Saturday, 25 May 2019 09:56

የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ፣ (ፖለቲካና ኢኮኖሚ በተናጋበት ዓለም)

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)


      1.   በአሜሪካ እና በቻይና ባላንጣነት በሚፈጠር ዓለማቀፍ ማዕበል ውስጥ፣ አገራችን መንገዷን ለማሳመር መጠንቀቅ አለባት፡፡
      2. ከቻይና ጋር በወዳጅነት መቀጠል፣ ፀረ አሜሪካ ዝንባሌን ደግሞ ማስወገድ ከመከራ ያድናል፡፡
የአገራት ህልውና፣ ፈታኝ የሆነበት ዘመን ላይ ነን፡፡
ዛሬ ዛሬ ኢትዮጵያን የመሰለ የአገር፣ ህልውናው ሲቃወስ፣ ራሱን ያድን እንደሆን እንጂ፣ ማንም አይደርስለትም፡። አጋዥ፣ ድጋፍ ሰጪ፣ ሸምጋይና አደራዳሪ ቢመጣ እንኳ ዋጋ የለውም፡፡ የአሜሪካ ድጋፍ፣ የአውሮፓ ህብረት እርዳታ፣ የዩኤን ሽምግልናና ድርድር፣ ስንት ዓመታቸው፣ ለሊቢያና ለየመን ምን ፈየዱ?
ይልቅ ከግራ ቀኝ፣ ላይና ታች፣ በየፊናቸው ቀውስን ለማባባስ የሚዘምቱ፣ ፀብ ፍለጋ የሚቅበዘበዙ መንግስታት ናቸው የበዙት፡፡ እንደ ሶሪያ የደርዘን መንግስታት መጫወቻ መሆንም አለ! ለትርምስ የሚውል መሳሪያና ገንዘብ ሞልቷል፡፡ “ጠብ ያለሽ በዳቦ” ለሚያሰኛቸው የአፍሪካና የአረብ መንግስታት፣ ሊቢያና የመን መጫወቻ አልሆኑም?
በየአቅጣጫው የአለም ፖለቲካ የተሳከረበት ዘመን ላይ ነን፡፡
ዛሬ ዛሬ የሃሳብ ትክክለኛነት ሳይሆን “የሃሳብ ብዝሃነት” ሆኗል - ተፈላጊው ነገር፡፡ ስልጡን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስርዓት በዘፈቀደ የሚከሰት፣ በዘፈቀደ ለዘላለም የሚሰነብት አስመስለነዋል፡፡  የስልጡን ፖለቲካ መሰረታዊ መርሆች (የግለሰብ መብትን የማስከበር መርህ፣ ሰርቶ የመኖር፣ ንብረት የማፍራትና የንብረት ባለቤት የመሆን መብት የሚከበርበት የነፃ ገበያ ሥርዓትን የማስፋፋት መርህ፣ እነዚህን እውን ለማድረግም፣ በሕግና በሥርዓት ፍትህን የሚያሰፍን፣ ሰላምን የሚጠብቅ የሕግ የበላይነትን የማጽናት መርህ) የሌላው ፖለቲካ ሁሉ መመዘኛነታቸው እየተሸረሸረ፣ ትርምስ የበረከተበት ዘመን ሆኗል፡፡
ያልተጠነቀቀ አገር ወዮለት፡፡ ለምን? የሚተራመሱና የሚፈራርሱ አገራትን ተመልከቱ:: (1) በጭፍን እምነትና በሃይማኖት ተከታይነት የሚያቧድኑ፤ (2) ሃብታምና ድሃ እያሉ፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ወይም ማህበራዊ ፍትህ በሚሉ ፈሊጦች፣ ዝርፊያን የሚጋብዙ፣ ውድመትን የሚቀሰቅሱ (3) መጤ እና ነባር እያሉ በብሔር በብሔረሰብ፣ በጎሳና በመንደር እያቧደኑ ለእልቂት የሚያነሳሱ የጥፋት ድምፆች የገነኑበት ዘመን ነው፡፡ ለዚያውም ቀን ከሌት ያለፋታ፣ ከሩቅም ከቅርብም ያለድንበር፣ እዚያው በዚያው የአሉባልታ ፉክክርን የሚያጧጡፍ፣ የጭፍን ውንጀላ እሽቅድምድምን የሚያጋግል፣ የሚያጋድል የሞባይልና የኢንተርኔት፣ የፌስቡክና የዩቱብ ዘመን ስለሆነ፣ ያልተጠነቀቁ አገራት ህልውናቸው ያበቃለታል፡፡
በቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ፣ በየአገሩ የኑሮ ቅሬታን የሚባባስበት ዘመን ላይ ነን::
አይነቱና መጠኑ ቢለያይም፣ ዛሬ ዛሬ፣ … የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ከዳር እስከዳር የዓለም አገራትን የሚያዳርስ በዋዛ የማይፈወስ በሽታ እየሆነ ነው፡፡
በዘጠኙ ሀብታም አገራት ውስጥ፣ በ25 ዓመታት ውስጥ የፋብሪካ ሰራተኞች ቁጥር ከ62 ሚሊዮን ወደ 47 ሚሊዮን መቀነሱን በማየት ብቻ፣ በፅኑ ህመም እንደተያዙ መገመት ይቻላል:: ባለፉት 10 ዓመታት፣ የአውሮፓ አገራት፣ ከ1% በላይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ተቸግረዋል፡፡ ገና ብዙ ያድጋል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የቻይና ኢኮኖሚም ከዓመት ዓመት እድገቱ እየተቀዛቀዘ ነው፡፡
የነፃ ገበያ መርሆች እንደወረት ቸል ቸል እየተባሉ፣ በዚያው ልክ የኢኮኖሚ ቀውስ የብዙዎቹ አገራት እጣ ፈንታ ሆኗል፡፡ መዘዙ ደግሞ ብዙ ነው፡፡
በየአገሩ ቅሬታ እየበረከተ፣ አለመረጋጋት እየበረታ፣ የሥራ አጥነት ወይም የኑሮ ችግር ለአመፅና ለግርግር ሰበብ እየሆነ፣ ወደባሰ ቀውስ የሚያስገባ አዙሪት እየበረከተ የመጣው አለምክንያት አይደለም፡፡
ከዓመት ዓመት እየጨመረ የሚሄድ እርዳታ ማግኘት ድሮ ቀረ!
ከኢኮኖሚ ውዝግብ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የፖለቲካ መዘዝ ደግሞ ሌላው ፈተና ነው:: በተለይ የአሜሪካ እና የቻይና የባላንጣነት ፖለቲካ እየከፋ፣ የጠላትነት ፍጥጫ እየተባባሰ ወታደራዊ አደጋዎች እየገነኑ መጥተዋል፡፡
መጥፎነቱ ደግሞ፤ በአሜሪካና በቻይና፣ በአውሮፓና በራሺያ፣ በህንድ እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ዙሪያ የሚፈጠሩ ፍጥጫዎች፤ መላውን ዓለም የሚያንገጫግጩ ናቸው፡፡ ከባላንጣነት ወደ ጠላትነት የሚሸጋገሩ ሃያል አገራት፣ ሌሎች አገራት ውስጥ እየገቡ የመፎካከሪያ ሜዳ፣ የግጭት መሞከሪያ፣ ጡንቻ ለመፈተሽና ለማሳየት የተኩስ መለማመጃ  ያደርጓቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሦስቱ መዘዞች እንድታመልጥ ከፈለግን፣ ፍቱኑ መድሀኒት፣ ቀድሞውኑ የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ቀውስን ማስወገድ ነው፡፡ የኢኮኖሚ እድገትን ከሚያደናቅፍ ማናቸውም ተግባር መቆጠብ ነው ቀናው መንገድ፡፡ ያኔ በሥራ አጥነትና በኑሮ ቅሬታ ሰበብ ወደ ባሰ የቀውስ አዙሪት ከመግባት መዳን ይቻላል፡፡
