Saturday, 08 June 2019 00:00

የቁም ነገር አምላክ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)


            “--እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ በአንዳንድ ሚዲያዎች ላይ አስተያየት ሰጪዎች፤ “ነጻ ገበያ ስለሆነ ነጋዴው እንደፈለገው መጨመር ይችላል…” ሲሉ ስንሰማ ትንሽ ግር ይላል፡፡ አሀ፣ ምንም ነገር ላይ “እንደ ልብ መሆን” ብሎ ነገር የለማ!…የትም ሀገር ለሁሉም ነገር ህግጋትና ስርአቶች አሉ፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ ማህበራዊ ሀላፊነት የሚሉት አለ፡፡--”
                    
              እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በከተማችን አንድ ጥግ የሆነች ምግብ ቤት አለች፡፡ እዛ የሚመገቡት የመንግሥት ሠራተኞች በወር ሦስት ቀን መጥተው ሀያ ሰባት ቀን የበላቸው ጅብ እንኳን አይጮህም፡፡ በእነሱም ምክንያት ቤቷ “ምች ምግብ ቤት…” ይሏታል፡፡ እነሱም ወር ደርሶ ብቅ ሲሉ “ምቾች መጡ” ነው የሚባሉት፡፡ ደግነቱ ለ‘ምች’ የሚሆን ፌጦ ምናምን ሳይነሰንሱባቸው በሦስተኛው ቀን ይጠፋሉ እንጂ!
እኔ የምለው…ኩንታል ጤፍ በሳምንት ጊዜ ውስጥ አምስትና ስድስት መቶ ብር የሚጨምርበት ዘመን ምን የሚሉት እርግማን ነው! የምር እኮ…አለ አይደል…እንዴት ነው አንድ እንጀራ ሰባት ብር እየተገዛ የሚዘለቀው! እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ በአንዳንድ ሚዲያዎች ላይ አስተያየት ሰጪዎች፤ “ነጻ ገበያ ስለሆነ ነጋዴው እንደፈለገው መጨመር ይችላል…” ሲሉ ስንሰማ ትንሽ ግር ይላል፡፡ አሀ፣ ምንም ነገር ላይ “እንደ ልብ መሆን” ብሎ ነገር የለማ!…የትም ሀገር ለሁሉም ነገር ህግጋትና ስርአቶች አሉ፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ ማህበራዊ ሀላፊነት የሚሉት አለ፡፡
የቁም ነገር አምላክ መከራውን ያቅልልንማ!
እኔ የምለው… በነገራችን ላይ አለቆቻችን ግልጽ የሆነ የኤኮኖሚ ፖሊሲ የላቸውም የሚባለው እውነት ነው እንዴ! በቃ ‘የኤኮኖሚ ኮምፓስ’ ምናምን የለም ማለት ነው! እናማ… “በዚህ አይነት ጤፍና ሽንኩርት ጣራ ቢነኩ ምን ይገርማል!” እንዳንል ነገርዬውን አናውቀው ነገር! የምታውቁ አስረዱንማ፡፡ ልክ ነዋ… እንዲሁ ዝም ብሎ አሁንም በቲቪ ዜና ከመስማት በስተቀር በምግብ ጠረዼዛችን ላይ የማናየውን የፈረደበትን “የምናምን ዲጂት እድገት ተመዝግቧል” የሚባለውን እየሰማን የት ድረስ ልንሄድ ነው፡፡ የምር ግን፣ አለ አይደል…እንዲህ ዓይነት ትርክቶች የሦስት ወይ የአምስት ዓመት እረፍት ቢሰጣቸው ጥሩ ነው፡፡ (በዛ ሰሞን አንድ ባለስልጣን “የምንከተለው ካፒታሊስት ኤኮኖሚ ነው…” ምናምን ሲሉ ሰማን ልበል!) እናማ…ስለ ኤኮኖሚ ትንታኔ ማወቅ የለብንማ!…አዳም ስሚዝ፣ ‘ዘ ወርልድ ኢዝ ፍላት’ ምናምን የሚሉ ነገሮች ማወቅ የለብንም!…
