Print this page
Saturday, 25 May 2019 10:00

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሩጫ ኋላ ያሳፍረናል!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)

አንድ የቅርብ ወዳጄ በቅርቡ ያወጋኝን ነገር፣ ለሀሳቤ ማጎልበቻ ማሟሻ አድርጌዋለሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- ወዳጄ፣ ባለቤቱና የ10 ዓመት ወንድ ልጁ ሸንጎ ተቀምጠው ይወያያሉ። ልጅ ቁጣና ጩኸት አያስፈልገኝም፤በቀስታ ከተነገረኝ በቂ ነው ይላል- ለእናቱ፡፡ እናት ደግሞ ዓመሉን ካላሳመረ ቁጣ ብቻ ሳይሆን ቅጣትም እንደሚከተለው ታስጠነቅቃለች፡፡ ይኸኔ አባት መሃል በመግባት እንዲህ ይላል፡-
“ልጃችን በጣም ጨዋና የሚነገረውን የሚሰማ፣ ከህጻንነቱ ጀምሮ እግዚአብሄር የባረከው በመሆኑ፣ቁጣም ዱላም አያስፈልገውም፤በፍቅርና በምክር ይስተካከላል!”
ይሄኔ  ልጁ ሳቁን ለቀቀው፡፡ ስቆም አላበቃም፡፡ “ዶክተር ዐቢይን መሰልከኝ!” አለው፡፡
እንግዲህ የልጁን ንግግር ሥናስተውል፣ በህጻኑ ልብ ውስጥ ስለ ፍቅርና መወያየት ምስል የፈጠረው ዶክተር ዐቢይ ነው፡፡ ከዱላና ከሃይል ይልቅ በንግግርና በውይይት ችግር እንፍታ! የሚለው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነው፡፡ ይህ በራሱ በቀጣዩ ትውልድ ላይ የሚፈጥረው በጐ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡
በተቃራኒው ከጠቅላዩ ጋር የኛ ፀብ ደግሞ “ዶክተር ዐቢይ ለምን ጠመንጃውን ታቅፎ ዝም ይላል?! ይተኩስበት” የሚል ነው፡፡ እኛ አስተኳሾቹም፣ ይተኮስባቸው የሚባሉትም ነውጠኞች፣ የሰውየው ሀሳብ የገባን አይመስለኝም:: ነውጠኞቹ የፈቀዱትን ቢያደርጉ እንደ ቀድሞ ግንባር ግንባራቸውን የሚላቸው ስለሌለ መፋነን ይፈልጋሉ፡፡ እኛም እነዚያን ነውጠኞች ከመደራደር ይልቅ ግንባራቸውን ብሎ እፎይ ማለት ይሻላል  ብለን እናምናለን፤ ልዩነታችን ይህ ነው፡፡
እውነት ነው፤ መሪነት ለትችት የሚያጋልጥ መድረክ ነውና፣ የኛም መሪ ከዚሁ ማምለጥ አይችሉም፡፡ ተቺዎች ከትችት አልፈው፣ ትችትን የሚቀንሱ ሰዎች እንዳይበዙ መዳከራቸውን የሥነ አመራሩ ምሁር ጆን ሲ. ማክስዌል ይናገራሉ:: እናም ልቆ መገኘት ይገባል ይላሉ፡፡ “አንገትህን ወጣ ለማድረግ በምትሻበት ጊዜ፣ ሌላው ሊቆርጠው ይፈልጋል። ትችትና ዛቻ ልትሆነው ከምትችለው ነገር ሁሉ እንዲያግድህ አትፍቀድ!” በማለት ይቋጩታል፡፡ የኛ ሀገር ምክንያት የለሽ ነውጦችና ትችቶች ሲጦዙ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጆሮዋቸውን ደፍነው ስራቸውን የሚሰሩት ለዚህ ይመስለኛል፡፡ ይኸው ዓይናችን እያየ በርካታ ስራዎችን ያለማቋረጥ እያከናወኑ ነው:: የማታ ማታ እሳቸው መከበራቸው፣ ወሬኞች ደግሞ ማፈራቸው አይቀርም፡፡
