Sunday, 02 June 2019 00:00

የዘፈቀደ ትርምስ በየአቅጣጫው

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(1 Vote)


           “age of fragmentation” ለሚለው አገላለጽ፣ ከሰሞኑ ተጨማሪ አሳዛኝ ማስረጃ መገኘቱ ሲነገር ሰንብቷል፡፡ ለዚያውም በአውሮፓ ህብረት ምርጫ:: ተሰነጣጥቆ የመፍረስ፣ ተፍረክርኮ የመበታተን፣ ተበጣብጦ የመተራመስ ምሳሌዎች፣ ብዙውን ጊዜ የአፍሪካና የአረብ አገራት፣ አልያም የኤስያና የደቡብ አሜሪካ አገራት ቢሆኑብን፣ ዘወትርም ሲጠቀሱ ብንሰማ፣ ከእውነታው የራቀ ግነት አይደለም፡፡ ግን አውሮፓና አሜሪካም እንደ ድሮ አይደሉም፡፡
በአፍሪካና በአረብ አገራት እንጀምር፡፡ ማሊ እና ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና የመን፣ ሶሪያና ሊቢያ… የተተራመሱ አገራት መብዛታቸው ብቻ አይደለም አሳሳቢው ችግር፡፡ የነዚሁ ሳያነስ፣ መፍትሔም ሳያገኝ፣ ሌሎች አገራት በየዓመቱ ወደ ትርምስ ዘው ብለው ይቀላቀላሉ፡፡ ሰሜን ሱዳን አዲስ ገቢ እየሆነች ነው፡፡
በመፈንቅለ መንግስት ለ30 ዓመታት ስልጣን ላይ የቆዩት ጄነራል አልበሽር፣ በየአካባቢው በተቃውሞና በአመጽ ሲታወኩ ከርመው፣ በመጨረሻ በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ሲወርዱ ብዙዎች እልል ብለዋል፤ በደስታ ጨፍረዋል፡፡ ግን አስቡት፡፡ በጄነራል አልበሽር ምትክ ሌሎች ጄኔራሎች ናቸው ስልጣን የያዙት፡፡ እናም ከእልልታው ማግስት ጀምሮ፣ ወደ ሌላ ዙር የተቃውሞና የአመጽ ቀውስ ተሻግራለች፡፡ “ጀነራሎቹ የመንግስትን ስልጣን ለሌላ ማስረከብ አለባቸው” የሚሉ መፈክሮችና ድምፆች ናቸው በየአቅጣጫው የበረከቱት፡፡
“ስልጣን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች አስረክብ” ብለው በደፈናው በወታደራዊው መንግስት ላይ  የሚጮሁ አሉ - ለየችኞቹ ፓርቲዎች ምን ያህል ስልጣን ማስረከብ እና ማከፋፈል እንዳለበት ግን እንደ ጉዳይ አይነሳም፡፡ በቢቢሲ ዜና ላይ እንደ ዋና ቁም ነገር ተመርጦ የተሰራጨ የአንድ ሰልፈኛ ንግግር እንዲህ ይላል፡፡ ወታደራዊው መንግስት ስልጣኑን መልቀቅ እንዳለበት እኚሁ ሰልፈኛ ሲገልፁ፤ “ከዚያ በኋላ ምን እንደሚመጣ ባላውቅም፣ ስልጣኑን ለህዝብ ማስረከብ አለበት” ብለዋል፡፡ ይሄ የአንድ ተራ ሰልፈኛ አነጋገር ቢሆንም፣ በርካታ ምሁራንና ፖለቲከኞችም ከዚህ የተለየ ሃሳብ ሲናገሩ አንሰማም፡፡ ወታደራዊ መንግስት ዛሬውኑ ስልጣኔን ላስረክብ ቢል፤ ለማን ማስረከብ እንዳለበትና ምን ውጤት እንደሚገኝ፣ ምን አይነት መንግስት እንደሚያስፈልግ በግልጽ የሚናገር ነው እየጠፋ የመጣው፡፡ “አቶ ህዝብ” ወይም “ወ/ሮ ህዝብ” የተሰኙ ፍጡራን ነገ ብቅ ብለው ስልጣን የሚረከቡ እያስመሰሉ መናገር፣ ነገርን ከማደናገር ያለፈ ጥቅም የለውም፡፡
