Tuesday, 21 May 2019 12:21

የአመቱ ባለብዙ ቢሊየነር አገራትና ከተሞች ይፋ ተደረጉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ዌልዝ ኤክስ የተባለው የጥናት ተቋም በፈረንጆች አመት 2019 በርካታ ቁጥር ያላቸው ቢሊየነሮች የሚገኙባቸውን የአለማችን አገራትና ከተሞች ደረጃ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ከአገራት አሜሪካ ከከተሞች ሳን ፍራንሲስኮ ቀዳሚነቱን ይዘዋል፡፡
ተቋሙ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው አመታዊ ሪፖርት እንዳለው፤ 705 ቢሊየነሮች የሚገኙባት አሜሪካ ከአለማችን አገራት በርካታ ባለጸጎች ያሏት ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ 285 ቢሊየነሮች የሚገኙባት ቻይና በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ጀርመን በ146፣ ሩስያ በ102፣ እንግሊዝ በ97፣ ስዊዘርላንድ በ91፣ ሆንግ ኮንግ በ87፣ ህንድ በ82፣ ሳዑዲ አረቢያ በ57፣ ፈረንሳይ በ55 ቢሊየነሮች እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሶስተኛ እስከ አስረኛ ደረጃን መያዛቸውንም ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
3 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርሰው የአሜሪካ ቢሊየነሮች አጠቃላይ የሃብት መጠን እስከ ዘጠኛ ደረጃ የያዙት ሁሉም አገራት ቢሊየነሮች ካላቸው ድምር የሃብት መጠን እንደሚበልጥ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ እስከ 15ኛ ደረጃ ያሉት አገራት 1 ሺህ 942 ቢሊየነሮችን ወይም የአለማችንን 75 በመቶ ቢሊየነሮች እንደያዙ ገልጧል፡፡ በእነዚህ 15 አገራት ውስጥ የሚኖሩት እነዚሁ ቢሊየነሮች በድምሩ 6.8 ትሪሊዮን ዶላር ሃብት እንዳላቸውም ጠቁሟል፡፡
ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት ላይ ከአለማችን ከተሞች መካከል ከህዝብ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቢሊየነሮች የሚገኙባት ከተማ ተብላ የተጠቀሰችው የአሜሪካዋ ሳንፍራንሲስኮ ስትሆን፣ ኒው ዮርክ፣ ዱባይ፣ ሆንግ ኮንግ እና ሎሳንጀለስ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

Read 1383 times