Monday, 03 June 2019 15:48

ሞትም ዓይነት አለው!

Written by  በስንታየሁ አለማየሁ
Rate this item
(1 Vote)


                “--እያሰቡ መሞት፣ ሳያስቡ ከመኖር የተሻለ መሆኑን ሲሰብክና ሲያስተምር የነበረ ሊቅ፤ ለሃሳብ ልዕልናና ለእውቀት መንበር ሲል እራሱን እስከ ሞት አሳልፎ በመስጠትም ጭምር በተግባር አሳይቷል፡፡ እየኖረ ከሚሞት፣ በሞቱ ውስጥ መኖርን መርጦ ሞተ፤ በዚህም በሞቱ ሞትን እንደ እየሱስ ድል ነሳ ማለት ነው፡፡--”
       

              እንደ መግቢያ
ሰው አፈጣጠሩ ልትገባ እንደምትወጣ ፀሐይ ወይንም ሊመሽ እንደሚነጋ ቀን ነው፡፡ የሰው ልጅ ሊሞት የተፈጠረ አስቂኝ ፍጥረት ነው፡፡ ሰው ያለ ሞቱ ሰው አይሆንም፤ እንደተወለደም ሊሞት ይችላል አሊያም እንደ ማቱሳላ ሊንዘላዘል ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ የህይወቱ ፍፃሜ ሞት ሊሆን ግድ የሆነበት ፍጥረት ነው፡፡ ለመሞት መወለድ ቢያስገርምም ቅሉ ከሞት በፊት ጠቃሚ ሆኖ ማለፍ ደግሞ ጀግንነት እየተባለ የሚፃፍ ገድል ነው፡፡ ከታደልንና እንስራበት ካልን፣ በሠላሳ አመት ውስጥ እንደ እየሱስ ስንት ተአምራትን መስራት እንችላለን፡፡ ካላለልን ደግሞ እንደ ማቱሳላ ዘጠኝ መቶ አመትም ብንኖር ምንም ሳንፈይድ እናልፋለን፡፡
የሕይወት በሞት የመገደብ ዋነኛ ጥቅሙ፤ ቶሎ ቶሎ ሰርቶ፣ ቶሎ ቶሎ ኖሮ የማለፍ ጉጉቱ ነው፡፡ ሞት እንዳለ ስለምናውቅ ብንችል ቶሎ ተሳክቶልን፣ ሁሉን በጊዜያችን አከናውነን ብንሞት እንወዳለን:: ሞት በመኖሩ ምክንያት የሰው ልጅ ከሞት ለማምለጥ ያልፈነቀለው ድንጋይ፣ ያልቧጠጠው ተራራ፣ ያላደረገው ጥረት የለም፡፡ ከባህላዊ እስከ ዘመናዊ የህክምና ተቋማትን በማስፋፋት፣ የህክምና ባለሙያዎችን በገፍ በማምረት፣ ትላልቅ የመድሃኒት ፋብሪካዎችን በማቋቋምና ወዘተ  ሞቱን ማስቀረት ባይችል እንኳ በተወሰነ ደረጃ ለማዘግየት ወይም ጥቂት ፈቀቅ ለማድረግ ሞክሯል፡፡ እየሞከረም ይገኛል፡፡ የሕይወት ትልቁ ትግል፤ ከሞት ጋር የሚደረገው ትንቅንቅ ይመስለኛል፡፡ በሞት ምክንያት የሰው ልጅ መንኮራኩር ሰርቷል፣ ሳተላይት ፈጥሯል፣ ኒኩሌር ቦንብ ፈብርኳል ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የጦር መሳሪያዎችን አምርቷል፣ ስንት ሺህ ረቂቅ የመሰለያና የመጠንቀቂያ መሳሪያዎችን አበጅቷል፡፡ ሞቱ ፍርሃትና ስጋትን ስለፈጠረበት ከዚህ ለመዳን ሲል፣ የሰው ልጅ አለሙን በብዙ ፈጠራዎቹ ሞልቷታል፡፡  