ለነገሩ፣ በመንግስት አስተዳደርና በፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ እንደ አውራ የሚታዩ አህጉራዊና አለማቀፋዊ ተቋማትም፣ ከተራው ሰልፈኛ የተሻለ ሃሳብ አልተናገሩም፡፡
ዩኤን እንደተለመደው፣ “በህዝብ ተሳታፊነት፣ በባለድርሻ አካላትና በሲቪል ማህበረሰብ ተካፋይነት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራዳሪነት”፣ አዲስ መንግስት ተቋቁሞ ተዓምረኛ መፍትሔ መገኘት እንዳለበት ማሳሰቢያ ይሰጣል፡፡ የዩኤን ማሳሰቢያ በተግባር ምን እንደሚመስል ለመገመት፣ በምናብ የተለያዩ መልካም ምኞቶችን ልታሰላስሉ ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን፣ “ህዝብ፣ ተሳትፎ፣ ድርድር” የሚሉ ቃላት በደፈናው ስለተደጋገሙ ብቻ፣ በደፈናው የሆነ አይነት ምኞት በእውን ይሳካል ማለት አይደለም፡፡
በተቃራኒው፣ ድፍን አባባል፣ መጨረሻው እንደማያምር፣ ዩኤን ፓርቲዎችን አሰባስቦ ሲያደራድር፣ የአገር መከራ እንደሚረዝም፣ ተስፋም እንደሚጨልም፣ ከሊቢያ እና ከየመን እጣፈንታ ማየት ይቻላል፡፡
ዩኤን፣ የሊቢያና የየመን ፓርቲዎችን ወደ ሃብታም የአረብ አገራት ወይም ወደ አውሮፓ እየጋበዘ፤ በባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ እየሰበሰበ፣ በየጊዜው መግለጫ ሲያሰራጭ፣ ዛሬውኑ ስምምነትን ፈጥሮ ዛሬውኑ ሰላምን የሚያሰፍን፣ ቢዘገይ ደግሞ ነገ ከነገ ወዲያ፣ ሳምንት ሳይሞላው መፍትሔውን የሚያበስር ይመስላል፡፡ ነገር ግን እንደምታዩት፣ ለዓመታት የዘለቀው የዩኤን አደራዳሪነት ከዓመታት ጦርነት ጋር እየቀጠለ ነው፡፡
ከ50 በላይ የሊቢያ ፓርቲዎችን ያሰባሰበ፣ በመቶ የሚቆጠሩ የፖለቲካ መሪዎችን ያሳተፈ  ጉባኤ እንደተካሄደ ሲገለጽ፣ አንዳች ትልቅ ስኬት የተገኘ ይመስላል፡፡ ግን ምንም አልተገኘም፡፡
እነዚያ ሁሉ ፖለቲከኞች፣ ከሳምንት በላይ በትልቅ ሆቴል ውስጥ በሰላም ሲዝናኑ መሰንበታቸው ነው የዩኤን ስኬት፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ባህር ላይ በመዝናኛ መርከብ ውስጥ ይጋብዛቸዋል፡፡
ይሄም ስኬት ነው፡፡ የአገሪቱ ጦርነትና ትርምስ ግን ያለመፍትሄ ይቀጥላል፡፡
ፓርቲዎች ስለተጋበዙና የፖለቲካ መሪዎች ስለተሰበሰቡ፣ በአንዳች ተዓምር ይስማማሉ ብሎ መጠበቅና፣ በደፈናው “የሁሉም ነገር መፍትሄ ተሳትፎና ድርድር ነው” የሚል የዩኡን አይነት አስተሳሰብ፣ መጨረሻው እንዲህ ነው … መቋጫው የራቀ ጦርነት!
