Saturday, 08 June 2019 00:00

ቃለ ምልልስ “ትልቋን ኢትዮጵያን አስቀጥለን ማየት እፈልጋለሁ”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  • ከድህነት ጋር የምናደርገውን ትግል ማሸነፍ አለብን
               • እኛ ያለ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም ነን
               • ወላይታ የኢንቨስትመንት ማዕከል እየሆነች ነው


            ከ125 ዓመታት በፊት የተቆረቆችው ወላይታ ሶዶ፤ ወደ ዕድገት እያኮበኮበች ያለች፣ ውብና አረንጓዴ ከተማ ናት፡፡ በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ኢንቨስትመንት እየተጧጧፈባት ትገኛለች፤ በተለይ የሆቴልና ሎጅ ኢንቨስትመንት፡፡ አረንጓዴዋ ወላይታ ሶዶ ከተማ፤ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ (ግንቦት 24 - 26) አራተኛውን ዙር የደቡብ ክልል የባህል ፌስቲቫል “ባህላችን ለሰላማችንና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል በድምቀት አክብራለች፡፡
በዚህ ፌስቲቫል ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳገቶ ኩምቢ ጋር ስለ ከተማዋ አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ ዞኑ ስላነሳው የክልልነት ጥያቄ፣ ስለ ወጣት የሰላም አምባሳደሮች፣ ስለ ዞኑ የቱሪስት መስህቦች፣ ስለ ኢንቨስትመንትና የፀጥታ ሁኔታ… አነጋግራቸዋለች፡፡ እነሆ፡-

           የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት መቼ ነው? ከዚያ በፊት በምን ኃላፊነት ላይ ሰርተዋል? የትምህርት ዝግጅትዎስ ምን ይመስላል?
ገና ከዩኒቨርሲቲ እንደወጣሁ የዳሞት ፑላሳ ፍትህ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ ቀጥሎም የወላይታ ዞን ፍትህ መምሪያ ከፍተኛ አቃቤ ህግም ነበርኩኝ:: ከዚያም የወላይታ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ ሆኜ ሰራሁ፡፡ የወላይታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ሆኜ ከሰራሁ በኋላ ነው ወደ ዞኑ ዋና አስተዳዳሪነት የመጣሁት፡፡  የመጀመሪያ ዲግሪዬን በህግ (LLB)፣ ሁለተኛ ዲግሪዬን (LLM) ደግሞ በሂውማን ራይትስና ክርሚናል ጀስቲስ ስፔሻላይዝ አድርጌያለሁ፡፡
የወላይታ ዞን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
አሁን በወላይታ ከፍተኛ መነቃቃትና እንቅስቃሴ የተፈጠረበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ እኛ ወደ ኃላፊነት ከመጣን በኋላ ሀገራዊ አንድነት ብሎም የወላይታ አንድነት ላይ አጥብቀን እየሰራን ነው:: አንድ ስንሆን እንሻገራለን የሚል እምነት አለን:: በተጨማሪም ማንኛውንም ችግር እኛው ራሳችን በመነጋገር መፍታት እንችላለን ብለን እናምናለን:: ችግራችንን ራሳችን መፍታት የምንችለው ደግሞ በተደራጀና በተባበረ መልኩ ስንቆም ነው፡፡ አሁን የህዝባችንና የአገራችን ትልቁ ጠላት ድህነት ነው፡፡ ከድህነት ጋር የምናደርገው ትግል ደግሞ ፈታኝ ነው፤ እንደ ሌላው ትግል በቀላሉ የምናሸንፈው አይደለም:: ቀላል ባይሆንም ማሸነፍ ግን አለብን፡፡ እኔን እንደምታይኝ፣ በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ ነኝ፡፡ እንደ ወጣትነቴም፣ በእኛ ጊዜ ይሄ ችግር መቆም አለበት የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ መቆም አለበት በማለት ብቻ ግን አይቆምም፤ ትልቅ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡ ይህን ለማሳካት ህዝባዊ አንድነት ወሳኝ በመሆኑ፣ በዚህ ላይ በሰራነው ስራ ህዝቡ ወደ አንድነት እየመጣ  ነው፡፡  አንድ ከሆንን በኋላ ደግሞ ወደ ቀጣይ ጉዟችን እንገባለን፡፡ ስለዚህ ወላይታ ላይ ከህፃን እስከ ሽማግሌ ሁሉም፣ በአንድነትና በሰላም ዙሪያ አንድ ዓይነት ቋንቋ መነጋገር የቻለበት ወቅት ላይ ደርሰናል ማለት ነው፡፡ የጋራ አጀንዳና የጋራ አቋም ይዘናል፡፡
“አረንጓዴ ወላይታን እንፈጥራለን” የሚል ዘመቻ ጀምራችኋል፡፡ እስቲ ስለ ዘመቻው ይንገሩኝ?
