Sunday, 02 June 2019 00:00

አደጋ የተጋረጠበት ነፃው ፕሬስ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

 የፕሬስ ነፃነቱንና የመረጃ ነፃነት አዋጁን በሚጥስ መንገድ ጋዜጠኞችን የማንገላታት፣ የማሰርና የማስፈራራቱ ተግባር እንደቀጠለ ነው፡፡ ሰሞኑን የአሀዱ ኤፍኤም 94.3 ሬዲዮ ጣቢያ ጋዜጠኛ ስቱዲዮ ውስጥ በስራ ላይ እያለ በታጠቁ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች ተይዞ ሰንዳፋ ላይ ለ3 ቀናት በእስር ከቆየ በኋላ በዋስ ተለቋል፡፡ የብሮድካስት ባለስልጣን ስለጉዳዩ የደረሰኝ መረጃ ሆነ ለተቋሙ አቤቱታ ያቀረበ አካል የለም ብሏል፡፡
ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ጋዜጠኛ ታምራት አበራ ስቱዲዮ ውስጥ በስራ ላይ በነበረበት ወቅት የታጠቁ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች ወደ ሬዲዮ ጣቢያው በመሄድና ስቱዲዮ ውስጥ በመግባት ጋዜጠኛውን በቁጥጥር ስር አውለው ወደ ሰንዳፋ በኬ 02 ፖሊስ ጣቢያ ለመሄድ ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ ሁኔታው ያላማራቸውና ጋዜጠኛውን የቤት ሰሌዳ በለጠፈች የግል መኪና ለመውደስ መሞከሩ ያልተዋጠላቸው የጋዜጠኛው የስራ ባልደረቦች ጋዜጠኛው መወሰድ የሚገባው ሬዲዮ ጣቢያው ወደሚገኝበት ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ እንጂ ወደ ሰንዳፋ የሚወሰድበት ምክንያት የለም የሚል ተቃውሞ በማቅረባቸው ለጊዜው ሲኤምሲ አካባቢ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ በመቀጠል ወደሰንዳፋ በኬ 02 ፖሊስ ጣቢያ ይዘውት ሄደዋል፡፡ ጋዜጠኛው ከግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም በእስር ከቆየ በኋላ በመታወቂያ ዋስ እንዲፈታ ተደርጓል፡፡
ከአምስት ወራት በፊት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተፈፀመን የመልካም አስተዳደር ችግርና ህገ ወጥ የሙስና ተግባር የተመለከተና በጉዳዩ ውስጥ አሉበት የተባሉትን አካላት ሁሉ በማነጋገርና የምርመራ ጋዜጠኝነት የሚጠይቀውን መስፈርት ሁሉ ያሟላ ዘገባ በጋዜጠኛ ታምራት አበራ ተሰርቶ እንደነበር ያወሱት የሬዲዮ ጣቢያው ስራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ ይህ ዘገባ ጋዜጠኛውን ሊያስከብርና ሊያሸልም የሚገባ እንደነበርና አሁን በጋዜጠኛውም ሆነ በሬዲዮ ጣቢያው ላይ በተፈፀመው ህገ ወጥ ተግባር በእጅጉ ማዘናቸውን ገልፀዋል፡፡
መሳሪያ የታጠቀ ኃይል ስቱዲዮ ድረስ ገብቶ ጋዜጠኛን አስሮ መውሰድ የፕሬስ ነፃነት አዋጁን የሚፃረር ህገ ወጥ ተግባር ነው ያሉት አቶ ጥበቡ ይህ ድርጊት በጋዜጠኛውም ሆነ በሌሎች ባልደረቦቹ ላይ ያስከተለው ስነ ልቦናዊ ቀውስ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኛው የህዝብን ሮሮ በመስማት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር በተሟላ መረጃ የስራውን ዘገባ ስም ማጥፋት ነው በሚል ሰበብ በህገ ወጥ መንገድ ጋዜጠኛውን ማሰርና ማንገላታት ፈፅሞ የመረጃ ነፃነት አዋጁን የሚፃረር ህገ ወጥ ተግባር ነው ብለዋል ጋዜጠኛ ጥበቡ፡፡
በጋዜጠኛው የተሰራውን ዘገባ አስመልክቶ የቀረበ ቅሬታ እንዳልነበርና ምንም ዓይነት መጥሪያ እንዳልደረሳቸው የነገሩን አቶ ጥበቡ ባለፈው እሮብ እሳቸውን ጨምሮ የሬዲዮ ጣቢያው ምክትል ዋና አዘጋጅ ሊዲያ አበበ፣ የዜና ክፍል ኃላፊ ሱራፌል ዘለዓለም እና በእስር ላይ የነበረው ጋዜጠኛ ታምራት አበራ በሰንዳፋ በኬ 02 ፖሊስ ጣቢያ ቀርበው ቃል መስጠታቸውንና የቦታ ካርታ ባለው ዋስ መለቀቃቸውን ገልፀዋል፡፡
በቀጣይም የፊታችን ሐሙስ ግንቦት 29/2011 ዓ.ም እንዲቀርቡ መታዘዛቸውን ተናግረዋል፡፡
የፕሬስ ነፃነት በአግባቡ ሊከበርና ሊጠበቅ እንደሚገባ የሚናገሩት ስራ አስኪያጁ፤ ጋዜጠኛው እውነትን መሰረት አድርጎና ማስረጃዎችን በአግባቡ አጠናክሮ በሰራው ዘገባ በዚህ መልክ ለእስርና ለእንግልት መዳረጉን ሁሉም አካል ሊያወግዘው ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተጠሪ የሆኑትን አቶ ታምራት ደጀኔን ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው ጉዳዩን የተመለከተ ምንም አይነት ቅሬታ ለተቋሙ እንዳልቀረበ ገልፀው እኛም ጉዳዩን የሰማነው እንደማንኛውም ሰው በሚዲያ ነው ብለዋል፡፡ እርምጃ ወሰደ የተባለው አካል ለተቋማችን ያቀረበው ቅሬታ የለም ያሉት አቶ ታምራት የቀረበልን ቅሬታ ኖሮ ቢሆን ኖሮ ተገቢውን የአሰራር ሂደት የተከተለ ሁኔታ ይፈጠር ነበር ብለዋል፡፡

Read 971 times