“በኋላ ምን እንደሚመጣ ባላውቅም፤ ማን ስልጣን እንደሚረከብ ባላውቅም፤ ያኛው መንግስት መውረድ አለበት፣ ይሄኛው መንግስት ስልጣኑን ማስረከብ አለበት፤ ለውጥ መምጣት አለበት” የሚል የዘፈቀደ የአላዋቂ አነጋገር ሆኗል - የነ ዩኤን ፈሊጥ:: በዘፈቀደ ደግሞ፣ ትርምስ እንጂ አንዳች የተሻለ ውጤት አይገኝም፡፡
የአፍሪካ ህብረትም በፊናው፣ የሱዳን ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን ማስረከብ እንዳለበት ከማሳሰብ አልፎ አስጠቅቋል፡፡ ለዚያውም በ15 ቀናት ስልጣን ካላስረከብክ ማዕቀብ ይወርድብሃል የሚል ዛቻ ተጨምሮበታል፡፡ በሁለት ሳምንት ውስጥ፣ ጄነራሎቹ ከስልጣን ቢወርዱ፣ ከዚያ በኋላስ? “ከዚያ በኋላ ሱዳንም እንደሊቢያና እንደየመን ብትሆን፣ የራሷ ጉዳይ” እንደማለት ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት፤ የማስጠንቀቂያ ጊዜውን ወደ ሶስት ወር መቀየሩን የገለፀው በግብፅ ስብሰባ ካደረገ በኋላ ነው፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንት ጄነራል አልሲሲ፣ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙ ጊዜ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያና የማዕቀብ ውሳኔ ደርሶባቸው ነበር - ከአፍሪካ ህብረት፡፡ ዛሬ በጄነራል አልሲሲ ሰብሳቢነት፣ የአፍሪካ ህብረት በሱዳን ጄነራሎች ላይ ይዝታል፡፡
በእርግጥ የአፍሪካ ህብረት፣ መፈንቅለ መንግስትንና አምባገነንነትን ለመከላከል መሞከሩ ጥሩ ነው፡፡ የህገ መንግስት ተገዢ የሆነና በምርጫ ስልጣን የያዘ መንግስት ወደ ስልጣን እንዲመለስ ለማድረግ መጣርም ተገቢ ነው፡፡
ችግሩ ምንድነው? በሱዳን የቀድሞው ጄነራል አልበሽር፣ በሌላ ጄነራል ነው የተፈነቀሉት፡፡ አዲሱ ጄነራል አሁን የያዙትን ስልጣን ለቀድሞው ፕሬዚዳንት ይመልሱ? አይ! እንደዚያ ሳይሆን …
“ታዲያ እንዴት?” ተብሎ ሲጠየቅ፣ ያው … “የኋላ ኋላ ምን እንደሚመጣ ባላውቅም፣ ወታደራዊው መንግስት ስልጣኑን ማስረከብ አለበት፡፡ ለማን እንደሚያስረክብ ባይታወቅም …” ከማለት ውጭ፤ ሌላ ግልፅ መልስ ከአፍሪካ ህብረት አታገኙም፡፡ በእንዲህ አይነት የዘፈቀደ አስተሳሰብ ነው፣ የመንና ሊቢያ የተተራመሱት፡፡
መቼም የትም ቢሆን፣ በዘፈቀደ ወደ ተሻለ ደረጃ ማደግ፣ ወደተቃና መንገድ መግባት አይቻልም፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ አገራት የስልጣኔ ግስጋሴም፣ በትክክለኛ አስተሳሰብና በእውቀት፣ በትክክለኛ መርህ እና በጠንቃቃ ጥረት፣ የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት ለመጠበቅ የሚያስችል ህግና ስርዓትን በመገንባትና በማስከበር እንጂ፣ በዘፈቀደ የተከሰተ ስኬት አይደለም፡፡
ዛሬ በእውነትና በእውቀት ምትክ፣ የሃሳብ ብዝሃነትና ፍጭትን የማምለክ የዘፈቀደ አስተሳሰብ በተስፋፋበት ዘመን፣ … በትክክለኛ መርህ ላይ የተመሰረተ ህግና ስርዓት ቸል እየተባለ፣ በማንኛውም ነገር ላይ፣ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጭምር መወያየትና መደራደር ያስፈልጋል የሚል መርህ የለሽ፣ ለዝርፊያና ለግድያ ሱሰኞች የተመቸ የዘፈቀደ አስተሳሰብ እየገነነ በመጣበት ዘመን፣ ነባሩ የአሜሪካና የአውሮፓ የስልጣኔ ጉዞ ቢንገራገጭና ቢደናቀፍ አይገርምም፡፡ እየተቃወሱም ነው፡፡ እየታመሙ መሆናቸው የሰሞኑ አውሮፓ ህብረት ምርጫ ይመሰክራል፡፡
ከእንግሊዝ፣ ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ብዙ ወንበር ለማሸነፍ የቻሉት አንጋፋዎቹ ሁለት ፓርቲዎች አይደሉም፡፡ ገና ከዓመት በላይ ዕድሜ ያላስቆረ ፓርቲ፣ ከነባሮቹ የበለጠ ብዙ ወንበሮችን አሸንፏል፡፡
በጣሊያንስ? ሁለቱ ነባር ፓርቲዎች ከተፎካካሪነት ተርታም እየወረዱ ነው፡፡ ብዙ ድምፅ ያገኙት ፓርቲዎች፣ ሌሎች ናቸው፡፡ በፈረንሳይም ተመሳሳይ ውጤት ነው የታየው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ለአውሮፓ ህብረት ብቻ ሳይሆን በየአገራቸው ፓርላማስ?
