Monday, 03 June 2019 15:54

አማራጭ ፍጻሜዎች

Written by  ደራሲ፡- ማርጋሬት አትውድ ተርጓሚ፡- ሀዊ
Rate this item
(1 Vote)

               ዮሐንስና ሜሪ ተዋወቁ፡፡  
ከዛስ ምን ተከሰተ?
ፍጻሜው የሚያምር ታሪክ ከፈለጉ ‹ሀ›ን ይሞክሩ::
ሀ)
ዮሐንስና ሜሪ በፍቅር ወደቁ፡፡ ከዛም ተጋቡ:: ሁለቱም ቋሚና ለክህሎታቸው ተመጣጣኝ ደሞዝ የሚከፍል ስራ አላቸው፡፡ ስራቸው ዘወትር የሚያነቃቃቸውና አዲስ ትጋት የሚፈጥርላቸው ነው፡፡ የሪል እስቴት ተመኑ ጣራ ከመንካቱ በፊት የሚገርም ቤት ይገዛሉ፡፡ በሂደት አቅማቸው ሲፈቅድ፣ ሁለት ልጆች ይወልዳሉ፡፡ እየተጋገዙ፣ ለልጆቻቸው ሙሉ ፍቅር እየሰጡ ያሳድጋሉ:: ልጆቹ ስኬታማ ይሆናሉ፡፡ ዮሐንስና ማሪ ንቁና ዘወትር በአዳዲስ ተሞክሮ የተሞላ የወሲብ ህይወት አላቸው፡፡ ዘላቂ ጓደኞችም አፍርተዋል፡፡ በደስታ ተጀምሮ የሚጠናቀቅ ሽርሽርም ያደርጋሉ፡፡ ከስራ የሚያርፉበት የጡረታ ዘመናቸው ይመጣል:: ሁለቱም ከስራቸው ባሻገር ዝንባሌ አላቸው፡፡ ዝንባሌያቸው ለሁለቱም የንቃትና የአዲስ ተሞክሮ ምንጫቸው ነው፡፡ በሂደት ዮሐንስና ሜሪ  ይሞታሉ:: ይህም የታሪኩ ማለቂያ ነው፡፡
ለ)
ሜሪ ከዮሐንስ ጋር በፍቅር ትወድቃለች፤ ግን ዮሐንስ ከሜሪ ጋር ፍቅር አይዘውም፡፡ ገላዋን የሚጠቀመው ለራስ ወዳድ ስሜቱ ማርኪያነት ነው:: የስሜት መርከቡ ነው፡፡ ያልሞቀ ወይም ያልቀዘቀዘ ስሜት፡፡ ወደ እሷ የመኖሪያ አፓርትመንት በሳምንት ሁለት ጊዜ ይከሰታል፤ እሷ እራት ትቀቅልለታለች:: በሂደት ለእሱ ያላት ዋጋ ወደ ከተማ ወስዶ እራት ለመጋበዝ የሚያበቃት ያህል እንዳልሆነ፡፡ የሰራችለትን እራት ከበላ በኋላ፣ ይተኛታል፡፡ ተኝቷት እንደጨረሰ ወዲያው እንቅልፍ ይወስደዋል፡፡ እሱ እንቅልፍ ላይ እያለ እሷ ተነስታ እራት የተበላበትን ሳህን ታጣጥባለች - ያንን ሁሉ ያልታጠበ እቃ አይቶ “ንጽህና የላትም” ብሎ እንዳያስብ፡፡ የከንፈር ቀለሟን ታድሳለች፣ ሲነቃ ውብ ሆና እንድትታየው:: ግን ከእንቅልፉ ሲነቃ ልብ ብሎ እንኳን አያያትም:: ካልሲውን፣ የውስጥ ሱሪና ሱሪውን፣ ሸሚዙን፣ ክራቫቱንና ጫማውን ያጠልቃል፡፡ ልክ እንዳወላለቁ በቅደም ተከተል፤ግን በቅደም ተከተሉ ግልባጭ:: እሷ ልክ በፍቅሩ ልትሞት እንደደረሰች በመሆን ትተውናለች፡፡
የአልጋ አጨዋወቱን ስለወደደችለት አይደለም:: እንዲያውም እዛ ላይ አልተመቻትም፡፡ ግን ዮሐንስ እንዳልተመቻት እንዲያውቅ አትፈልግም:: ምክንያቱም ደጋግመው ካደረጉት እየለመዳት እንደሚመጣ እርግጠኛ ናት፡፡ በእሷ ላይ መተማመን ይጀምራል እና … ይጋባሉ፡፡ ግን ዮሐንስ በበሩ ወጥቶ ይሄዳል፤ ‹ደህና እደሪ› ብሏታል ብሎ ማረጋገጥ የማይቻል ሰላም ታሰጥቶ፡፡ ከሶስት ቀናት በኋላ ወደ ምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት ገደማ በድጋሚ ይከሰታል፡፡ ያንኑ ነገር በድጋሚ ያከናውናሉ፡፡ ሜሪ የስነ ልቦና መፍረስ ያጋጥማታል፡፡ ማልቀስ መጥፎ ስለመሆኑ ማንም ያውቃል፤ ሜሪም ታውቃለች:: ግን ለቅሶ ማቆም ያቅታታል፡፡ መስሪያ ቤት ያሉ ባልደረቦቿ ልብ ይላሉ፡፡ ጓደኞቿ ዮሐንስ አይጥ፣ አሳማ፣ ውሻ መሆኑን ይነግሯታል፡፡ ለእሷ የሚመጥን እንዳልሆነ፡፡ እሷ ግን ማመን ያቅታታል፡፡ በዮሐንስ ውስጥ ሌላ ዮሐንስ እንዳለ ታምናለች፤ የውስጠኛው ዮሐንስ ደግሞ መልካም ስለመሆኑ፡፡ ይሄ መልካሙ ዮሐንስ፤ እንደ ቢራቢሮ ሽፋኑን ፈልቅቆ ብቅ እንደሚል ትጠብቃለች፡፡ ይኼኛው ዮሐንስ ትንሽ ቢጨመቅ፤ ያንኛው ዮሐንስ ብቅ ይላል፡፡ ከእለታት አንድ ምሽት፣ ዮሐንስ፤ በሰራቸው እራት ምክኒያት ማማረር ይጀምራል፡፡ ከዚህ ቀደም ምግቧን አማሮ አያውቅም፡፡ ሜሪ  ይከፋታል፡፡
ጓደኞቿ፣ ዮሐንስን ከሌላ ሴት ጋር በሆነ ሬስቶራንት ውስጥ እንዳዩት ለሜሪ  ይነግሯታል፡፡ የሌላኛይቱ ሴት ስም ማጅ ነው፡፡ ማጅ አይደለችም፣ ሜሪን ያስቀየመቻት፡፡ ሬስቶራንቱ ነው፡፡ ዮሐንስ ሜሪን ደህና ሬስቶራንት ወስዷት አያውቅም፡፡
ሜሪ ያገኘችውን የእንቅልፍ መድኃኒትና አስፕሪን ሰብስባ በጣፋጭ ወይን ትውጠዋለች:: እዚህ ላይ ምን አይነት ሴት እንደሆነች በግልጽ ሊታያችሁ ይችላል:: በጣፋጭ ወይን ፋንታ ዊስኪ እንኳን ማድረግ አትችልም፡፡ ለዮሐንስ በወረቀት ላይ መልዕክት ጽፋ ታስቀምጣለች፡፡ ወድቃ ሲያገኛት አፋፍሶ ሆስፒታል እንዲወስዳት ነው ተስፋ ያደረገችው፡፡ ከወሰዳት በኋላም ተጸጽቶ ንስሓ እንዲገባና የጋብቻ ጥያቄ እንዲያቀርብላት፡፡ ግን ይሄ ሳይከሰት እሷ ትሞታለች::
ዮሐንስ ማጅን ያገባና ሁሉም ነገር ‹ሀ› ላይ በተዘረዘረው መሰረት ይቀጥላል፡፡  
ሐ)
ዮሐንስ እድሜው ገፋ ያለ ሰው ይሆናል፤ ከሜሪ ጋር ፍቅር ይይዘዋል፡፡ ሜሪ ደግሞ እድሜዋ ለጋ፣ ሃያ ሁለት ዓመት የሆነች ኮረዳ በመሆኗ ለዮሐንስ ታዝንለታለች፡፡ የምታዝንለት ስለፀጉሩ በመጨነቁ ምክኒያት ነው፡፡ ፀጉሩ በመርገፍ ላይ ይገኛል፡፡ ከእሱ ፍቅር ባይዛትም አብራው ትተኛለች፡፡ የተዋወቀችው ስራ ቦታ ነበረ፡፡ እሷ የእውነት ፍቅር የያዛት ደምሴ (ጀምስ) ከሚባል ሰው ጋር ነው፡፡ ደምሴ እድሜው ሃያ ሁለት ነው፤ በትዳር ለመታሰርና ለመረጋጋት ገና ዝግጁ አይደለም፡፡
ዮሐንስ በተቃራኒው አግብቶ ከተረጋጋ ቆይቷል:: መረጋጋቱ ነው የሚያስጨንቀው፡፡ የሚያስከብር ስራ አለው፡፡ በሚሰራበት ዘርፍ የተሻለ የልቀት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ህይወቱ ቀጥ ያለ ነው፡፡ ግን ሜሪ በእሱ ስኬት ብዙም አትመሰጥም፡፡ እሷን የሚስባት ደምሴ ነው፡፡ ደምሴ ሞተር ብስክሌትና ድንቅ የሆነ የሙዚቃ ስብስብ አለው፡፡ ነፃነት ለወንዶችና ለሴቶች ትርጉሙ ለየቅል ነው፡፡ ስለዚህ ሜሪ  ዘወትር ሐሙስ ማታ ከዮሐንስ ጋር ታሳልፋለች፡፡ ዮሐንስ ከስራ ነጻ የሆነ የእረፍት ጊዜ የሚያገኘው ሐሙስ ቀን ብቻ ነው፡፡
