Sunday, 19 May 2019 00:00

ሃሳብና ተግባር ሲጣረሱ፤ መንፈስና ስሜት ሲፋለሱ

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)

 ሃሳብና ተግባር ሲጣረሱ፤ መንፈስና ስሜት ሲፋለሱ

                                         (በአቤል ተስፋዬ የዘፈን ስንኞች)
                                       
           በዓለም የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ፣ በስም ለመጠቀስ ብቻ ሳይሆን፣ በተወዳጅነት ለመታወቅ፤ ከዚያም አልፎ ወደ ዝነኞች ማማ ለመውጣት፣ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ለመድረስ መብቃት፣ የተዓምር ያህል እጅግ ሩቅ ነው፡፡ ኖቤል ተሸላሚ ሳይንቲስቶች፣ ባለ ሪከርድ የኦሎምፒክ ጀግኖች… ምን ያህል ጥቂት እንደሆኑ አስቡት፡፡ ከመቶ ሚሊዮን ሰዎች መካከል፣ ሁለት ወይም ሶስት ሰዎች ናቸው፣ በብርቅዬ ብቃት እንዲህ ዓይነት ድንቅ ስኬትን መቀዳጀት የሚችሉት፡፡
ከእነዚህ አንዱ አቤል ተስፋዬ ነው፡፡ ለምርጥ ዘፋኞች እጅግ ብርቅ የሆነውን አመታዊ የግራሚ ሽልማት ማግኘቱ ብቻ አይደለም ስኬቱ፡፡ ከሽልማቶቹ ሁሉ፣ ዋናውን ሽልማት ወስዷል፡፡ አልበሙ በቢልቦርድ ሰንጠረዥ አናት ላይ፣ ቁጥር 1 ለመሆን በቅቷል፡፡ ሁለት ዘፈኖቹም በየተራ በሽያጭ ብዛት ቀዳሚ ሆነዋል፣ የዘፈኖች ሰንጠረዥ ላይ በአንደኛነት ተፈራርቀውበታል፡፡
ከዋናው ዘፈን፣ ጥቂት ስንኞችን ቆንጥረን ብንጠቀም፣ አቤል ተስፋዬ የሚከፋው አይመስለኝም፡፡ ይህች ምናላት? እጅግ የባሰ መከራ ውስጥ እንደሆነ ነው አቤል በዘፈኑ ግጥም የሚያሳየን፡፡ መከራውም እለት ተእለት እየከበደ እንደሚመጣበት፣ የከፋ ዘመንም እንደሚጠብቀው ይነግረናል፡፡ የዘፈኑ አዝማች እንዲህ ይላል፡-
I can’t feel my face when I’m with you
But I love it …
አቤት የስሜቱና የመንፈሱ ርቀት! የድንዛዜ ባዶ ስሜትና የፍቅር መንፈስ! …. ቅንጣት ታህል ስሜት መስጠት ያቆመ ክፉ አመል፣ ሸክሙ ብቻ የቀረ ከባድ ሱስ የተጠናወተው ያህል፣ ከንቱ ስቃይ ሆኖበታል:: ሃሳቡና ተግባሩም ለየቅል ናቸው፡፡ በአንድ በኩል፣ የፍቅር መንፈስ አያስቀምጠውም፡፡ አብሯት ለመሆን ይወዳል፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? ከቁማር ፍቅር ብዙም አይለይም፡፡ የሚጓጓለት የቁማር ማዕድ ላይ ለመታደም ይሄዳል፤ ግን የሚቀመስ መብል የለም፡፡ መበላት ብቻ ነው፡፡ ባዶ ኪስ መመለስ፡፡ እንዲያም ሆኖ፣ ነገም ከነገ ወዲያም ወደ ቁማር ይሄዳል፡፡
እየተበላ ባዶ ኪስ የመቅረት ያህል፣ ስሜት አልባ ባዶ ድንዛዜም፣ አስቀያሚ እንጂ ተወዳጅ ነገር እንዳልሆነ አልጠፋውም፡፡ ያውቃል፡፡ “ነገር ግን” … ይላል ዘፈኑ፡፡
“But I love it …”
