Print this page
Sunday, 02 June 2019 00:00

አይጢቱ ከሌለች ጉድጓዱ ኬት መጣ?

Written by 
Rate this item
(3 votes)


           አንድ ፀሐፊ እንዳለው “We said what we had to say, but as no one listens we shall say it again (ማለት ያለብንን በወቅቱ ብለን ነበር፡፡ ግን ማንም አልሰማንም፡፡ ስለዚህ እንደገና ማለት አለብን” (እኛም ይሄንኑ አካሄድ እየተጋራን ነው?!
ከዕታት አንድ ቀን አንድ ባልና ሚስት አንድ ልጅ ነበራቸው፡፡ ልጁ በጣም አልቃሻ ነበረ፡፡
አባት - ዝም በል፡፡ ዋ! ለጅቡ ነው የምንሰጥህ
እናት - ዝም በል ተብለሃል ዝም በል፡፡ አባትህ ያሉህን ማክበር አለብህ
(ልጅ - ማልቀሱን ይቀጥላል)
አባት - ዝም ብትል ይሻልሃል አታስጨንቀን
እናት - አባትህ ያለህን ብትሰማ ይሻልሃል
(ልጅ አሁንም ማልቀሱን አላቋረጠም)
ለካ ይሄ ሁሉ ሲሆን ሳለ ጅብ እደጅ ሆኖ ያዳምጥ ኖሯል፡፡ ቀስ በቀስ ልጁ ማልቀሱን ተወ፤ ጥያቄው የተመለሰለት ይመስል፡፡ ቤቱንም የዝምታ አዘቅት ዋጠው፡፡ ጅቡ ተጨናንቆና ፡-
“እነዚህ ሰዎች የልጁን ነገር ተዉት ማለት ነው እንዴ?” ሲል እራሱን ይጠይቃል፡፡
አካባቢው ዝም፣ ጭጭ ብቻ ሆነ፡፡ ጅቡ ወደ ቤቱ ደጃፍ ሄደ፡፡ በሩን ተደግፎ ለማዳመጥ ሞከረ፡፡ ምንም ድምፅ የለም፡፡
የልጁም ትንፋሽ አይሰማም፡፡ የወላጆቹም ድምፅ አይሰማም፡፡ በመጨረሻ ጅቡ ቢቸግረው ወደ በሩ ተጠግቶ፤ “ኧረ ለጅቡ እንጥልሃለን ያላችሁትን ልጅ ነገር ምን ወሰናችሁ?” እነሱ ለጥ ብለዋል!
***
“ኧረ የልጁን ነገር አንድ ውሳኔ ላይ ድረሱ?” ማንም መልስ የማይሰጠው ጉዳይ ሆነ!
ከመኪና መጥፋት እስከ መርከብ መሰወር በቀላሉ በሚታይበት አገር፤ ሙስና እንደዋዛ መቆጠሩ የማይገርም ሆኗል፡፡
በጥንት ዘመን ሶስት ወዳጆች ግን ሌቦች ነበሩ ይባላል፡፡ የአንደኛው ስም ለማ፣ የሁለተኛው ስም ቢተው ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ጀምበር ነው ስሙ፡፡
ሰፈሩን ክፉኛ መዘበሩት! የመንደሩ ሰው ተሰበሰበ፡፡ ስም እየጠሩ አንዱ ሽማግሌ መናገር ጀመሩ፤ ግን ዘዴኛ ሰው ነበሩና በቀጥታ አይደለም ስም የጠቀሱት፡፡ የተወሰነ ቅኔ ተጠቀሙ፤ እንዲህ ሲሉ፡-
“ጎበዝ፤ ሌባው ለማ
ቢተው ይተው
አለበለዚያ ጀንበር በሰረቀ ቁጥር ህዝቡ መሰቃየት የለበትም!” አሉ፡፡
ህዝባችን ሀሳቡን ለመግለፅ አይቸገርም!! አንድ ጊዜ ጃንሆይ ንጉሥ ኃ/ሥላሴ፤ ት/ቤቶች ሲጎበኙ፣ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ለልጆቹ ጃንሆይ ሲመጡ፤
አባትህ ማነው ሲሉህ - ኃ/ሥላሴ
እናትህ ማናት? ሲሉህ - ኢትዮጵያ
አንተ ማነህ? ሲሉህ - ህዝብ
በል ተባሉ፡፡
ይህ ሆነ፡፡ ፕሮግራሙ አለቀ፡፡
ወደ ቤቱ ሄደ፡፡
አባትና እናቱ ተኝተው ደረሰ፡፡ ርቦታል፡፡ ወቸ ጉድ!
“የዚች አገር ጣጣኮ አያልቅም፡-
ኃ/ሥላሴ ኢትዮጵያን ይዞ ተኝቷል
ህዝብ ተርቧል!” አለ፡፡
ዞሮ ዞሮ ሌብነት እያለ አገር አማን አትሆንም፡፡ አንድ ጥያቄ ብቻ ነው መጠየቅ ያለብን
“አይጢቱ ከሌለች ጉድጓዱ ኬት መጣ???”
ይህቺ ዓለም ለየዋህነት ቦታ የላትም፡፡ ለብልጣብልጦች ግን ጊዜያዊ ታዛ አላት፡፡ ጥንትም እንደዚያ ናት፡፡ ዛሬም እንደዚያው ናት፡፡ ወደፊትም አይቀርላትም፡፡ ዓለም ምንጊዜም ስፍራ የምትሰጠው ለብልጣብልጦች፣ ለጨላጦችና ለዘራፊዎች ነው፡፡ በውስጧ የሚኖሩትም በውስጧ መፍረምረማቸውን እንጂ የእሷን ደህንነት ለመጠበቅም ሆነ ለማሻሻል ጥረት ሲያደርጉ አይታዩም፡፡
ተስፋዬ ሳህሉ ነብሳቸውን ይማረውና “ዓለም እንዴት ሰነበተች?” የሚል ዘፈን ነበራቸው፡፡
“ዓለም እንዴት ሰነበተች
እስቲ እንጠይቃት
ሰላም ጤና ነች ወይ
ከፋት ወይስ ደስ አላት
ማነው ከልጆቿ በጎ ሚመኝላት
ከሥቃይ እንድትድን ዓለም የሁሉ ናት!”
የኢትዮጵያን ገጣሚያንና ደራሲያን ልዩ የሚያደርጋቸው በአብዛኛው ከቅርፅ ይልቅ መልዕክት ላይ ማተኮራቸው ነው፡፡
…     “ፅድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም
ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም”
(ከበደ ሚካኤል)
…     “ቅንዝንና የቀን ጎባጣን
ስቀህ አሳልፈው ቢያምርህ ሰው መሆን፡፡
 (ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ)
…     “ሰማዩን በአንካሴ ቆፍሬ ቆፍሬ
ለወሬ ሱሰኞች አገኘሁኝ ወሬ”
(መስኮት)
… “አትሁን አኒማል አትሁን ስቶን
ፕሊስ አንደርስታንድ የነገርኩህን
ነገ ፍሪ ከሆንክ ከሌለብህ ወርክ
እንጫወታለን ዴይ እስኪሆን ዳርክ
የነገው ቀጠሮ ቀልድ እንዳይመስልህ
ትመጣለች እኮ ገርል ፍሬንድህ”
(የፍቅር ሜጋቶን)

Read 5426 times
Administrator

Latest from Administrator