በቅርቡ ነው ይህን እንቅስቃሴ የጀመርነው - “አረንጓዴ ወላይታን እንፈጥራለን” በሚል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ልማት የሚጀምረው ከዚህ ነው:: የአካባቢው የአየር ሁኔታ ተስተካክሎ፣ ሁሉም ነገር አረንጓዴ ሲሆንና ጤናማ መንፈስ ሲያሳድር ነው ሌላው ልማት የሚከተለው፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ ሰው የራሱን አስተዋጽኦ በማድረግ፣ ለዚህ ትልቅ አላማ መሳካት የበኩሉን ይወጣል:: አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ ወላይታ በጣም በተረጋጋና ሰላማዊ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ሰላም የመጣው ራሱ ህዝቡ የሰላም ባለቤት ስለሆነ ነው:: ወጣቱ ለሰላሙ መምጣት ከህዝብ ጎን በመቆሙ ነው:: በሌላው አካባቢ የሚታየው አንዳንድ ችግር በወላይታ ያልታየው፣ እኛም አመራሮቹ፣ ከህዝቡ ጋር በቅርበት መስራት በመቻላችን ነው፡፡ ይህ ሰላም በእጃችን ገብቷል፡፡ አረንጓዴ ወላይታን ለመፍጠር የምናደርገው የትኛውም እንቅስቃሴ፣ ሰላም እስካለ ድረስ ይሳካል፡፡ ሰላም ካለ ልማትና ኢንቨስትመንት ይከተላል፡፡ ከተማዋ ትልቅ የኢንቨስትመንት ማዕከል እየሆነች ነው፡፡ ትልቅ አቅምም በከተማዋና በዙሪያዋ አለ፡፡ ከዚህ አቅም የተነሳ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ይታያል፡፡ ለምሳሌ ክቡር ዶ/ር ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ፤ በወላይታ የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ቅርንጫፍ የሆነ ትልቅ ሎጅ በፍጥነት እየገነባ ነው፡፡ አሁን እኔና አንቺ ቁጭ ብለን የምንነጋገርበት ሌዊ ሪዞርት፤ ሃዋሳ ላይ ብዙ ቅርንጫፎች ያሉት ትልቅ ሪዞርት ነው፡፡ አበበ ዘለቀ ሆቴል፣ ሰማያት ሆቴልና ሌሎች በርካታ ኢንቨስትመንቶች አሉ፡፡ በቅርቡም ሌላ ሎጅ ሊገነባ በሂደት ላይ ነው፡፡ የተሻሉ የልማት እንቅስቃሴዎች አሉ ማለት ይቻላል፡፡
ከተማዋን ከ4 ዓመት በፊት አይቻት ነበር፡፡ አሁን በርካታ ለውጦችን አይቼባታለሁ፡፡ ምናልባት ለዚህ ለውጥ መፋጠን የዞኑና የከተማዋ አመራሮች በወጣት ኃይል መተካቱ አስተዋፅኦ አድርጎ ይሆን?
እንዳልሺው ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ሶዶ ከተማ ላይ በርካታ ለውጦች መጥተዋል፡፡ ከሶዶም አልፎ ወላይታ ላይ፡፡ ይህ ለውጥ በፍጥነት የመጣው ከበፊት አካሄድ በተለየ መልኩ ህዝቡን ማሳተፍ ላይ ስለሰራን ነው፡፡ ሕዝቡ የስራው ባለቤት፣ ህዝቡ የንብረቱ ባለቤት እየሆነ ስለመጣ በርካታ ለውጦችና ውጤቶች መጥተዋል፡፡ ይህን ለውጥ በማስተባበር ረገድ የአመራሩ ሚና ጉልህ ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ህዝብን ዝቅ ብለው ማገልገል የሚችሉ ሰዎች ወደ መዋቅሩ በመምጣታቸው፣ ባለፉት ሶስት አመታት እንዳልሽው በርካታ ለውጥ መጥቷል፡፡ ለዚህ የአመራሩ ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፣ በአመራር ብቻ የመጣ ለውጥ የለም፡፡ ህዝብ ሲለወጥና ሲቀየር፣ እኔም እራሴ እቀየራለሁ፤ እለወጣለሁ ብሎ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ ይሄን አስተሳሰብ በሁሉም ዘንድ ማስረፅ ከተቻለ፣ ሁሉንም ነገር መለወጥና መቀየር አያዳግትም፡፡
ወላይታ ይበልጥ የምትታወቅበትና የምትለይበት ነገር ምንድን ነው?
