Sunday, 02 June 2019 00:00

ቃለ ምልልስ የሴቶች የንግድ ሥራ ፈጠራ - የ6 ዓመት ጉዞ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 “ፕሮጀክቱ ብዙዎችን ባለሃብት አድርጓል”

 • ለሴቶች ሥራ ፈጣሪዎች ከ50 ሺ ብር - 1 ሚሊዮን ብር ያበድራል
• ባለፉት 6 ዓመታት ከ17 ሺ በላይ ሴቶች የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል


           የሴቶች ኢንተርፕሪነርሽ ልማት ፕሮጀክት፣ ከ6 ዓመት በፊት መንግስት በብድር ባገኘው ገንዘብ የተጀመረ ሲሆን በርካታ ሴቶችን በንግድ፣ በአገልግሎትና በምርት ዘርፍ አሰልጥኖ፣ ብድር በመስጠት፣ ብዙ ሴቶችን ለስኬት አብቅቷል:: ፕሮጀክቱ ብዙዎችን ባለሃብት አድርጓል ይላሉ - የፕሮጀክቱ አስተባባሪ፡፡
ባለፉት 6 ዓመታት በዚህ ፕሮጀክት፣ ከ17 ሺህ በላይ ሴቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ይሄ ፕሮጀክት በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ላይ የሚጠናቀቅ ቢሆንም፣ መንግስት ከአውሮፓ ህብረት ተጨማሪ የ30 ሚሊዮን ዩሮ ብድር በማግኘቱ፣ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት  እንዲራዘም ፈቅዷል፡፡
የሚዲያ ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ አግኝተው ለሴቶች ግንዛቤ መፍጠር እንዲችሉ በሚል ዓላማ፣ ባለፈው ሳምንት፣ በአዳማ  የሦስት ቀናት ሥልጠና ተዘጋጅቶ ነበር:: በስልጠናው ላይ የተሳተፈችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ ዙሪያ ከፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ሰለሞን ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡


              ስለዚህ ፕሮጀክት አመሰራረትና አላማ ጠቅለል አድርገው ቢያስረዱኝ?
ፕሮጀክቱ የሴቶች ኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት ይባላል፡፡ ፕሮጀክቱ ለሴቶች ብቻ የተቀረፀ ፕሮጀክት ነው፡፡ ከሴቶችም ለጀማሪዎች ሳይሆን ቀደም ሲል በራሳቸው አቅም በንግድ፣ በአገልግሎትና በምርት ዘርፍ ተሰማርተው ህጋዊ ሰውነት ያላቸውን ሴቶች ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ እንደሚታወቀው መንግስት  ጀማሪዎችን ለማደራጀት፣ ለማሰልጠንና የብድር አገልግሎት አግኝተው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ እየሞከረ  ነው፡፡ ከዚያ ወጥተው ሻል ያለ ስራ ለመስራት ሲሞክሩ፣ የፋይናንስ አቅም ያጥራቸዋል፤ የተሻለ እውቀትም ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ ይሄ ፕሮጀክት ፋይናንስ በማቅረብ የሚያግዛቸው አብዛኞቹ ወደ አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የሚሸጋገሩት ናቸው፡፡ እነዚህ ከባንክ ለመበደር ባንኮች ስለማይቀበሏቸው ፕሮጀክቱ ትልቅ የሽግግር ድልድይ እየሆናቸው ነው፡፡ እኛ ጋ ይመጡና የተሻለ ስልጠናና የተሻለ ብድር አግኝተው፣ አቅማቸውን አጎልብተው ይሄዳሉ፡፡ ስራቸውን እያስፋፉና እያሳደጉ፣ በቀጣይ ወደ ባንክ ተበዳሪነት ያድጋሉ ማለት ነው፡፡ የእኛ ደንበኞች ዝቅተኛ ተበዳሪዎች 50 ሺህ ብር፣ ከፍተኛ ተበዳሪዎቹ ደግሞ እስከ 1.ሚ ብር እስከ መበደር ደርሰዋል፡፡ በተጨማሪም ቶሎ ቶሎ እየሰሩ ከመለሱ፣ ደግመው ደጋግመው የመበደር እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በዚህ እድል ተጠቅመው ከራሳቸው የንግድ ማስፋፋት አልፈው ለሌሎችም የስራ እድል እየፈጠሩ እንዳሉ በዚህ ስልጠና ካሳየናችሁ በተጨማሪ በምሳሌነት የተጠቀሱትን ቦታው ድረስ ወስደን አስጐብኝተናችኋል፡፡ የአይን ምስክር ናችሁ ማለት ነው፡፡ ከየት ተነስተው የት ደረሱ የሚለውንም ተመልክታችኋል፡፡ ፕሮጀክቱ በጣም ትልቅ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል ብዬ አስባለሁ::
የምታበድሩት ገንዘብ ምንጩ ከየት ነው? ተዘዋዋሪ ፈንዱስ ምን ያህል ነው?
