Monday, 20 May 2019 10:51

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(4 votes)

  “ማንነትና የአዕምሮና የአስተሳብ ፀጋ ነው”
                 ጨዋታ መሆኑን እያሰብክ፣ የእናቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ አንድ “Mystic story” ብነግርህ ምን ይልሃል?
ሰውየው ምርጥ ሰዓሊ ነው፡፡ ውንብድና በተበራከተበት የአውሮፓ ከተማ የሚኖር፡፡ አንድ ስዕል ከጨረሰ በኋላ ወደ ገበያ ለማቅረብ ሲዘጋጅ ወይም ኤግዚቢሽን ለማሳየት ሲሰናዳ በአስገራሚ ፍጥነት ተመሳሳይ ስዕሎችና ኮፒዎች (duplica) የከተማውን የስዕል ሱቆች ያጨናንቁታል፡፡ በህግ ለመከላከል ቢሞክርም ከአቅም በላይ እየሆነ ልፋቱና ፈጠራው የወሮበሎች ሲሳይ ከመሆን አልተረፈም፡፡
ልጅ እያለ ወደፊት አስተዋይና ጎበዝ ሰው እንደሚሆን እናቱ ደጋግማ ነግራዋለች፡፡ የዚያኑ ያህል በመንገዱ እየተደነቀሩ፣ አላራምድ የሚሉ እሾህና አሜኬላዎች እንደሚበዙም አልደበቀችውም፡፡ እናትና ልጅ የተለያዩት ዕድሜው ባልጠናበት ዘመን ሲሆን አሁን አርባኛ ዓመቱን ይደፍናል፡፡
ሰውየው ዛሬ ወደ ሌላ ከተማ መብረር አለበት፡፡ … የማይቀርበት ጉዳይ አለው፡፡ ለመሄድ እንደተዘጋጀ የሳሎኑን በር ሲቆልፍ ከውስጥ በኩል ኃይለኛ ድምፅ ተሰማ፡፡ ተመልሶ ሲገባ ግርግዳ ላይ የነበረው የእናቱ ፎቶግራፍ ነበር ወለሉ ላይ የወደቀው፡፡ ባለመሰበሩ እየተገረመ ብደግ አድርጎ ሲደባብሰው፣ አንዳች ኃይል በደምስሮቹ ሲዘዋወርና ደስ ደስ የሚል ስሜት ሲወረው ታወቀው፡፡ ወዲያውም ጨርሶ ረስቶት የነበረውን፣ ሳያስተጓጉል ሲያከብረው የኖረው የልደት ቀኑ ዛሬ እንደሆነ አስታወሰ፡፡ ሁሌም በዚህ ቀን ከቤቱ አይወጣም፡፡
ጉዞውን በመሰረዙ እያዘነ ልብሶቹን ቀያይሮ፣ ከአቅራቢያው መደብር የገዛቸውን ሻማዎችና የሽቱ መዓዛ ያላቸውን ሰንደሎች ለኳኩሶ፣ እንደ ስቱዲዮ በሚጠቀምበት ሳሎኑ ውስጥ ተመቻችቶ ተቀመጠ፡፡ ዓይኖቹ ግን ከቴሌቪዥኑ ይልቅ ያተኮሩት እንደ ቀስተ ደመና ተለምጦ፣ ከአሮጌው ጣራ ጥግ ወደሚታይ የኮርኒስ ቀዳዳ የሚንዠቀዠቀው የሰንደል ጢስ ላይ ነበር፡፡ ጣሪያው ላይ ቀዳዳ መኖሩን እስከዛሬ ልብ ብሎ ዓይቶት ባለማወቁ ተገረመ፡፡ ወንበሩን ወደዚያው ጥግ በመውሰድ ቆመበትና ተንጠራርቶ ሲመለከት፣ ያጋጠመውን ማመን አልቻለም፡፡ .. የረቀቀ የሚስጢር ካሜራ ነበር፡፡ በሪሞት ኮንትሮል የሚሰራ፡፡ … ስዕሎቹ እየተቀረፁ የሚዘረፍበት:: ራሱን ይዞ መጮህ ቃጣው፡፡ ወደ እናቱ ፎቶ ሲመለከት … ፈገግ አለችለት፡፡
ካሜራውን እያገላበጠ ስለተቀዳጀው ድል ሲያወጣና ሲያወርድ ረዥም ሰዓት አሳለፈ፡፡ ከሃሳቡ የተቀሰቀሰው ወደ ሌላ ከተማ ለመብረር ቲኬት የቆረጠበት አውሮፕላን የበራሩ ቁጥሩ ተነግሮ፤ አደጋ የደረሰበት መሆኑ ከቴሌቪዥኑ ሰበር ዜና ሲሰማ ነው፡፡ ሳያስበው ከመቀመጫው ዘለለ፡፡ … “ምን ዓይነት ቀን ነው?” አለ፤ ጮክ ብሎ፡፡ አሁንም የእናቱን ፎቶግራፍ ትክ ብሎ ተመለከተ፡፡ … ትከሻዋን ነቀነቀችለት፡፡ እንደገና የተወለደ መሰለው፡፡ …
When the new sun comes to life
… the old moon dies.
Slowly, like racism, like yesterday.
መልካም የእናቶች ቀን!!