ሰሞኑን የሸገር እራት ላይም ሰበብ እየፈለጉ የሚንጫጩ ሰዎች ቢኖሩም፣ ሰውየው ህልማቸውን እያቀላጠፉት ወደ ግባቸው እየገሰገሱ ነው፡፡ እውነት ለመናገር፣ የትችቱ መነሻና ግብም ውሃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ ሰውየው ራሳቸው አቅደው፣ በራሳቸው ራዕይ ዕቅዶችን ነድፈው፣ ከተማ ለማልማትና ሃገርን ከፍ ባለ ስፍራ ለማስቀመጥ ሲደክሙ “ከጎንዎ አለን!” ከማለት ይልቅ የራሳችንን ጉድጓድ እየቆፈርን፣ ለማሰናከልና ለማጣጣል መሯሯጥ ከትዝብት በቀር ትርፍ ያለው አይመስለኝም፡፡ ከተማችን ከቆሻሻ ተምሳሌትነት ወደ ውበትና ማራኪነት ማደጓ ነውር የሆነበት ምክንያት ለኔ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ዛሬ ይህ ያለ እረፍት የሚሰራው ስራ፤ ነገ የትውልድ ሀብትና ኩራት መሆኑን ዘንግተናል፡፡ ምናልባትም በተለያየ መንገድ በግፍና በገፍ ገንዘብ የሚሰበስቡ አኩራፊዎችን አሉባልታ ተከትለን፣ የገዛ ቤታችንን ለማፍረስ ወዲያ ወዲህ ማለታችን በእጅጉ ያለማስተዋል ይመስለኛል፡፡
ሲጀመር ሀገርና የሀገር ጉዳይ እንዲሁ በአውሎ ነፋስና በስሜት ላይ የተንጠለጠለ መሆን የለበትም:: ዛሬ ያለንበት ላይ ሆነን ትናንት ምን ይመስል እንደነበር፣ ሀገራችን ከነምናምኗ ፈርሳ ልትጠፋ የደረሰችበትን ሰቆቃና ሥጋት በቀላሉ መዘንጋት የለብንም፡፡ ከዚያ ጨለማና መደናበር ለመውጣት የተከፈለውን ዋጋና ዛሬ ላለንበት  የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ሽግግር ያደረሰንን ጠባብ መንገድ መካድ አይገባንም፡፡ ሰዎች ነውጥ ለመፍጠር ሲፈልጉ ከጀርባቸው ያለውን ምኞት ሳንፈትሽ “ሆ!” ብለን መውጣትና መከተል የለብንም፡፡ ብዙ ጊዜ፣ ጥቅማቸውን ያጡ፣ እንደ ቀድሞው ለመሆንና ለማድረግ አቅማቸውን የተነጠቁ ሁሉ ስለ ኪሳቸው እንጂ ስለ ሀገር ደንታ እንደሌላቸው ማወቅ አለብን፡፡
በምንም ተዓምር ትናንት በመመሳጠር፣ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ሀብት ያካበቱ ሰዎች፣ በጤናማው መንገድ “ተወዳድራችሁ ስሩ” ቢባሉ አይዋጥላቸውም፡፡ ይህንን ስል የህውሓትን ሰዎች ብቻ እንዳታስቡ! ከእነዚህ ሰዎች ጋር ተመሳጥረው ይሰሩ የነበሩ ጥገኞች፣ ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም:: እናም አሁን ያለው ለውጥ ለነርሱ አፈናፋኝ አይደለም፡፡ በዕውቀት ወይም በስልት በልጠው ማሸነፍ ስለማይችሉ፣ ዛሬ ከባለስልጣናት ጋር ተለጥፈው መስራትን ይፈልጋሉ፡፡ ጫማ ስመው ብራቸውን ለመቆለል ላይ ታች ይላሉ፡፡ ይህ መንገድ ደግሞ እየጠበበና እየተከለከለ ነው፡፡ ጠቅላዩ ብቻ ሳይሆኑ ሥርዓቱ አይፈቅድም፡፡ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች ኤቤቤ ደግሞ በዚህ በኩል የሚያኮራ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡
ዛሬ በሀገራችን ላይ በተለያዩ ቦታዎች የተፈጠሩ ግጭቶች መነሻም ስልጣንና ጥቅም ነው፡፡ በቂ ችሎታ ሳይኖራቸው፣ ከባለስልጣናት ጋር በመለጠፍ ስልጣን ያገኙ፣ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ነግደው ወይም ዘርፈው ብር ያገኙ ሰዎች በሮች ሲዘጉባቸው፣ ሌሎቹም ከተጠያቂነት ለማምለጥ እንዳበደ ውሻ ተቅበዝብዘዋል፡፡ በተለያዩ ቀዳዳዎች፣ በተለይም የብሔር ልዩነት በመጠቀም፣ አንዳንዴም ሃይማኖትን ተገን በማድረግ  ሀገሪቱን ለማናወጥ በርካታ የጥፋት ሴራዎች አሲረዋል፡፡
ጥቂት ነገሮችን በማጋነን፣ “በሬ ወለደ” በማለት ወዘተ ያልሞከሩት ነገር  የለም፡፡ ይሁን እንጂ በጥቂት መስዋዕትነት ትልልቅ አደጋዎችን ማምለጥ የተቻለው በግምት ጉዞ አይደለም፡፡ አርቆ በማሰብና በቂ ስሌት ተሠርቶበት፤ ቂምና ቁርሾ እንዳይኖር፣ ከፍተኛ ጥፋት እንዳይደርስ በማድረግም ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ የነገውን ትውልድ ህይወት ከስጋት ለማላቀቅም ጭምር መሠራቱ አይካድም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በሶማሌ ክልል ውስጥ የነበረውን ሆን ተብሎ ለብዙ ዓመታት እንደመጠባበቂያ የተዘጋጀውን የጥፋት ዓላማ በቀላሉ ማክሸፍ መቻሉ ነው፡፡ በልዩ ሃይል ስም ከፍተኛ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀና በቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት የሚመራው ቅልብ ጦር፤ ዘግናኝ ጥፋት እንዳያደርስ ለማክሸፍ የተሰራው ጥበብ የተሞላበት ስራ የሚደነቅ ነው፡፡ ምናልባትም ወያኔ መራሹ መንግሥት አከርካሪውን የተመታ ያህል የተዘረረው ያኔ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህን ለአብነት ጠቀስኩ እንጂ በየቦታው ለረዥም ዓመታት የታሰበባቸውና “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” በሚል ክፋት፤ “እኛ ከሌለን ሀገሪቱ መቀጠል አትችልም” በሚል መሠሪ ሴራ፣ በህዝቡ ውስጥ የተቀበሩ ፈንጂዎች ቀላል አልነበሩም፡፡ አሁን እንኳ ሰሞኑን የገቢዎች ሚኒስቴር ለኦቢኤን 58 ቢሊየን ብር የሰጠ አስመስለው፣ በባለማህተም ደብዳቤ፣ በማህበራዊ ሚዲያ የለቀቁት እነዚሁ ጥቅም የጎደለባቸው ሸፍጠኞችና ተላላኪዎቻቸው ናቸው:: ከዚያም ካለፈ አሁንም አጋጣሚውን ተጠቅመው ሥልጣን ለመያዝ የተጠሙ ሴረኞች፡፡
