Monday, 10 June 2019 11:37

በናይጀሪያ በየቀኑ 100 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ይዘረፋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ሳኒ አባቻ በእንግሊዝ ባንክ ያስቀመጡት 267 ሚሊዮን ዶላር ተወረሰ

              በአፍሪካ በነዳጅ ሃብቷ ቀዳሚውን ስፍራ በምትይዘው ናይጀሪያ፣ በየቀኑ በአማካይ 100 ሺህ በርሜል ያህል ድፍድፍ ነዳጅ በህገ ወጦች እንደሚዘረፍ ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
በመላው ናይጀሪያ የነዳጅ መተላለፊያ ቱቦዎችን እየሰረሰሩ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ የሚዘርፉ ሰዎች ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን ያህል እንደሚደርስ የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም አገሪቱ ከነዳጅ ኤክስፖርት የምታገኘው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ማድረጉንም አመልክቷል፡፡
በናይጀሪያ ነጋ ጠባ የሚዘረፈውና በመቶዎች በሚቆጠሩ ትናንሽ የነዳጅ ማጣሪያዎች እየተጣራ በህገ ወጥ መንገድ ለሽያጭ የሚቀርበው ነዳጅ በገንዘብ ሲተመን የአገሪቱን የበጀት ጉድለት ሙሉ ለሙሉ የመሸፈን አቅም እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፤ በአገሪቱ የሚገኙ የነዳጅ ኩባንያዎችም የዝርፊያው ሰለባ መሆናቸውን ገልጧል፡፡
ታዋቂው ሼል ኩባንያ በናይጀሪያ ባለፈው የፈረንጆች አመት (2018)፣ በየቀኑ 11 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በወንጀለኞች መዘረፉንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሳኒ ኣባቻ፣ በስልጣን ዘመናቸው በሙስና ያፈሩትና በእንግሊዝ ውስጥ በሚገኝ ባንክ ከዝነውት የነበረ 267 ሚሊዮን ዶላር እንዲወረስ መወሰኑ ተዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ ከ1993 አንስቶ በሞት እስከተለዩበት 1998 ድረስ አገሪቱን የመሩትና በአምባገነንነታቸው የሚታወቁት ሳኒ ኣባቻ፤ በህገ ወጥ መንገድ ከአገር አስወጥተውታል የተባለውና ላለፉት 5 አመታት እንዳይንቀሳቀስ ታግዶ የነበረው ይህ ገንዘብ፣ ለናይጀሪያ ለአሜሪካና ለእንግሊዝ እንደሚከፋፈል ተነግሯል፡፡


Read 1232 times