Saturday, 25 May 2019 10:03

ቃለ ምልልስ “ደፍርሶ ይጠራል የሚል ቸልተኝነት፣ አገርን ያፈርሳል”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  • እኛ የዚህ ዘር ነን ብለን ከምናስበው በላይ በእጅጉ የተቀየጥን፣ የተቀላቀልን ነን
                   • በየማሕበረሰብ ሚዲያው የሚራገበውን ተከትሎ መክነፍ ከህዝብ አይጠበቅም
                   • እግርና እጅ የሌለው አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲፈጠር መገፋፋት የለብንም
                   • መንግስት እርምጃ ወስዶ የጎበዝ አለቃውን ሁሉ ማስታገስ አለበት

        በጌምድር ተወልደው የቀድሞዋ መንቆረር የአሁኗ ደብረ ማርቆስ ውስጥ ነው ያደጉት፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በደብረ ማርቆስ ተከታትለዋል፡፡ በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አ.አ.ዩ) የታሪክ ትምህርታቸውን ተከታትለው፣ በ1965 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ከዚያም ወደ ይርጋለም ሄደው በይርጋለም ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፤ “በኔ ትውልድ ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል” የሚሉት አብዮት ሲፈነዳ፣ በደርግ ላይ ሸፍተው፣ ለ3 ዓመታት ያህል  በጫካ ውስጥ መሽገው አሳልፈዋል - የዛሬው እንግዳችን የታሪክ ምሁሩና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ፡፡
ትግሉ ከከሸፈ በኋላ አንዳንድ ጓደኞቻቸው ወደ ውጭ አገር ሲወጡ፣ ከፊሎቹ በወቅቱ እያየለ የመጣውን  የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ትግል መቀላቀላቸውን ያስታውሳሉ፡፡ እሳቸው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አሁንም በታሪክ ትምህርት ከተቀበሉ  በኋላ እዚያው በመምህርነት እስከ 1978 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡ በ1978 አጋማሽ ላይ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒኤችዲ) ለመሥራት ወደ አሜሪካ የተሻገሩ ሲሆን ለ27 ዓመታት “ምን አገር አለኝ” በሚል በስደት ቆይተዋል፡፡ ለመሆኑ ምን አገር አለኝ የሚያስብል ምሬት ውስጥ ያስገባቸው ምን ነበር? ይህንን ሁሉ ዓመት በአሜሪካ ምን ሲሰሩ ቆዩ? አሁንስ እዚህ መጥተው ምን እየሰሩ ይገኛሉ? ስለ ለውጡስ ምን ይላሉ? አገራቸውን በተመለከተ ተስፋና ስጋታቸው ምንድን ነው? በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ የሀዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም 7ኛ ዓመት አውደ ጥናት ላይ የተገኘችው  የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ  አነጋግራቸዋለች፡፡ እነሆ፡-               በ1978 ዓ.ም ሦስተኛ ዲግሪዎን ለመስራት ወደ አሜሪካ ከሄዱ በኋላ በዚያው ነው የቀሩት፡፡ ምን ነበር የገጠምዎት?
 በእርግጥ ፒኤችዲዬን ከጨረስኩ በኋላ ወደ አገሬ መጥቼ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ:: ትምህርቱን ጨርሼ ጓዜን ጠቅልዬ ወደ አገሬ ልመለስ ስል፣ እነዚያ 42 ትላልቅ መምህራን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባረሩ፡፡ በወቅቱ የነበረን ብቸኛው ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው:: አሉ የሉም የሚባሉት ደግሞ እነዚሁ መምህራን ነበሩ፡፡ አብዛኛዎቹም የኔ አብሮ አደግ ጓደኞቼ፣ በሀሳብም የምመሳሰላቸው ነበሩ፡፡ ነገሩ ሆን ተብሎ፣ መረጣው በጥንቃቄ ተካሂዶ ነው የተባረሩት:: ይሄ  አገር ሁሉ የሚያውቀው ሴራ ነው፡፡ ሰዎች ብሔር ተኮር ነው ይላሉ፤ እኔ ግን ኢትዮጵያዊነት ተኮር ነው እላለሁ:: ኢትዮጵያን የማጥቃት ዘመቻ ነው የተካሄደው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ማን ያራምዳል የሚለው እዚያው ዩኒቨርሲቲው ባሉ የህውሓት ደጋፊዎች ተጠንቶ ነው የተባረሩት፡፡ ዋናው የእነዚህ መምህራን ጥፋት፣ ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀናቸው ነበር:: ህወሓት መምህራኑን እንደ ትልቅ ተግዳሮት ነበር ያያቸው፡፡ እነሱን ካላስወጣን ዩኒቨርሲቲውን መቆጣጠር አንችልም ብለው ነው  በአንድ ደብዳቤ ያባረሩዋቸው፡፡  
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ አብዛኞቹ ጓደኞቼና በሀሳብ የምንመሳሰል በመሆናችን፣ የእኔም ዕጣ ፈንታ ከ42ቱ የተለየ እንደማይሆን ተገነዘብኩኝ፡፡ ከዚያ እዚያው አሜሪካ ተቀጥሬ ማስተማር ጀመርኩኝ:: ያለፉትን 27 ዓመታት ቨርጂኒያ፣ ክርስቶፎር ኒውፖርት ዩኒቨርሲቲ፣ በታሪክ መምህርነት ነው ያገለገልኩት፡፡ ግን  ከአገር ወጥቼ በሰው አገር መቅረቴ አብዝቶ ይቆረቁረኝ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ አገር ውስጥ ያለው የትምህርት ሁኔታ በምን ዓይነት አስከፊ ደረጃ ላይ እንዳለ እሰማ ስለነበረ፣ የሌላ አገር ዜጋ ግንባታ ላይ ጊዜዬን ሳጠፋ፣ አገሬ ላይ ትንሽ እንኳን አስተዋፅኦ ሳላደርግ እንዳልሞት እያልኩ አስብ ነበር፡፡ እናም እንደምንም ተጣጥሬ፣ አቅሙም ሲፈቅድልኝ፣ “ዩኤስ ፉል ብራይት ስኮላርስ” የሚባል ፕሮግራም አለ፡፡ ፕሮግራሙ አሜሪካን አገር ያሉ ምሁራን ሌላ አገር ሄደው እንዲያገለግሉ የሚፈቅድ ነው፡፡ እኔም በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ የፒኤችዲ ፕሮግራም ለማስጀመርና ለማጠናከር ነው ወደ ኢትዮጵያ  የመጣሁት፤እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም፡፡
ከለውጡ  በፊት ነዋ የመጡት?