ዮሐንስ፣ ካገባት የቆየች ማጅ የምትባል ሚስት አለችው፤ ሁለት ልጆች ወልደዋል፡፡ የሪል እስቴት ዋጋ ከፍ ከማለቱ ትንሽ ቀደም ብለው የገዙት የተመቸ ቤት አላቸው፡፡ ከስራቸው ባሻገር ባልና ሚስቱ የግል ዝንባሌ አላቸው፡፡ ዝንባሌያቸው፣ ለሁለቱም የንቃትና አዲስ ተሞክሮ ምንጫቸው ነው፡፡ ጊዜ ሲያገኝ፣ ዮሐንስ ለሜሪ “እንዴት በሕይወቱ ውስጥ ዋና ጉዳይ እንደሆነች” ይነግራታል፡፡ ግን በእርግጥ ሚስቱን ለእሷ ብሎ መፍታት አይችልም፤ ምክኒያቱም ኃላፊነት ኃላፊነት ነውና፡፡ ስለ ኃላፊነቱ ዘለግ አድርጎ ሲያወራ፣ ሜሪ እንደሚጠበቀው ይሰለቻታል፡፡ ቢሆንም እድሜያቸው የገፋ ሰዎች በአልጋ ጨዋታ ላይ ዘለግ ያለ ቆይታ ማድረግ ስለሚችሉ … ብቻ በጥቅሉ ጥሩ ጊዜ ከዮሐንስ ጋር ሐሙስ ላይ ታሳልፋለች፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ደምሴ፤ ሜሪ ዘንድ በዶቅዶቄ ከች ይልና፣ በጣም ውድ ዋጋ ባለው የካሊፎርኒያ እጽ አብረው ይጦዛሉ፡፡ ሜሪ መድረስ ይቻላል ብላ በማታስበው ከፍታ የተመነጠቀች ይመስላትና ሁለቱም በስተመጨረሻ በአንድ አልጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡ ነገሩ ሁሉ በውኃ ስር የተከናወነ በሚመስል ወሲባዊ ሲቃ ውስጥ ሳሉ፣ ዮሐንስ ድንገት ወደ ሜሪ  መኖሪያ አፓርትመንት ይደርሳል፡፡ የአፓርትመንት ቁልፍ ስላለው ከፍቶ ይገባል፡፡ በእጽ ጦዘው፣ በእርቃን ገላ ተጣምረው ያገኛቸዋል፡፡ ሚስት ያለው ሰው መቅናት የተገባ መሆን አልነበረበትም:: ቢሆንም ግን ሊቆጣጠረው በማይችለው የልብ ስብራት ይወረሳል፡፡ በሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ ወደ ሙሉ አዛውንትነት እድሜ የሚገባ መሆኑና ጸጉሩ ተመልጦ፣ የራስ ቅሉ እንቁላል መምሰሉ ያንገሸግሸዋል፡፡ የተኩስ ልምምድ ለማድረግ በሚል ሰበብ ሽጉጥ ይገዛል፡፡ (ይኼ ስስ ሊባል የሚችለው የሴራው ክፍል ነው … ግን እሱን በኋላ ማስተካከል ይቻላል፡፡)
በገዛው ሽጉጥ የሁለቱን ፍቅረኛሞችና የራሱን ህይወት ይቀጥፋል፡፡ ማጅ ለባሏ ሃዘን መርሻ ተገቢ የሚባል ጊዜ ከሰጠች በኋላ .. እሷን በሚገባ የሚረዳትን ፈረደ (Fred) የተባለ ሰው ታገባለች፡፡
ሁሉም ነገር ከዛ በኋላ ልክ በ ‹ሀ› ስር እንደተዘረዘረው፣ ስሞቹ ብቻ ተለውጠው ይቀጥላል::
መ)
ፈረደና ማጅ ምንም ችግር የሌለባቸው ጥንዶች ናቸው፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ተግባብተው መኖር ይችላሉ፡፡ ችግርም ከመጣ ተግባብተው ጥቃቅኑን እክል ሁሉ የመፍታት ብቃት አላቸው:: ግን የገዙት ቤት በባህሩ ዳርቻ የሚገኝ በመሆኑ አንድ ቀን የባህሩ ማዕበል ተነስቶ ይመታዋል፡፡ የባህሩ ማዕበል የሪል እስቴት ዋጋ መውደቅ ነው፡፡ … ከዚህ ቀጥሎ የሚከተለው የሁለቱ ጥንዶች ታሪክ፣ የተነሳባቸው ማዕበል እንዴት እንደመጣና እንዴት ሊያመልጡት እንደቻሉ ነው፡፡ ያመልጡታል፡፡ ብዙ ሺ ብሮችን ተበድረው፡፡ ግን ፈረደና ማጅ፤ ሰናይና እድለኛ የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ በስተመጨረሻ፣ ከመዐበል አምልጠው ደረቅ መሬት ያለበትን ከአደጋ ነጻ የሆነ ስፍራ ሲረግጡ እርስ በርስ ይተቃቀፋሉ፡፡ ውሃው ከላያቸው እየተንጠባጠበ፣ እድለኝነታቸውን ተቃቅፈው ያመሰግናሉ፡፡