እንደ ሀሳቡ ቢሆን ኖሮ፣ ወደ ባዶ ድንዛዜ መሄድ አይፈልግም፡፡
በተግባር ግን ይሄዳል፡፡
መከራ ነው፡፡
ሃሳብና ተግባር፣ መንፈስና ስሜት፣ የስነ ምግባር መርህና ባሕርይ ሲጣጣም፤ ትርጉሙ አንዱ የሕይወት ገፅታ ሲለመልም፣ ሌላው ገፅታ ያብባል:: ከውስጥም ከውጭም ያማረ ይሆናል፡፡
“የአይን ብርሃን፣ ልብን ደስ ያሰኛል፡፡
ደስ ያለው ልብ፣ ፊትን ያበራል፡፡” ብሏል ጠቢቡ::
ድንቅ የሕይወት ጣዕም ማለት ነው - ሕይወትን ማጣጣም ማለት ነው፡፡
በተቃራኒው በአቤል ዘፈን እንደምናየው፣ መንፈስና ስሜት ሲፋለሱ፣ ሃሳብና ተግባር ሲጣረሱ ግን፣ … ከባድ ፈተና ነው፡፡ ስቃይም እንጂ፡፡ ኧረ ከዚያም የባሰ ሆኖበታል - ገና የከፋ ይገጥመኛል ይላል በዘፈኑ፡፡ አውቃለሁ፣ መጥፊያዬ ትሆናለች ይላል - መከረኛው፡፡
And I know she’ll be the death of me,
At least, we’ll both be numb,
And she’ll always get the best of me,
The worst is yet to come.
መጥፊያው እንደምትሆንበት፣ እድሜውን እንደምታሳጥርበት እያወቀም፣ እሷ ዘንድ መሄድን ይወዳል፡፡ እሷ እንደማትምረው ብቻ ሳይሆን እሱም እንደማያመልጣት፣ …ከእለት እለት የከፋ ህመም፣ የባሰ መዘዝ ይዛበት እንደምትመጣ እየገባውም፣ እለት ተእለት ይሄዳል፡፡ ይቅርብኝ አይልም፡፡ “አይጣል ነው!” ያስብላል፡፡ ገና ምኑን አይታችሁ! ከእሷ ጋር ገጥሜ ገና የባሰ ይጠብቀኛል፡፡ ግን ምርኮኛ ነኝ “… But I love it…” እያለ ይደጋግማል፡፡
ክፉ ሆና አይደለም፡፡ እንደ ቁማር፣ እንደ ሱስ ቁጠሯት፡፡ እያሳደደ የሚይዝ ሱስ የለም:: ከሄድክበት ግን አይምርም፡፡ ለጊዜው እያባበለ ምርኮኛ ያደርጋል፤ ይለመዳል፡፡ ለወግ ያህል አልያም በጊዜያዊ ስሜት ሰበብ ተጀምሮ፣ እንደ ዘበት ውሎ አድሮ፣ ቁራኛ ይሆናል፡፡ በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ከተተረጎመው “ሐምሌት” ትያትር ላይ ሶስት ስንኞችን እዩ …
ዛሬ ለወግ ያደረግሺው፣ … ወይ ለነገ
ይለምድብሻል፣
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል፣ ወይ
ያጠፋል
ከርሞም የሰለጠነ እንደሁ፣ ተፈጥሮ ይሆናል …
የአቤል ዘፈን ላይ፣ እንደ ክፉ ልማድ የተጠናወተው ነገር፣ የዋዛ አይደለም፡፡ “ወይ ይጠፋል” የተባለው አይነት ልማድ ሳይሆን፣ “ወይ ያጠፋል” የተባለው አይነት ክፉ ልማድ ነው የተቆራኘው፡፡
እያባበለ የሚወስድ፣ መጨረሻው የማያምር አመል ይመስላል፡፡ ከመጥፊያዬ ጋር ነው የገጠምኩት፤ ገና ብዙ የባሰ መከራ ይጠብቀኛል … እያለ ይጨነቃል፡፡ ግን በአንድ በኩል እንደ ማፅናናት ታባብለዋለች፡
she told me, “don’t worry about it” …
We both knew, we can’t go without it … ይላል፡፡