አዎ! ለውጡ ገና እየተንቻቻ ነው የመጣሁት፡፡ ሁለቱን ዓመት በፉል ብራይት ስኮላርስ ፕሮግራም ቆየሁ፡፡ አንዱን ዓመት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከቨርጂኒያው ዩኒቨርሲቲ ጡረታ ወጥቼ፣ ወደ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ገብቼ  የጀመርኩትን የፒኤችዲ ፕሮግራም እያስቀጠልኩና እያጠናከርኩ ነው የምገኘው፡፡
ጠቅልለው ነው ወደ አገር ቤት የገቡት?
ቤት ንብረታችን እዚያው ነው፡፡ እኔና ባለቤቴ ነን የመጣነው፡፡ ሙሉ በሙሉ ከዚያ አልወጣንም:: ልጃችም እዚያው ናት፤ ትልቅና ራሷን የቻለች በመሆኗ እኛን አትፈልገንም፡፡ ስለዚህ እኔም ባለቤቴም ነፃነት ስላለን ጊዜው እስከፈቀደና አቅሙ እስካለ ድረስ እዚሁ እንቆያለን፡፡ በበኩሌ በፊት ውጭ ሆኜ፣ እዚህ ባለማገልገሌ ይቆጨኝ ስለነበር፣ ቀሪ ጊዜዬን እዚሁ ሳገለግል ባሳልፍ የአዕምሮ እርካታ ይሰጠኛል፤ ግን ከአሜሪካ ሙሉ በሙሉ ነቅለን አልመጣንም፡፡
42 መምህራን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲባረሩ ምን አገር አለኝ ብለው መቆጣትዎንና እዚያው መቅረትዎን ነግረውኛል፡፡ ኩርፊያዎንና ቁጣዎን በአደባባይ አውጥተው ተቃወሙ ወይስ በውስጥዎ አምቀው ያዙት?
የለም የለም! ያን ጊዜ እንዳልኩሽ፣ አንዱና ብቸኛው ቀጣሪ መንግስት ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህ  መንግስት አንድን ሰራተኛ ካባረረ፣ ያ ሰው፣ ቤተሰቡን ይዞ ጎዳና ላይ ልመና ነበር የሚወጣው፡፡ ይሄ ነገር እኔን ያንገበግበኝ ነበር፡፡ ህውሓቶቹም የፈለጉት  ይህንኑ ነው፡፡ እነዚህን ምሁራን አዋርደን አባርረን፣ ድጋሚ ግቢው እንዲህ ዓይነት ሰው እንዳይወጣበት እናደርጋለን ብለው ነው የተነሱት፡፡ ይሄ ነገር በእጅጉ አሳስቦኝ ስለነበር መጀመሪያ ያደረግሁት፣ እኔንና የማውቃቸውን በማሰባሰብ፣ እነዚህ ምሁራን ቢያንስ ከዕለት ችግር እንዲወጡ፣ የእነሱን እንዲህ መሆን ያየ ሌላውም ተሳቅቆና ተሸማቅቆ እንዳይቀር፣ እነሱን መርጃ ዓለም አቀፍ ድርጅት አቋቁመን ነበር፡፡ እኔ የተማርኩበት “ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢሊኖ”፣ ኢትዮጵያን የሚያውቅ የእኔም አስተማሪ የነበረበት፣ ፈንዱን ሆስት እንዲያደርግልን እሱን ለምነን፣ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገናል፡፡ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን ጉዳይ፣ የአካዳሚ ነፃነት መገፈፍና ምሁራን እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው፣ ለዚህ ችግር መዳረጋቸውን የሚያጋልጥ ብዙ እንቅስቃሴም አድርጌያለሁ፡፡
ይህን ሁሉ እንቅስቃሴ  ህወሓት/ኢህአዴግ ያውቅ ነበር ማለት ነው?