ከዛ በኋላ ታሪኩ ልክ ‹ሀ› ላይ እንደተገለጸው ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ሠ)
አዎ፤ ግን ፈረደ የልብ ህመም አለበት፡፡ የተቀረው ታሪክ እርስ በራሳቸው እንዴት ግሩም በሆነ ሁኔታ እንደሚተሳሰቡና ደጎች እንደሆኑ ነው፤ ፈረደ በልብ ሕመሙ ሰበብ እስኪሞት ድረስ፡፡ ከፈረደ ሞት በኋላ ማጅ ራሷን በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ትጠምዳለች:: … ልክ በ ‹ሀ› ላይ እስከተገለጸው የታሪክ ማለቂያ ድረስ:: የማለቂያውን ትክክለኛ መንስኤ ደስ ያላችሁን ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ ማጅ፣ በካንሰር ወይንም በጸጸትና ግራ መጋባት ወይም አእዋፍ በመመልከት ብዛት ሞተች ልትሉ ትችላላችሁ፡፡
ረ)
እስካሁን የተተረከው የታሪክ አማራጭ፣ የኃብታም ከበርቴ ታሪክ ከመሰላችሁ ዮሐንስን አብዮተኛ ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ ሜሪ  ደግሞ የስለላ ካውንተር ኢንተለጀንስ፣ የደህንነት ጓድ አድርጋችሁ በመሞከር ታሪኩ የት እንደሚያደርሳችሁ ተመልከቱ:: አስታውሱ፤ ይሄ ካናዳ ሀገር ነው፡፡ የፈለገውን ዓይነት መንገድ ብትሞክሩ በስተመጨረሻ ማረፊያችሁ ‹ሀ› ነው፡፡ ምንም እንኳን በመኃል በታሪኩ ተጠልፋችሁ ለአንዱ ገጸ ባህሪ አድልታችሁ ብታለቃቅሱ ወይም ብትመሰጡበትም መጨረሻው አንድ ነው፡፡ የዘመናችን ገድል ሲጠቃለል ልትሉት ትችላላችሁ፡፡
ስለዚህ እውነቱን ፊት ለፊት ተጋፈጡት፡። በአስፈለገ አኳኋን ብትሰነጥሩት ፍጻሜው ተመሳሳይ ነው፡፡ ተለዋጭ ፍፃሜ አለ ብላችሁ አትጭበርበሩ:: ሁሉም ሌላ አይነት ፍፃሜዎች ውሸት ናቸው:: ውሸት እንዲሆኑ ሆነ ተብለው ወይም በአንዳች የመሰሪና የማጭበርበር ፍላጎት ግብ የተጠነሰሱ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም አጉል በሆነ መልካም አሳቢ ብርሐንተኝነት ስሜት ተነሳስተው ስለሚተረኩ ሊሆን ይችላል፡፡ የዋህ ብርሐንተኝነት ካልሆነ፣ የዋህ ሩህሩህነት ነው፡፡
ብቸኛውና ትክክለኛው ፍጻሜ ይኼ ከስር የተቀመጠው ብቻ ነው፡፡
“ዮሐንስና ሜሪ ይሞታሉ፡፡ ዮሐንስና ሜሪ ይሞታሉ፡፡ ዮሐንስና ሜሪ ይሞታሉ፡፡”   
ስለ ፍጻሜ ይሄንን ያህል ካልን ይበቃል፡፡ ከፍፃሜ ይልቅ ጅማሮ የበለጠ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ያጫውታል፡፡ ለህይወት እውነተኛ ጣዕም አቃቂር አውጪዎች ግን በፍጻሜና በጅማሮ መኃል ያለውን ርዝማኔ ነው የሚመርጡት፡፡ በዛ መሃል ቤት አንዳች ነገር አከናውኖ ማለፍ ከባድ ስለሆነ፡፡  

Read 1134 times