ምሳሌ የሆኑን ሞቶች (ቅዱስ ሞቶች)
1ኛ. ሶቅራጥስ
ምንም እንኳ በሞት የተከበበ ሕይወት እንዳላቸው ቢያውቁም፣ አንዳንድ ልዩ ግለሰቦች ግን ስለ መጪው ሞት ሳይሆን ስለ ዛሬው የእነሱ የህይወት ህልም፣ የእድሜ ዘመን ግብና ስኬት ነው የሚጨነቁት፡፡ እንደ ሶቅራጥስ ያሉቱ እድሜ ልካቸውን ለእውቀት ሲታትሩ፣ ድንቁርናን ሲጠየፉ፣ ማሰላሰልን ሲያስተምሩ፣ ምክንያታዊነትን ሲያስታጥቁ ነበር የኖሩት፡፡ በዚህም ምክንያት ሶቅራጥስ ለእውቀት ህልውና ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ዘመናትን የተሻገረ ድንቁርና፤ በሶቅራጥስ መስዋዕትነት ላይጨልም ዳግመኛ ወደ ብርሃን ማማ ተሰቀለ፡፡ በዚያ በአቴንስ ከፍተኛ የሆነ የሃሳብ ነፃነት እጦት፣ የሃሳብ ልዩነትም ድርቅ ነበር፤ ጣኦታትንና አማልክትን አለምክንያት መቀበልና በእነርሱም ማመን የሁሉ ሰብ ግዴታ ነበር፡፡ በዚያ ከጭሰኝነትና ከአጎብዳጅነት ብሎም ከገባሪነት ሌላ የግል ሰብአዊ ኑሮና አስተሳሰብን ማሻሻል የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ከመንጋ ትቢያ ህይወት መካከል በድንገት የእራስ ቅሉ ቅርፅ የሚያስቅ፣ ሰፊ ኮስታራ ፊቱና ጢሙ ከግዴለሽ አለባበሱ ጋር ተደምሮ የጎዳና እብድ የሚመስል አንድ ሰው በአቴንስ ጎዳና ብቅ አለ፡፡ በአቴንስ በኑሮ ትርምስ መካከል የሚገኙትን ብኩን ሰዎች መዳረሻው በማድረግ ሰብስቦ ማስተማር ጀመረ፡፡ በተደጋጋሚ እንዲህ በማድረጉና የተከታዮቹም ቁጥር በመጨመሩ ሶቅራጥስ ውጤታማ እንደሆነ አሰበ፤ ስለሆነም በየቀኑ እንዲያ ማድረጉን ይደጋግመው ዘንድ ወደደ፡፡
በስተመጨረሻ ሶቅራጥስ በተለይም የወጣቱን አዕምሮ ማብሰልና መከርከም ቻለ፡፡ Unreasonable Life is Unworthy of Man (ምክንያታዊ ያልሆነ ኑሮ መኖር የሌለበት ህይወት ነው እንደማለት ነው) ይህንን ብርሃን በመፍጠሩ ሶቅራጥስ ነፍሱን ሲያስደስት፣ በዘመኑ የነበሩ ንጉሶችና ሹሞች ግን “ወጣቱን አንቅተህና ቀስቅሰህ፣ አማልክቶቻችን ላይ እንዲያላግጡና እንዳያምኑባቸው፣ ለአማልክቶቻችንም እንዳይሰግዱ አድርገሃል” በሚል ተከሶ፣ ዘብጢያ ወርዶ፣ የሞት ፍርድንም ተቀበለ፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ጉዳይ የሞት ፍርዱ ሳይሆን ሶቅራጥስ የሞት ፍርዱን የተቀበለበት መንገድና ስለ ሞት የነበረው አመለካከቱ ነው፡፡ እያሰቡ መሞት፣ ሳያስቡ ከመኖር የተሻለ መሆኑን ሲሰብክና ሲያስተምር የነበረ ሊቅ፤ ለሃሳብ ልዕልናና ለእውቀት መንበር ሲል እራሱን እስከ ሞት አሳልፎ በመስጠትም ጭምር በተግባር አሳይቷል፡፡ እየኖረ ከሚሞት፣ በሞቱ ውስጥ መኖርን መርጦ ሞተ፤ በዚህም በሞቱ ሞትን እንደ እየሱስ ድል ነሳ ማለት ነው፡፡