ለካ እሷ ብቻ አይደለችም መጥፊያ የሆነችበት:: እሱም መጥፊያ ሆኖባታል፡፡ በጋራ “ጥሎብን” እያሉ መጨረሻቸውን የሚጠብቁ ይመስላሉ፡፡ ሕይወታቸውን እለት ተእለት ይባስኑ እያጨለመ፣ እድሜያቸውን ከሚያሳጥር መጥፎ ልማድ ጋር ተቆራኝተዋል፡፡ ክፋቱ ደግሞ፣ ከአጥፊው ልማድ መላቀቅ አንችልም፤ ከዚህ አመል ተለይተን ቆመን መራመድ፣ ውለን ማደር አይሆንልንም እያስባላቸው ነው፡፡ ታዲያ እድሜያቸውን ማሳጠር ፈልገው አይደለም፡፡
እንደ ሀሳባቸውና እንደ ምኞታቸው ቢሆንማ ኖሮ፣ ከፍቅር መንፈስ ጋር የሚጣጣም የሚያነቃቃ ጤንነትን፣ ከሕይወት ጋር የሰመረ ልማድና ተግባርን እንደሚመኙ ነው ዘፈኑ የሚያሳየን፡፡   
ፍቅራቸው እድሜን የሚያሳጥር ሳይሆን የሚያስረዝም፤ እየሸረሸረ የሚያጠፋ ሳይሆን ሕይወትን የሚያለመልም እንዲሆንላቸው ነው ሃሳቡ፡፡ የሚያደበዝዝ፣ የሚያጠወልግ ፍቅር ሳይሆን፣ በአበቦች ወደ ተንቆጠቆጠ የደስታ መስክ የሚወስድ፣ አምሮ የደመቀ የእርካታ አምባ ላይ የሚያወጣ፣ ከመልካም ውድ ስሜት ጋር የሰመረ፣ በጐ ክቡር ፍቅር ለማግኘት ነው ምኞቱ፡፡
ወደ ባሰ መከራ ሳይሆን፣ ወደተሻለ የሚያመራ፣ ቢወድቅ እንኳ ተነስቶ የሚያንሰራራ ምሉዕ፣ የስሜትና የመንፈስ ስምረትን ቢያስብ ምን ይገርማል? መልካም ሃሳብ ነው፡፡ አይቀሬ መዘዞችን እየጐነጐነ ቁልቁል የሚጐትት፣ ወደ አይምሬ መቀመቅ ወርውሮ የሚፈጠፍጥ ፍቅርን ሳይሆን፤ የሕይወት መንገድን የሚያቃና፣ ከመቀመቅም ወደ እንጦሮጦስ የሚያወርድ ሳይሆን፣ ከፍ ከፍ ወዳለ ወደከበረ ሕይወት የሚያራምድ ፍቅርን ቢያስብ፣ ደግ ነው ሃሳቡ፡፡
ከሚያጨልም ይልቅ የሚያፈካ፣ የተሳከረ ሳይሆን የተስተካከለ፣ የጠመመ ሳይሆን የተቃና፣ ከክስረት ይልቅ የስኬት በረከት፣ ከባዶ ድንዛዜ ይልቅ የሚያነቃ የሕይወት ጣዕም፣ ከወረደ ይልቅ የከበረ መንፈስ ለሰው ልጅ ተገቢ ነው፡፡ ለድንቅ የሰው ተፈጥሮ የሚመጥን ሃሳብና ምኞት እንዲህ ነው፡፡
ግን ምን ዋጋ አለው? ከነባሩ ትክክለኛ ሃሳባችን ጋር በማይገጥም ነባር ልማድ ከተያዝን፣ ከበጐ አላማና ምኞት ጋር በማይስማማ የእለት ተእለት ተግባር ከተጓዝን፣ ከመልካም የፍቅር መንፈስ ጋር በማይጣጣም፣ ጣዕም የለሽ ድንዛዜ ከተመረዝን፣ ከባድ መከራ ውስጥ ገብተናል ማለት ነው፡፡
መከራው፣ ከቀን ወደ ቀን እየከፋ የሚመጣ በመሆኑም፣ መውጫ አሳጥቶ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሊሆንብን ይችላል፡፡ ነገር ግን፣ ከባድ ቢሆንም፣ ተስፋ አስቆራጭ እንጂ፣ ተስፋ የለሽ አይደለም:: “በማናመልጠው ቁራኛ ተይዘናል” ከሚያስብል ሁኔታ መውጣት ይቻላል፡፡
የፍቅር መንፈሱን፣ ልማዱንና የእለት ተእለት ተግባሩን፣ ከሃሳቡና ከስነምግባር መርሁ ጋር ለማስተካከልና ወደ ሰመረ ሕይወት ከፍ ለማለት ቀን በቀን መታገል ምን እንደሚመስል፣ “ደሞ መሸ፣ አምባ ልውጣ” በሚለው የሎሬት ፀጋዬ ግጥም አይተናል፡፡ ይሄ ጥረት ሲሳካ ምን እንደሚመስል ለማየት፣ አንድ ግጥም ብንጨምር መልካም ነበር፡፡ ለሌላ ጊዜ እናድርገው፡፡  

Read 1635 times