Monday, 03 June 2019 15:55

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)


                        “መቶ ውሸት ቢጨመቅ አንዲት ጠብታ እውነት አይወጣውም”
                          
                  ምክንያታዊ (ሚዛናዊ) አስተሳሰብ በሚታይና በተጨበጠ ነገር ላይ ከተመረኮዘው (empirical) የአስተሳሰብ ስልት የሚለየው ሰዎች ወደውና ፈቅደው የተስማሙበትን ጉዳይ “ህግ አድርጎ” መቀበሉ ነው:: ለምሳሌ ሁለት ሲደመር ሁለት አራት መሆኑን፡፡ የማቲማቲካል ፕሮግሬሽንን ህግ መሰረት አድርገን፣ በቀደምለት የታሰበውን “ግንቦት 20” ትርፍና ኪሳራ ብናሰላ፡-
28+1 =   29 - 1 = 28 ---  29 28 = 1= 1 ይሆናል፡፡
አልከሰርንም፡፡ አንድ ዓመት ከአንድ ወር ያህል አትርፈናል፡፡ ህግ ሽረን በተገላቢጦሽ ብናሰላው ደግሞ የአንድ አመት ከአንድ ወር ጊዜ ኪሳራ ይሆናል፡፡ ህግ መሻር ግን ያስቀጣል፡፡ ተገቢው ቅጣት እስኪበየን ደግሞ አጥፊው በ‹ተጠርጣሪነት› ይሰነብታል፡፡ “Innocent until proved guilty” እንደሚሉት፡፡
ወዳጄ፡- ‹መጠርጠር› የሚለው ቃል ሲጠብቅና ሲላላ፣ ሁለት ተቃራኒ መንፈስ አለው፡፡ በነዚህ ሁለት መንፈሶች መሃል ህይወት ትንከላወሳለች፡፡---
“የመጀመርያው ተግባሬ ማንኛውንም ነገር “ዕውነት” ነው ብዬ አለመቀበል ነው፡፡ ይህን ማድረጌ ከሃሜት፣ መኖሩ ካልተረጋገጠና መሰረተ ቢስ ከሆነ አስተሳሰብ (prejudice) ያርቀኛል:: ተጠራጣሪ መሆኔን ስጠራጠር እያሰብኩ እንደሆነ አልጠራጠርም፡፡ ማሰቤ መኖሬ ነው:: መኖሬን ካልተጠራጠርኩ ሌላውም ዓለም እንዳለ አልጠራጠርም፡፡ እዚህ ጋ፣ የማወቅ ‹ሀሁ› ይጀምራል::” የሚለን ታላቁ ዴስካርተስ ነው፡፡
ሰውዬአችን የመብት ተሟጋች ነው፡፡ ምስልና ድምፅ የሚቀርፅ የረቀቀ ኤሌክትሮኒክ መሳሪያ አለው ተብሎ ተጠርጥሯል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ኤሌክትሮኒክ ሴንሰር ባላቸው የፍተሻ መሳሪያዎች በሚጠበቁ ሆቴሎች ሲስተናገድ መሳሪያዎቹ ምልክት ስለሚያሳዩ ነው፡፡ ይህን ነገር ለማጣራት የፀጥታ ሰራተኞች ያልገለበጡት ድንጋይ የለም፡፡ ለምሳሌ ከአብሮ አደጎቹ ጋር ‹በርጫ› ሲያደርግ፣ ሽርጥና ካኒቴራ ስለሚለብስ፣ ወደ መፀዳጃ ቤት በሚሄድበት ሰዓት ኪሶቹ ተፈትሸዋል፡። ምንም ነገር አልተገኘም:: የፀጥታ ሰራተኞቹ እንዳይተውት ስጋት፣ ፊት ለፊት እንዳይጋፈጡት ደግሞ የማያዋጣ ሆነባቸው፡፡ እሱም እነሱን፣ እነሱም እሱን እየተተጠረጠሩ ብዙ ጊዜ አለፈ፡፡ እውነቱ የተገለጠው ከብዙ ጊዜ በኋላ ነበር፡፡ … እውነቱ ምንድነው?
***
ወዳጁ፡- መቶ ውሸት ቢጨመቅ አንዲት ጠብታ እውነት አይወጣውም፡፡ ችግሩ እውነትን በቀላሉ ፈልጎ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑ ነው፡፡ ረዥም ጊዜና መራር ትግልም ይፈልጋል፡፡ እውነትን የሚፈልግ ሰው ራሱ እውነተኛ ሆኖ ካልተገኘ፣ የእውነትን ጣዕም አያውቅም፡፡