2ኛ. አቡነጴጥሮስ
የእኛው ጀግና አቡነጴጥሮስም ህይወት እንደ ሶቅራጥስ ያለ ነው፡፡ የሰው ልጅ በአንድም ሆነ በሌላ የሚሞትለት አላማ ሲኖረው ደስ ይላል:: ልንሞትላቸው ከምንችለው አላማዎች መካከል ሀገር፣ እምነት፣ እውነት፣ እውቀትና ህልም ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ሶቅራጥስ ለእውቀት ሲል ሞተ፤ እየሱስ ለእውነት ሲል ሞተ ፤ አቡነጴጥሮስ ለእምነት ሲሉ ሞቱ፤ አጼ ቴዎድሮስ ለህልሙና ለሀገሩ ሲል ሞተ:: ከእየሱስ ውጭ እነዚህ ሰዎች እንደ ማንኛችንም አይነት ህይወት መኖር ይችሉ ነበር፡፡ ችላ በማለት፣ አይቶ በማለፍ፣ ቀን ያልፋል በማለት፣ አስመስሎና ተመሳስሎ በመኖር፤ በፍርሃትና በዝምታ፣ ሁሉን በመቀበልና እሺ ብሎ በመታዘዝ መኖር ይችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ መንጋው በቀደዱለት ቦይ የማይፈስ ህያው ማንነታቸው፣ የነፍሳቸው ጥሪም ቢሆን፣ ከፍ ላለ ህልውና በመፈጠሩ፣ እንደ ፈጣሪ ለራሳቸው ሳይሆን ለአብዛኛው ህይወት መለወጥና መጠበቅ ሲሉ እስከ ሞት አፋፍ እራሳቸውን ለመግፋት ፈቅደው ተነሱ፡፡ ክርስቶስን ያልተቀበለች አለም ግን አቡነጴጥሮስንም አሻፈረኝ በማለት በግፍ በሞቷ በላቻቸው፤ የተከፈተ ራዕያቸውን በመቃብር አዳፈነችባቸው፡፡ አቡኑ ግና ሞታቸው ለሌላው ህይወት ነው ብለው በማመናቸው፣ እየቆጫቸው ሳይሆን በሞታቸው ደስ ተሰኝተው ነው ያለፉት፡፡ በዚያ ውሳኔያቸው ምክንያት ያዳኑትንና የሚያድኑትን ህዝብ እያሰቡ ይመስላል ሲሞቱ በኩራትና በጀብደኝነት ነበር፡፡ ፕሌቶ ሲናገር፤ My Eternity is in the grateful memory of men (የኔ ዘላለማዊነት በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ነው እንደ ማለት) ብሏል፡፡ ዘላለማዊነት ከሞት ወዲያ ህይወት አለ ብለን በማመን ብቻ አይደለም፤ በኛ በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ተቀምጦ የሚቀር አንዳች ከፍ ያለ ስራንም ይጨምራል፡፡ ሲኖር---ሲኖር---ሲኖር ቆይቶ ሞተ ወይንም አረፈ ቢባል እንደ ማቱሳላ ምን ይጠቅማል?....ምንም፡፡ ባለችን ጥቂት እድሜ ሰርተንባት ካለፍን፣ በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ለዘለአለም ታትመን እንቀራለን፣ በዚያ ስማችን ዘወትር ይዘከራል፤ ሃውልትም ይቆምልናል፤ በስማችን ብዙ ነገር ይከናወናል....ቀጣይ ትውልድም ያለፉትን ሰዎች መንፈስ በመረከብ ልዕልናውን ይበልጥ ተቀብሎ ያቀጣጥላል .....ይሄ ነው ዘላለማዊነት፡፡
