Print this page
Monday, 03 June 2019 15:45

የእጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ሐሳብ ላይ የቀረበ ሒሳዊ አስተያየት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(2 votes)


            “--ባህሩ ዘውዴ በመፅሐፋቸው ባያካትቱትም፣ ኢትዮጵያን የማዘመን ሐሳብ በሦስተኛው የአብዮቱ ትውልድም ቀጥሏል፡፡ ይህ ትውልድ ሶሻሊስቷን ሩሲያን እንደ አብነት በመውሰድ ትውፊታዊ የሆነውን ነገር በሙሉ ኋላ ቀር አድርጎ በመቁጠር፣ የሥር ነቀል አብዮታዊ መንገድን ያቀነቀነ ነው፡፡ --”
                
             (ይህ ፅሁፍ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል፣ ከግንቦት 19-20፣ 2011 ዓ.ም
ባዘጋጀው 6ኛው አገር አቀፍ የባህል አውደ ጥናት ላይ የቀረበ ነው)
በኢትዮጵያ የምሁራን ታሪክ ውስጥ የእጓለ ስፍራ
ኢትዮጵያን የማዘመን ሐሳብ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ወደ ቤተ መንግስት ካስገቡት በኋላ በተከታታይ የመጡ ነገስታትም፣ ይሄንን ሐሳብ በራሳቸው መንገድ ሲፈፅሙት ቆይተዋል፡፡ ሐሳቡን ከነገስታቱ በመቀበል በየዘመኑ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራንም የተለያዩ ጥናቶችን አድርገውበታል፡፡
ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር) ‹‹Pioneers of Change in Ethiopia›› (2002) በሚለው ታዋቂ መፅሐፋቸው ውስጥ በኋላ ቀርነታችን ተቆጭተው፣ ሀገራቸውን ለመቀየር ቆርጠው የተነሱ ምሁራንን በሁለት ትውልድ ይከፍሏቸዋል - የመጀመሪያ ትውልድና ሁለተኛ ትውልድ በማለት፡፡ ይህ የምሁራን አከፋፈል፣ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን  መጨረሻ አንስቶ እስከ 1966ቱ አብዮት ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው፡፡
የመጀመሪያ ትውልድ ምሁራን የሚባሉት፤ እስከ ጣሊያን ወረራ (1928) ድረስ ያሉ ምሁራንን የሚያካትት ሲሆን እነሱም ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ፣ አለቃ አፅመ ጊዮርጊስ፣ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ፣ ነጋድረስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፣ በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማሪያም፣ ከንቲባ ገብሩ ደስታ፣ ብላታ ገብረ እግዚአብሔር ጊለ ማርያም፣ መርስኤ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ፣ ብላታን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የመሳሰሉትን የሚያካትት ነው፡፡ ይህ ቡድን በአፄ ምኒሊክ ዘመን የነበረና የሀገሪቱን የፖለቲካል ኢኮኖሚ ለውጦች በተመለከተ ለዘብተኛ አቋም ሲያራምድ የነበረ ሲሆን፣ በይበልጥ አስተዳደራዊ ነገሮች ላይ ያተኩራል፡፡
የሁለተኛ ትውልድ ምሁራን የሚባሉት ደግሞ ከጣሊያን ወረራ በኋላ የመጡትን ምሁራን የሚያካትት ሲሆን፣ ይህ ቡድን በንጉስ ተፈሪ መኮንን የሚመራ ነው፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ አብዛኛዎቹ ባለስልጣናት፣ በዚህ ‹‹የተራማጆች›› (Progressive) ቡድን ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ የዚህ ቡድን ዓይነተኛ መገለጫ ጃፓንን እንደ ሞዴል በመውሰድ፣ ‹‹የዘመናዊነታችን አቅጣጫ ትውፊታዊውን ባህልና ዕውቀት ከዘመናዊው ትምህርት ጋር ማጣመር መሆን አለበት›› የሚል ሐሳብ የሚያራምድ መሆኑ ነው፡፡ እጓለ ገብረ ዮሐንስም፤ እዚህ ሁለተኛው ትውልድ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡
ባህሩ ዘውዴ በመፅሐፋቸው ባያካትቱትም፣ ኢትዮጵያን የማዘመን ሐሳብ በሦስተኛው የአብዮቱ ትውልድም ቀጥሏል፡፡ ይህ ትውልድ ሶሻሊስቷን ሩሲያን እንደ አብነት በመውሰድ ትውፊታዊ የሆነውን ነገር በሙሉ ኋላ ቀር አድርጎ በመቁጠር፣ የሥር ነቀል አብዮታዊ መንገድን ያቀነቀነ ነው፡፡
‹‹በተዋህዶ ከበረ››
እጓለ ‹‹ዘመናዊነታችን ትውፊታዊውን ባህልና ዕውቀት ከዘመናዊው ትምህርት ጋር ያጣመረ መሆን አለበት›› ከሚለው ከሁለተኛው ትውልድ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆኑ ለዚህ ሐሳብም ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› የሚል ፍልስፍናዊ ትንታኔ ሰጥተውታል፡፡
እጓለ የዘመናዊነት ሐሳባቸውን ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› በማለት ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› መፅሐፋቸው ውስጥ ሰፋ አድርገው ተንትነውታል፡፡ የዚህ መፅሐፉ የመጀመሪያ ዕትም በ1956 የወጣ ሲሆን እኔ ለዚህ ፅሁፍ የተጠቀምኩት ግን በ2003 ዓ.ም የታተመውን ሁለተኛውን ዕትም ነው፡፡ በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› የሚለው ምዕራፍ፣ መፅሐፉ የተፃፈበትን ዋነኛ ዓላማ የያዘ ነው፡፡
‹‹በተዋህዶ ከበረ›› የሐሳቡ አመጣጥ ሃይማኖታዊ መነሻ ቢኖረውም (ገፅ 79)፣ ሆኖም ግን እጓለ ሐሳቡን የተጠቀሙት ፍልስፍናዊ አድርገው ነው፡፡ እናም እጓለ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ሲሉ ኢትዮጵያ በወቅቱ ያጋጠማትን ‹‹የመንፈስ ችግር›› ለመፍታት ያመነጩት ፍልስፍናዊ ፕሮጀክት ነው፡፡ ቃሉ የሁለት ተፈላጊ ነገሮችን መጣመር፣ አንድ ላይ ተስማምቶ መኖርን የሚያመላክት ሲሆን፤ ዶ/ር እጓለም የቃሉን ትርጉም የሁለት የተለያዩ ሥልጣኔዎችን ጥምረት አስፈላጊነት ለማመላከት ተጠቅመውበታል፡፡
በመሆኑም፣ እጓለ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ሲሉ ኢትዮጵያዊው ሥልጣኔ (እሳቸው ‹‹ያሬዳዊ ሥልጣኔ›› ይሉታል) መንፈሳዊ እውቀቱንና ትውፊታዊ እሴቱን እንደጠበቀ ከአውሮፓ ዘመናዊ ትምህርትና ቴክኖሎጂ ጋር የሚዋኻድበትን ሐሳብ ለማመላከት ነው፡፡ ዶ/ር እጓለ ይሄንን ሐሳብ ያቀረቡት ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ ሳይንሳዊ እውቀትን በማመንጨትና ቴክኖሎጂን በመፍጠር ረገድ ጉድለት አሳይቷል›› ብለው በማመናቸው ነው፡፡
ሆኖም ግን፣ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ውስጥ ግልፅ ያልሆኑ፣ ጥያቄን የሚያጭሩና የተሸፈኑ (implicit) ሐሳቦች ያሉበት ነው፡፡ በመሆኑም፣ ይህ ፅሁፍ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ውስጥ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን፣ ግልፅ ያልሆኑና የተሸፈኑ ሐሳቦችን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡
በዚህም፣ ጥናታዊ ፅሁፉ ይሄንን የእጓለ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ሐሳብ መነሻ አድርጎ አምስት መሰረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ይሞክራል፤
‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ውስጥ የሚዋኻዱት ምንና ምንድን ናቸው?
‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ፖለቲካዊ ወይስ ፍልስፍናዊ መፍትሔ?
ምዕራባዊው ሥልጣኔ የተመሰረተው ‹‹በግለሰብ ሉዓላዊነት›› ላይ ነው። በአንፃሩ፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ደግሞ ማህበረሰባዊ (ባህላዊና ሃይማኖታዊ) እሴቶች ላይ የተመሰረተ ነው። እናም ጥያቄው፣ ዶ/ር እጓለ ወደ አውሮፓ ሲያማትሩ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ውስጥ የግለሰብ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?
የ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አንደምታዎቹ ምንድን ናቸው?
ዶ/ር እጓለ ከአውሮፓ በትክክል የፈለጉት ነገር ምንድን ነው? ምዕራባዊውን ትምህርትና ህሊና ነው? ወይስ ምዕራባዊውን ቴክኖሎጂ? ወይስ ሁለቱንም?
ይህ ጽሁፍ፤ የእጓለ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ሐሳብ በውስጡ የተሸከመውን ፍልስፍናዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምልከታዎች  ይፈትሻል፡፡ በዚህም ጽሁፉ፤ የእጓለ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ሐሳብ ‹‹ምን ይሻላል?›› ለሚለው ፖለቲካዊ ጥያቄ መልስ የሰጠ እንጂ፣ ‹‹የችግሩ ሥረ መሰረት ምንድን ነው? ለሚለው ፍልስፍናዊ ጥያቄ መልስ ያመጣ ሐሳብ አይደለም›› በማለት ይከራከራል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፣ ፅሁፉ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› የሚለው ሐሳብ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምልከታው ለመንግስት ከፍተኛ ሥልጣን በመስጠት የግለሰብን ነፃነትና ሉዓላዊነት የሚያቀጭጭ ነው የሚል መከራከሪያ ሐሳብም አለው፡፡ ዶ/ር እጓለ ‹‹በተዋህዶ ከበረ››ን ይዘው እስኪመጡ ድረስ ኢትዮጵያን የማዘመኑ ምሁራዊ ሐሳብ የ50 ዓመታት ዕድሜን አስቆጥሮ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ሐሳቦችም ባህል፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ የሚያተኩሩ ነበሩ:: ከእነዚህ ሐሳቦች አንፃር፣ የእጓለን አቀራረብ ለየት የሚያደርገው ሦስት ነገሮች አሉ፡፡
የመጀመሪያው፣ ኢትዮጵያን የማዘመኑ ሐሳብ ከተለመደው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሐሳቦች በመውጣትና የውጭ ሞዴል ከመፈለግ አባዜ በመላቀቅ ፍልስፍናዊ አቀራረብን መከተሉና ለዘመናዊነቱ ሐሳብ ፍልስፍናዊ መሰረት መስጠቱ ነው፡፡ ሁለተኛ፣ በሰው ልጅ የሥልጣኔ ታሪክ ውስጥ ሀገራችን ያለችበትን ስፍራ ማሳየት መቻሉ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ፍልስፍናዊ በሆነ መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳዩን ዶ/ር እጓለ ናቸው፡፡ በዚህም፣ የያሬዳዊውን ሥልጣኔ መሰረታዊ ባህሪና ኪነ ጥበባዊ መሰረቱን አሳይተውናል፡፡
በክፍል-2 ፅሁፌ፣ እጓለ የአውሮፓንና የኢትዮጵያን ሥልጣኔ የተነተኑበትን ሐሳብ እንመለከታለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው፡-  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.   ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 2478 times