በሚገባ ያውቃል እንጂ፡፡ እንደውም እኔና ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ “ኢትዮጵያ ሬጅስተር” የተሰኘ አንድ መፅሔት እናሳትም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሁኔታው በእጅጉ አስግቶን ነበር፡፡ አገሪቱም እንደ አገር ትቀጥል ይሆን የሚለው ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብን  ስለነበረን፣ ምናልባት በትንሹም ቢሆን ቢያግዝ ብለን ነው መጽሔቱን የጀመርነው:: መጽሔቱ ለአምስትና ስድስት ዓመት ያህል እየታተመ ቀጥሏል፡፡ በዋናነት የኢትዮጵያን አንድነት የሚያንጸባርቁ ሃሳቦች፣ በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው ግፍና ሰቆቃ ለንባብ የሚበቃበት ነበር፡፡ እኔም “ኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ የታወጀ ጦርነት” የሚሉና  ሌሎች ከ20 በላይ ፅሁፎችን በመፅሔቱ ላይ አስነብቤያለሁ፡፡ አብዛኛው ጽሁፍ  ከውጭ ቢመጣም፣ እዚህ ታትሞ እየተሸጠ የተባረሩትን መምህራን ለመደገፍ ዓላማ ነበር የሚውለው፡፡ በዚያ መፅሔት በኢትዮጵያና በህዝቧ ላይ የተጋረጠውን አደጋ፣ የህውሓት አጀንዳ ምን እንደነበር ሁሉ ሳጋልጥ ነው የቆየሁት፡፡
እርስዎ ወደ አገር የገቡት ለውጡ ሳይመጣ  በ2009 ዓ.ም ነው፡፡ በውጭ ሳሉ የሚያራምዱት  አቋም ደግሞ ይታወቃል፡፡ ወደ አገር ቤት ሲገቡ የደረሰብዎት ተፅዕኖ ወይም ችግር የለም?
እኔ ወደ አገር ቤት በመጣሁበት ሰዓት ውጥረት ነበር፡፡ ህወሓቶችም ሌላ ጠላት ስላፈሩ፣ እኔን በወቅቱ ልብ አላሉኝም፡፡ የአምባገነን ባህሪ ይሄው ነው፡፡ ደርግም አምስትና ስድስት ተከታታይ ጠላቶች ነበሩት፡፡ መጀመሪያ ኢህአፓ ቀጥሎ መኢሶን፣ ከዚያም ሰደድ--እንዲህ እያለ ነው በጠላት የተከበበው፡፡ ህወሓትም እኔ በመጣሁ ጊዜ ዙሪያውን ውጥረት ላይ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ እኔም ይህንን ፈርቼ ከዚያ በፊት መምጣቴን አላቆምኩም፤ እየመጣሁ እመለስ ነበር፡፡ ለመኖር ባልመጣም አገሬን ለማየትና ዘመዶቼን ለመጠየቅ ሦስትና አራት ጊዜ መጥቼአለሁ፡፡ መጨረሻም ላይ ስመጣ የደረሰብኝ  ነገር የለም፡፡ በእርግጥ አንዳንዴ ስለ እኔ የሚፅፉት ነገር ነበር፤ በኢ-ሜይሌም የሚመጣ ያልተገባ ነገር ነበር፤ ግን ብዙም ከቁም ነገር አልቆጠርኩትም፤ አልፈራኋቸውም፡፡ በህይወቴ ብዙ ትላልቅ ፈተናዎችን ስለተጋፈጥኩና ስላለፍኩ፣ የሚያስደነብረኝ ነገር አልነበረም፡፡ በእኔ እድሜ ያለና በቀይ ሽብር ዘመን ያለፈ፣ ይሄኛውን አክብዶ አያየውም፡፡ ያንን አልፈን በህይወት መቆየታችንንም እንደ ተዓምር ነው የምንቆጥረው፡፡  
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሀዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ማዕከል 7ኛ ዓመት ጉባኤ  ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ ታላቁ ደራሲና ዲፕሎማት ሀዲስ አለማየሁ ለአገራቸው ችግር መፍትሄ ለማምጣት ያደረጉትን ትግል አስመልክተው ባቀረቡት ጽሁፍ፣ ከወቅቱ የአገራችን ጉዳይ ጋር በማነጻጸር “ደፍርሶ ይጠራል በሚል ቸልተኝነት መቆየት አገርንና ህዝብን ወደ መደርመስ የሚወስድ ቁማር ነው” ብለዋል፡፡ እስቲ ይሄን  ያብራሩልኝ …