ከአቡነጴጥሮስም በሞታቸው ልንማር የተነሳነው፣ በልባችን ውስጥ ዘላለማዊ መሆን ስለቻሉ ነው፡፡ባንዳ ሆነው ማለፍ፣ በገዳማት እየጸለዩ  ማሳለፍ ሲችሉ.... ለሰውነት መታገል ድንበር የለውም በማለት ከአርበኞች ጋር ወግነው፣ ሰውን ከምድረ ገፅ እያጠፋ የመጣውን የጠላት ጦር ወጉት፡፡ “እኔን ከተቀበልክ እምርሃለው” ያለውን ጣሊያንንም አሻፈረኝ በማለት፣ እንኳንና ህዝቡ መሬቱ ጭምር ለጣልያን እንዳይገዛ ገዘቱ፡፡ በሞት አደባባይ ሲቆሙም፣ የራሳቸውን ሞት እራሳቸው እንጂ ማንም እንዳይመርጥላቸው ሲያሳዩ፣ በኩራት ለእውነትና ለእምነት በመቆም፣ በዚያ በፍፅምናቸው  ቀጠሉ.......፡፡ እንኪያስ መሞት ካለብን ለእንዲህ ያለው ሞት ነው። ለከንቱ ዝባዝንኬ ሞት መሰናዳት፣ አጉል ደመ ክልብነትና ከታሪክም ሆነ ከዘልቦና መፋቅ ይመስለኛል።
3ኛ. አጼ ቴዎድሮስ
የእሳቸው ኑሮና አስተዳደር ከዘመኑ በእጅጎ ልቆ የተከሰተና የተወለደ በመሆኑ ከነጭ ጠላቶቻችን አስቀድሞ ለውጡን መቀበል ያቃታቸው፣ የእኛው የሀገሬው ሰዎች ነበሩ፣ እንደ ጠላት ያዩአቸው:: አጼው ከፍ ላለ ህልማቸው፣ ከፍ ያለ ቆራጥ እርምጃ መውሰዳቸውን እንደ ሌላ አሉታዊ መንገድ የሚቆጥሩት መንፈሰ ሰንካሎች ቢኖሩም፣ በጥበብና በእይታቸው፣ በንባባቸውና በአስተዳደራቸው፣ እንዲሁም በቆራጥ አመራራቸው ሀገሪቱን ሊወስዷት የፈለጉበትን መዳረሻ አሳይተዋል፡፡ መላ የአለም ህዝብ የተደመመባቸው ንቁና ራዕየ ሰፊ ንጉስ  ነበሩ:: ከጀመሯቸው ስራዎች በላይ የሞቱበት መንገድ ለዝንተአለም መመራመሪያ እንደሆነ እስካሁንም ቀጥሏል....ነገም ከነገ ወዲያም እንዲሁ እያወያየ የሚቀጥልም ይመስለኛል፡፡
ጋሽ ፀጋዬ ስለ አጼ ቴዎድሮስ በፃፈው ተውኔት.....
“እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ እጅ ተይዞ ሊወሰድ” ይላል፡፡ በዚህ ውስጥ የምናየው አንድ ትልቅ እውነት፤ ተራ እምቢተኛነትን አይደለም ይልቁንስ.......የአጼው እጅ መስጠት ያለውን ሀገራዊ አንድምታ፣ ክሽፈት፣ ንቀት፣ ሽንፈት፣ ስንፈት...... በሱ ማጎብደድ ስር ኢትዮጵያ እንደምታጎበድድ፣ በሱ ማነስ ስር ሀገር እንደምታንስ ሲያመሰጥር ነው፡፡ ጋሽ ፀጋዬ በቃለ-ተውኔቱ ይቀጥላል…..