ወላይታ በጣም ብዙ መለያ ባህሪያትና አንጡራ ሀብቶች አሏት፡፡ ለምሳሌ አንዱና መሰረታዊው መለያ፤ ከጥንት ጀምሮ የራሱ አስተዳደራዊ ስርዓት ያለው ህዝብ መሆኑ ነው፡፡ የወላይታ ህዝብ፤ ሶስት ስርወ መንግስትና ከ50 በላይ ነገስታት ተራ በተራ መርተውታል፡፡ ያ የወላይታ የጥንት አስተዳደራዊ ስርአት፤ አሁን ላለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መነሻ የሚሆኑ ሀሳቦች የፈለቁበት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- መሪዎች በህዝብ ፍላጎት የሚመረጡበት፣ ኃላፊዎች አጥፍተውና በድለው ሲገኙ፣ በዛው ልክ በህዝብ ፍላጎት ከኃላፊነት የሚነሱበት፤ ፍትህ የማፈላለጉ ሥርዓት እውነትን መሰረት ያደረገ መሆኑ … በአጠቃላይ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይሄ አንዱ መለያው ነው፡፡ እንደሚታወቀው የወላይታ የመጨረሻው ንጉስ ካዎ ጦና ናቸው፡፡ እስከ ካዎ ጦና ዘመን፣ ህዝቡ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ልምድ ያለው አካባቢ ነው፡፡
ወላይታ ከጥንት ጀምሮ የንግድ ማዕከል ነበረች:: የራሳቸው የሆነ፣ ከብረት የተሰራ፣ የህዝቡን ፍልስፍና ግምት ውስጥ ያስገባ መገበያያ ገንዘብ የሰሩ ናቸው - ወላይታዎች፡፡ ገንዘቡ “ማርጩዋ” ይባላል:: ያኔ ሌላው አካባቢ፣ እህልን በእህል እየተለዋወጠ በሚገበያይበት ዘመን፤ የወላይታ ህዝብ የራሱ መገበያያ ገንዘብ ነበረው፡፡ ሌላውና መሰረታዊው የወላይታ መለያ ሰላም ነው፡፡ የሰላም ጉዳይ ሲነሳ ሁሉም ሰው በወላይታ ነፃነት ይሰማዋል:: አሁን ባለው ሁኔታ፤ አንቺና ጓደኞችሽ ከሌላ ቦታ ስለመጣችሁ፣ ያለውን ነገር ትገነዘቡታላችሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ህዝቡ በጣም ሰላማዊ ህዝብ ነው:: ከሌላ አካባቢ የመጣ ሰው፤ በእንግድነቱ ተከብሮ፣ ተደስቶ የሚመለስበት አካባቢ ነው፡፡ የወላይታና የህዝቡ ሌላው መለያ ባህሪ ስራ ወዳድነት ነው:: ህዝቡ የትኛውም ቦታ ማንኛውንም ዓይነት ስራ ሳይንቅ የሚሰራ ህዝብ ነው፡፡ ለወላይታ ወጣት ከባድ ነው ወይም ይከብደዋል ተብሎ የሚለይ ስራ የለም:: ስራ በፍቅር የሚወድ ህዝብ ነው፡፡ የወንድማማች ህዝብ ፍቅር፣ አቃፊነትና ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብሮ የመኖር እሴትና ፍላጎት ያለው አካባቢ ነው፡፡
ልዩ ልዩ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች አሏት - ወላይታ፡፡ ለምሳሌ ያህል፡- አጆራ ፏፏቴን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የሚታወቅ ትልቅ ፏፏቴ ነው፡፡ ሌላው እዚህ ከተማ ላይ ያለ ከ58ሺህ ዓመታት በፊት ሰው ይኖር እንደነበረ የሚያመለክት ሞቼና ቦራጎ ዋሻ አለ፡፡ በጣም ትልቅ ዋሻ ነው:: ጁንየን ዘመናዊ የወጣቶች መዝናኛ ፓርክም አለ:: የሚገርምሽ በዚህ ፓርክ ውስጥ  ውሻና ጅብ አብረው ይኖራሉ፡፡ አዞና ዘንዶ አሉ፡፡ አብረው ነው የሚኖሩት፡፡ አሁን አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ተልካሻ በሆነ ምክንያት ሰዎች ተጋጭተው፣ ግጭቱ ወደ ተለያየ አቅጣጫ ሲሄድ እንመለከታለን፡፡ ይሄ ፓርክ ግን ትልቅ ትምህርት የምንወስድበት ነው፡፡ እንኳን ሰው ከሰው ጋር ጅብና ውሻ እንዲሁም ሌሎችም የማይመሳሰሉ እንስሳት አብረው መኖር ይችላሉ፡፡ ሌሎችም በርካታ የቱሪስት መስህቦች አሉ፡፡ ስለዚህ ወላይታ የቱሪስት መዳረሻ ናት፡፡
በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የ “”ክልል እንሁን” ጥያቄን መሰረት ያደረገ ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጎ ነበር…?