የእኔ ስጋት ምን መሰለሽ---አሁን ካለው እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ አልፎ ወደ ማይመለስበት የመደርመስ ደረጃ ይደርሳል የሚል ነው፡፡ ከደፈረሰማ ቆየ እኮ:: መቼ ነው የሚጠራው? እየደፈረሰ የሚቆየውና የሚራዘመው ነገር በወቅቱ እልባት ካልተሰጠው፣ ወደ መደርመስ መሄዱ አያጠያይቅም፡፡ አሁን ችግሩ ምንድን ነው ያልን እንደሆነ፣ ብዙ ሰው አገር ተደርምሶ አይቶ ስለማያውቅ፣ በዚያ ጉዳይ ላይ ያለው ጥንቃቄ አነስተኛ ነው፡፡ ወደ መሰላቸትና መማረር ብቻ ነው ያዘነበለው፡፡ እርግጥ ነው ያለው ነገር ያማርራል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በእጅጉ ሳስታለች፡፡ ተቋማቷም ሳስተዋል፡፡ የመደርመስ አደጋ ያጋጠመው እንደሆን መልሶ የማቃናት እድላችን እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡ ምናልባት በእድሜዬ መግፋት የተነሳ ፍርሃቱ ለእኔ በርትቶ ታይቶኝ ይሆናል፡፡ የአንዳንድ አገራትን ዕድልና እጣ ፈንታ ቀረብ ብዬም ስላየሁት ከዚያም የመነጨ ሊሆን ይችላል፤ የኔ ፍርሃት፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ወድቆ መነሳት በጣም ነው የሚያስቸግረን፡፡ በጣም አዘንብለናል፡፡ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው፣ አሁን ያለንበት ችግር ከመስመር አልፎ ወደ ማንመለስበት ደረጃ እንዳይደርስ፣ በተቻለው ሁሉ ደግፎ ማቆየት አለበት፡፡ ይህንን ስል አሁን ያለው ሁኔታ ይቀጥል ማለቴ አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ልንቀጥል አንችልም:: ነገር ግን ለለውጥ እየታገሉ፣ ሁኔታው ወደ መፍረስ እንዳይሄድ ጥንቃቄ ማድረግ  ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሁለት መንታ ትግል ሊኖርብን ነው ማለት ነው፡፡ ይህ መንታ ትግል ሁኔታው እንዲለወጥ እንፈልጋለን:: ለውጥ ካልመጣ፣ ከዚህ ሰቆቃ መውጣት አንችልምና:: ነገር ግን እስከዚያው ድረስ እግርና እጅ የሌለው አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲፈጠር መገፋፋት የለብንም:: አሁን የማያቸው የመንጋ አስተሳሰቦች፣ ለሌላው ሰው መብትና ህይወት ግድ የማጣት ጉዳዮች በመጨረሻ ወደሚያባላ ደረጃ ይደርሳሉ፡፡ ብዙ ሰው እነዚህን ግዴለሽነቶች እየተጋራና ከጨዋነት እየራቀ ሳየው ስጋት ያድርብኛል፡፡ ጭካኔና ግዴለሽነት እየተስፋፋ ነው፡፡ በፍርሻ ደህና ነገር ይመጣል የሚል አስተሳሰብ እየተስፋፋ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ኃይል ሊመከር ይገባዋል፡፡ በጎሳና በጎጥ የተሰባሰቡትንም ያየሽ እንደሆነ፣ ከመፍረስ የተሻለ ነገር ይመጣል ብለው የሚያስቡና የሚጠብቁ ናቸው፡፡ እርግጠኛ ሆኜ የምነግርሽ፣ ከእነዚህ ሰዎች 99.9 በመቶው፣ ነገ የሚፀፀቱና የሚያዝኑ፤ አንገት የሚደፉ ናቸው:: የመከራው ከፍተኛው ቀስት በእነሱ ላይ ነው የሚያነጣጥረው፤ ገፈት ቀማሽም ናቸው፤ ነገር ግን አሁን አይታያቸውም፡፡ ይሄ ነገር ቀድሞ የሚታየው ሰው፣ ከፍ ብሎ መጮህ አለበት፡፡
አሁን በአገሪቱ ላይ ለተፈጠረው ቀውስ ጽንፈኛ ብሔርተኝነት በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡  እርስዎ ምንድነው የታዘቡት?