“…ህይወቱን እራሱ መርጦ እንደኖራት ሞቱንም እራሱ ከጠላት መንጋጋ ፈልቅቆ እንደሚሞታት እኔም የራሴን ሞት እራሴው ልሙታት....” ይላል፡፡ የራሳችን ህይወት ባለቤት ሆነን፣ እኛው ከኖርናት በጀግኖች አባባል ሞታችንንም ማንም ሊመርጥልንና ሊበይንልን አይገባም፤ እኛው መርጠን መሞት አለብን ይላሉ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ እንዲህ ያለ የላቀ ሰብዕና ነበራቸው......መሞታቸው ላይቀር ተይዞ ተልከስክሶ ሞተ ከመባል የራሳቸውን ህይወት እራሳቸው እንደኖሯት ሁሉ፣ ሞታቸውንም እራሳቸው እንደሚሞቷት ለማሳየት.....እጅ ባለመስጠት ሀገርን ከውርደት ለማስጣል፣ ህልማቸውን እንዳለሟት በገዛ እጃቸው ደግሞ በሞት አጅበው፣ ዝናና ክብርን ብሎም ዘላለማዊነትን በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ለማኖር ያደረጉት ገድል ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ማንም እራሱን እንደሚያጠፋ፣ ከንቱ ልበ ስውር የሚታይ አሟሟት ሳይሆን ከፍ ያለ ሰብዕናን የተላበሰ ሞት ነው ፤የአጼው ሞት.......ምሳሌ ሊሆነን የሚችል ሞት ነው፤ የእሳቸው ሞት፡፡ ሎሬቱ በቃለ ተውኔቱ እንዳለው...
..ያለፈ ጥረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ......ማለቱ ከነገረ ታሪኩ አንፃር እውነተኛ የቴዎድሮስ ንግግር ሁሉ ይመስለኛል....ህልሙን ሳይቋጭ ለተቋጨ አንድ ንጉስ፤ በትክክልም ሊል የሚችለው እንዲያ ነው፡፡ ብቻ ግን ሞት ሁሉ እኩል ሞት እንደማይባል ያመሰጠረ ድንቅ ምሳሌ የሚሆን ሞት ነው፤ የአጼ ቴዎድሮስ ሞት፡፡ እሳቸው ተይዘው ቢሆን ኖሮ፣ የሚዶለትባቸው የእንግሊዝ ቀልድና የሞራል ድሽቀት፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለውን ውርደትና ንቅትም ስናስብ፣ ያኔ የንጉሱን ጥልቅ እይታና ጥበብ በሞታቸው ውስጥ እንማራለን፡፡
ሞት ግን ምንድን ነው ?
የነፍስ ከስጋ መለየት ነው? በህይወት ሳሉ ተቸግሮና ታፍኖ፣ ሰብአዊ መብትን አጥቶ መኖር ነው? የስጋ በመሬት ውስጥ መቀበርና የነፍስ ወደ ሰማይ ማረግ፣ ከዚያ በአካል በምድር ላይ አለመታየት ነው? የትኛው ነው ሞት ማለት? አዎ ሞት ማለት ሁሉም የተጠቀሱት መንገዶች ናቸው:: የስጋና ነፍስ መለያየትና ስጋ መሬት ሲቀበር፣ ነፍስ ወደ ፈጣሪዋ ለፍርድ የምትሄድበት ስርአት ሞት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሞተውን ሰው ዳግመኛ በአካለ ስጋ አናየውም፤ አንዳስሰውም፤ አንጨብጠውም፤ አናናግረውም፤ ከዚያ በኋላ በአይነ ህሊና ብቻ ነው የሞተን ሰው የምናይ የምናናግረው፤ ስለዚህ ይሄን ነው ሁሉም ሰው በዋናነት ሞት ብሎ የሚጠራው:: በአካለ ስጋ እየኖሩ፣ እየተወዛወዙ፣ እየተንቀሳቀሱ፣ እየበሉ እየጠጡ፣ አብረው ከህዝቡ ጋር እየታዩ የሚሞቱትን ሞት ግን እንደ ሞት አናየውም:: ምናልባት ሁላችንም ሙቶች ስለሆንን ይሆን? እላለሁ፤ አንዳንዴ፡፡
ድምፃዊ ቴዎድሮስ ታደሰ፤ በአንዱ ዘፈኑ ላይ ከሞተው ባላንስም ከአለው ግን ትንሽ ነኝ ይላል:: ዘፈኑ የተዘፈነው ለሌላ ጉዳይ ቢሆንም፣ እንደው ሞቱ ከምንላቸው በአካለ ስጋ ብቻ ከተለዩን ሰዎች የምንበልጥበት ጉዳይ ምን የተሻለ ነገር ኖሮን ነው ከሞተው አናንስም የምንለው? በመንፈሳውያን አባቶች የምትጠቀስ አንድ አባባል አለች......ሰው በአካለ ስጋ ሲለየን፣ ከዚህ አለም ተለይቶን ሲሄድ አረፈ እንጂ ሞተ አይባልም ይላሉ፡፡ ሞት ማለት በተለይም በክርስትና እምነት መሰረት፤ ነፍሳችን ፍርድ ተቀብላ ወደ ገሃነም የወረደች እለት ነው:: በተለይ ትልቅ ስራን በምድር ላይ ሰርተው የሚያልፉቱ፤ አረፉ እንጂ ሞቱ አይባሉም፡፡  
አምፖልን ፈጥሮልን ካለፈ ሰውና በየቀኑ መብራት ከሚያጠፋብን ማንኛው ነው የሞተው? ለኑሮ ቅለት  መኪና ፈብርኮልን ካለፈውና በየቀኑ በመኪናው ከሚደፈጥጠን ሰው ማንኛው ነው የሞተው? ለነፃነትህ ተዋግቶ ነፃነትህን አስከብሮልህ ካለፈው ሰውና በየቀኑ የምትናገረውንና የምታስበውን ቆጥሮ ለመስጠት ከሚያስበው ማንኛው ነው የሞተው? አየህ ሞት ማለት በአካለ ስጋ ወደ መቃብር መውረድ ማለት አይደለም፡፡ ሞት ማለት የሚያስብ አዕምሮ ይዞ አለማሰብ ነው፤ ሞት ማለት ሰው ሆኖ ተፈጥሮ፣ የሰውን ትክክለኛ ግብር አለመፈጸም  ነው፤ ሞት ማለት የሰው ልጆችንም ይሁን የእንስሳን አለም በጨለማና በድንቁርና አጨቅይቶ መኖር ነው፤ ሞት ማለት እኔ ብቻ ልኑር - ስግብግብነት ነው፤ ሞት ማለት ያለ ስልጣናችን ሌላውን መግደልና እንዳይኖር የመከልከል አላማና ድርጊት ነው፤ ሞት ማለት ፈጣሪ ያስረከበንን ውብና ምቹ አለም፣ አጎረባብጦና አቆርፍዶ፣ ለህይወት እንዳትመች ለማድረግ መትጋት ነው..... ሌላም ሌላም፡፡   
በአጠቃላይ አንዳች ቁም ነገርን ሰርተን ማለፍ እስከተቻለን ድረስ ስለ ሞታችን አናስብ፤ የወጠንነው ዓላማና ግብ ከኛ የግል ህይወት የተሻገረ ማህበረሰባዊና ሀገራዊ ፋይዳ ካለው፣ እስከ ሞት አፋፍ ብንዘልቅም ልንፈራ አይገባም.....ምክንያቱም በዚህ መልኩ ብናልፍ ትርፉ፣ በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ዘላለማዊነትን መቀዳጀት ነው፡፡ ቸር እንሰንብት!

Read 2888 times