Sunday, 26 May 2019 00:00

ዳንጎቴ ከአመቱ የአለማችን ታላላቅ መሪዎች አንዱ ሆነዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)


            ናይጀሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ ንግድን፣ በጎ አድራጎትንና ስነጥበብን ወደተሻለ ደረጃ ያሸጋገሩ ናቸው በሚል ከፎርቹን መጽሄት የአመቱ 50 የአለማችን ታላላቅ መሪዎች አንዱ በመሆን ተመርጠዋል፡፡
የአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለጸጋው ኢሊኮ ዳንጎቴ፣ በፎርቹን መጽሄት የ2019 የአለማችን 50 ታላላቅ መሪዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ብቸኛው አፍሪካዊ ሲሆኑ፣ በዝርዝሩ ውስጥ የ11ኛነት ደረጃን ነው የያዙት፡፡ ታዋቂው ፎርቹን መጽሄት ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው የ2019 የአለማችን 50 ታላላቅ መሪዎች ዝርዝር ውስጥ የአንደኛነት ደረጃን የያዙት የማይክሮ ሶፍት ኩባንያ መስራች አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስና ባለቤታቸው ሚሊንዳ ጌትስ ናቸው፡፡
በአመቱ በቢዝነስ፣ በመንግስት አስተዳደር፣ በበጎ ምግባርና በስነጥበብ መስክ አለማችንን ወደተሻለ ደረጃ ያሸጋገሩና በሌሎች ዘንድ መነሳሳትን የፈጠሩ አርአያዎች ናቸው በሚል ፎርቹን ይፋ ባደረገው የታላላቅ መሪዎች ዝርዝር ውስጥ የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን የሁለተኛ፣ የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ልዩ አማካሪ ሮበርት ሙለር የሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ በፎርቹን የአመቱ ታላላቅ መሪዎች ዝርዝር ውስጥ በአራተኛነት የተቀመጡት የቴንሰንት ኩባንያ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ፖኒ ማ ሲሆኑ፣ የማይክሮ ሶፍት ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳትያ ናዴላ የአምስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡

Read 1106 times