Monday, 03 June 2019 15:22

ቃለ ምልልስ “በሀገሪቱ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

• “የመጀመሪያውን ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት አሰርተናል
                   • የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ፖለቲካ ነፃ መሆን አለበት
                   • ፖለቲከኞች፤ ህዝቡን ኮርቻቸው ማድረግ ማቆም አለባቸው
                   • ማዕከላዊ ውስጥ አሳዛኝ ነገር ይፈፀም እንደነበር አውቃለሁ

          ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ ይባላሉ፡፡ ምርጫ 97ን ተከትሎ የታሰሩትን የቅንጅት አመራሮች ለማስፈታት በተደረገው የሽምግልና ጥረት የጎላ ሚና ነበራቸው፡፡ በእስረኞች ሰብአዊ አያያዝ ዙሪያ በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ የሚገኙት ፓስተር ዳንኤል፤ ስለ ሀገር እርቅና ሠላም፣ ስለ ሽምግልና ሂደቶች እንዲሁም ራሳቸው የሚመሩት “ጀስቲስ ፎር ኦል” ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡


            “ጀስቲስ ፎር ኦል” የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት መቼና እንዴት ተመሠረተ?
የተመሠረተው ከዛሬ 26 ዓመት በፊት ነው:: በዋናነነት በተለያየ መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው በደርግ ዘመን በእምነትና በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ የታሰሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነሱን መነሻ አድርጐ ነው የተመሰረተው፡፡ እኔም በእምነት ምክንያት ታስሬ ነበር፡፡ በእስር ቤት ሳለሁ ብዙ ኢ-ሰብአዊ ተግባራትንና የእስር ቤት አሰቃቂ ገጽታዎችን አስተውል ነበር፡፡ እንግዲህ እዚያው እስር ቤት ሆኜ ነው፣ ለወደፊት በእስረኞች ጉዳይ መስራት እንዳለብኝ የወሰንኩት፡፡ ከእስር ቤት ከወጣን በኋላ አብረን የታሰርን  ሰዎች በጋራ ነበር ይሄን ያሰብነውና የጀመርነው፡፡ በተለይ አቶ ብርሃኑ ነበር ይሄን ነገር በዋናነት ሲሰራበት የነበረው፡፡
እኔም ጅማ ፖሊስ ጣቢያ ታስሬ በነበርኩ ጊዜ እግዚብሔር ሆይ ለእስረኞች፣ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ለመስጠት፣ ለሰው ልጅ ክብርና ሰላም እንዲሁም ፍትህ መናገር እንድችል እርዳኝ የሚል ፀሎት ነበረኝ፡፡ እንግዲህ ይህን ይዤ ደርግ ወድቆ ከእስር ስንፈታ ከጓደኞቼ ጋር ሆን ፕሪዝን ፌሎሺፕ ብለን ጀመርን፡፡ በመጀመሪያ የጀመርነው ስራ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ውስጥ የእስር ቤት ደረጃን ያሟላ እስር ቤት በወቅቱ አልነበረም:: ስያሜውም ሳይቀር አሰቃቂ ነበር፡፡ ለምሣሌ፡- የመጀመሪያው እስር ቤት የነበረው አሁን የአፍሪካ ህብረት ህንፃ ያለበት ቦታ የነበረው “ዓለም በቃኝ” እስር ቤትን ማንሳት እንችላለን፡፡ በነገራችን ላይ አፄ ኃይለሥላሴ ይሄን እስር ቤት ያሠሩት፣ ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል ሆና ልትመዘገብ ስትል፣ እንዴት አንድ ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት የሌላት ሀገር አባል ትሆናለች? የሚል ጥያቄ ሲነሳባቸው ነው:: ወዲያው የፈረንሳይ መሃንዲሶችን ለምነው፣ በፍጥነት አለም በቃኝ የተባለውን እስር ቤት እንዳሠሩ ይነገራል፡፡ ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ እስር ቤት አልነበረም፡፡ ያንን መነሻ በማድረግ ምናልባት ለሀገሪቱ ሞዴል ሊሆን ይችላል ያልነውን ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት ለመስራት ነው የተንቀሳቀስነው፡፡ በውጭ ሀገር ዞረን ገንዘብ አሰባስበን፣ ማረሚያ ቤቱን ለመስራት በቂ ገንዘብ ካገኘን በኋላ ለፌደራል መንግስት የመሬት ጥያቄ አቀረብን፡፡ በወቅቱ የፌደራል መንግስት መሬት ሊሰጠን ፍቃደኝ አልሆነም፡፡ እኛም ጥያቄያችንን ይዘን ወደ ኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሄድን፤ ክልሉ ጥያቄያችንን ተቀብሎ አዳማ ላይ ቦታ ሰጠን፡፡
በዚህ መሬት ላይ እንግዲህ አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት ገነባን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያውን ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት የሠራው ድርጅታተን ነው፡፡ ከዚያ በፊት ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት አልነበረም፡፡ ከዚያ በኋላ የዘጠኙንም ክልል መንግስት ጠርተን ማረሚያ ቤቱን አስጐብኝተናል፡፡ እነሱም ሞዴሉን በመውሰድ በየራሳቸው ክልል ተመሳሳይ ማረሚያ ቤቶችን ገንብተዋል፡፡
ለምሳሌ ቢጠቅሱልን?
