Saturday, 08 June 2019 00:00

ወንጀልና ቅጣት ቀይ ሽብር፥ ሰብዓዊ ወንጀል፥ ስደት፥ ስጋት፥ እስር

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(0 votes)


                “--የሆላንድ ፍርድ ቤቶች፣ በየትኛውም የዓለም ክፍል በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀልን የማየት ሥልጣን አላቸው። በዚህም የተነሳ እሸቱ የተከሰሰው መረጃን በማጭበርበር ሳይሆን በቀጥታ በቀይ ሽብር ላይ በነበረው ተሳትፎ ነው። ተፋራጆችን ዘሄግ በሚገኘው ፍርድ ቤት የተጋፈጠው መቶ አለቃ፤ ለተፈፀመው ግድያ ይቅርታ ጠይቋል። -”
            ለአስራ ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ ደህንነት መስሪያ ቤት ሀላፊ የነበሩት  አቶ ጌታቸው አሰፋ በሰብዓዊነት ላይ በተፈፀመ ወንጀልና በሙስና ተከስሰዋል። አቶ ጌታቸውን ይዞ ህግ ፊት የማቅረቡ ጉዳይ በሀገሪቱ ካለው የፖለቲካ ምስቅልቅል አንፃር ለጊዜው አስቸጋሪ ሆኗል። ግለሰቡ በክልል ደረጃ ከለላ በማግኘታቸው ለፍርድ መቅረብ አልቻሉም። ለምን ያህል ጊዜ ከህግ ሸሽተው እንደሚቆዩ ማንም አያውቅም። ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሀገርም ሆነ በውጪ በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሁኔታ ጠባብ ነው።
ከዚህ ቀደም በቀይ ሽብር ወንጀል ተከስሰው በተለያዩ ቦታዎች ለመሰወር የሞከሩት ክፉ እጣ ገጥሟቸዋል። በሀገር ውስጥ ጣሊያን ኤምባሲ ተሸሽገው ከነበሩ አራት ከፍተኛ የደርግ ባለሥልጣኖች አቶ ሃይሉ ይመኑና ለአንድ ሳምንት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሌተና ጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን በሞት ሲለዩ ሻምበል ብርሃኑ ባይህና ሌተና ጄኔራል አዲስ ተድላ ደግሞ ላለፉት 28 ዓመታት በአንድ ግቢ ተከርችመው ሕይወታቸውን ለመግፋት ተገድደዋል። የዊኪሊክስ ድረገፅ መስራች ጁሊየን አሳንዥ ለንደን ውስጥ በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ ለሰባት ዓመታት መቆየቱ ብዙዎችን ቢያስገርምም ኢትዮጵያ ውስጥ የተረሱት እነዚህ ባለሥልጣኖች በአንድ ቦታ ተከልሎ በመቀመጥ ክብረወሰን ሳይጨብጡ አይቀሩም።  
በተለያየ መንገድ ወደ ውጪ የወጡና ክሳቸው በሌሉበት የታየም በርካቶች ናቸው። የቀድሞው ጎንደር ክፍለ ሃገር የደርግ ተጠሪ ሻለቃ መላኩ ተፈራ፣ በጅቡቲ መንግሥት ተላልፎ ተሰጥቷል። አውሮፓና አሜሪካ ከተሸሸጉት ውስጥ የተወሰኑት የተጋለጡበት ሁኔታ ልብወለድ እንጂ እውነተኛ ታሪክ  አይመስልም። በሀገር ውስጥ ከቀይ ሽብር ጋር የተያያዙትን ጉዳዮች እንዲመረምር የተቋቋመው የልዩ አቃቤ ሕግ ክሱን በመሰረተበት የመጀመሪያዎቹ አመታት ሂደቱ፣ የህብረተሰቡን ትኩረት አግኝቶ ነበር። ጉዳዩ እየተጓተተ መሄድ ሲጀምር፣ በተለይም ደግሞ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ራሱ አፈናና እስር ላይ ሲበረታ፣ ነገሩ ሁሉ “ማን ሆነሽ ማንን ታሚያለሽ” መሆን ጀመረ።