***
ወዳጄ፡- ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ‹ሰው ነኝ› ብሎ በማሰቡ ብቻ ሰው ነው፡፡ ማንነቱ የሚገለፀው ግን በሚፈፅመው ተግባርና በሚንፀባረቅበት ውስጣዊ ባህሪ ነው፤ … በሚያስመስልበትና በሚደልልበት ሳይሆን፡፡ “ሰው” ከሚለው ቃል ፊት ለፊት ወይም ጀርባ … ጥሩ፣ ባለጌ፣ ጎበዝ፣ አስተዋይ፣ ውሸታም ወዘተ … የመሳሰሉት ቅጥያዎች (prefix) ከሌሉ ‹ሰው› የሚለው መጠሪያ ድንጋይ፣ ወረቀት፣ አህያ … ከሚባሉ ስሞች አይለይም፡፡
ማንነት ሲባል ሰውየው የሚገለጥበት አስተሳሰብ (culture) ማለት ነው፡፡ ይህም ሰውየው ዓለምን የሚረዳበት የስልጣኔ አቅም ወይም ደረጃ፣ ባህሪ (ቀጠሮ አክባሪነት ወዘተ)፣ ግብረ ገብነት (ትህትና፣ አክብሮት ወዘተ)፣ ስራውን የመውደድና ያለመውደድ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ የአፈፃፀሙ ትጋት (ኃላፊነት፣ ዕውቀት፣ የጊዜ አጠቃቀም ወዘተ) እና የመሳሰሉትን ይጨምራል፡፡
“culture” የሰውየው የግል “ዋጋ” እንጂ ከዘር፣ ከጎሳ፣ ከብሔርና ከመሳሰሉት ጉዳዮች ጋር የጠበቀ ቁርኝት የለውም፡፡ “ባህላዊ ድርጊቶች የምንላቸው ልማዶች (custom, tradition) የሚጠሩት በማህበራዊ ዕድገት ጉዞ ውስጥ በታሪክ አጋጣሚ ተገናኝተው፣ በአንድ አካባቢ ለረዥም ጊዜ በሚኖሩ ሰዎች ነው” የሚል ጥናት አለ፡፡ ሲወርድ፣ ሲዋረድ ከሚወርሱት እምነት፣ ቋንቋ፣ የሰርግ፣ የሃዘን፣ የጨዋታ፣ የጠብ ወይም የግጭት፣ የአመጋገብ ሌሎች በጋራ የሚያዳብሩት መሰል ልማዶች ድግግሞሽ በተወሰነ የታሪክ ጉዞ ወቅት ለዚያ ማህበረሰብ እንደ መታወቂያና መለያ ያገለግላል፡፡ ለምሳሌ ራቁት መኖር፣ ጥሬ ስጋ መብላት፣ ጉግስ መጫወት ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ቋሚና ዘላቂ ሆነው አይቀጥሉም:: … በስልጣኔ ሂደት እየደበዘዙ፣ እስከነ አካቴው እስኪረሱ ድረስ ብቻ ይቆያሉ፡፡
ወዳጄ፡- ቀስት ማፈናጠርና በቫይረስ መውረር፣ መሳሪያ ተሸክሞ ጫካ ለጫካ፣ በረሃ ለበረሃ በመንከራተትና ድሮንስ አሰማርቶ በሪሞት ኮንትሮል በመቆጣጠር መሃከል ያለውን ልዩነት ስታስበው፣ ሃሳብህ ወይም አዕምሮህ የማንነትህ መገለጫ መሆኑን አትጠራጠርም፡፡
የፍራንክ ካፍካ “ሜታሞርፎሲስ”ን ጨምሮ የሰው ማንነት አእምሮው ወይም ሃሳቡ መሆኑን የሚገልፁ ታሪኮች ብዙ ናቸው፡፡ እነሱን መሰረት አድርገን የራሳችንን ምሳሌ እንውሰድ፡-
አንድ ሰው በመንገድ ሲሄድ አብሮ አደግ ጓደኛውን ወይም ጎረቤቱን አገኘ እንበል፡። ሰላምታ ሊሰጠው ወይም አቅፎ ሊስመው ሲንደረደር ሰውየው ግራ ይገባዋል፡፡ “ምነው ምን ሆንክብኝ … እገሌ አይደለህም ወይ?” ሲለው “አይደለሁም ተሳስተሃል ይለዋል፡። ለማስረጃም በቦርሳው የያዛቸውን የልጅነቱን፣ የቤተሰቡን፣ የልጆቹንና የጓደኞቹን ፎቶግራፎች እያሳየው፣ የሚሰራበትን የተማረበትን ት/ቤትና የሚኖርበትን አድራሻ በዝርዝር ሲነግረው ሌላ ሰው እንደሆነ ገባው፡፡ “አቤት መመሳሰል!” ብሎ ከማለፍ ሌላ ምን ያደርጋል?
ሌላ ጊዜ ደግሞ አንዲት ወፍ አናቱ ላይ እየበረረች ስሙን ጠርታ፣ አብሮ አደግ ጓደኛው መሆኗን ነገረችው፡፡ ስለ ቤተሰቦቻቸው፣ ስላሳለፉት ጊዜም በዝርዝር አስረዳችው፡፡ የሚጠይቃትን ሁሉ በትክክል እየመለሰች ወደ ወፍነት የተቀየረችበትን አጋጣሚም አብራራችለት፡፡ ጓደኛው “እንደሆነች” የሚያጠራጥር ነገር አላገኘባትም፡። አንተስ ወዳጄ፡- ማንነት አካልና የአኗኗር መገለጫ ሳይሆን የአእምሮና የአስተሳሰብ ፀጋ መሆኑን ትጠራጠራለህ?
ሠላም!!

Read 1477 times