ትክክል ነው!
ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ሌላውም እንዲሁ የክልልነት ጥያቄ እያነሳ ነው፡፡ ስለ አንድነት መዘመር በሚያስፈልግበት በዚህ ወቅት እንዲህ ያለው ጥያቄ ለአንድነት አደጋ አይሆንም?
እንዳልሽው የክልል እንሁን ጥያቄ አቅርበናል:: ይህንን ጥያቄ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 47 ላይ በተደነገገው መሰረት ነው የጠየቅነው፡፡ አንቀፁ ማንኛውም ብሄር ክልል የመሆን ጥያቄ፣ በብሄሩ ምክር ቤት ሁለት ሶስተኛ ድምጽ አስወስኖ ለክልል ምክር ቤት ያቀርባል፤ ከዚያም ለምርጫ ቦርድ ይቀርብና፣ ምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔ ካካሄደ በኋላ መብቱ እንደሚረጋገጥ ተቀምጧል፡፡ በዚህ መሰረት እኛ 379 ቀበሌዎች አሉን፡፡ በሁሉም ቀበሌ ውይይት ተደርጎ፣ የህዝብ አጀንዳና ጥያቄ ሆኗል፤ የክልልነት ጥያቄ፡፡ ይሄ ጥያቄ በዞን ም/ቤትም ፀድቆ ወደ ክልል ተልኳል፡፡ የክልል እንሁን ጥያቄ የአደረጃጀት የመብት ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄው በተለያዩ አካባቢዎች ላይ እንደተጠየቀ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ይሄ ጥያቄ አብሮ ከመኖር፣ ከኢትዮጵያዊ አንድነት ችግር ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ወይም በጋራ አብሮ ከመኖር ፅንሰ ሀሳብ ጋር የሚጋጭ አይደለም፡፡ የተጠሪነትና የአደረጃጀት ጉዳይ ነው፡፡
እኛ ከሲዳማ፣ ከጎፋ፣ ከጋሞ፣ ከኦሮሚያና ከሌላውም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በጋራ ለመኖር እንፈልጋለን፡፡ እኛ ያለ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም ነን፡፡ ነገር ግን ያደረጃጀት ጥያቄ ተጠየቀ ማለት የህዝብን አብሮነት ያላላል ማለት አይደለም፡፡ ለህዝቡ የክልል አስተዳደር ሥርዓት በቅርባቸው ያግኙ ነው እያልን ያለነው፡፡ ክልል ድረስ ሄዶ የሚያገኛቸውን የአስተዳደራዊ ጉዳዮች በቅርብ በቀዬው አድርገንለት፣ የህዝብን ሸክም እናቅልል ነው የምንለው፡፡ ይሄን ከመበታተን ከመለያየት ጋር የሚያያይዝ ካለ ጤንነቱን እጠራጠራለሁ፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፤ የወላይታ ህዝብ በአቃፊነቱ የሚታወቅ፣ የትኛውም አካባቢ ሄዶ ማንኛውንም ስራ ሰርቶ የሚኖር፣ ሰላማዊና ስራ ወዳድ ህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ የመብትና የአደረጃጀት ጥያቄ መጠየቅ፣ አብሮ ከመኖርና ከኢትዮጵያዊ አንድነት ጋር የሚጋጭ አይደለም፡፡ የሌላውን አገር ተሞክሮ መውሰድ ይቻላል፡፡ ደቡብ ሱዳን በቅርቡ ነው አገር የሆነችው፣ 32 ክልሎች አሏት፡፡ ደቡብ አፍሪካ 26 ክልሎች አሏት፡፡ ናይጄሪያም እንደዚያው፡፡ ስለዚህ የክልል ቁጥር በዛ ማለት ለህዝቡ አስተዳደራዊ ጥያቄ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ያስችላል እንጂ አብሮነትን አያላላም፡፡
ከወዲሁ ግን ከጀርመን ባንዲራ ጋር የሚመሳሰል ቀለም ያለው ባንዲራ፤ የወላይታ ክልል ባንዲራ ተብሎ፣ ወጣቶች በብዛት ለብሰውት አይቻለሁ፡፡ ይሄስ ጉዳይ እንዴት ነው?