አሁን ግን ጉዳዩ ከመቀዝቀዝ አልፎ እየተረሳ የመጣ ይመስላል። በዚሁ በቀይ ሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ ሰሞኑን ከሀገር ውጪ የተፈረደበት ግለሰብ ጉዳይ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት አለመሳቡ የዚህ ውጤት ይመስላል::  የሚገርመው ነገር ደግሞ የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት በቅድሚያ የሞት ፍርድ ቀስ ብሎ ሞቱ ወደ እድሜ ይፍታህ ተቀይሮላቸው በሀገሪቱ ህግ መሠረት የዕድሜ ፍርደኛ የሚገባውን ሃያ አመት በመታሰር እዳቸውን ከፍለው ወጥተዋል። የተወሰኑት የሚገርም ብርታት አግኝተው ለማጣቀሻነት የሚውሉ መፃሕፍት አሳትመዋል። በተቃራኒው ግን የቀበሌና የከፍተኛ አብዮት ጥበቃ አባላት በመሆን አነስ ያለ ሚና የነበራቸውና ከሀገር ወጥተው አዲስ ሕይወት የጀመሩ ግለሰቦች፤ ማንነታቸው በታወቀበት ጊዜ ቀላል የማይባል ዋጋ ከፍለዋል። አንዳንዶቹ በሕይወት እያሉ ከወህኒ አይወጡም። ከነዚህ መካከል የአራት ግለሰቦችን ታሪክ እንመለከታለን።
መርጊያ ንጉሴ
ሰሞኑን በዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ ግዛት፣ የሀሰት ማስረጃ በማቅረብ፣ የአሜሪካ ዜግነት ወስዷል የተባለው መርጊያ ንጉሴ ሀብተየስ፤ የ37 ወራት እስራት ተፈርዶበታል። አቶ መርጊያ በዋናነት የተከሰስው ኢትዮጵያ ውስጥ በ1960ዎቹ መጨረሻና በ70ዎቹ መጀመሪያ ተፋፍሞ በነበረው የቀይ ሽብር ዘመቻ ተሳታፊ እንደነበር፣ ነገር ግን የዜግነት ጥያቄ ማመልከቻ ቅፅ በሚሞላበት ወቅት የተሳሳተ መረጃ በመስጠት እውነተኛ ማንነቱን ደብቋል በሚል ነው። ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱም ከእስሩ በተጨማሪ ዜግነቱ ተገፎ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል።
አቶ መርጊያ በወቅቱ በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ሦስት ተብሎ በሚጠራው ሰፈር መርማሪ ነበር። ተጠርጣሪው በልዩ አቃቤ ህግ፣ በቀይ ሽብር ክስ ተመስርቶበት፣ በሌለበት የ25 አመት እስራት ተፈርዶበታል።
የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ አቶ መርጊያ የተከሰሰው ስለ ራሱ ማንነት በሞላው ቅፅ “ባትጠየቅበትም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በዘር፥ በሀይማኖት፥ በጎሳ ወይም በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት በማድረግ  ሰዎች ላይ እንግልት ፈፅመህ ታውቃለህ ወይ” ለሚለው ጥያቄ “ፈፅሞ ተሳትፌ አላውቅም” ሲል የሀሰት ቃል በመስጠቱ እንደሆነ አስታውቋል። አቶ መርጊያ፤ በቨርጂኒያ ግዛት የአሌክሳንድሪያ ከተማ ነዋሪ ሲሆን ወደ አሜሪካ የመጣው  በ1991 ዓ.ም ነው። በ2000 ዓ.ም ደግሞ ዜግነት ወስዷል። በተያዘበት ወቅት የተሽከርካሪ መስተናገጃ አገልግሎት ሠራተኛ ነበር። አቶ መርጊያ መሣሪያ የተረካከበበት ሰነድ ማንነቱን በማረጋገጥ በኩል በማስረጃነት የቀረበበት ሲሆን መርማሪ ሆኖ በሰራባቸው ጊዜያት  የሚያውቁት ሰዎችም መስክረውበታል። ይሁንና የተከሰሰበት ጉዳይ ከመርማሪነቱ ጋር በተያያዘ ሳይሆን ባልተገባ መንገድ ዜግነት ማግኘቱ በማስረጃ በመረጋገጡ ነው።