የህዝባችን ኑሮ በየእለቱ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ፣ ተርቦ መጉረስ፣ ታክሞ መዳን አስቸጋሪ እየሆነ… በኤኮኖሚ ስለ መመንጠቅ ምናምን ማውራት ሆድ ከማሻከር ውጪ የሚፈይደው የለም፡፡ በየቤቱ ያለውን እውነት ለማየት አለመቻል፣ ወይም ለማየት አለመፈለግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሰሞኑን ባለሙያዎች ከኑሮ መወደድ ጋር በተያያዘ ሰልፍ መውጣታቸው የብልጽግና ምልክት አይደለም፡፡
ስሙኝማ…በኤኮኖሚ ችግሮቻችን ላይ እንኳን በቅጡ እንዳንነጋገር … ከጣት መቀሳሰር መውጣት አልቻልንም እኮ! ሁልጊዜም ጣት መቀሰሪያ አይጠፋም፡፡ “የእኔ ጥፋት ነው” ብሎ ነገር በራስ ላይ እድሜ ይፍታህ መፍረድ አይነት እየሆነ ነው:: ሁልጊዜ ያኛው ወገን ነው ጥፋተኛው፡፡ ሁልጊዜ የዲያብሎስ ጭራና ቀንዱ ያለው እዚያኛው ሰው ላይ ነው፡፡ በየትኛውም መስክ በሉት ጥፋትን፣ ጉድለትን መቀበል ብሎ ነገር እየጠፋ ነው፡፡ ፖለቲካው ላይ ሁልጊዜም ነገር የሚያበላሹት እነዚያኞቹ ናቸው፡፡ እኛ ምን ጊዜም ልክ ነን፡፡ መስሪያ ቤት ስሌት ሲሠራ ቁጥሩን ያሳሳተው ሂሳብ ሠራተኛው አይደለም:: ይልቁንም የኮምፒዩተር ሠራተኛዋ ገልብጪ የተባለቸውን አበላሽታ ነው፡፡ የሂሳብ ሠራተኛው የዞረ ድምሩ አልለቅ ብሎትም ይሁን፣ እንትናዬው ቢጫ ካርድ ስላሳየች  አአምሮው ተናግቶ ይሁን ባሳከረው ቁጥር፣ ሀጢአቱ ከእሱ ትከሻ ወርዶ ሥራዋን በትጋት ወደምትሠራው ምስኪኗ የኮምፒዩተር ሠራተኛ ላይ ይጫናል፡፡
የቁም ነገር አምላክ መከራውን ያቅልልንማ!
ስሙኝማ…እግረ መንገድ…‘ማኩረፊያ ወዳጅ አያሳጣህ’ የምትባል አሪፍ ነገር ነበረች፡፡ ልጄ፣ ዘንድሮ ወዳጅ አይደለም ማኩረፊያ ሊሆን… አለ አይደል…ራሱ ነው ቀድሞ የሚያኮርፈው፡፡ እናንተ ልትገምቱት በማትችሉት ምክንያት ሊያኮርፋችሁ ይችላል፡፡
እናላችሁ… የጤፉ መወደድ ምክንያት የነጋዴዎቹ ስግብግብነት ሳይሆን በመሀል ያሉ ደላሎች ናቸው...ህገ ወጥ ደላሎች፡፡ እና ሀላፊነቱ ከምናውቀው ነጋዴ ትከሻ ወደ ማናውቀው ደላላ ትከሻ ይተላለፋል፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የገንዘባችን ኦዲት ነገር ጉድ አይደለም እንዴ! ግርም የሚለው ምን መሰላችሁ… ሌሎች ሀገራት ቢሆን ይሄኔ  ስንቱ ነገር ተደበላልቆ ነበር፡፡ በአንድ በኩል እነ እከሌ ስንትና ስንት መቶ ሚሊዮን ብር አሸጋግረዋል፤ ይመለስልን ምናምን እያልን እየተካሰስን፣ መስሪያ ቤቱ ሁሉ ሙልጩ እየወጣ አይደለም እንዴ! ይሄ ያላስደነገጠን፣ ይሄ ያላሳሰበን ምን ሊያሳስበን ነው! እያንዳንዷ ብር ውድ በሆነችበት ጊዜ “ግብዣ በዛ፣ ‘ብሉ፣ ጠጡ’ በዛ” እየተባባልን እኮ ነው!
