Saturday, 08 June 2019 00:00

የኢዜማ መሪዎች ከአሜሪካ ደጋፊዎቻቸው ጋር እየተወያዩ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

“አገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ትሆናለች አትሆንም የሚለው ገና ያልጠራ ጉዳይ ነው”
                              - ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ

              የኢዜማ መሪዎች በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የድጋፍና ገቢ ማሰባሰቢያ ስብሰባዎችን እያካሄዱ ሲሆን ፓርቲው በሃገር ውስጥ መነሻቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የልኡካን ቡድኖችን በአምስት የሃገሪቱ አቅጣጫዎች አሰማርቷል፡፡
ባለፈው ሳምንት ወደ አሜሪካ የተጓዙት የፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ናትናኤል ፈለቀ፤ የመጀመሪያ ስብሰባቸውን በካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ ከተማ ባለፈው ማክሰኞ ያካሄዱ ሲሆን በነገው እለት ደግሞ በዋሽንግተን ተመሳሳይ ስብሰባ ከደጋፊዎች ጋር ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
ፓርቲው ከተመሰረተ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የሎስ አንጀለስ ደጋፊዎች ውይይት ላይ በተደረገ የገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራም፤ 25 ሺህ ዶላር (ከግማሽ ሚ. ብር በላይ) መሰባሰቡም ተገልጿል፡፡
ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በተደረገው የሎስ አንጀለሱ ውይይት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ፤ ኢዜማ በቀጣይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራባቸውን ጉዳዮች አስረድተዋል፡፡
ኢዜማ በዋናነት በሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል ያሉት አቶ ናትናኤል፤ የመጀመሪያው ትኩረቱ የሃገር መረጋጋት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
“የዜጎች መረጋጋት ከሁሉም በፊት ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው ነው፤ ሰው በሰላም ወጥቶ የሚገባበት፣ ሰርቶ የሚያድርበት የተረጋጋ ሁኔታ ለመፍጠር፣ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት በሙሉ ኃላፊነት እንደግፋለን” ብለዋል፤ አቶ ናትናኤል፡፡
ገለልተኛ የዲሞክራሲና የመንግስት ተቋማት እንዲፈጠሩ ማገዝ ደግሞ ፓርቲው በሁለተኛነት ያዘው የትኩረት አቅጣጫው ነው፡፡ “ገለልተኛና ነፃ ተቋማት ሳይፈጠሩ ለምርጫ ፉክክር መቅረብ ለሃገሪቱ አደገኛ መሆኑን ተረድተናል” ያሉት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ “ከምርጫ በፊት ገለልተኛና ነፃ ተቋማት እንዲፈጠሩ ከመንግስት ጋር በቅርበት እንሰራለን” ብለዋል፡፡
ስለ ሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ለደጋፊዎች ማብራሪያ የሰጡት የፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ “ሃገሪቱ አሁንም ያለችው ያለቀለት ሽግግር ላይ አይደለም” ብለዋል፡፡
“ሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ትሆናለች አትሆንም የሚለው ገና ያልጠራበት፣ ውዥንብር ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው” ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ፤ “የሽግግር ሂደቱም ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግ ነው” ብለዋል፡፡
“ሚናውን ገና ባልለየው የሽግግር ጊዜ፣ በመሃል ሊመጡ የሚችሉ ችግሮች ምንድን ናቸው? ችግሮች ሲመጡ ምን ማድረግ ያስፈልጋል? ልንደርስበት የምንፈልገው ቦታ የት ነው? የሚሉትን በተመለከተ ሰከን ያለ ውይይት ማድረግ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን” በማለት ፕ/ር ብርሃኑ ለደጋፊዎቻቸው አስረድተዋል፡፡
ኢዜማ በውጭ ሃገር ከሚያደርገው የድጋፍ ስብሰባና ውይይት ጎን፣ ለጎን በሃገር ውስጥም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ያስታወቀ ሲሆን፤ ከግንቦት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ መነሻቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ አምስት ቡድኖች፤ ወደ አምስት የሃገሪቱ አቅጣጫዎች ተንቀሳቅሰዋል ተብሏል፡፡
ቡድኖቹ በዋናነት ለ216 የኢዜማ የምርጫ ወረዳዎች ጊዜያዊ እውቅና ደብዳቤ፣ የገንዘብ ማሰባሰብያ ደረሰኝ፣ የአባላት ምልመላ ፎርምና የድርጅቱን ደንብና መመሪያ ለማስተዋወቅ መንቀሳቀሳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የመጀመሪያው ቡድን ከአዲስ አበባ በደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ወልዲያ አድርጐ መዳረሻው ሰቆጣ  ሲሆን ሁለተኛው ቡድን ከአዲስ አበባ ፍቼ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ባህር ዳር አድርጎ መዳረሻው ጎንደር ነው ተብሏል፡፡ ሶስተኛው ቡድን ደግሞ ከአዲስ አበባ ሻሸመኔ፣ ሃዋሳ፣ ጌድኦ፣ አለታ አድርጎ መዳረሻው አዶላ (ክብረ መንግስት) ሲሆን አራተኛው ቡድን፤ ከአዲስ አበባ አምቦ፣ ነቀምት፣ ጊምቢ ጅማ አድርጎ፤ መዳረሻው ቤንቺማጂ ይሆናል፡፡
አምስተኛው ቡድን ደግሞ ከአዲስ አበባ አዳማ፣ አሰላ፣ ወላይታ፣ ሃዲያ፣ ዳውሮ፣ ወልቂጤ ከዚያም መዳረሻውን ጉራጌ ዞን እንደሆነ ታውቋል፡፡ ተጓዥ ቡድኑ በየአካባቢው የማረጋጋት ተግባራትን እንደሚፈፅምም ተገልጿል፡፡

Read 6390 times