Print this page
Sunday, 19 May 2019 00:00

ዶላር ያጠራት ዚምባቡዌ 98 ዝሆኖችን ለመሸጥ ተገድዳለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 - ለቻይናና ለዱባይ ከተሸጡት ዝሆኖች 2.7 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል
                            - የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት በመባባሱ ሚኒስትሩ ከስራ ተባርረዋል


                  ከፍተኛ የዶላር እጥረት ያጋጠመው የዚምባቡዌ መንግስት ችግሩን በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ በማሰብ 98 ዝሆኖችን ለቻይናና ለዱባይ በመሸጥ 2.7 ሚሊዮን ዶላር  ማግኘቱን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት ሙጋቤን ተክተው ወደ ስልጣን የመጡት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋዋ ያደጉ፣ አገራት ብድር እንዲሰጧቸው ሲለምኑ መክረማቸውንና የዶላር እጥረት መባባሱን ያስታወሰው ዘገባው፤ የዝሆኖቹ መሸጥ የዶላር እጥረትን ለመቅረፍ ጭንቀት የወለደው ውሳኔ ነው ቢባልም፣ የአገሪቱ የፓርኮችና የዱር እንስሳት አስተዳደር ባለስልጣን ቃል አቀባይ ግን ዶላሩ የዱር እንስሳትን ለመንከባከብ የሚውል ነው ሲሉ ማስተባበላቸውን ገልጧል፡፡
አንዱ ዝሆን ከ13 ሺህ 500 እስከ 41 ሺህ 500 ዶላር በሚደርስ ዋጋ መሸጡን የጠቆመው ዘገባው፤ የተሸጡት ዝሆኖች በቻይና እና በዱባይ ወደሚገኙ ፓርኮች መወሰዳቸውንም አመልክቷል:: በዚምባቡዌ ከ85 ሺህ በላይ ዝሆኖች እንደሚገኙ የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፤ ድርቅ መከሰቱን ተከትሎ ዝሆኖቹ የሚበሉት በማጣታቸው መንግስት ለምግባቸው ድጎማ ሊያደርግላቸው የቻላቸው 55 ሺህ ያህሉን ብቻ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ በዚምባቡዌ የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረትና መቆራረጥ በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱንና ህዝቡ ምሬት ውስጥ መግባቱን ተከትሎ፣ የአገሪቱ የኢነርጂ ሚኒስትር ጆራም ጉምብ ከስራ መባረራቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
ለሃይል መቆራረጡ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በምክንያትነት በመጥቀስ የሚታወቁትን ሚኒስትሩን በአጭር ደብዳቤ ከስራቸው ያሰናበቱት ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንግዋ፤ በቦታቸው የትራንስፖርት ሚኒስትር የነበሩትን ፎርቹን ቻዚን መሾማቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 1126 times
Administrator

Latest from Administrator