Print this page
Tuesday, 21 May 2019 12:41

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 ጸሎት- ለኢትዮጵያ
                               ግዛው ለገሠ


 አንተ የሰማየ-ሰማያት ምጥቀት፣
የእልቆ-ቢሱ ጠፈር ባለቤት፣
የድቅድቁ ጨለማ ውበት፤
አንተ የፀሐየ-ፀሐያት ፈጣሪው፣
የከዋክብት ብርሃን አፍላቂው፣
የህይወት ዑደት ዘዋሪው፤
አቤቱ ፈጣሪ ሆይ - ሕዝብህን አሁን አድን፣
አቤቱ ፈጣሪ ሆይ - ልመናችንን ስማን፣
የኋሊት መመልከትን - ተጠማዞ ማየትን፣
እንደ’ለት ግብር ወስደን - ብዙ ዘመናት ኖርን::
ግና አንገትም ደከመና - ጥምዝ መዞር ቢሰለቸው፣
ላለፈ ታሪክ ትርክት - የኋሊት ቁልምም ቢመርረው፣
ዓይን ቦታ ቀየረ፣
ከግንባር ነቀለና ከማጅራት ደኩኖ ከተመ።
እኛም የኋሊት ተቸንክረን - የፊት እይታችን አከተመ፤
የተፈጥሮ ሕግ ተዛብቶ - ራዕያችንን አ.ፀ.ለ.መ፡፡
አቤቱ ፈጣሪ ሆይ - ዛሬ ሕዝብህን አድን፣
ወደፊት ማየት አቅቶን - ወደፊት መሄድ ተሳነን፤
ለደንቡ ብንራመድም - ባለንበት ‘ረገጥን፡፡
አንተም እንደምታውቀው - እኛም ፅፈን እንዳነበብነው፣
የኋላ ታሪካችን - ብዙ ቀለማት አለው፤
ላንዱ ብሶት ቁጭቱ - ላንዱ ኩራት ጌጡ ነው፡፡
እንደ ቃልህ ነጋሪ - እንደ ጳውሎስ ‘ሚመክረን፣
                       ሁነኛ ሰው የታለን
                       የአዋቂ ምንዱባኖች ነን።
ኩራቴ ያለው ብራና - የገዛ ወንድሙን ሲያስከፋ፣
ቀዳዶ ‘ሚጥል ባይኖር፣
«ያለፈ አልፏል» ባይ - እንዴት አንድ ሰው ይጥፋ?!
የፊት ጨለማ ሕዝብህን - አቤቱ ፀሎቱን ስማው፣
የኛ ሰው ዓይኑ - ከኋላው ከማጅራቱ ነው፤
በ’ትየለሌ ጥበብህ - አንተው ቦታው መልሰው!

Read 3226 times
Administrator

Latest from Administrator