ይሁንና ዛሬም በለውጡ የተሰራውን ስራ በማቃለል፣ የግል ጥቅምና የስልጣን ጥም ያሰከራቸው ወገኖች፤ የትኛውንም ቀዳዳ ለመጠቀም ሲቅበዘበዙ ይታያል፡፡ አንዳንዶቹ ለህዝብ የተቆረቆሩ፣ የብሔራቸው ህመም ያመማቸው ቢመስሉም፣ ውስጣቸው ሲፈተሽ ግን ዐላማቸው ሆድና ስልጣን ነው፡፡ ባይሆን ኖሮ ሆድና ስልጣን ያላሰከረው፣ የህዝቡ ህይወት ግድ የሚለው ወገን ሲናገር፣ በጥንቃቄና ከሌሎች ጋር በሚያግባባ መልኩ እንጂ የቆጥ የባጡን እያነሱ ነገር በመለኮስ አይደለም:: እውነት ነው፤ አንድ ሰሞን በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የነበረው ንትርክ የሁላችንንም ልብ አሳዝኖት፣ በመሪዎችም ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርብን አድርጎን ነበር፡፡ ይሁንና ነገሮች እየሰከኑና መልክ እየያዙ ሲመጡ፤ ሁኔታዎች ይፋ ሆነው ተረጋግተናል:: ዛሬም “ሕግ ይከበር” የሚለው ጥያቄ ቢነሳ ክፋት የለውም፣ እኔም በግሌ ተቃውሞ የለኝም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩንም መቃወም ይቻላል:: ተቃውሞው ግን ተጨባጭና ምክንያታዊ መሆን አለበት፡፡ ሀገር የሚጐዳ፣ ወይም አንድ ወገንን የሚያገል ሥራ ሲሰራ፣ ያንን መነሻ በማድረግ መቃወም ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የሀኪሞቹን የሥራ ማቆም አድማ እንጂ ጥያቄ ማቅረባቸውንና ሠልፍ መውጣታቸውን እኔ በበኩሌ አልቃወምም፤ ምክንያቱም ጥያቄዎቻቸው በአብዛኛው አሳማኝ ናቸውና! ከዚያ ውጭ ግን ግራ የሚያጋቡ ጩኸቶች መጨረሻቸው ለጯሂዎቹም ሆነ ለእኛ ጥቅም የለውም፡፡ ስንጮህም ግባችን ምን እንደሆነ ማወቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡ እውነት ለመናገር፤ አሁን የፈቀደውን ያህል ብንናገር፣ የፈቀደንን ያህል ብንቃወም አንታሠርም፡፡ አንደበደብም። ጥፍራችን አይነቀልም፡፡ ወህኒ አንወረወርም፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ወደድንም ጠላንም ዓለም እየጮኸለትና  እያስተጋባው ያለው፣ እነ ቶማስ ጀፈርሰን የዲሞክራሲ ፈርጥ ያሉት ዐቢይ ጉዳይ፤ ሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲያዊ መብት እየተከበረ ነው፡፡ እንደ ልብ መናገር፣ እንደ ልብ መጻፍ! እኛ ግን ከዚህ አጥር የዘለልን ይመስለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን  መተቸት ብቻ ሳይሆን መሳደብ ጀምረናል፡፡ ለመሆኑ ሰውየውን ልንሰድብ የምንችልበት በቂ ምክንያት አለን? መተቸትስ  መሳደብ ነው? ያከበሩንን መሳደብ የኢትዮጵያውያን መገለጫስ ሊሆን ይገባል? ኢትዮጵያዊነት ምን ይመስል እንደነበር የምኒልክን ባለሥልጣናትና አጋፋሪዎች ህይወት ማየት ይበቃል:: ኢትዮጵያውያን እንከባበራለን፡፡ አሉላ - ገበየሁን፣ ራስ መኮንን - ምኒልክን ያከብሩ ነበር፡፡  
