Saturday, 08 June 2019 00:00

ምክር ቤቱ በፀረ ሽብር አዋጁ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ተወያየ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

  · ረቂቅ አዋጁ። የሲቪል መብትን በመጠቀም መንግስትን ለማስገደድ መሞከር መብት ነው ይላል
                · በድብቅ የሚደረግ ብርበራ፣ ከአዋጁ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ ተደርጓል
                                 
               የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት፤ የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚጋፉና የሚጥሱ አንቀፆች ተካተውበታል የተባለውን የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ የሚያሻሽለውን አዲሱን የሽብር ወንጀል የመከላከልና የመቆጣጠር ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ጉዳዩን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል::
ምክር ቤቱ ከትናንት በስቲያ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ፤ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ የመከረ ሲሆን፣ የቀድሞው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ የዜጎችን መብትና ነፃነት ያለአግባብ እንደሚጥስ መንግስት የፖለቲካ አላማውን ለማሳካትና የሚቃወሙትን ለማጥቃት ሲጠቀምበት እንደቆየም ተገልጿል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ረቂቁን የማዘጋጀት ኃላፊነቱን በመውሰድ የጥናት ዳሰሳ ማካሄዱንና በጥናቱም አዋጁ፤ የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚጋፋና አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያደርስ መሆኑን እንዳረጋገጠ ለምክር ቤቱ የቀረበው ማብራሪያ ያመለክታል፡፡
የሽብር ድርጊት፤ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ፣ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት አደጋ የሚሆን ተግባር መሆኑን የሚገልፀው የረቂቅ አዋጁ  ማብራሪያ፣ የህዝብንና የመንግስትን ሰላምና ደህንነት ከሽብር ለመከላከል እንዲሁም፣ የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት በአግባቡ እንዲጠበቅ ለማድረግ አዋጁን ማሻሻልና በሌላ አዲስ አዋጅ መተካት አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት አመልክቷል፡፡
በረቂቅ አዋጁ፤ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን ለማሸበር፣ ለማስፈራራት ወይም ለማስገደድ በሰው አካል ላይ ጉዳት ያደረሰ፣ የሰውን ህይወት ለአደጋ ያጋለጠ፣ በአገር ንብረት ላይ ጉዳት የፈፀመ ከ10 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡ የደረሰው ጉዳት ህይወትን ያስጠፋ፣ በታሪካዊ ወይም የባህል ቅርስ ላይ ከፍተኛ ውድመት ያደረሰ ከሆነ ደግሞ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ቅጣት አሊያም በሞት እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል - ረቂቅ አዋጁ፡፡
ማሻሻያ ረቂቁ፤ የሲቪል መብቶችን በመጠቀም መንግስትን ለማስገደድ መሞከር የዜጎች መብት እንደሆነ የሚገልፀው ረቂቁ፤ የስራ ማቆም አድማ፣ ሰላማዊ ሰልፍና፣ ስብሰባ ማድረግና መሰል ተግባራት የሽብር ድርጊት ሆነው አይቆጠሩም ይላል፡፡
የሽብር ድርጊትን ለመፈፀም መዛት፣ ማስፈራራት፣ ማቀድና መዘጋጀት ከድርጊቱ ፈፃሚዎች እኩል የሚያስቀጡ ተግባራት እንደነበሩ ያስታወሰው ረቂቅ አዋጁ፤ ይሁንና ድርጊትና ቅጣት መመጣጠን ስለሚኖርባቸው እንደ ድርጊቱ ክብደት፣ ውስብስብነትና ቅለት መጠን ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት እንዲቀመጥላቸው መደረጉ ተገልጿል፡፡
አሁን በተሻሻለው የሽብር ወንጀል መከላከልና መቆጣጠር ረቂቅ አዋጅ ውስጥ እንዳይካተቱ ከተደረጉት ጉዳዮች መካከል በድብቅ የሚደረጉ ብርበራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በድብቅ የሚደረግ ብርበራ፤ የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብትና ነፃነት የሚፃረር ድርጊት በመሆኑና በመደበኛው የብርበራ ስርዓት ድርጊቱን ማከናወን ስለሚገባ የድብቅ የብርበራ ሂደት ሙሉ በሙሉ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተጠርጣሪዎች ስለሚያዙበት መንገድ፣ የጊዜ ቀጠሮና ማስረጃዎችን የተመለከቱ ጉዳዮች በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ እንዳይካተቱ ተደርጓል፡፡
የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ በህግ አካላት ላይ የሚፈፀሙ ህገ ወጥ ተግባራትና የመብት ጥሰቶችን በተመለከተም በረቂቅ አዋጁ እንደተጠቀሰው፤ የህግ አስፈፃሚ አካላት በሽብር ወንጀል ተጠርጣሪው ላይ የህግ ጥሰት ከፈፀሙና ይህም በማስረጃ ከተረጋገጠ፣ የህግ ጥሰቶችን የፈፀመው ሰው ወይም ተቋም ለተጎጂው ከአንድ ሺ ብር እስከ ሀምሳ ሺ ብር የሚደርስ የህሊና ጉዳት ካሳ እንዲከፍሉ በዚያው በተያዘው የክርክር መዝገብ ላይ መወሰን ይችላል፡፡

Read 827 times