Saturday, 25 May 2019 09:33

አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን (Old Wine in a new Bottle)

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን አያ አንበሶ የዱር አራዊትን ሰብስቦ፣ “ዛሬ የጠራኋችሁ፤
1ኛ/ የምታከብሩኝን ከምትወዱኝ ለመለየት
2ኛ/ የምትፈሩኝን ከምትንከባከቡኝ ለመለየት
3ኛ/ የምታከብሩኝን፣ የምትወዱኝን፣ የምትፈሩኝንና የምትንከባከቡኝን ለማጣራት ነው፤
ስለዚህ ቦታ ቦታችሁን ይዛችሁ፣ ለመናገር ተራ በተራ እጃችሁን እያወጣችሁ ሀሳባችሁን ስጡ፡፡”
በመጀመሪያ ነብር እጁን አወጣና።-
“አከብርዎታለሁ እወድዎታለሁ”
አያ አንበሶም፡-
“አሃ፣ አትፈራኝም? አትንከባከኝም ማለት ነው? ታገኛታለህ!”
ነብር ዝም አለ፡፡
“ሌላ ሀሳብ?” አለ አያ አንበሶ፡፡
ዝሆን እጁን አወጣ፡-
“እኔ አያ አንበሶን በከፊል እወደዋለሁ። በከፊል እንከባከበዋለሁ”
አያ አንበሶም፡-
“በከፊል ሀሳብህ ደህና ነው፡፡ ነገር ግን እንደምታሻሽለው ቃል ግባ?!”
አያ ዝሆን፡-
“እንዳሉኝ አደርጋሁ ጌታዬ!”
ቀጥሎ ጅብ ተነስቶ፡-
“ጌታዬ አቶ አንበሶ፤ በጠሩኝ ቦታ ሁሉ እገኛለሁ፡፡ ያዘዙኝን ሁሉ እፈፅማለሁ፡፡ ያለ እርሶ ማን አለን? የሚለውን መርህ አከብራለሁ፡፡ ምንጊዜም እርስዎን እጠብቃለሁ”
የተለያዩት የዱር አራዊት የተሰማቸው ስሜት ላይ ተንተርሰው ሀሳባቸውን ሰጡ፡፡
አያ አንበሶ ግን በማናቸውም ስላልረካ፡-
“ጦጢትስ ምን ትያለሽ?” ሲል ሀሳቧን ጠየቀ፡፡
ጦጢትም፡-
“የእኔ አስተያየት፤ እራሳቸው አያ አንበሶ የትኛውን እንደሚፈልጉ ቢነግሩንና እፎይ ብንል ጥሩ ነው!”
ሁሉም በጦጣ ሀሳብ ተስማሙ!
*   *   *
አንበሳ የዱር አራዊት ንጉሥ ነህ ላሉት አራዊት፣ የበላይ መሆኑን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከረ ከመጣ ወዲህ ራሱም ሆነ ተገዢዎቹ ማመናቸው የማይታበል ሀቅ ሆኗል፡፡ ምናልባትም የማይነቀነቅ አምድ ሆኗል፡፡ የመጀመሪያው አንበሳ መቼ እንደነገሰ በታሪክ አይታወቅም ይሆናል! ምናልባት ለመመርመር የተጨነቀ ሰውም አይኖር ይሆናል፡፡ የአንበሳን የበላይነት ተምሳሌት ማድረግ ግን ዋና ነገር ነው፡፡ ተምሳሌትነቱ ለሰውም ጭምር መሆኑ አስደማሚ ነው፡፡ እያንዳንዱ የበላይ የየራሱ አንበሳ ነው ማለት የተሻለ አካሄድና እሳቤ ነው፡፡ እያንዳንዱ የየራሱ ንጉሥ ነው እንደማለትም ነው፡፡
አገራችን እስከ ዛሬ ያልወጣችበት አረንቋ የቢሮክራሲ ው - ጣ - ው - ረ -ድ ነው፡፡ አዳዲስ ተሿሚው ቢሮክራት አዲስ መሳሪያ እንዳገኘ ወታደር፣ አዲሱን ስልጣኑን ለመፈተሽ በአዲስ ጉልበት ይነሳሳል፡፡ ሆኖም አዲሱ ጉልበት አሮጌ ለመሆን ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ የተለመደው ቢሮክራሲ ዋጥ - ስልቅጥ ያደርገዋል፡፡ ያው ስርአት መልሶ አደባባይ ይወጣል፡፡ ህብረተሰቡም እንደነበረው አሮጌ ሥርዓት ያየዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ለውጥ - ለውጥ ሲባል የቆየው ሁኔታ ተመልሶ ጥሬ ይሆናል፡፡  ክቡም ቀለበት ዙሩን ይቀጥላል፡፡ ስለ ለውጥ በደቦ ማሰብ ቀላል አይደለም፡፡ በጥቂት አርቆ አሳቢዎች መመራት የሚበጅ አካሄድ ነው፡፡ ግባችንን ከወዲሁ መተለም፣ ለትልማችን አቅጣጫ መስጠት፣ አልሆን ቢል እንኳ ደግሞ ለመሞከር ዝግጁ መሆን ወሳኝ ነው!
ከሁሉም በላይ ግን ጉዞው ረጅም እንደሚሆን አበክሮ ማመን ያስፈልጋል፡፡ በጭፍን ማመንን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ “ያመኑት ፈረስ ጣለ በደንደስንም” አለመርሳት ነው፡፡” የአገራችን ህዝብ አንደበተ ቀና ይወዳል፡፡ ስለዚህም ጮሌ ተናጋሪ የመመረጥ እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ያን ስህተት ላለመስራት መትጋት ያሻናል፡፡ ከታሰበበት የማይሳካ ነገር የለም፡፡ እያንዳንዱ አደጋ የብራ መብረቅ የሚሆንብን አስቀድመን ችግሮች ከመወሳሰባቸው በፊት በጥልቀት ባለማሰባችን ነው፡፡ ችግሮችን ከመፍራት ይልቅ ለመፍታት የተዘጋጀ ጭንቅላት እንዲኖረን እንጣር፡፡ እንጠይቅ፡፡ እንመርምር፡፡ እንንቃ፡፡ ከደራሲ ከበደ ሚካኤል ጋር፤
“ለሁሉም ጊዜ አለው ብሏል ሰለሞን
እጠይቀው ነበር በተገናኘን
ሞት እራሱ እሚሞት ምን ጊዜ እንደሆን”… እንበል፡፡
“አትሙት ላለው መላ አለው” ሆኖ ነው እንጂ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሳሳቢ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ጥናት አቅራቢዎች በጥኑና ለዘላቂው ጉዞ መመልመልና ለውጥ አጋዥ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉን ነገር ፖለቲካዊ ማድረግ አያዋጣም፡፡ ፖለቲካ የኢኮኖሚው ጥርቅም መልክ ነው ይላሉ ፀሐፍት (Politics is the concentrated form of the economics እንዲል)፡፡
ተለወጠ ያልነው ነገር የጥንቱን የሚደግም ከሆነ፣ ወይም “ባለበት ሃይ” የምንል ከሆነ፤ ጊዜ እየገፋ ሲሄድ የበለጠ ኋላ ቀር እየሆንን ነው ማለት ነው፡። ፈረንጆቹ እንደሚሉት፤ Old Wine in a new Bottle መሆኑ ነው - ‹አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን›! ከዚህ ይሰውረን! ማስተዋያውንም ይስጠን! ለመፍትሄው ያዘጋጀን!  

Read 11213 times