አሁን አሁን ህዝቦች በአንድ ላይ መኖራቸውን እንደ መበለጥ፣ የተለያዩ ጎሳዎች መጋባታቸውን እንደ ነውር የሚቆጥሩ ሰዎች እያየን ነው፡፡ ይህ እንደ ኢትዮጵያዊነት አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ ብዙ  ሰዎች ያለ ሀፍረት፣ ብዙ ሰው በሚያየውና በሚያዳምጠው ሚዲያ፣ ልጆች ሁለት ቋንቋ ቢናገሩ ጉዳት ላይ እንደሚወድቁ እየተናገሩ ነው፡፡ ይሄ መቼም የናዚ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሰው ሰለጠነ የሚባለው እይታው እየሰፋና እየተደባለቀ በሚሄድበት ጊዜ ነው፡፡ እንደዚህ ያለውን ሰርገኛ ጤፍ የሆነ ህዝብና አኗኗራችንን እናጥራው ከተባለ፣ ከፍተኛ ሰቆቃ ውስጥ ነው የምንገባው፡፡ ልንለያይ ልንነጣጠል እንደማንችል፣ ከኛ በፊት የነበሩት  አውቀውታል፡፡ እንለይ ብለው የተነሱትም ምን ያህል ጥፋት ላይ እንደወደቁ አይተናል፡፡ አንድ ሰው እሳት እንደሚያቃጥል ለማወቅ እጁን እሳት ውስጥ መማገድ አይጠበቅበትም፡፡ ሌሎቹን አቃጥሏቸው ጠበሳቸውን አይቷላ! ከዚህ በፊት በዘረኝነት ምክንያት ፈርሰው፣ ታሪካቸው ላይ ጥቁር አሻራ ጥለው ያለፉ አገሮችንም እናውቃለን አይደለም እንዴ!? ይሄ እየታወቀ ለምን በእኛ ላይ እንሞክረዋለን፡፡ አሁን እያየሁት ያለው  ችግር፣ ነውረኛውን ነውረኛ ያለማለት አባዜ ነው፡፡ የራሱን ነውረኛ ጭራሽ ደብቆለት፣ ነውረኛ እንዳልሆነ ያደርገዋል፡፡ ሰዎች አይጋቡ፤ ልጆች ከተለያዩ እናትና አባቶች አይፈጠሩ ማለት በዚህ በሰለጠነ ዘመን፣ ነውርና ፀያፍ ነው፡፡
አፍሪካው  ከአውሮፓው፣ ኤዥያው ከምዕራቡ እየተጋባ ዓለም በደም እየተሳሰረ ነው፡፡ በተለይ የእኛን ታሪክ ቢያጠኑት፣ የዚህ ዘር ነኝ ብሎ መናገር፣ ሞኝነት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም እኛ የዚህ ዘር ነን ብለን ከምናስበው በላይ በእጅጉ የተቀየጥን፣ የተቀላቀልን ነን፡፡ እኔ ንፁህ አማራ ነኝ፣ እኔ ንፁህ ኦሮሞ ነኝ የሚል አላዋቂ  ብቻ ነው፡፡ ያ እንዳልሆነ በታሪክ የምናውቅ እናውቀዋለን፡፡ ልጆች ሁለት ቋንቋ መናገራቸው ጉዳት አለው የሚለው አነጋገር፣ ከድንቁርና የመነጨ ነው፡፡ የቋንቋ ሊቃውንት እንደሚሉት፤ አንድ ልጅ ሁለት ቋንቋ ካወቀ፣ ከየትኛውም ልጅ የበለጠ በተለይ አንድ ቋንቋ ከሚናገረው የላቀ ተፎካካሪ ይሆናል፡፡ በልጅነታቸው ሁለት ቋንቋ የሚናገሩ ልጆች፣ የአንዱን ስታይል ወደ ሌላው የመዋስና የማሸጋገር እድልና ክህሎት ስለሚኖራቸው፣ አንድ ቋንቋ ከሚናገረው የበለጠ አንድን ነገር የመግለፅና የማስረዳት አቅማቸው በእጅጉ የላቀ ነው፡፡ ይሄ በሳይንስ የተጠናና የተረጋገጠ ነው፡፡ ሁለት ቋንቋ መናገር ጉዳት አለው ማለት ወንጀልም ነው፤ ምክንያቱም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተቀላቀሉ ቤተሰቦች ላይ መፍረድም ነው፡፡ በአብሮነት በመቻቻልና በመደጋገፍ የኖረውን ማህበረሰብ እሴትም መናድ ነው፡፡ አሁን እያየን  ያለነው ቀውስና ችግርም፣ የዚሁ የድንቁርና አስተሳሰብ ውጤት መሆኑ ምርምር የሚያስፈልገው አይደለም፡፡
የብሔር አቀንቃኝነትና የብሔር ፌደራሊዝም አገሪቱን ለቀውስ ዳርጓታል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርሰዎ ምን ይላሉ?
ሁለቱን ነገሮች ባናጣምማቸውና ባናቀላቅላቸው የብሔር አቀንቃኝነት ስጋት ሊሆን አይችልም ነበር:: አሁን ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን፣ የፌደራል አወቃቀር አይጥመኝም የሚል የለም፤ አይሰራም የሚልም አይኖርም፡፡ እጅግ በጣም ስልጡን የሆነ፣ ለህዝቦች ነፃነት እጅግ ጠቃሚ አወቃቀር ነው፡፡ ዴሞክራሲን እናስፍን ካልን፣ ፌደራሊዝም ግዴታ ነው፡፡ ምክንያቱም ስልጣን ሳይማከል ወደ ታች ከወረደ፣ ከታች ያሉ ሰዎች ሀሳባቸውን በነፃነት ከገለፁ፣ አካባቢያቸውን ተቆጣጥረው የአካባቢያቸውን ዕጣ ፈንታ መወሰን ከቻሉ፣ ፌደራሊዝም በትክክል ተተገበረ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ፌደራሊዝምን ህዝቦች ራሳቸውን በቋንቋ ከልለው፣ በዘር አጥረው፣ ሌላው እንዳይደርስባቸው መከላከያ መሳሪያ ነው ያደረጉት፡፡ ለህዝቦች ነፃነት ማረጋገጫ፣ የስልጡን ሥርዓት መግለጫ ተብሎ የተፈጠረውን ፌደራሊዝምን፣ እነሱ የዘረኞች መሳሪያ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው፡፡
ስለዚህ የፌደራሊዝም ፅንሰ ሀሳብ ሳይሆን የእኛ አገር አተገባበር ነው ችግሩ እያሉኝ ነው?