የአውሮፓ ነባር ፓርቲዎች፣ እንደቀድሞው ስልጣን ለመያዝ የሚያበቃ የምርጫ ድምፅ ማግኘት አቅቷቸዋል፡፡ ድሮ ቀረ፡፡ ከ50% በላይ ድምፅ ለማግኘትና ስልጣን ለመያዝ የሚችል ነባር ፓርቲ ጠፍቷል - በአውሮፓ ምድር፡፡ ይህም የወረርሽኝ ምልክት ነው፡፡ ካሁን በፊት ያልነበረ በሽታ ነው:: በፈረንሳይ፣ በጣሊያን፣ በስፔን፣ በግሪክ … ከቁብ የማይቆጠሩ ወይም ድንገት የተፈለፈሉ ፓርቲዎች ስልጣን ይዘዋል፡፡ ግን እነዚህም ቢሆኑ፣ ድንገተኛው የምርጫ ስኬትና ስልጣን፣ በድንገተኛ ተቃውሞና ንትርክ እየተናጠ ነው፡፡
ለበርካታ አስርት አመታት በስክነትና በደልዳላነት የሚታወቁ ዋናዎቹ የአውሮፓ አገራት፣ እንግሊዝ እና ጀርመን እንኳ ጤና አጥተዋል፡፡ በጀርመን የፖለቲካ ምርጫ፣ በየተራ እያሸነፉ ስልጣን ላይ ሲፈራረቁ የነበሩ ሁለት አንጋፋ ፓርቲዎች፣ ዛሬ እየከሰሩ ነው:: አንደኛው ፓርቲ ከ20% በላይ ድምፅ ማግኘት አቅቶታል፡፡ የአንጌላ ሜርከል ፓርቲም፣ ከ30% ብዙም አይበልጥም፡፡ ለዚህም ነው አንጌላ ሜርክል፣ ከስልጣን እለቃለሁ ለማለት የተገደዱት፡፡
የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትርም እንዲሁ፣ የአገራቸው ቀውስ ከስልጣን እለቅቃለሁ አሰኝቷቸዋል፡፡ የእንግሊዝ አንጋፋ ፓርቲዎችም፣ ዛሬ ዛሬ በምርጫ አስተማማኝ የድጋፍ ድምፅ ማግኘት የሩቅ ዘመን ህልም ሆኖባቸዋል፡፡ በዚያ ላይ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት የመውጣት ውሳኔ፣ ተጨማሪ ቀውስ ደረበባቸው፡፡
ያልታመመ አገር እየጠፋ ነው፡፡
ሌላው ሌላው ሁሉ ይቅርና አሜሪካ እንኳ እየተደነቃቀፈች ነው፡፡ በአንጋፋዎቹ ፓርቲዎች ውስጥ፣ ቅንጣት ቦታና ተቀባይነት ያልነበራቸው ዶናልድ ትራምፕ፣ ታዋቂና አንጋፋ ተፎካካሪዎችን አሸንፈው ስልጣን መያዛቸው ብቻ አይደለም አስገራሚው ክስተት፡፡ ያለ አንዳች ማስረጃ፣ ፕሬዚዳንቱን በሀሰት ለመክሰስና ከስልጣን ለማውረድ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ዘመቻም፣ የአሜሪካ ፖለቲካ ከዘመኑ ወረርሽኝ እንደላመለጠ ይጠቁማል፡፡     

Read 1146 times