እኛ ገና ክልል አልሆንም፤ ጥያቄ አቀረብን እንጂ:: የወላይታን ህዝብ ጥያቄ መንግስት እንዲመልስ እየጠየቅን ነው ያለነው፡፡ ያ ጥያቄ ሲመለስና ሲፈቀድ ከባንዲራ፣ ከአርማና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያያዥነት ያላቸው ነገሮች ቀጥለው ይመጣሉ፡፡ ምናልባት አንቺ ያየሻቸው ወጣቶች ይዘው የወጡት ባንዲራ፣ ወደፊት የሚመኙትን የሚፈልጉትን ለመግለፅ ያደረጉት ይሆናል እንጂ እኛ በደቡብ ክልል ውስጥ ያለን አንድ ዞን ነን፡፡ እውቅና የሰጠነው ባንዲራ የለም፡፡ ወጣቶች ምኞታቸውን ለማንፀባረቅ ያደረጉት ይሆናል፡፡ የባንዲራ ጉዳዮች በአዋጅና በህዝብ ተወስኖ፣ የህግ ማዕቀፎችን አልፎ ይፋ የሚሆን ነው፡፡
ወንድማማች ከሆነው ከሲዳማ ህዝብ ጋር ግንኙነቱ እንዴት ነው?
ቀደም ሲል በሲዳማና በወላይታ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ላይ ኦፊሻል የሆነ እርቅ መፈፀሙ ይታወቃል፡፡ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የእርቅና የንስሀ የአብሮነት ኮንፈረንስ አካሂደናል:: ይሄ ኮንፈረንስ አንድ ጊዜ ከወላይታና ከሲዳማ የተመረጡ ሽማግሌዎች አንድ ላይ ውይይት አድርገው ችግሩን ፈትተዋል፡፡ ሀዋሳም ላይ መድረክ ተፈጥሯል፡፡ ኮንፈረንስ ተካሂዷል፡፡ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ነበሩ፡፡ በተመሳሳይ ያ መድረክ ወላይታም ላይ ተደርጓል፡፡ በጉተራ አዳራሽ የክልላችን ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስና የሰላም ሚኒስትሯም በተመሳሳይ በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
እዚህ ከተማ ላይ ሰው ሲደነቅ ያየሁትና እኔም የተገረምኩበት የ“ሰላም አምባሳደር” ወጣቶቻችሁ ቅንጅትና ሰላም የማስከበር ሚና ነው፡፡ የሰላም አምባሳደሮቹ እንዴት ተፈጠሩ?
ወጣቶችን ለሰላምና ለልማት እንጠቀምባቸው የሚል የዞኑ አስተዳደር ፅኑ እምነት ነበረ፡፡ በዚህ መሰረት ወላይታ ላይ ካሉ ወጣቶች ጋር መድረክ ፈጥረን ተወያይተናል፡፡ የአካባቢን ሰላም የማስከበር ጉዳይ የወጣቱ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን አለበት ብለን በዚህ ጉዳይ ላይ መግባባት ላይ ከደረስን በኋላ ወጣቶችም ኃላፊነት ወስደው “የወላይታ የሰላም አምባሳደር ወጣቶች ማህበር” አደራጅተናል፡፡ በዚህ ማህበር የተደራጁ ወጣቶች ፖሊስ ወይም ሌላ ሶስተኛ ወገን የፀጥታ አካል ሳይጠብቁ፣ በያሉበት ቦታ የአካባቢውን ሰላም የሚያስጠብቁ የሰላም አምባሳደሮች ናቸው፡፡ ይህ ትልቅ ተልዕኮ ነው:: ቅድም እንዳልኩሽ፤ ሰላም ሲኖር ነው ልማትና ኢንቨስትመንት የሚመጣው፤ ስራ አጥነትን መቀነስ የምንችለው፡፡ ሰላም መሰረታዊ ነገር በመሆኑ ማንኛውም ችግርና አለመግባባት ሲፈጠር በውይይት ነው የሚፈታው፡፡ ጥያቄም ካለ ህጋዊ በሆነ መንገድ ነው የሚፈታው፡፡ ጥያቄዎችን ባልተገባ መንገድ ለመጠየቅ የሚፈልጉ አካላት ቢኖሩ እንኳን የሚያስተምሩና መንገድ የሚያሳዩ እኒህ ወጣቶች ናቸው፡፡ ወጣቶቹ ትልልቅ ዝግጅቶችን ወላይታ ላይ በብቃት እያስተባበሩ፣ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ የክልልነት ጥያቄውን አስመልክቶ በተካሄደው ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ፤ ያ ሁሉ ህዝብ ወጥቶ፣ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድምፁን አሰምቶ ሲመለስ፣ የእነዚህ ወጣቶች ሚና በጣም ትልቅና ወሳኝ ነበር፡፡ ወጣቱ ከመንግስት፣ ከህዝብና ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆሙ ነው በስኬት የተጠናቀቀው፡፡ የክልሉ የሰላም ፌስቲቫል ላይም አይተሻቸዋል፡፡ ፌስቲቫሉ በጥሩ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በትጋት ሲሰሩ ነበር፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ክብርት ሚኒስትር ሂሩት ካሳውም እውቅና ሰጥታቸዋለች፡፡ የወላይታ ዲቻ ጨዋታ ሲኖር፣ የሌላ ቡድንም ሆነ የዲቻ ደጋፊዎች በብዛት ስታዲየም ሲገቡ፣ ሙሉ የፀጥታውን ስራ እነዚህ ወጣቶች ናቸው የሚሰሩት፡፡ በቀጣይም በማንኛውም የሰላም ስራ፣ ከመንግስት ጎን ሆነው ይሰራሉ፡፡ ይህንን ተሞክሮ በሁሉም ወረዳና ከተማ ላይ እንዲወርድ የማድረግ ስራ እየሰራን ነው፡፡ እንደ አገርም ተሞክሮው ቀላል አይደለም፡፡ ሁሉም ሊማርበት ይገባል፡፡
የሀገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል? እንደ ወጣት አመራርነትዎ ለአገርዎ ምን ይመኛሉ?
አገሪቱ ላይ የማይካድ ለውጥ አለ፡፡ ይህንን ለውጥ የመደገፍ ድርሻ ደግሞ የሁሉም ነው::  ከወጣቱ፣ ከምሁሩ፣ ከሽማግሌው፣ ከሃይማኖት መሪው፣ ከመንግስት ሰራተኛው፣ ከነጋዴው… በአጠቃላይ ከሁሉም ወገን የሚጠበቅ ነው፡፡ አንድ አገር ላይ ለውጥ ሲመጣ ያንን ተከትሎ የሚፈጠሩ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ለውጥ ለማምጣትና ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት ላይ ሁሉም የድርሻውን የመወጣቱ ጉዳይ በአፅንኦት ሊታይ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ለውጡ በደንብ ጎልቶ እንዳይታይ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ የፀጥታ ጉዳይ ነው፡፡ የፀጥታ ጉዳዮች በትኩረት ሊታዩ ይገባል፡ መንግስትም የህዝቡን የፀጥታ ሁኔታ የማስከበር ቀዳሚ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በየአካባቢው ያሉ የፀጥታ ችግሮች፣ መፈናቀሎች፣ ሰው ለውጡን በጥርጣሬ እንዲያየው ያደርጋል፡፡ ሆኖም አሁን ነገሮች መስመር እየያዙ ነው፡፡ ህዝቡ ከመንግስት ጋር ሆኖ በአግባቡ ከደገፈ፣ መንግስትም ኃላፊነቱን ከተወጣ ማስተካከል ይቻላል፡፡ ሁሉም ክልል የአካባቢውን ፀጥታ የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡
ሁሉም በየአካባቢው ለሰላም ዘብ ከቆመ ሀገራችን ሰላም ትሆናለች፡፡ ሀገራችን ሰላም ከሆነች የምንናፍቃትና የምናልማት ኢትየጵያ እውን ትሆናለች፡፡ አገራዊ አንድነት ይጠነክራል፡፡ ያጣነውን አገራዊ ፍቅር መልሰን፣ ትልቋን ኢትዮጵያን አስቀጥለን ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህም ከባልደረቦቼ ጋር ሆኜ የበኩሌን ኃላፊነት እወጣለሁ፡፡

Read 1075 times