የቱፋ መጨረሻ
የከፈለኝ አለሙ ወርቁ መጨረሻ በአሳዛኝነቱ ይጠቀሳል። ከኢትዮጵያ የወጣው የመንግሥትን ለውጥ ተከትሎ ነው። ለ13 ዓመታት ቱፋ የሚል ስም ይዞ ከኖረባት ኬንያ ወደ አሜሪካ የዘለቀው በ1996 ነው። ከኤርትራ ተሰዶ ኬንያ፣ ከዚያም በስደተኛ ፕሮግራም፣ አሜሪካ የተሻገረ ሰብዕና የወሰደው ሀብተዓብ በርሄ፤ የማንንም ቀልብ ሳይስብ ኖሯል። በዚሁ አዲስ ማንነቱ ያለ ምንም ችግር  ዜግነቱን ተቀብሏል። መኖሪያው ባደረጋት ዴንቨር የሚገኘው የኮዚ ካፌ ባለቤት አቶ ግርማ ባዬ፣ ለከተማው ቴሌቪዥን በሰጠው ምስክርነት፣ እድሜው ከ60 እስከ 65 ሊጠጋ እንደሚችል፣ ጥሩ ሰው እንደሆነና በሰላም ገብቶ የሚወጣ መሆኑን  ገልጿል። “እውነቱን ለመናገር ለምን እንደተያዘም አልገባኝም።” ብሏል፤ አቶ ግርማ፡፡  ሌሎች ግለሰቦችም ለከተማው ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት፤ ሰዎች ሲጣሉ የሚያስታርቅ፥ ጨዋታ አዋቂ፣ የጥላሁን ገሠሠን ዘፈኖች የሚያንጎራጉር፣ ሲለውም ፒያኖ የሚጫወት ሰው እንደሆነ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ስለ ራሱ ታሪክ እንደማያወራ ግን አልሸሸጉም፡፡
ኢትዮጵያ ሲኖር አመት ከስድስት ወር በእስር ቤት የተንገላታው ክፍሉ ከተማ፤ ከፈለኝን በግንቦት 2003 ዓ.ም ኮዚ ካፌ ውስጥ አግኝቶ ያፋጥጠዋል። ከፈለኝም፤ “አንተ የምትለው ሰው አይደለሁም፤ ምናልባትም ከወንድሜ ጋር ተምታትቼብህ ሊሆን ይችላል” ብሎ ጉዳዩን ይክዳል። በልዩ አቃቤ ሕግ ፅ/ቤት የተዘጋጀው “ደም ያዘለ ዶሴ” የተሰኘው ጥንቅር፤ ከፈለኝ አዲስ አበባ ውስጥ የከፍተኛ 15 ካድሬ እንደነበር ይገልፃል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የከፈለኝ ሕይወት አቅጣጫዋን ትቀይራለች። ሰዎቹ ለህግ አካላት ጉዳዩን ያሳውቃሉ። በቂ ማስረጃ እንዳለው ያመነው አቃቤ ሕግም ክስ ይመሰርታል። በክሱ ሂደት ምሥክርነት የሰጡ ተጎጂዎች እንደገለፁት፤ ከፈለኝ የ14 ዓመት ወጣትን ጨምሮ በርካታ እስረኞችን ለሞትና ለስቃይ ዳርጓል። በወቅቱ እስረኛው የነበረች ተጎጂ ለችሎቱ በሰጠችው ምስክርነት፤ በተከሳሹ በሰደፍ ተመትታ፣ለቀናት ሲያስመልሳት እንደነበር አስታውሳ፤ተከሳሹ የሟቾች አስከሬን የተጣለበትን ቦታ ቢያሳይ የህሊና እረፍት ሊያገኝ እንደሚችል መክራለች። ከፈለኝ በበኩሉ፤ እሱ ራሱ ስድስት ዓመት የታሰረ የሥርዓቱ ሰለባ እንጂ በየዕለቱ ለሰላሳ ደቂቃዎች ሰዎችን የሚገርፍ ሰብዕና እንደሌለው አስረድቷል።