እንግዲህ ስንጀምር፣ መንግስት ከአለም ባንክ ተበድሮ ለፕሮጀክቱ የሰጠን ገንዘብ 50 ሚ. ዶላር ነበር፡፡ ይህ ገንዘብ በስድስት ከተሞች የሙከራ ሥራ ላይ ነው  የዋለው፡፡ አጠቃላይ የሴቶቹን አቅም በስልጠና፣ በማጐልበትና ብድር በመስጠት፣ የስራ እንቅስቃሴያቸውን፣ ብድር የመመለስ ቁርጠኝነታቸውንና ፍላጐታቸውን ለማወቅ የመሞከር ስራ ላይ ነው የዋለው፡፡ መንግስት ይህን ውጤት በማየት ተጨማሪ 50 ሚ. ዶላር  ሰጠን፤ ከጃፓን መንግስት ተበድሮ፡፡ ከጣሊያን መንግስት ደግሞ ሌላ 15 ሚ. ዩሮ ተገኘ፡፡ ይሄ ገንዘብ ሲጨመር አገልግሎቱን ከስድስት ከተሞች ወደ 10 አሳድገን አስፋፋን፡፡ የማበደር አቅማችንም በዚያው መጠን አደገ፡፡ ይሄ ፕሮጀክት በሚቀጥለው አመት ታህሳስ ወይም በፈረንጆቹ 2019 መዝጊያ ላይ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት፣ ተጨማሪ 30 ሚ. ዩሮ ብድር ከአውሮፓ ህብረት አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ፕሮጀክቱ ለሌላ ሁለት ዓመት እንዲቀጥል መንግስት ፈቅዷል፡፡ ተጨማሪ ከተሞችን ለማካተትና አገልግሎቱን ለማስፋት በማጥናት ላይ ነን፡፡ በዚህ መልክ ነው ፕሮጀክቱ  እያደገ ያለው፡፡
ባለፉት ስድስት አመታት 20 ሺህ ሴቶችን አሰልጥናችሁ ለማበደር አቅዳችሁ እንደነበር በስልጠናው ወቅት ገልፃችሁልናል፡፡ ለመሆኑ ከእቅዳችሁ ምን ያህሉን አሳክታችኋል?
እስካሁን 17ሺህ 588 ሴቶችን አሰልጥነን ብድር ሰጥተናል፡፡ ይሄ ቁጥር አሁን ካለንበት አንድ ወር ወደ ኋላ የተመዘገበ ነው፡፡ ከዚህ ቁጥር በኋላ አንድ ወር ሙሉ ተጨማሪ አገልግሎት ሰጥተናል፡፡ ብዙ አዳዲስ ሴቶችም ስልጠና ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ እስከ ፕሮጀክቱ መጠናቀቂያ ዲሴምበር 2019 ዓ.ም ድረስ ሙሉ በሙሉ እቅዳችንን እናሳካለን ብለን እናምናለን:: ከዚያም ገፋ ያለ አገልግሎት ልንሰጥ እንችላለን፡፡  
ኢንተርፕሪነር ሴቶች ገንዘብ ሲበደሩ የሚያስይዙት (ኮላተራል) አለ? ወለድስ ይከፍላሉ?
