Saturday, 25 May 2019 09:11

በአዲስ አበባ በህገወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶች ሊፈርሱ ነው

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

 ባለሀብቶችና ፖለቲከኞች እጃቸው አለበት ተብሏል
                                       
           በአዲስ አበባ ከአንድ ዓመት ወዲህ በህገወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶችን በሁለት ሳምንት ውስጥ ለማፍረስ የማጣራት ሒደት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ መስተዳድር አስታውቋል፡፡
ከመሬት ወረራና ህገወጥ የቤት ግንባታዎቹ ጀርባ ባለሀብቶችና ፖለቲከኞች እንዳሉበት ደርሼበታለው ያለው መስተዳድሩ፤ ቤቶቹ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኙ ነዋሪዎች ሊሰሩ እንደማይችሉ በማጣራት ሂደቱ መረጋገጡን ጠቁሟል፡፡
“ከተማዋን አስወርሬ ማለፍ አልፈልግም” ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ፤ ድርጊቱ ፖለቲከኞችና ባለሀብቶች መሬትን ባልተገባ መንገድ ለማግኘት ሆን ብለው የፈፀሙት ሴራ ነው ብለዋል፡፡
ህገወጥ ግንባታ የገነቡ አካላት ከገጠር ያመጧቸውን ሰዎች ከነልጆቻቸው በቤቱ ውስጥ እንዲኖሩ በማድረግ የክ/ከተማው አጣሪ ቡድን ሲሄድ “መውደቂያ የሌለን ነን” እያሉ የመንግስትን ገጽታ ለማጠልሸት ሙከራ እያደረጉ ነው ያሉት ከንቲባው፤ ይህንን እውነት ሚዲያዎች ለህብረተሰቡ በማስተላለፍ መስተዳድሩን እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡
በተለይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በርካታ ቤቶች በህገ ወጥ መንገድ መገንባታቸውንና የመሬት ወረራ መፈፀሙን፤ በክፍለ ከተሞች ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ፖሊስም ጭምር መረጋገጡን መስተዳደሩ ጠቁሟል፡፡
ጤናማ ከተማ ውስጥ የመኖር ህጋዊ መብት ያላቸው መሆኑን የተናገሩት ከንቲባው፤ በአዲስ አበባ ከተማ የህገወጥ ቤቶች ግንባታና የመሬት ወረራ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መጥቷል ብለዋል፡፡
በተለይም በቦሌ፣ በንፋስ ስልክ፣ በጉለሌ፣ በየካና በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተሞች ከፍተኛ የመሬት ወረራ መፈፀሙን መስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
ባለሃብቶች፣ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት፣ ደላሎችና የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ኃይሎች ጭምር ተሳትፈውበታል የተባለውን የህገወጥ ቤቶች ግንባታና የመሬት ወረራ የፈፀሙ ወገኖች ድርጊታቸውን አውቀው በሁለት ሳምንት ውስጥ ራሳቸው እንዲያፈርሱ መልእክት ደርሷቸዋል:: ይህንን የሚያደርጉ አካላት ላይ መስተዳደሩ ከማፍረስ በተጨማሪ እንደየ ደረጃቸው በህግ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡
የህዝብን ሃብት ከህገ ወጦች ለመከላከል የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ የገለፀው የከተማ አስተዳደር፤ ከመሬት ወረራና ህገወጥ ግንባታ ባሻገር የከተማዋን ሠላም በሚያውኩ ህገ ወጦችም ላይ ምህረት የለሽ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡

Read 1272 times Last modified on Saturday, 25 May 2019 09:33