ትክክል ነው! ህወሓት ያቋቋመውና የተገበረው ፌደራሊዝም፣ እውነተኛውን የፌደራሊዝም ፅንሰ ሀሳብና ሳይንስ የማይወክልና ትክክል ያልሆነ ነው:: ህወሓቶች ኢትዮጵያን እንዴት እናጠቃታለን፣ በምንስ እንበትናታለን፣ ይህንን የተበታተነ ህዝብ እንዴት አድርገን እንገዛዋለን ብለው አጥንተው፣ እንደ መሳሪያ ነው የተጠቀሙበት፡፡
ግን ህወሓቶች ኢትዮጵያዊያን አይደሉም እንዴ?
ተመልከች፤ እነሱ በእኔ እድሜ አካባቢ ያሉ ትልልቆች ናቸው፤ በዕድሜ ነው ትልቅ ያልኳቸው:: ያኔ እኛ የመደብ ትግሉ ቅድሚያ ይሰጠው የሚል ነበር ሀሳባችን፤ እነሱ የብሔር ጥያቄ ያታግላል ነበር የሚሉት፡፡ ስለዚህ መታገያ መሳሪያቸው ብሔር ነበር:: አንድ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል አካል፣ ስለ መላ አገሩና ስለ መላ ህዝቡ ያስባል ይታገላል እንጂ በብሔር ታጥሮና ሌላውን በብሔር አጥሮ ይበታትናል እንዴ? ይሄን ቡድን ኢትዮጵያዊ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ለ27 ዓመታት በስልጣንና በጨቋኝነት ያቆያቸውም ይሄ ሥልታቸው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጣሊያንም ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት አቅዶና ነድፎ የመጣው፣ ኢትዮጵያውያንን በዘርና በጎሳ ከፋፍሎ መግዛት ነበር፡፡ እነሱ ኢትዮጵያን እንደ አገር ሳይሆን የብሔር ስብስብ አድርገው ስለሚያስቧት፣ እነዚህን ብሔሮች በየቋንቋቸው ብንበታትናቸው፣ እርስ በእርሳቸው ሲናቆሩ፣ እኛ በቀላሉ እንገዛቸዋለን በሚል አገሩን በአምስት የዘርና የቋንቋ ክልል ከልለው አቋቋሙት:: ለደቡብና ለኦሮሞው ክልል አንድ አስተዳደር ጅማ ላይ ዋና ከተማ አድርገው አቋቋሙ፡፡ ለአማራው “ገቨርኖ አማራ” ብለው ጎንደር ላይ አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪን ብቻ ከለሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ ከዚያኛው ሶማሌ ጋር ተቀላቅሎ፣ ዋና ከተማውን ሞቃዲሾ  አደረጉት፡፡ ትግራይና ኤርትራን ቀላቅለው፣ ዋና ከተማውን አስመራ አደረጉ፡፡ አዲስ አበባን የኮምሳሬቱ መቀመጫ አድርገው ብቻውን በማዋቀር ነው አምስት ዓመት የቆዩት፡፡ ሲመጡም ይህንን በደንብ አጥንተውና ነድፈው ነው፡፡
ህውሓትም እንዲህ ነው ያደረገው፡፡ አገርን በጎጥ ማዋቀር በአጠቃላይ የቅኝ ገዢዎች ባህሪ ነው፡፡ እንደ ህንድና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትልልቅ አገሮችን እንገዛለን ብለው ሲመጡ፣ ያንን ሁሉ ህዝብ በጦር ወግተውና አዳክመው ሊገዙት እንደማይችሉ ስለሚያውቁ፣ እርስ በእርሱ አናቁረውና አናክሰው ነው ለመቆየት የዘየዱት፡፡ ህወሓትም ይህንኑ ነው ያደረገው፡፡ ገና እንደመጣ ኢትዮጵያን ያለ ተጠያቂነት ለመግዛትና ሀብትና ንብረቷንም ለመጠቀም፣ የግድ እርስ በእርሳችን መናከስ ነበረብን፡፡ በዘርና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ መግነን ነበረበት፡፡ አገራዊ ስሜቱ ሲፈርስ እያንዳንዱ ሰው ትኩረቱ በነሱ ላይ መሆኑ ይቀርና፣ በጎረቤቱና በዘሩ ላይ ይሆናል፡፡ ይሄ ላለፉት 27 ዓመታት ሰርቶላቸዋል፡፡ አሁንም በአገሪቱ ላይ የሚታየው፣  ያኔ የተዘራው ዘር ፍሬ ነው፡፡ ሆኖም ይሄ የአጭር ተመልካች አስተሳሰብ ነው፡፡ በመጨረሻ የሚጎዳው የተከፋፈለው ህዝብ ብቻ ሳይሆን ከፋፋዩም ራሱ ጭምር ነው፡፡ በሌላው ላይ የሚነደው እሳት በራሱም ላይ ነድዶ ይለበልበዋል፡፡ ይህን አስቀድሞ አለማሰብ፣ የአጭር እይታ ተመልካችነት ውጤት ነው፡፡
በለውጥ ማግስት በርካታ ህዝብ ተፈናቅሏል፤ የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ አለመረጋጋት ተከስቷል፡፡ እርስዎ በአሁኑ ወቅት  ለውጥ አለ ብለው ያምናሉ? አሁን የምናየው ግጭትና ቀውስ ምንጩ ምንድን ነው ይላሉ?
እኔ መቼም በግሌ ለውጥ አለ ብዬ ነው የማምነው፡፡ እሰራለሁ ብሎ የቆረጠና ያመነ ካለ፣ የሚያሰራው መድረክ ተከፍቶለታል፡፡ አሁን እስር ቤቶች በፖለቲከኞች አልተጣበቡም፤ ሜዳው ነፃ ሆኗል፡፡ እኛ እነዚህን ነፃ መድረኮች ተጠቅመን ሁኔታውን ባናሻሽል፣ በአብዛኛው ጥፋቱ የእኛው ይሆናል፤ ስለዚህ እኛ እራሳችንም ተጠያቂዎች ነን፡፡ እኔ ለውጥ አለ የምለው ቢያንስ ወደፊት ለመግፋት አጋጣሚው ተፈጥሯል፤ በዚህ ተጠቅሞ ችግሮችን ማቅለልና አገሪቱን ወደተሻለ እምርታ ማድረስ የሚቻልበት አጋጣሚ በመኖሩ ነው፡፡ አሁን አንድ የማየው ከፍተኛ ድክመት ግን አለ፡፡ ድክመቱን የማየው በማዕከላዊ መንግስትና የለውጥ አራማጆች በሚባሉት ላይ ነው፡፡ አንደኛ፤ የመንግስትን ብቃት ማረጋገጥ የራሱ የመንግስት ኃላፊነት ነው፡፡ ይሄ የተምታታባቸው ይመስለኛል፡፡ የመንግስትን ኃይል ተጠቅሞ ማረጋጋትና ለውጡን ማስቀጠልና እንዲሁ ህዝቡን ፈትቶ መልቀቅ፣ ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛው ኃላፊነት ነው፤ በአጋጣሚም ይሁን በታቀደ መንገድ የመንግስት ስልጣን ይዘዋል፡፡ አንዴ የመንግስት ስልጣን እጃቸው ላይ ከወደቀ በኋላ ሀገርን የማረጋጋት፣ የህዝብን ደህንነት የመጠበቅና ሰላም የማስፈን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ህዝብን ከውድቀትና ከከፍተኛ አደጋ የመከላከል ኃላፊነት የመንግስት ነው፡፡ መንግስት የምናቋቁመው ለዚህ ነው፡፡ ያለበለዚያማ ለምንስ ግብር እንከፍላለን? ለምንስ ዕለት ተዕለት በላያችን ላይ ጫና የሚያሳድር አለቃ እናስቀምጣለን? የግድ መንግስት ስለሚያስፈልግ እኮ ነው፡፡ ማንም የሰለጠነ ህዝብ ያለ መንግስት እኖራለሁ ብሎ አያስብም፡፡ መንግስት በዋናነት መስራት ያለበት፣ ሀይል በመንግስት እጅ ብቻ መኖሩን ማረጋገጥ  ነው፡፡ ያ በመንግስት እጅ ያለን ሀይል ደግሞ በስርዓትና በህግ፣ ፀጥታውን ለማስከበር መዋል አለበት፡፡ አሁን መንግስት እጁን ከዚያ ላይ  አንስቷል፡፡
መንግስት ፀጥታ ከማስከበር እጁን አንስቷል እያሉኝ ከሆነ፣ በቸልተኝነት ነው ወይስ በአቅም ማነስ?
እሱን መመለስ ያስቸግራል፡፡ በአመራር ደረጃ ያሉት እንደ እኛ ችግሩን ነጭና ጥቁር አድርገው አላዩት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ከችግር ፈጣሪዎቹ ውስጥ አንዳንዶቹ ከነሱ መሃል ናቸው፡፡ አብረዋቸው ስለኖሩ ወይም እነሱ የሚያቀነቅኑትን ሀሳብ ባይስማሙበትም፣ አምርረው ሊዋጉት ባለመፈለጋቸውና በእነሱ ላይ ልባቸው መቁረጥ ስላልቻለ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ በመንግስት በኩል መወሰን አለመቻል ያለ ይመስለኛል፡፡ አሻሚ ሁኔታ ገጥሟቸው ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ Divided loyality የሚባል ነገር አለ፡፡ ይሄ ግን አደገኛ ነገር ነው፡፡ እኔ በእውነቱ ቅንነታቸውን አልጠራጠርም:: እስካሁን የሰሩትንና ያደረጉትንም አስተዋፅኦ አልክድም፡፡ ባልተጠበቀ መልኩ አገሪቱን አሁን ላለችበት ሁኔታ አድርሰዋታል፡፡ ይሄንን ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ነው የምናነጻጽረው፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ቢያደርጉም፣ ፍሬ የሚያፈራው ግን ቀጣይነትና አስተማማኝነት ሲኖረው ነው፡፡ መሀል መንገድ ላይ ቆሞ መዋዠቅ እነሱንም ለአደጋ ያጋልጣል፤ እነሱንም ተጠያቂ ያደርጋል የሚል ፍርሃት አለኝ፡፡ ነገር ግን አሁንም ደግሜ የምናገረው፣ በቅንነታቸው አልጠራጠርም፡፡ ለሚከተሉት የአመራር ዘዴ ጊዜ እንስጠው የሚባለው