ለምሣሌ ባህርዳር፣ መቐሌ፣ አዋሣ ሀረር --- ላይ ተሠርቷል፡፡ እኛ የመጀመሪያውን ተነሳሽነት ወስደን ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት መስራታችን፣ የሀገሪቱን የማረሚያ ቤቶች ሁኔታ ለመቀየር የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በሰብአዊ መብት አጠባበቅና እስረኞች አያያዝ ላይም ስልጠናዎች ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ እኛ በዋናነት ትኩረታችን ማረሚያ ቤቶች ላይ ነበር፡፡ በእርግጥም በሠራናቸው የማሰልጠን ስራዎች በማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብት አያያዝን ማሻሻል እንደቻልን አምናለሁ፡፡ እንደሚታወቀው አብዛኛው የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈጸም የነበረው ማረሚያ ቤት ሳይሆን በፖሊስ ጣቢያዎች ነበር፡፡ ማዕከላዊን መጥቀስ እንችላለን:: እኛ በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ብዙም አልሰራንም፡፡
ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት መገንባቱ ብቻውን፣ የሰብአዊ መብት አያያዝን ያሻሽላል?
ሲስተሞቹ ተገንብተዋል ግን ሲስተሞቹንና የህግ ስርአቱን እንደሚገባው ማጣጣም አልተቻለም:: ጉድለቶችና በርካታ ችግሮችም ነበሩ፡፡ ችግሮቹ ደግሞ ከፖለቲካ አመለካከት የሚነሱ ናቸው፡፡ ፖለቲካና ሙያ እኛ ሀገር ተነጣጥሎ አይታይም፡፡ ባለፉት 26 ዓመታት ብንነግራቸውም አንሰማም ያሉን ሙያና ፖለቲካን ነጣጥሉ የሚለውን ምክራችንን ነው፡፡ ፖለቲከኛ የፍትህ ስርአት ውስጥ ሊሠራ አይችልም፤ ታዛዥ ነው፡፡ የፍትህ ባለሙያ ከሆነ ግን ፍትህና ሰብአዊ መብትን ለማረጋገጥ አይቸገርም፡፡ ስለዚህ ችግር ሆኖ የቆየውና በተደጋጋሚ ብንናገርም ብናሰለጥንም ሊታረም ያልቻለው፤ ሙያና ፖለቲካ አለመነጣጠላቸው ነው፡፡ የኛ ሀገር የፍትህ ስርአት ፖለቲካ የተጫነው ነው፡፡ ማረሚያ ቤቶቹም የዚህ ነፀብራቅ ናቸው፡፡ የኛ ሀገር ዳኛ እኮ ደሞዝ የሚመደብለት ከፖለቲከኞች ነው፡፡ ገለልተኛ የሆነ የራሱ ተቋም የለውም፡፡ ከዚህ አንጻር ፖለቲካው ቢጫነው የሚደንቅ አይደም፡፡ ስለዚህ ሲስተሞች በሀገሪቱ ተገንብተዋል፡፡ ነገር ግን በፖለቲካው ተጽዕኖ የተነሳ  የሚጠበቅባቸውን ስራ ሊሰሩ አልቻሉም፡፡
በማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈፀም ስልጠና ሰጥተን ውጤታማ ሆነናል ብለዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ በማረሚያ ቤቶች አሰቃቂና የሚነወር የሰብአዊ መብት ጥሰት ጭምር ሲፈጸም እንደነበር የሚያሳይ በዘጋቢ ፊልም ቀርቧል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