መቼም ብድር ሲባል ከወለድ ነፃ የሆነ ብድር ያለ አይመስለኝም፡፡ ከወለድ ነፃ የሚባለው እንኳን የአገልግሎት ምናምን ተብሎ ይከፈላል እንጂ የተወሰደው ገንዘብ ብቻ አይመለስም፡፡  በነፃ ገበያ ህግጋት መሰረት፣ ማንኛውም ተበዳሪ፣ ለተበደረው ገንዘብ የአገልግሎትና የወለድ ክፍያ እንደሚከፈል ይታወቃል፡፡ ወለዱ እንደየ አበዳሪዎቹ አይነት፣ ባህሪና መጠን ሊለያይ ይችላል፡፡ እርግጥ ወለድ ላይ በተበዳሪዎችም በኩል አንዳንድ ጥያቄዎች ይነሳሉ:: እኛ አንዱ ስልጠና የምንሰጥበትም ጉዳይ ይሄው ነው፡፡ መበደር አስፈላጊ ነው፡፡ የዓለም ንግድና አገልግሎት የሚንቀሳቀሰው በብድር ነው፡፡ ነገር ግን ትኩረቱ ወለድ ላይ አይደለም፡፡ ተበዳሪው የሚሰማራበት ሥራ፣ የተበደረውን ገንዘብና ወለድ ለመክፈል ያስችለዋል ወይ ብቻ ሳይሆን የእሱን ደሞዝ፣ የሰራተኛ ክፍያ፣ የቤት ኪራይና የመንግስትን ግብር ሁሉ ጨምሮ መክፈል የሚችል ነው ወይ የሚለውም መታወቅ አለበት፡፡ ያንን ካወቁ መበደር ከባድ አይሆንም፡፡ ይበደራል ይሰራበታል፤ እንደገና ሌላ ብድር ይወሰዳል፡፡ ስራውም ብድሩም እየሰፋ ይሄዳል፤ ትርፍና ገቢውም ያድጋል፡፡ ለብድሩ ኮላተራል ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን የቤት ካርታ ሊብሬና መሰል ነገሮችን ያስይዙ ነበር፡፡ እያስያዙም ነው የሚበደሩት፡፡ አሁን አዳማ ላይ አንድ የተጀመረ ሙከራ አለ፡፡ ወሳሳ የተባለው ማይክሮ ፋይናንስ፣ አዳማ ላይ ያሉ ሴቶችን ያለ ኮላተራል ማበደር ጀምሯል፡፡ ይሄ የሚገርምሽ፣ የሴቶቹን የስራ ፍላጐት፣ ቢዝነሳቸውን የማስፋፋት ጉጉትና በራስ የመተማመን ስሜታቸውን ጨምሮላቸዋል፡፡ ይህንን ስመለከት  ያለ ማስያዣ (ኮላተራል) ማበደር ቢፈቀድ፣ ለጀማሪ ሴቶች ማበደር እንጀምር ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡
እንዴት ማለት?
ሴቶቹ መጀመሪያ ስልጠናውን ሰጥተናቸው ወደ ሥራው ቢገቡ ጥሩ ይሆናል፡፡ ወጪና ገቢያቸውን አስልተው፣ የመሸጫ ዋጋቸውን ተምነው፣ ምን አይነት ስራ በምን አይነትና በምን ያህል ጊዜ ሰርተው ወደ ትርፍ እንዳሚሻገሩ ቀድመው አውቀው ይገባሉ፡፡ መንገዱ ሁሉ ብሩህ ይሆናል:: አየሽ አሁን የእኛ ደንበኞች ስንት ውጣ ውረድና ኪሳራ አልፈው ነው እዚህ የደረሱት፡፡ የብዙዎቹን መነሻ ሰምታችኋል፤ ነግረዋችኋል፡፡ አሁንም ወደ ስልጠናው የምናመጣቸው በብዙ ጥረት ነው፡፡ ከመጡ በኋላ ግን ስልጠናውን ሲጨርሱ ተደስተው፣ አስተማሪዎቻቸውን አመስግነውና ሸልመው፣ ወደ ስራቸው በተሻለ አቅም ይገባሉ፡፡ እስካሁን ውጤታማ ናቸው፡፡
ሴቶቹን ወደ ስልጠና ለማምጣት ብዙ ትግል የሚገጥማችሁ ለምንድን ነው?
በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሴቶች በብዙ ሀላፊነት የተጠመዱ ናቸው፡፡ ስራቸውን ሲሰሩ ይውሉና ወደ ቤታቸው፣ ወደ ልጆቻቸው ይሮጣሉ፡፡ ቤታቸውም ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ልጆቻቸውን ከት/ቤት ለማምጣት እንኳን የሚያግዛቸው ሰው የላቸውም፡፡ በብዙ መልኩ ጊዜ ያጥራቸዋል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ጠንክረን በማስረዳት ማሳመን ከቻልን ወደ ስልጠናው ይመጣሉ፡፡ ከሰለጠኑ በኋላ ግን እጅግ ደስተኞች ሆነው ነው የሚመለሱት፡፡
ለሚዲያ ባለሙያዎች በሴቶች ኢንተርፕሪነርሺፕ ዙሪያ፣ በአዳማ ከተማ፣ የ3 ቀናት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ የሥልጠናው አላማ ምንድን ነው?