ጉዳይ ግን አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ ለምን ካልሽኝ፣ ብዙ ጊዜ እየሰጠን በሄድን ቁጥር ብዙ ቦታ እየለቀቅን እንሄዳለን፡፡ በተለቀቀው ቦታ ላይ ደግሞ የማይፈለገው ሀይል እየተጠቀጠቀ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንገባና ነገሩ ወደማይመለስበት ደረጃ እንደርሳለን፡፡ አንዴ ከእጃቸው ሀይል ከወጣ ከፍተኛ አደጋ ይፈጠራል:: በእርግጥ ሃይልም መጠቀም የመጀመሪያ አማራጭ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩትን መንግስታት የምንጠላበት ምክንያት የሀይል አጠቃቀማቸው ትክክል ባለመሆኑ ነው፡፡ ሀይልን በቁጠባ መጠቀም የብልህ መሪዎች ከፍተኛው ዘዴ ነው፡፡ እኔ መቼም እንደገና ደብድቡን፣ እሰሩን፣ ዱላ ይወድልናል----እያልኩ አይደለም፡፡ የህዝቡ ደህንነት ግን መጠበቅ ይገባዋል፡፡ የሀገሪቱ ቀጣይነት መረጋገጥ አለበት፡፡ ይህንን ባላደረግን ቁጥር  አደጋው እያየለ  ይሄዳል፡፡ ሌላው ደግሞ ህዝቡ በመንግስት ላይ እምነት እያጣ ሲሄድ  ጥሩ አይሆንም፡፡
የሚወደድ መንግስት ካፒታል አለው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ገና ወደ ሥልጣን ሲመጡ እጅግ ብዙ ካፒታል ነበራቸው፡፡ ፖለቲካል ካፒታል ነበራቸው:: ህዝቡ ያለ የሌለ ነገሩን በእርሳቸው ላይ ጥሎ፣ ባሰለፍከን እንሰለፋለን ብሎ ነበር፡፡ ያ ግለት አሁን ያለ አይመስለኝም፤ ግን ደግሞ ጨርሶ አልጠፋምና ሊመልሱት ይችላሉ፡፡ ያንን ካፒታል ማጣት ግን አንድ ነጋዴ ወረቱን እንደማጣት ነው፡፡ አንድ ነጋዴ ወረቱን ካጣ ምንድነው የሚገዛው? ምንድንስ ነው የሚሸጠው? ሌላ ትንሽ የሚያሰጋኝ ነገር፣ ይሄ ታምቆ የኖረው ትንሽ ይተንፍስ የሚባል ነገር ነው፡፡ ታምቆ የነበረ ነገር ሲለቀቅ መርዝ ሊሆን ይችላል’ኮ! ያ መርዝ የሆነው ነገር ተለቅቆ ብዙ ሰው ሊመርዝና ሊገድል ይችላል፡፡ ታፍኖ የነበረ ሁሉ ዕድል ሊያገኝ አይገባም፡፡ ያ መርዘኛ የሆነው እኮ ሁሉም መድረክ እንዳያገኝ ህዝቡን ሲከለክል የኖረ ነው፡፡ ይሄም አደጋ እንዳለ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ህዝቡ ነፃነቱን በአግባቡ መጠቀም አልቻለም ነው የሚሉኝ?
ይሄ ከዚያ ያልፋል፤ቀጥታ አፍራሽነት ነው እያየን ያለነው፡፡ ነፃነትን በአግባቡ አለመጠቀም ከሚለው ያልፋል፡፡ ከዚያ በላይ አቅም ያለው ስጋትና ሁከት ነው፡፡ አሁን እየተከሰተ ያለው ነገር አይተሽ እንዳላየ የምታልፊው አይደለም፡፡ ለሁሉም ታንክ አሰልፎ ስለማይቻል፣ በቀላሉ በምክርና በተግሳፅ የሚታለፉ ይኖራሉ፡፡ አሁን የምናየው የተደራጀ አቅም ያለው ቡድን ግን አገራዊ ስጋት  ነው፡፡
መፍትሄው ምንድን ነው  ይላሉ ታዲያ?
መንግስት እርምጃ ወስዶ የጎበዝ አለቃውን ሁሉ ማስታገስ አለበት፤ ስርዓት አልበኝነትን ማጥፋት ይገባዋል፡፡ የህዝቡ ደህንነት መጠበቅ አለበት፡፡ በአሁኑ ወቅት በየሶሻል ሚዲያው የሚራገበውን ነገር ተከትሎ መክነፍ ከህዝብ የሚጠበቅ አይደለም:: ህዝቡም ለደህንነቱ ዘብ መቆም አለበት፡፡ ምሁራን ለአገር የሚበጀውን ሁሉ ለመንግስት መምከርና ማማከር አለባቸው፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች ሃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ሀይሎችና አክቲቪስቶች የሚያለያይ ነገር ላይ ከመስራት ተቆጥበው ለአገር ህልውና በማሰብ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ከማንም በላይ መንግስት የአገርና የህዝብን ደህንነት መጠበቅ አለበት፡፡

Read 983 times