ለመሆኑ ጠ/ሚኒስትሩ በየትኛው ጉባዔ፣ በየትኛው ስብሰባ፣ በየትኛው መገናኛ ብዙሀን ቀርበው ሰድበውናል? ሰዎችን ከማድነቅና ከማከበር፣ ለሀገር አንድነት ከመዘመር በቀር ምን የሚያስከፋ ነገር ተናግረው ያውቃሉ? የሃይማኖት አባቶችን እንደ ልጅ ቀርቦ ማግባባትና ማስታረቅ ያሰድባል? የሀገር ልጆችን ከየታሰሩበት ወህኒ እያስለቀቁ ይዞ መምጣት ያስንቃል? ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የተከማቸ እሾህ እየለቀሙ ሌትና ቀን መባተት ወንጀል ነው? ይህ ትናንትን መርሳት ይመስላል፡፡ የሃይማኖት ተቋማትን በመከፋፈልና በማጋጨት፣ የፖለቲካ ቁማር ሲሰራብን የነበረበትን ጊዜ ለምን ቶሎ ረሳነው? ለምን ለትችት ቸኮልን? ትናንት በሺህ መንገድ ስንሰለል፣ በየመንገዱ ላይ በወታደር ስንሰደብ፣ “ለምን አየኸኝ” ተብለን ስንረገጥ  የነበረበትን ጊዜ መርሳት፣ የፈጣሪን ዐይን መውጋት ነው፡፡
በጣም በሰለጠነ መንገድ ራሱን ለህዝብ ቅርብ ያደረገ፣ ሃሳባችንን የሚሰማ፣ ምሁራንን ሰብስቦ “ሃሳብ ስጡኝ” የሚል የሰለጠነ መሪ ሲገኝ፣ ምላሹ ስድብ መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ ለመሆኑ ይህ ሰው ባይኖር ቀጣዩ ዕጣ ፈንታችን ምን ይሆናል? ብለንስ አስበን እናውቃለን? ቁርጡን ልንገራችሁና እንበታተናለን፤ እንተራረዳለን፡፡ ሁላችንም በየጐጣችን ስንቆም፣ ብሔሩን ሳይሆን ሀገሩን ወክሎ የቆመ ጠንካራ መሪ መሆኑን አትርሱ፡፡ ሥልጣን የጠማቸውም - የተጠሙትን ሳይጠጡ፣ ፅዋቸው በደምና በሰቆቃ እንደሚሞላ ሊያውቁት ይገባል፡፡  
ይህንን ስል ግን አሁንም መሳደብ ብቻ ሳይሆን ሥጋውን ቢበሉ ደስ የሚላቸው ሰዎች  ለምን ኖሩ? አልልም፡፡ እንደ ልባቸው የፈለጉትን ማድረግ፣ በፈለጉት መንገድ መዝረፍ የለመዱ ቢቃጠሉ አይገርምም፡፡ ጥቅም ነዋ! የማዝነው ከዚህ በፊት የጭቆና ቀንበር ተሸክመን፣ በመሳቀቅ እንኖር የነበርን ሰዎች፤ ዛሬም ወደ ኋላ ተመልሰን፣ የለውጡን ትሩፋቶች ለማጣጣል መሞከራችን ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ፌደራል ፖሊስ ባየን ቁጥር የሚያጥወለውለን ነገር ቀርቶ፣ ቀይ መለዮ ያደረገ ወታደር ሥናይ መንገድ ለመቀየር እግራችን የተሳሰረበትን ጊዜ እንዴት እንረሳለን? ዛሬ ጀግና መምሰል ቀላል ነው፡፡ ትናንት ግን የት እንደነበርን ህሊናችንና የሚያውቁን ይታዘቡናል፡፡  
ጋዜጠኞች የትናንቷን ኢትዮጵያ መርሳት የለባችሁም፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀላል አይደለም፡፡ እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ ርዕዮት ዐለሙ ላይ የደረሰውን ግፍና መከራ መርሳት ያለብን አይመስለኝም፡፡