እኔ መቼም ብሶት ለመቀስቀስ ብዬ ብቻ አልናገርም፤ እወኑቱን ነው የምናገረው፡፡ ስንት ቦታ ነው የሰብአዊ መብት ጥሰት የነበረው? ለምሣሌ ትልቁ ችግር የነበረው ማዕከላዊ የምርመራ ጣቢያ ነው፡፡ እሱ እንዳለ እኛም እናምናለን፡፡ እንደውም ገብተን ለማጣራትና ምልከታ ለማድረግ ፈልገን በወቅቱ ተከልክለናል፡፡ ማዕከላዊ፤ እስረኛ መጠየቅ አንችልም ነበር፡፡ ቃሊቲ ግን ገብተን እንጠይቃለን:: ማዕከላዊ ገብተን ያለውን ነገር ተመልክተን፣ ለማስተካከል እድሉን አላገኘንም፡፡ የሰው ልጅ፤ ከፍተኛ የሰብአዊ በደል በማዕከላዊ እየተፈፀመበት መሆኑን ግን ለመንግስት ጥቆማ ሰጥተን ነበር፡፡
ለጥቆማችሁ የመንግስት ምላሽ ምን ነበር?
ምን አገባችሁ የሚል ነበር፡፡ ምን አገባችሁ ተብለን ተመልሰናል፡፡ የኛ አቅም መናገር ነው፡፡ ከመናገር ያለፈ አቅም የለንም፡፡ ከማዕከላዊ ውጪ ግን በክልል ማረሚያ ቤቶች የተሻለ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ነበር ማለት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም የብሔር አወቃቀሩ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲጨካከን አያደርግም፡፡ ያ ነገር ጠቅሟል፡፡ በፌደራል በተለይ በማዕከላዊ አሳዛኝ ነገር ይፈፀም እንደነበር አውቃለሁ:: ነገር ግን በመጠኑም ቢሆን የኛ አስተዋጽኦ ባይኖር፣ ነገሮች ከዚህም የከፋ ይሆኑ እንደነበር አምናለሁ፡፡  
ቃሊቲና ቂሊንጦ ማረሚያ ቤቶች እንዴት የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈጸምባቸው ሆኑ? የእናንተ ምልከታ ምንድን ነው የሚሳየው?
እኔ እንግዲህ ያየሁትን ነው የምናገረው፡፡ እኔ ማረሚያ ቤቶቹን በጐበኘሁ ሰአት ሁሉንም እስረኞች እጠይቃለሁ፡፡ በአብዛኛው ድብደባና ማሰቃየቱ ደረሰብን የሚሉት ፖሊስ ጣቢያ ነው፡፡ ነገር ግን ማረሚያ ቤት ውስጥ ታራሚዎች ራሳቸው የሚያቋቁሙት ኮሚቴ አለ፡፡ ያ ኮሚቴ በህግ ከለላ የተሰጠው አይደለም፡፡ ራሳቸው እስረኞች ሲያጠፉ፣ እርስ በእርስ ለመቀጣጣት የሚያቋቁመት ኮሚቴ ነው፡፡ በዚህም ፍ/ቤት ሳያውቅ ግለሰቦች እስረኞችን ይቀጣሉ፡፡ ቃሊቲ ውስጥ እንዲህ ያለው ነገር እንዳለ በጥናትም አረጋግጠናል፡፡ እርምት እንዲደረግበትም ለሚመለከተው አካል አቅርበናል፡፡ ያው የኛ ስራ እርምት እንዲደረግ መጠቆም ነው፡፡ ከዚያ ያለፈ ስልጣን የለንም፡፡
ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት ሲባል ምን ማለት ነው?
