሉት:: በ97ም ያጠፋቸው ይሄው ነው፤ አሁንም የሚያጠፋቸው ይሄ አስተሳሰብ ነው፡፡ እነሱ ስለፈለጉ ግን እኛ አሁንም ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ መቼውንም ቢሆን አንጠፋም፡፡ ይሄ ኢዴፓ ቢጠፋ ሌላ ኢዴፓ ፈጥረን፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎአችንን እንቀጥላለን፡፡
በእርስዎና በፕ/ር ብርሃኑ ነጋ መካከል ያለው ችግር ምንድን ነው?
እኔ ከፕ/ር ብርሃኑ ጋር የሚያጣላኝ ግላዊ ምክንያት የለኝም፡፡ ችግሩንም በምንም መልኩ ግላዊ አድርጌ ወስጄው አላውቅም፡፡ ገና ኢዴፓን ስንመሰርት ፕ/ር ብርሃኑን የፓርቲው ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ጠይቄያቸዋለሁ፡፡ መሪያችን እንዲሆኑ ጠይቀናቸዋል፡፡ እኔ ለሳቸው የነበረኝ ፍላጐት ቀና ነው፡፡ እሳቸው ግን በተለይ ቅንጅት ውስጥ ከገቡ በኋላ ሌት ተቀን እኔን ከፖለቲካ መድረኩ በማስወገድ ስራ ላይ ነው የተጠመዱት፡፡ ውጪም ሀገር በነበሩ ጊዜ የደከሙት በዚህ ሥራ ላይ  ነው:: ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ጊዜም በስታዲየም ውስጥ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት በሌለው ሁኔታ የኔን ፎቶግራፍ ነው አዘቅዝቀው አስይዘው ሲቀሰቅሱብኝ የነበረው፡፡ ይሄን ሁሉ ቢያደርጉብኝም፣ ፕ/ር ብርሃኑ፣ ለኔ የአባቴ ገዳይ አይደሉም፡፡ የማውቃቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ነው፡፡ አቋማቸውን ካስተካከሉ፣ የሴራ ፖለቲካቸውን ካቆሙ ከእሳቸው ጋር መነጋገር ብቻ ሳይሆን አብሬ ለመስራት ዝግጁ ነኝ፤ ችግር የለብኝም፡፡ ህዝቡ ማወቅ ያለበት፣ እኔ ከፕ/ር ብርሃኑ ጋር የተለየ ጠብ የለኝም፡፡ እሳቸው ግን እኔን የአባታቸው ገዳይ አድርገው ማየታቸው ጥሩ አይደለም፡፡
በአጠቃላይ በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉትን የፓርቲ ውህደቶች በተመለከተ ምን ይላሉ?
አሁን ተባበሩ ተዋሀዱ የሚለው ጥያቄ ከመንግስትም ከህዝብም በከፍተኛ ሁኔታ ሲቀነቀን ይሰማል፡፡ ጥያቄው መነሳቱ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ከመጠን በላይ መለጠጡ አግባብ አይደለም፡፡ 97 ላይም ለችግር የዳረገን ይሄው ጥድፊያ ነው፡፡ በሰከነና ጥናትን መሠረት አድርጐ ነው ትብብርና ውህደት የሚያስፈልገው፡፡ ሁለተኛ መታወቅ ያለበት፣ በ97 ምርጫ’ኮ ያ ሁሉ ፓርቲ ባለበት ሶስት ቡድኖች ናቸው ጐልተው የወጡት፤ቅንጅት፣ ህብረትና ኢህአዴግ፡፡ ሌላው እንዳልነበር ነው የሆነው፡፡ አሁንም ትክክለኛ ምርጫ ከተደረገ፣ ነጥረው የሚወጡት ሃሳብ ያላቸው ብቻ ነው የሚሆኑት፡፡ በግፊትና በጫና የሚፈጠር ውህደት ጥሩ ውጤት የለውም፡፡ ውህደት በመርህ ላይ ካልተመሠረተ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው፡፡ ውህደትን እኮ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ያመጣው ኢዴፓ ነው፡፡ ኢዴፓ የአራት ፓርቲዎች ውህደት ነው፡፡ ስልጣንን አሳልፎ መስጠትን ያለማመደው ኢዴፓ ነው፡፡ ኢዴፓ ከፖለቲካ መድረኩ በህገ ወጥ መንገድ ተገፍቷል ተብሎ ይቅርታ ሊጠየቅ ይገባዋል፡፡ ኢዴፓ ሳይወድ በግድ ነው፣ አሁን ከሀገሪቱ ፖለቲካ የተገለለው፡፡ ይህን ህዝቡ ማወቅ አለበት፡፡ እኛ አሁንም ፓርቲያችንን ይዘን መቀጠል እንፈልጋለን፤ ካልሆነ ግን አዲስ ፓርቲ አቋቁመን፣ ወደ ፖለቲካ መድረኩ እንመጣለን፡፡  

Read 8141 times