Friday, 24 May 2019 00:00

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት ተማሪዎች አማረሩ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

 · የትምህርት ክፍሉ እንዲሟላ ወይም እንዲዘጋ ጠይቀዋል
                  · “በመስከረም ሁሉም ነገር የተሟላ እንዲሆን እየሰራን ነው”
                             
                በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች የላብ ቁሳቁሶች ባልተሟላበት ሁኔታ መማራችን እየጎዳን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገለፁ፡፡ የትምህርት ክፍሉ የዘሬ ሶስት ዓመት የተከፈተ ሲሆን ዘንድሮ የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎች ይመረቃሉ፡፡ እነዚህ ምሩቃን ባለፉት 3 ዓመታት የላብ ክፍል ባለመኖሩ ያለምንም የላብ የተግባር ትምህርት፣ የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ብቻ ሲማሩ መቆየታቸውን የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የተግባር ስልጠና ለመውሰድ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ድረስ ሄደው የ15 ቀን ሥልጠና ብቻ ወስደው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ከአዳማ የመጣውና የሁለተኛ ዓመት የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተማሪው ወጣት ሚካኤል በለጠ። ትምህርቱ በላብ ያልተደገፈ በመሆኑ ደካማ ነው ይላል፡፡ የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎች ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ድረስ በመሄድ የድምጽ፣ የቪዲዮ፣ የጽሑፍና የፎቶ ኤዲቲንግ ስልጠና ለ15 ቀን ወስደው መመለሳቸውን በመጥቀስም፤ ይሄ ስልጠና በተለይ ለተመራቂ ተማሪ በቂ እንዳልሆነና በዚህ ሁኔታ ተመርቆ የወጣ ተማሪ በስራ ላይ ተፎካካሪ መሆን እንደማይችል ይገልፃል:: “የተግባር ልምምዱ በተደጋጋሚ ካልተሰራ የሚረሳ ነው” የሚለው ሚካኤል፤ እኛ ተማሪዎችና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ፣ ዩኒቨርሲቲው ኮምፒዩተር ገዝቶ ላብ እንዲያሟላ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም ብሏል፡፡ “እኔ እድለኛ ሆኜ በዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ ሬዲዮ ላይ የመስራት እድል ስለገጠመኝ ሁሉን ነገር ከወዲሁ መልመድ ችያለሁ” ያለው ወጣቱ ተማሪ፤ የሌሎች ጓደኞቹ እጣ ፈንታ ግን እንደሚያሳስበው አልደበቀም፡፡
የሁለተኛ ዓመት ተማሪዋ ብሩክታዊት ወሰን የለህ በበኩሏ፤ “ዲፓርትመንቱ ምንም አይነት ለትምህርት ክፍሉ የሚሆን ነገር ሳይሟላ የዲፓርትመንት ቁጥር ለማብዛት ተብሎ ብቻ የተከፈተ ነው፤ ላለፉት ሶስት አመታት ላብ እንዲሟላለትና ከንድፈ ሃሳብ ባለፈ የተግባር ትምህርት እንድንማር ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም” ብላለች፡፡
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው ይህንን ሳያሟላ ከኛ በኋላ ሌላ ተማሪ መቀበል የለበትም፤ የትምህርት ክፍሉም መዘጋት አለበት” ይላሉ - በምሬትና ተስፋ በመቁረጥ ስሜት፡፡ “ዲፓርትመንቱ የሚቀጥል ከሆነ ግን የሚያስፈልገው በአስቸኳይ ተሟልቶ ተማሪ ብቁ ሆኖ መውጣት አለበት” ባይ ናቸው - ተማሪዎቹ፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ ስለ ጉዳዩ ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ፤ የትምህርት ክፍሉ በእርግጥም አለመሟላቱን አምነው፣ ይሄ የትምህርት ክፍል ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂ ኮሌጅም እስከዛሬ ሳይሟላ መቆየቱን ጠቁመው፣ በቅርቡ በተለቀቀ 264 ሚ. ብር በፍጥነት እየተደራጀ መሆኑን አስረድተዋል:: የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍልም በ2012 ዓ.ም በደንብ እንደሚሟላ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ ለዚህ ትምህርት ክፍል የሚያስፈልጉ የላብ ቁሳቁሶችን በትክክልና በአግባቡ ለማሟላት ከባለሙያዎች ጋር ምክክር እያደረግን ነው ብለዋል::

Read 2727 times