አንድ ማረሚያ ቤት ደረጃውን ጠብቆ ተሠራ የሚባለው፣ ታራሚ ከቤተሰቦቹ ጋር በነፃነት መጠያየቅ የሚችልበት፣ ከህግ አማካሪው ጋር የሚገናኝበት፣ የህክምና አገልግሎት ተደራሽ የሆነበት፣ ሦስት ጊዜ በቀን በልቶ ጠጥቶ ማደር የሚችልበት፣ የመጸዳጃ ቤቶች ንፁህ መሆን፣ በክፍሎች ውስጥ ብርሃን ገብቶ ነፋሻማ ሆኖ የሚኖርበት እንዲሁም እምነቱን የሚተገብርበት (የሚያመልክበት) ምቹ ሁኔታ ሲኖር ነው፡፡
በእነዚህ መመዘኛዎች አሁን ያሉት ማረሚያ ቤቶች ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?
ብዙዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም፤ ደረጃውን አያሟሉም፡፡ በእውነት ነው የምናገረው፤ በጣም አስከፊ ሁኔታ ላይ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ አሁንም መንግስት ልዩ ትኩረት መስጠት አለበት:: ችግሮቹ እስካሁን አልተቀረፉም፡፡ መቀረፍ አለባቸው፡፡ ማረሚያ ቤቶች ተለወጡ የሚባለው ደረጃቸውን የጠበቁ ሆነው ሲገኙ ነው፡፡ እስረኛ ሲባል ምንም ጥቅም የሌላው ነው የሚለው ፖለቲካዊ አመለካከት ግን እየተለወጠ ነው፡፡ ይሄ የአስተሳሰብ ለውጥ መጠናከር አለበት፡፡
እርስዎ በሽምግልና እርቅ ውስጥም ተሳትፎ ያደርጋሉ፤ አሁን የተጀመሩ የእርቅና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን እንዴት ያዩዋቸዋል?
አንዳንዶች ችግሩ 15 አመት ሞልቶታል ይላሉ:: ሌሎች 27 አመቱ ነው ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ 50 አመቱ ነው ይላሉ፡፡  በመጀመሪያ እነዚህ አመለካከቶችን ሊያስታርቅ የሚችል ሰነድ መዘጋጀት አለበት፡፡ ለምሣሌ ከህገ መንግስቱ ጀምሮ አብሮ የሚያኖረን፣ ሊያፋቅረን የሚችል ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ መነሳት አለበት፡፡ በደሎች አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ ለነበሩት በደሎች እውነተኛ ኑዛዜ ተደርጓል ወይ? እኔ በብሔሬ ተተንኩሻለሁ ካልኩ፣ የበደለኝ ሰው ይቅርታ ቢጠይቀኝ ምንድን ነው ችግሩ? እውነተኛ ኑዛዜ ቢኖር ምን ጉዳት አለው?
እርቅ በሀገር ደረጃ እንዴት ነው መከናወን ያለበት?
እኔ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንዲኖር አልፈልግም፡፡ መንግስት ከህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም ሆነ ከእርቅ ላይ እጁን ማንሳት አለበት:: በኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ያለ ከፖለቲካ መፍትሔ የበለጠ የባህል እርቅና ፀጋ አለ፡፡ ያንን ፀጋ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲጠቀሙባቸው መንግስት ከእነዚህ ሂደቶች ላይ እጁን በጊዜ ማንሳት አለበት:: ኢትዮጵያ በተለያየ ባህልና እሴት ስትመራ የኖረች፣ የስነ ምግባር ፀጋ ያለው ህዝብ ባለቤት ነች፡፡ ስለዚህ እነዚህ ፀጋዎች በፖለቲካ መዳመን የለባቸውም:: ጐልተው እንዲወጡ መንግስት እጁን ማንሳት አለበት፡፡ ለምሣሌ እኔ ሽምግልና ውስጥ ነበርኩ:: ወደ ሽምግልና የገባሁት አባቴን አርአያ አድርጌ ነው:: አባቴ በጅማ የታወቁ አስታራቂ ሽማግሌ ነበሩ፡፡ ከእሣቸው የተማርኩት ብዙ አለ፡፡ ሽምግልና ትልቅ እሴት ነው፡፡ ስለዚህ ከስረ መሠረቱ እርቅ ለመጀመር የሀገሪቱ የሽምግልና ባህልና እሴት ተገቢውን ቦታ መያዝ አለበት፡፡ መንግስት ለዚህ እሴት ቦታውን መልቀቅ ይኖርበታል፡፡ ህግና ስርአትን ማበጀትና መቆጣጠር ላይ ነው መንግስት ማተኮር ያለበት፡፡