እኔ የምለው…አሁን፣ አሁን እኮ ልንደነግጥባቸው በሚገቡ ነገሮች በትንሹ እንኳን ግንባር መቋጠር እየተውን ነው፡፡ የችግር አይነት ተራ በተራ ከመፈራረቁ የተነሳ መልመድ የማይገባንን እየለመድነው ይመስላል፡፡ ብዙ ነገራችን በ“የባሰ አታምጣ!” አራት ነጥብ ሲደረግለት ልክ አይሆንም፡፡ “የባሰ አታምጣ” እያልን የተውናቸው ነገሮች ናቸው በብዙ እጥፍ እየባሱ እየተመለሱብን ያሉት፡፡
እኔ የምለው … ህይወት ይቀጥላል ምናምን የሚሏት ነገር አለች፡፡ እውነት ለመናገር አሁን እየጨነቀን ያለው የዛሬ ዓመት “ይደረጋል”፣ “አይደረግም” እያሉ ‘የሚነዛነዙበት’ ምርጫ ሳይሆን ውለን ቤታች ስንገባ ከቤተሰባችን ጋር ምን ቀምሰን እንደምናድር ነው፡፡ ‘ኑሮን መኖር’ ቀርቶ ነገርዬው ‘በህይወት መቆየት’ (‘ሰርቫይቫል’) የሚሉት ነገር ውስጥ ሆነን፣ ስለ ዛሬ ዓመት የምርጫ ኮረጆ ማሰብ…አለ አይደል…ነገር ነው የሚመስለው:: ፖለቲከኞቻችን ይሄን ለመረዳታቸው አሳማኝ ምልክቶች እያየን አይደለም፡፡
የምር ግን… እውነት እንነጋገር ከተባለ ይሄ ሁሉ ጉድ እየደረሰባትም፣ የመከራው  ባቡር አልቆም ብሎ ጣቢያዎቹን እየጣሰ እየገሰገሰም፣ ይቺ ሀገር ‘ቆማ መሄዷ’ የአንድዬ ጥበቃ እንጂ እንደ ሁኔታችን እኮ…ብቻ ግራ ግብት የሚል ነገር ነው፡፡
የቁም ነገር አምላክ መከራውን ያቅልልንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል.. ይሄ የብድር ነገር አንዳንዴ እኮ ግራ ያጋባል፡፡ በቃ መበደር፣ መበደር፣ መበደር ነው! አሀ…በፊት እኮ “እንትን የሚባል ድርጅት በረጅም ጊዜ የሚከፈል ይህን ይህል አበደረን”፣ “እንትና የምትባል ሀገር በአነስተኛ ወለድ ይህን ያህል ዩሮ አበደረችን” ሲባል እናጨበጭብ ነበር፡፡ ልማት ላይ ከዋለ ጥቅሙ የሁላችንም ይሆናል ብለን ነዋ! አሁን ግን እዳው፣ መብዛት አይደለም፣ ልንገምተው እንኳን የማንችለው የቁጥር ድርደራ ሆኖብን፣ ስለ ብድር ሲነሳ የሚታሰበን ነገር ቢኖር… “ያው መቼም እድሜ ልካችንን መክፈል አንችልም፤ የሆነ ‘ሪሶርሳችንን’ “መቶ ዓመት ተጠቀሙበት” ብለን ለመልቀቅ የምንገደድበት ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡ እናማ… የመጪውን ትውልድ ንብረት አሁን ያለው ትውልድ በእዳ የማስያዝ መብት የለውም፡፡ (ስሙኝማ... ‘አክቲቪስትነት’ እንዲህ ነው እኮ የሚጀመረው! በሌላው ሀገር ፕሬሚየር ሊግ የሆነው ‘አክቲቪስትነት’፤ እዚህ ሀገር የጤና ቡድን ክብር እንኳን ይጣ! እንደ ቋንቋ አካዳሚዎች የ‘አክቲቪስትነት’ አካዳሚ ይቋቋምልንማ!)
ስሙኝማ…በዚህ ሁሉ መሀል ግን ምን መሰላችሁ፣ ውሸት በዛ! ቅጥፈት በዛ! ዓይን በጨው ማጠብ በዛ! ውሸት መናገር አንገት ማስደፋቱ ቀርቶ ደረት የሚያስነፋ ሆኗል፡፡ ኮሚክ እኮ ነው… ከነጋ ጀምሮ አንድ መቶ አንድ ቅጥፈት ስንናገር አርፍደን… አለ አይደል… “ስማ ምሳ እንብላ…” ሲሉን “አይ ጾም ላይ ነኝ…” የምንል በበዛንበት፣ መፍትሄ ማግኘት እጅግ ፈታኝ ነው፡፡ ፈተናውን ያቅልልንማ!
በሀሰት ሲለውጧት እውነትን በአፋቸው
የቁም ነገር አምላክ ይቅር ይበላቸው
ገሸሽ አድርገዋት ታላቋን ፍቅር
ሆነው ለተገኙ የሀሰት ምስክር
በእውነት ጨክነው ቃላቸውን ላጠፉ
ይቅር ይበላቸው ላሉትም ላለፉ
የቁም ነገር አምላክ መከራውን ያቅልልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1446 times