ሁለተኛ ነገር፣ የኢኮኖሚ እድገት እስካለ ድረስ፣ ከውጭ የሚመጣ እርዳታ ባይጨምርም እንኳ ችግር የለውም፡፡ ቢቀንስም ብዙ አይጎዳም:: ደግሞም፣ ከጠቅላላው ኢኮኖሚ ጋር ሲነፃፀር፣ የውጭ እርዳታ እየቀነሰ እንደሚሄድ ጥያቄ የለውም፡፡ የእርዳታ በሩ ይበልጥ እየጠበበ ከመሄዱ በፊት፣ ለጊዜው ተሯርጦ የተገኘውን ያህል እርዳታ ለመሰብሰብ መጣር ግን ይቻላል፡፡
ሶስተኛው መዘዝ፣ እየገነነ ከመጣው የአሜሪካና የቻይና ባላንጣነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የሁለቱ አገራት ፍጥጫ፣ ሰሞነኛ ፍጥጫ አይደለም፡፡ ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ፣ የዓለም አገራትን በጎራ ለማሰባሰብ የሚገፋፋ ሰፊ መዘዝ ነው - ባለረዥም እድሜ፣ ባለረዥም እጅ መዘዝ፡፡ በሁለት መሪዎች ስምምነትም ሆነ በሁለት ወር ድርድር መፍትሄ የማያገኝ ፍጥጫ ነው - የአሜሪካና የቻይና ባላንጣነት (ዘኢኮኖሚስት መጽሔት በዚህ ሳምንት እትም፣ Special report በሚል ስያሜ በልዩ ትኩረት የተዘጋጁትን ዘገባዎች መመልከት ይቻላል)፡፡
ዋናው ጥያቄ፣ ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት፣ ኢትዮጵያ ይህንን ዓለማቀፍ ማዕበል እንዴት ትወጣዋለች የሚል ነው፡፡  
ካሁን በፊት በተከሰተው ዓለማቀፍ ፍጥጫ ሳቢያ፣ ኢትዮጵያ ላይ ምን እንደተፈጠረ ይታወቃል:: ያ የቀድሞ የአገራችን አሳዛኝ ታሪክ፣ ዛሬ መደገም የለበትም፡፡ በዓለማቀፍ የሶሻሊዝም ማዕበል ምክንያት ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው የያኔው መከራ፣ አሁን የማስጠንቀቂያ ትምህርት ሊሆነን ይገባል፡፡ በመከራ የተገኘ ምክር ነው፡፡
ዘኢኮኖሚስት እንደሚለው፣ የዛሬ 75 ዓመት ገደማ፣ ዓለምን በሁለት ጎራ የከፋፈለ አስፈሪና አጥፊ የጠላትነት አሰላለፍ የተፈጠረው፣ በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ነው፡፡ የጠላትነት ፍጥጫውና ትንቅንቁ “ቀዝቃዛ ጦርነት” ተብሎ ቢሰየምም፣ ብዙ አገራትን አቃጥሏል፡፡
በአንድ ወገን ከአሜሪካ ጎን የተሳለፉ የምዕራብ አውሮፓ አገራት፣ ይብዛም ይነስ የግለሰብ ነፃነትን፣ የንብረት ባለቤትንና የሕግ የበላይነትን የሚያከብር የካፒታሊዝም ስርዓት የተስፋፋባቸው አገራት ናቸው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ፣ በራሽያ መሪነት፣ የምስራቅ አውሮፓ አገራትን የሚጠቀልል የሶሻሊዝም ስርዓት ነበረ - የግለሰብ ነፃነትን በማንቋሸሽ የሚኮራ፣ ንብረት በመውረስ የሚያቅራራ፣ የመንግስት አምባገነንነትን የሚያሞግስ ስርዓት፡፡