እውነተኛ ሽምግልና የለም የሚል ትችት ይቀርባል፡፡ ለዚህም እናንተ በ1999 የቅንጅት አመራሮችን ያስፈታችሁበት ሂደት ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
በወቅቱ በ1997 በምርጫ ምክንያት ችግር ሲከሰት ብዙ ኢትዮጵያውያን ልሂቃን የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው፡፡ ህዝቡንም ሚዲያው አደናግሯል፡፡ በዚያን ጊዜ በተከሰተው ችግር የቅንጅት መሪዎች እስር ቤት ገቡ፡፡ የአለም መንግስታት፤ መንግስትን እስረኞቹን እንዲፈታ ቢያሳስቡም የሚሠማ አልነበረም፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና መንግስታት መጥተው እንኳ እስረኞቹን መጐብኘት አልቻሉም ነበር፡፡ ነገር ግን በርካታ ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ ወደ ጠ/ሚኒስትር መለስ ቢሮ በመሄድ፣ “እባክዎ ፍቷቸው” ይላሉ:: ጠ/ሚኒስትሩ፤ “እናንተ እነማን ናችሁ ፍቷቸው የምትሉት? በመጀመሪያ አንድ ላይ ተደራጁና ኑ” አሉ፡፡ እኔ በወቅቱ እስረኞችን መጠየቅ ባህሌም ስራዬም ስለሆነ፣ በየጊዜው እጐበኛቸው ነበር፡፡ ልክ እንደኔው ሁሉ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅም እስረኞችን ይጐበኙ ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነውም ቃሊቲ ሁለታችንም እስረኞችን ስንጐበኝ ነው፤ በኋላ ከእሣቸው ጋር ተነጋገርን፤ “ለምን ተሰባስበን  እነዚህን ሰዎች አናስፈታም” አልን፡፡ አላማችን እስረኞቹን ማስፈታት ብቻ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው ሽምግልና፤ እንደ ሩዋንዳው የእውነተኛ አፈላላጊና እርቅ ኮሚሽን፣ ህጋዊነት የተሰጠው አይደለም:: ሄደህ አንደኛውን ደጅ የምትጠናበት የሽምግልና አካሄድ ነው፡፡ እኛም አላማችን እስረኞችን ማስፈታት ብቻ ስለነበር ጠ/ሚኒስትር መለስ ጋር ሄደን ጠየቅናቸው:: “ለመጀመሪያው ጊዜ ጥያቄያችሁን ለጓደኞቼም አስተላልፌ፣ መክረን እናሳውቃችኋለን” አሉ:: ቀጥሎ እስር ቤት ሄድን፡፡ እነሱንም ጠየቅን፡፡ በነገራችን ላይ ጠ/ሚኒስትሩ ጋ ስንሄድ፣ “እናንተ የቅንጅት ተላላኪዎች” ይሉን ነበር፡፡ ደግሞ እስረኞቹ ጋ ስንሄድ፣ “እናንተ የመለስ ተላላኪዎች” እንባል ነበር:: እኛ ግን ያ አያስጨንቀንም ነበር፡፡ ምክንያቱም አላማችን እነሱን ከእስር ቤት ውጪ ማየት ነው:: በወቅቱ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ነበር፤ እኛ ባንሸመግላቸው ታዲያ እጣ ፈንታቸው ምን ይሆን ነበር? ዛሬ ይኸው ሃገር ለመምራት እየተወዳደሩ ነው፤ አንዳንዶቹም ሹመት እያገኙ  ነው፡፡ ያን ጊዜ ባገኘናት ቀጭን መንገድ ባንጠቀም፣ ዕጣ ፈንታቸው ዛሬ ምን ይሆን ነበር?