ከዚህ ባሻገር ዛሬ አልፎ አልፎ የማያቸው ትችቶች፤ በራሳቸው በጠቅላዩ ገርነት ምክንያት የመጣ ይመስለኛል፡፡ ሁኔታቸውን ልብ ብሎ ላጤነ ሰው፣ የሀገራችን ሥነ ልቡና የገባቸው አይመስልም:: እኛ ሀገር በአደባባይ ላይ አንድን ሰው ስናደንቅ፣ ከጐኑ ያሉ ሰዎች ፀጉራቸው እንደሚቆም የገባቸው አልመሰለኝም፡፡ አንድ ጋዜጠኛ ሲደነቅ፣ ጐኑ ያሉ ሰዎችን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ጉዳይ የሀገራችንን ዐመል የገባን ሁሉ ስለምናውቀው፣ በጥንቃቄ የምንይዘው ስስ ብልት ነው፡፡ እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እኛ ፀሐፍት እንኳ አንዱን ስናደንቅ፣ ሌላው በማኩረፉ የምንቀበለውን ዋጋ ተምነን ነው፡፡
አንድ የታሠረ ሰው ስናደንቅ፣ ሌላ የታሠረ ሰው ያኮርፋል፤ ብቻ ተመሳሳይ ሞያ ወይም መደብና ሌላም ነገር ውስጥ የሚፈጠረውን እሳት ማጥፋት የሚቻለው ስም ባለመጥራት ነበር፡፡ የዚህ ቀላል የሚመስል ነገር ጦሱ ብዙ ነው፡፡ ከየአቅጣጫው ሰበብ እየፈለጉ በባላንጣነት ያቆማል፡፡ እናም ጠቅላያችን በራሳቸው ሰብዕና ባይመዝኗት ጥሩ ነው፡፡ በሽታው ከአስተዳደጋችን ጋር የተያያዘ ነውና ስሩ ሩቅ ነው፡፡
ምክንያቱም ለብዙዎቻችን ሀገር ሽፋን ናት፡፡ እኛን ከፍ ካላደረገች፤ እኛን ካልጠቀመች ሀገር ገደል ትግባ! ትፍረስ! የምንል እንበዛለን፡፡
ገጣሚ አበረ አያሌው በግጥሙ እንዲህ ብሏል፡-
አንዳንዱ ሀገሩን - በድስትና ኪሱ - ሰፍሮ ነው የሚያያት
ጨዋታ ነው ታሪክ - ተረት ነው ዝብዘባ - አጥንት፣ ደም፣ አያት፡፡
ሌላው ሜዳ ፈሶ - በውን እንዳልታየች - የያዕቆብ መሰላል
ባዶ ድስት ታቅፎ - የከበረች ሀገር - በህልሙ ይስላል::
ከዚህ ቀደም ያለፈውን የሀገራችንን ታሪክ ብንፈትሽ፣ አሁንም ያለንበትን ሁኔታ ብናስተውል ብዙ ጦስ የሚያመጣው ራስ ወዳድነትና ጥቅመኝነት ነው፡፡
በርካታ ጀግኖች በወደቁበት ሀገር የማዳን ጦርነት በማይጨውና በአድዋም ሠራዊት መካከል የዚህ ዓይነት ሰዎች ነበሩ፡፡ በብዛት ባይዋጡ ኖሮ ውጤቱ ሌላ ይሆን ነበር፡፡  አሁንም ይኖራሉ፡፡ ዋናው መከራ ግን ፍላጐታችን በብሔር ጥላ ሥር ሆኖ፣ ሌሎችንም ጨለማው ባህር ላይ ለመንከር ሲዳክር ነው፡፡ ዛሬ ለእኛ የሚያስፈልገን ዳቦና መጠለያ እንጂ መበላላት አይደለም፡፡ አሁንም ከአበረ አያሌው ጥቂት ስንኞች እንውሰድ፡-
ትልሰው ትቀምሰው - ምናምኒት ያጣች
በልጆቿ ክፋት - ወዟ ሁሉ ደርቆ- እንደ ጨው የነጣች!
ፍሬ ለግሞባት - ከብዛት ልትፈልግ - እልፍ ዘር በትና
እልፍ ሰይጣን በቅሎ - እልፍ ህዝብ ይፈጃል- በምርጦች ጐዳና!

Read 822 times