Saturday, 25 May 2019 09:18

የ“ኢትዮጵስ” ጋዜጠኛ በፖሊስ ድብደባ እንደተፈፀመበት ገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 የ“ኢትዮጵስ” ጋዜጣ ከፍተኛ ዘጋቢ። በፀጥታ ኃይሎች ተደብድቦ መታሰሩን፣ ወከባና ዛቻ እንደደረሰበትም ተናገረ፡፡
ጋዜጠኛ ምስጋና ጌታቸው፤ አራት ኪሎ አካባቢ የሚገኙ ቤታቸው የፈረሰባቸው ነዋሪዎችን አነጋግሮ ዘገባ ለማጠናቀር ወደ አካባቢው ባቀናበት ወቅት በአምስት የፀጥታ ኃይሎች ተደብድቦ መታሰሩን ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
ገና በቦታው ደርሼ ለቀረፃና ለዘገባ መረጃ ማጠናከር ፖሊሶች ደርሰው ስራዬን በማስቆም፣ እያዋከቡና እየደበደቡ ለስራ ይዤው የነበረውን ካሜራና የእጅ ሰአቴን መንጠቅ ጀመሩ ያለው ጋዜጠኛው፤ ከዚያም በመኪና ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱን ተናግሯል፡፡
ፖሊስ ጣቢያ ውስጥም ለምን ያለ ፈቃድ ቀረፃ አካሄድክ የሚል ጥያቄ እንዳቀረቡለትና በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ስለሚመራው “የአዲስ አበባ ባለአደራ ም/ቤት” የሚያውቀውን መረጃ እንዲናገር መጠየቁን ገልጿል፡፡
በኋላም በጠበቃው አማካይነት ከፖሊስ ጣቢያ ምሽት ላይ በመታወቂያ ዋስትና መለቀቁን ጋዜጠኛው ተናግሯል፡፡

Read 8373 times