አንዱ አወዛጋቢ የነበረው --- ይቅርታ ጠይቀው እንዲወጡ የቀረበላቸው ሰነድ ነው ---
አዎ እኛ በመጀመሪያ በታሠሩ በ3ኛ ወራቸው ስንጠይቃቸው፣ በኛ በኩል የቀረበው፣ “በማወቅ ባለማወቅ ለሠራነው ጥፋት ይቅርታ እንጠይቃለን፤ መንግስትም የእሱን ስህተቶች ያስተካክላል” የሚል ነበር የፃፍነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፍ ለማዘጋጀት እቅድ አለኝ፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱን ሂደትና ንግግር ሰው ማወቅ አለበት:: በመጽሐፉ ላይ እያንዳንዱን ሂደት በዝርዝር አቀርባለሁ፡፡ ለአሁኑ ግን በአጭሩ ነው የምገልፀው፡፡ እኛ ያንን ሰነድ አርቅቀን ሳለ፣ አቃቤ ህግ በሌላ በኩል ክሱን አጧጧፈ፡፡ እንደዚያ አይነት ፈጣን የፍርድ ሂደት በኢትዮጵያ ታይቶ አይታወቅም፡፡ ፍ/ቤት ጥፋተኛ ሲላቸው፣ “በማወቅ ባለማወቅ የሠራነው ጥፋት” የሚለው ዋጋ አጣ ማለት ነው፡፡
በወቅቱ የሽማግሌዎች ሊቀ መንበር የነበሩት ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ፤ መጀመሪያ ባረቀቅነው ሰነድ ይሁንልን ብለው ጠ/ሚኒስትሩን ሲጠይቋቸው፣ “በቃ አሁንማ ፍ/ቤት ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጦ ወሰነ’ኮ ፍ/ቤት ከወሰነ በኋላ በማወቅ ባለማወቅ የሚለው አይሠራም፣ ፍ/ቤቱ በወሰነው መሠረት ፈርመው ይውጡ” አሉን፡፡ ከዚያ እኛም በእጅጉ አዘንን፤ ነገሩ ሁሉ ተቀየረብን፡፡ ያልጠበቅነው ነገር ነው ያጋጠመን፡፡ ስለዚህ የሀገር ሽማግሌዎቹ ሂደታቸው የበለጠ ቀጭን ገመድ ላይ ሆነ፡፡ በዚህ ቀጭን ገመድ ሄደው ነው፣ ሁኔታውን ያስተካከሉት እንጂ ተላላኪ ሆነን አይደለም፡፡ ሁላችንም የየራሳችን ህይወት ያለን ሰዎች ነን፡፡ ፕ/ር ኤፍሬም፤ አቶ መለስ እግር ስር በእንብርክካቸው እየሄዱ ተማጽነዋል፡፡ በተመሳሳይ፤ በዚህ እድሜያቸው ኢ/ር ሃይሉ ሻውል ስር ድንጋይ በነጠላቸው ጫፍ ቋጥረው ተንበርክከው ለምነዋል፡፡ ከመጋረጃው ጀርባ ብዙ ሂደቶች ናቸው የነበሩት፡፡ ሁላችንም ግን በመጨረሻ በገጠመን የአካሄድ መገለባበጥ አዝነናል፡፡
በመጨረሻ ታዲያ “ይቅርታ ጠይቃችሁ ፈርሙ” የሚለው ሰነድ እንዴት ተዘጋጀ?
እውነቱን ለመናገር ያንን ሰነድ እኔ አላረቀቅሁትም:: እጄ ተንቀጥቅጦ እምቢ አለኝ:: አላረቅም ብዬ ተውኩት፡፡ ከኔ ጋር የነበሩትም በተመሳሳይ ለማርቀቅ እጃቸው ተንቀጠቀጠ:: ፕ/ር ኤፍሬም አላረቀቁትም፡፡ ያረቀቁት ሌሎች ሰዎች ናቸው፡፡ አንድ ነገር ማስተዋል ያለብን ግን ፕ/ር አስራት ወልደየስ እኮ በወቅቱ እንዲህ ያለ እንቅስቃሴ የሚያደርግላቸው ባለማግኘታቸው ነው ውድ ህይወታቸው እስር ቤት ያለፈው::  ያኔ አስብ የነበረው፣ እነዚህ ሰዎች የእሣቸው እጣ ፈንታ እንዳይደርሳቸው በየትኛውም መንገድ ከእስር መውጣት አለባቸው የሚለውን ነበር፡፡ የኔ የመጀመሪያ ሃሳብ፤ ሰውን ማዳን ነው፤ ዛሬ እነዚያ ሰዎች ህይወታቸው ቀጥሎ በተስፋ ሙላት ስራቸውን እየሠሩ ማየት ትልቅ ነገር ነው፡፡
አሁንም ማሸማገሉን ቀጥላችሁበታል? ለምሳሌ፡- የትግራይና አማራ ክልል የእርቅ ስነስርአት ይጠቀሳል:: የእርቅ ሥነስርዓቱ እውነተኛና ከልብ ነው ማለት ይቻላል?