እኛ አገር በተለያዩ የፀጥታና የፖለቲካ ድርጅት ስራ ላይ የተሰማሩ “ብዙ” ሰዎች፣ ከድንቁርናቸው በተጨማሪ በጠባብ አመለካከት የተተበተቡ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሌብነትና ከዘረፋ ተግባር ጋር የተነካኩ መሆናቸው ግልፅና ግልፅ ጉዳይ ነው:: ፊት ለፊት በሚደረገው እንቅስቃሴ ስለማይሳተፉ ማንነታቸው ድብቅ ይሁን እንጂ ከጀርባ ሆነው የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ሚስጢራችንን ወይም ማንነታችንን ያውቃል የሚሉትን ሰው ለማጥቃት ይተጋሉ፡፡ ይህን በማድረግም ራሳቸውን የጠበቁና የተከላከሉ ይመስላቸዋል፡፡ ያልተጠየቁትን መመለስ፤ ‹እዚህ ነኝ ያለሁት› ብሎ ከማለት እንደማይለይ አልገባቸውም፡፡
ሴትየዋ፡- “አንቺ ልጅ፤ እዚህ ጋ ፍራንክ አስቀምጬ ነበር፣ አላየሽም?” ቢሏት …
“የምን ሃምሳ ብር? ኧረ እኔ አላየሁም፡፡” አለች አሉ፡፡
ልጅት… ራሷን በራሷ አጋለጠች፡፡ ውሸታም መሆን… ራስን በራስ ማሰር ነው፡፡
ወዳጄ፡- የግንቦት ሃያ ሰሞን ነውና፣ ካለፈ ስህተት መማር ብልህነት ይመስለኛል፡፡ … የዛሬ ሳምንት ዓመት ገደማ ሁለት ጓደኞቻችን ከስራ መልስ ሰውነታቸውን ሊለቃለቁ ፍል ውሃ ጎራ ይላሉ፡፡ ከሁለቱ አንደኛው፣ በውጭ አገርና በሃገር ውስጥ በህቡዕ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲ ‹መሪ› ነው እየተባለ ይወራበታል:: ሰውነቱን ታጥቦ እንደወጣ አንድ የሚያውቀውን ሰው (ምናልባትም ሲከታተለው የነበረ) ያገኘውና፣ ሰላምታ ይለዋወጣሉ፡፡ ሰውየው “ቁልፍ የመንግስት ሰላይ” የሚባል ነበር፡፡ ይኸ ከሆነ ከጥቂት ቀናት በኋላ የያኔው ጠ/ሚኒስትር በብሔራዊ ቴሌቪዥን ብቅ ብለው፡- “ልምድ ያላቸው የዚህ ፓርቲ (ስሙን ጠርተው) ሰዎች፤ ህዝብ በሚበዛባቸው እንደ ፍልውሃ ዓይነት ቦታዎች ላይ የሽብር ተግባር ለመፈፀም እያጠኑ ናቸው” በማለት መግለጫ ሰጡ፡፡ እጅግ የሚያሳፍር ነገር ነው፡፡ የሃሰት መረጃ በማቅረብ ያሳሳታቸው ‹ያ› ሰውዬ ነበር፡፡ ‹ወሬ አመላላሾች!› እንዳሏቸው ሁሉ፣ ወሬአቸውን ሰምተው ተሳሳቱ፡፡ እዚህ ጋ ነው በገዛ ቅዠት መጠፍነግ! … በሌለ ነገር ፓራኖይድ መሆን!!
ወዳጄ፡- ዶ/ር ዐቢይ ‹አሸባሪዎቹ እኛ ነን!” በማለት እውነቱን የተጋፈጡት ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ ዜጎች ጨርሶ በማያውቁት ምክንያት መንግስት ጉያ የተሸጎጡ “አላዋቂዎች” በሚያቀርቡት የሃሰት መረጃ፤ እንዴት ሲጠቁ እንደነበረ ጠንቅቀው በማወቃቸው ነው፡፡ ኢህአዴግንም የካንሰር በሽተኛ ያደረጉት እነዚሁ በውስጡ የፈሉት የነቀርሳ ሴሎች ናቸው፡፡ እኔ እንደሚገባኝ፣ “ህገ መንግስትን መጠበቅ” ማለት፤ መሳቢያ ውስጥ ለተቆለፈ ወይም መደርደርያ ላይ ለተከማቸ ወረቀት ዘብ መቆም አይደለም፡፡ የእያንዳንዱን ዜጋ መብት ማስከበር መቻል እንጂ!!
ጥያቄው፡- “ለመሪዎች መረጃ የሚያቀርቡ የደህንነት ተቋማት እንዳሉ ሁሉ የሚቀርበውን መረጃ ትክክለኛነትና የመረጃ አቅራቢዎቹን ማንነት የሚያጣራ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የማቴሪያል ብቃት ያለው ተቋም ወይም Counter Intelligence አገራችን አላት ወይ?” የሚል ነው፡፡ ከግንቦት 20 ጋር ስንተላለፍ፣ እነዚህንና መሰል ጉዳዮችን እንድናስብ ተገደናል፡፡ አይመስልህም ወዳጄ? … ወይስ ትጠራጠራለህ? ለማንኛውም መልካም በዐል!
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- በፍተሻ የማይገኘውና ሴንሰር ላይ ግን ምልክት የሚታይበት ምክንያት፤ ሰውየው በልጅነቱ በተደረገለት የአጥንት ቀዶ ጥገና ላይ  ለጥገና እንዲያግዘው ተብሎ ሰውነቱ ውስጥ  የተቀበረ ብረት ስለነበረ ነው፡፡
ሠላም!!

Read 529 times