Saturday, 25 May 2019 09:10

ደቡብ ሱዳን በበጀት እጥረት 39 ኤምባሲዎቿን ልትዘጋ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


            በተለያዩ የአለማችን አገራት ውስጥ የሚገኙ ኤምባሲዎቹን ለማስተዳደር ከፍተኛ የበጀት እጥረት ያጋጠመው የደቡብ ሱዳን መንግስት፣ ወጪውን ለመቀነስ በማሰብ፣ 39 ኤምባሲዎቹን ለመዝጋት ማቀዱን ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል፡፡
የአገሪቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማዌን ማኮልን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ መንግስት በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኤምባሲዎቹን ወጪ ለመሸፈን የማይችልበት ሁኔታ ላይ በመድረሱ የተወሰኑትን ለመዝጋት ተገድዷል፡፡ ቃል አቀባዩ፤ የአገሪቱ መንግስት ያን ያህል ውጤታማ ስራ እያከናወኑ አይደለም ያላቸውን 39 ኤምባሲዎቹን በቅርብ ጊዜ እንደሚዘጋ ከመግለጽ ውጭ በየትኞቹ አገራት ውስጥ የሚገኙ ኤምባሲዎቹን ለመዝጋት እንደወሰነ ግን በግልጽ የሰጡት መረጃ እንደሌለ ዘገባው ገልጧል፡፡
የደቡብ ሱዳን መንግስት ከሳምንታት በፊት በስራ ገበታቸው ላይ አይገኙም፣ ስራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ አይደለም ያላቸውን 40 ያህል ዲፕሎማቶቹን ሙሉ ለሙሉና ለተወሰነ ጊዜ ከስራ ማባረሩንና ለኤምባሲ ሰራተኞችና ለዲፕሎማቶች ደመወዝ ለመክፈል ተቸግሮ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
አብዛኛውን ገቢ ከነዳጅ ሽያጭ የምታገኘው ደቡብ ሱዳን፣ የእርስ በእርስ ጦርነት ለአመታት መቀጠሉን ተከትሎ፣ የነዳጅ ምርትና ገቢዋ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም አገሪቱን ለከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ዳርጓታል ብሏል፡፡


Read 2093 times