አሁንም መቶ በመቶ ፖለቲከኞች እጃቸውን ካላወጡ በስተቀር በሀገሪቱ የሚካሄዱ እርቆች እውነት አይሆኑም፡፡ ከንቱ ድካም ነው፡፡ እኛም እርቅ ስናመቻች ለማስታመም እንጂ ከስር መሠረቱ ችግሩን ለመፍታት ያለመ አልነበረም፡፡ ችግሩ ከስር መሠረቱ የሚፈታው በራሳቸው በሁለቱ ክልል አመራሮች ነው እንጂ በሽማግሌዎች አይደለም:: የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ግን ከፖለቲከኞችና ፖለቲካ ነፃ መሆን አለበት፡፡ አሁን ችግር የሆነው ፖለቲከኞች ለራሳቸው ጥቅምና ስልጣን ሲሉ፣ ህዝቡን ኮርቻቸው እያደረጉት ነው፡፡ ህዝቡን ኮርቻቸው ማድረግ ማቆም አለባቸው፡፡ እኛ በእርቅ ጉዳይ ወደ አራቱም ክልሎች ተጉዘናል፡፡ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ደቡብ --- ከእያንዳንዱ ክልል 300 ሰዎችን መርጠን አነጋግረናል፡፡ እነዚህ የህዝብ ተወካዮች፤ “እርቅ እንዲመጣ መጀመሪያ ፖለቲከኞች እጃቸውን ያውጡ” ነው ያሉን፡፡ “ፖለቲከኞች ናቸው የሚያባሉን፤እጃቸውን ከህዝቡ ውስጥ ያውጡ፤ከዚያ ሀገሪቱ ሠላም ትሆናለች” ብለዋል፡፡
መቐሌ ሄዳችሁ “እዚህ ሠላም ነው፤ ከፈለጋችሁ ችግር ያለበት ቦታ ሂዱ” ተብላችኋል ይባላል፡፡ እውነት ነው?
እኛ ስንሄድ፤ የቀረበልን አቤቱታ መንገድ ተዘግቶብናል፤ ልጆቻችን ታስረዋል፣ለምን ዝም ትላላችሁ? የሚል ነው፡፡ መንገድ በመዘጋቱ እህልና መድሃኒት እየመጣልን አይደለም፤ ይሄ ለምን ይደረጋል? እኛ ህዝብ አይደለንም ወይ? የሚል ቅሬታ ነው የተነገረን፡፡ በእውነቱ ይሄ ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ የተወሰነ ሰው ባጠፋው ህዝብ መድሃኒትና ምግብ እንዲያጣ መደረግ የለበትም፡፡ ህዝብ እንደ ጥፋተኛ ተቆጥሮ መንገድ መዘጋት ተገቢነት የሌለው ነው፡፡ እንደ ሰው ስናስበው ቅሬታቸው ተገቢ ነው:: ለወደፊት እንግዲህ እነዚህ ችግሮች ሲፈቱ ሁሉም ወደ ቦታው ይመለሳል፡፡ እናም የሠላምና እርቅ ጥሪያችንን ማቅረብ እንቀጥላለን፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከመጡ በኋላ እኔ የማስበውን “እውነት የማውሪያ ጊዜ” አግኝተናል፡፡ እውነቱን ተነጋግረን በይቅርታ መተላለፍ የምንችልበት ጊዜ ላይ ነን ብዬ አምናለሁ::  
በመጨረሻ --- ለሀገሪቱ ምን ይመኙላታል?
የኢትዮጵያ ህዝብ ሠላም አግኝቶ ሠርቶ፣ በልቶ፣ ከድህነት ወጥቶ፣ ኢኮኖሚው አድጐ በፍቅር እንዲኖር ነው የምመኘው፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ ተብላ እንድትጠራ ነው ምኞቴ፡፡ የኔም ድርሻ፤ በሀገሪቱ ፍትህ ሠፍኖ ሰብአዊ መብቶች ሁሉ ተከብረው እንዲኖሩ ማገዝ ይሆናል፡፡         

Read 2290 times