ኢትዮጵያ፣ ከ66ቱ አብዮትና ከ67ቱ መፈንቅለ መንግስት በኋላ፣ ሶሻሊዝምን አንግሳ፣ በአሜሪካ ላይ ጠላትነትን አውጃ፣ ወደ የራሺያ ጎራ በመቀላቀሏ፣ ኢትዮጵያውያን ብዙ አበሳ አይተዋል፡፡ የእርስበርስ ጦርነት፣ የአብዮተኞች ሽብርና ግድያ፣ ድህነት፣ ረሃብና ስደት በአገሬው ላይ ተፈራርቀውበታል፣ ላይ በላይም ተደራርበውበታል፡፡ ዛሬ፣ ተመሳሳይ ስህተት መደገም የለበትም፡፡
በእርግጥ የዘመናችን የአሜሪካና የቻይና ባላንጣነት፣ ከቀድሞው ይለያል፡፡ አዎ፣ የፖለቲካ ልዩነት፣ እንደቀድሞው ዛሬም የባላንጣነት መንስኤ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ጎልቶ የሚታየው የጠላትነት ሰበብ፣ በኢኮኖሚና በንግድ ዙሪያ የሚያጠነጥን ስለሆነ፣ በብልሃት ሊታለፍ ይችላል፡፡ እንዴት?
ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ቀውስን ማስወገድና አቅጣጫዋን ወደ እድገት ማስተካከል ከቻለች፤ እርጋታንና ሰላምን፣ ህግና ስርዓትን ማደላደል ከጀመረች፤ … በጣም የምትፈለግና የምትከበር ትልቅ አገር መሆን ትችላለች:: የኢኮኖሚ ዕድገትንም ሆነ ሰላምን ለማግኘት ደግሞ፤ የስልጡን ፖለቲካ መሰረታዊ  መርሆዎችን ለማስፋፋትና ለማፅናት መትጋት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ አነጋገር፣ በግለሰብ ነፃነት ላይ ተመሰረተ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መርሆች፣ ዋነኛ የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች እንዲሆኑ መጣር ይኖርብናል፡፡
ይህ ማለት ግን በአሜሪካ እና በቻይና የባላንጣነት ሽኩቻና ፍጥጫ ውስጥ ዘሎ መግባትና በማዕበል ግራ ወይም ቀኝ መላጋት ማለት አይደለም፡፡
የአሜሪካ ወይም የቻይና ጎራዎችን የመቀላቀል ግፊት ቢኖርም፣ በአንዱ ጎራ ለመጠቃለልና ሌላኛው ጎራ ላይ ጠላትነትን ለማወጅ የሚያስገድድ ሃይል የለውም፡፡ ኢትዮጵያ፣ በየትኛው ወገን ላይ ጠላትነትን እስካላራገበች ድረስ፣ አሜሪካም ሆነች ቻይና ቅር አይላቸውም፡፡  
በቻይና ላይ፣ ኢትዮጵያ የወዳጅነት እንጂ የጠላትነት ስሜት አይታይባትም፡፡ በዚሁ ሰክኖ መቀጠል ጥሩ ነው፡፡
በአሜሪካ ላይ ግን፣ በተለይ በዩኤን ስብሰባበዎችና ውሳኔዎች ዙሪያ፣ የኢትዮጵያ አቋምና ድምፅ፣ ብዙውን ጊዜ “ፀረ አሜሪካ” ሊባል የሚችል ነው፡፡ ከነቬኒዝዌላ፣ ከነ ኢራን አቋም ጋር የሚመሳሰል ፀረ አሜሪካ አቋም መያዝ፣ ትክክልም፣ ጠቃሚም አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ነባር ስህተት በጊዜ ማስተካከልና ማረም ይገባዋል፡፡

Read 8546 times