ጥሩ! ይሄ እጅግ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ለሴቶች ይበልጥ ስራውን ለማስፋትና በተለይ በእኛ ፕሮጀክት ለመሰለጥንና ለመበደር ለሚፈልጉ፣ ነገር ግን መረጃው ለሌላቸው በመገናኛ ብዙኃን በኩል እንዲደርሳቸው እንሻለን፡፡ መገናኛ ብዙኃን መረጃውን ለማድረስ ደግሞ የግድ ቀድመው ስለ ፕሮጀክቱ አላማና ግብ ግንዛቤ ማግኘት አለባቸው:: የስልጠናው ዋና አላማም ይሄው ነው፡፡ ከዚህ በፊት ለጋዜጠኞች በሰጠናቸው ስልጠና መሰረት፣ ብዙዎች የእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን በቅተዋል:: ሥራው ብዙ የሚዲያ እገዛ የሚፈልግ ግን ደግሞ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አንድ ሥራ በእውቀት ሲደገፍ ውጤታማ ይሆናል፡፡ እህቶቻችን በልምድ ገብተው ነው የሚሰሩት፡፡ እርግጥ በልምድም ውጤታማ የሆኑ አሉ፡፡ በእውቀት ቢያግዙት ደግሞ የበለጠ ውጤት ያስመዘግባሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከእኛ ጋር የሚያገናኛቸው ሚዲያ ነው፡፡
ሴቶቹ ስልጠና ለሚሰጧቸው ተቋማት የሚከፈልላቸው ገንዘብ ያለ ይመስለኛል እስኪ በዚህ ላይ ማብራሪያ ይስጡኝ?
ከተለያዩ አገራት የሚገኘው ገንዘብ ለብድር ብቻ ነው የሚውለው፡፡ የስራ ማስኬጃውንና ለሴቶቹ ስልጠና የሚያስፈልገውን ወጪ  መንግስት ከአለም ባንክ ነው የሚያገኘው፡፡ በነገራችን ላይ ለሴቶቹ ለስልጠና ከሚሰጠው ገንዘብ አሰልጣኝ ተቋማት ያን ያህል ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ሀገራዊ ግዴታችን ነው ብለው ነው አብረውን የሚሰሩት፡፡ በተለይ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ማዕከላቱ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን የማሰልጠን ከፍተኛ ተልዕኮ አላቸው፡፡
ከዚህ አንፃር፣ የእኛ ሰልጣኞች ሥልጠና በተወሰነ የጊዜ ገደብ የሚጠናቀቅ ስለሆነ ነገ ዛሬ እንዳይባል፣ እስኪሪብቶና ደብተር አልተገዛም ተብሎ እንዳይጓተት የተወሰነ ክፍያ ነው የሚከፈለው፡፡ እንደውም አሁን ይህን አስረድተን፣ የግል ኮሌጆችም አብረውን ለመስራት ፈቃደኛ ሆነዋል፡፡ በዚሁ በምንከፍለው ዋጋ ማለት ነው፡፡
ለአንዲት ሰልጣኝ ምን ያህል ትከፍላላችሁ ማለት ነው?
ለአንዲት ሴት ለ40 ሰዓት ሥልጠና 840 ብር እንከፍላለን፡፡ በጣም አጫጭር ኮርሶች አሉ፡፡ 20 ሰዓት ሲሆን 420 ብር ይከፈላል፡፡ በቴክኒክና ሙያ ደረጃ ለሚሰለጥኑት 1366. 50 በሰው እንከፍላለን:: ከሚሰጡት ስልጠና አንፃር፣ የጥሬ እቃና መሰል ጥቃቅን ወጪዎች ይሸፍን እንደሆነ እንጂ ክፍያ አይባልም፡፡ ለአንዲት ሴት ይሄ ክፍያ አንዴ ከተከፈለ፣ 1 ወርም  ትሰለጥን 3 ወር፣ ምንም አይነት ጭማሪ አያስከፍሉንም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡ አገራዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ነውና፡፡
በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ---
ይህ ፕሮጀክት ብዙዎችን ባለሀብት አድርጓል፤ እያደረገም ነው፡፡ ለተጨማሪ ሁለት አመት እንዲራዘም፣ መንግስት ተጨማሪ ብድር አግኝቷል:: በንግድ ስራ ላይ ያሉ ሴቶች፣ ወደ እኛ መጥተው፣ ስልጠና ወስደውና ብድር አግኝተው፣ ስራቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡

Read 745 times