ያም ሆኖ ግን ዋናው የክስ ጭብጥ ቀይ ሽብር ሳይሆን በዜግነት መጠየቂያ ቅፅ ላይ “ማንኛውንም ሰው ለእንግልት አልዳረግኩም” ለሚለው ሃሰተኛ ምላሽ ሰጥተሃል፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሌላ ሰውን ማንነት በመውሰድ ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል ፈፅመሃል እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ የአሜሪካ ዜግነትን አግኝተሃል የሚል ነው። ከፈለኝ ማንነቱን መቀየሩንና አሜሪካ ለመኖር ሲል ይህንን እንዳደረገም አምኗል። ሆኖም ግን “በጊዜው ለሆነው ነገር ተጠያቂ አይደለሁም፤ ያደረግኩትም ነገር ቢኖር በወቅቱ የነበርኩበት አስቸጋሪ ሁኔታ የሚጠይቀውን ነው። እዛ ውስጥ እኔ አንድ ትንሽ ዓሣ እንጂ የመንግሥት ባለሥልጣንም አልነበርኩም” ሲል ለፍርድ ቤቱ ቃሉን ሰጥቷል።
ከፈለኝን ልዩ የሚያደርገው ከኬንያ አሜሪካ የገባበት ሁኔታ ነው። በግለሰቦች ቃል ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ የተድበሰበሰ ሁኔታ ይታይበታል። ከዚህ የማጭበርበር ወንጀል ጋር ተያይዞ በአባሪነት የተከሰሱት ሰዎች ከአቃቤ ህግ ጋር በገቡት ስምምነት መሰረት፤ በእሱ ላይ ከመሰከሩ ከክሱ ነፃ ይሆናሉ። በዚህም መሠረት ጉዳዩን አስረድተዋል። ኬንያ ውስጥ በስደተኝነት የቆዩ አራት ኤርትራውያን፣ ከአባታቸው ጋር በመሆን አሜሪካ እንዲሄዱ ወንድማቸው ያመቻችላቸዋል። ነገር ግን ሊሄዱ አካባቢ አባትየው ይታመማሉ፥ አእምሯቸውም ይታወካል። የመሄዳቸው ጉዳይ ያበቃለት መሰለ። ልጆቹ አባታቸውን ትተው እንዳይሄዱ ፈቃዱ የመጣው በሳቸው ስም ነው። ያለፈረሱ ጋሪውን የሚጎትት አይኖርም። በዚህ ጊዜ መላ ተዘየደ። በአካባቢው ቱፋ በሚል ስም የሚታወቀውን ከፈለኝን ያነጋግሩትና እሱ እንደ አባት ሆኖ የሰውየውን ማንነት ተላብሶ እንዲሄድ ይስማማሉ፡፡ ሀብተዓብ በርሄ ሆኖ ከልጆቹ ጋር ይመጣል። ይህን ታሪክ በመሃላ ለፍርድ ቤት ያስረዳው ጉዳዩን ከአሜሪካ ሲያስፈፅም የነበረው ሳሙኤል ሃብተዓብ በርሄ ነው።
በዚህ ሁኔታ አሜሪካ የገባው ከፈለኝ፤ በኮዚ ካፌ ውስጥ በተጎጂዎቹ እስከታየበት ጊዜ ድረስ በሰላም ሲኖር ነበር። በተያዘበት ወቅት የዴንቨር ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች አውቶቢስ  ሹፌር ነበር። በሶስቱ ክሶች የ22 ዓመት እስራት ሲፈረድበት፣ ዜግነቱንም አጥቷል። እድለኛ ሆኖ እስራቱን ከጨረሰ በህጉ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ ይባረራል። እዚያ ደግሞ በሌለበት ሞት ተፈርዶበታል፡፡
ቀልቤሳ ነገዎ
ከሁሉም በፊት በነዚህ ተመሳሳይ ወንጀሎች የተከሰሰው የቀድሞ ከፍተኛ ዘጠኝ ሊቀመንበር፣ ቀልቤሳ ነገዎ ነበር። እስካሁን አሜሪካኖች ለኢትዮጵያ ሕግ አስከባሪዎች ያስረከቡት ብቸኛ ሰው ነው። የቀልቤሳ ሁኔታ ለህግ አካላት አዲስና ውስብስብ የነበረ በመሆኑ 17 ዓመታትን ፈጅቷል:: አሜሪካኖቹ በቀይ ሽብር ስለመሳተፉ ኢትዮጵያ ድረስ ባለሙያዎች ልከው በፅሁፍና በፎቶ የተደገፈ በቂ ማስረጃ አሰባስበዋል። “ፀረ-አብዮተኞችን በመመንጠር” ስለተወሰደው እርምጃ፥ ተጨማሪ ትጥቅ፥ ጥይቶችና የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን እንዲሰጠው የጠየቀበት ደብዳቤዎች ሁሉ ተገኝተዋል። የልዩ አቃቤ ህግም በርካታ ምስክሮችን አሰምቶበታል። በከፍተኛ ዘጠኝ አድራጊ ፈጣሪ እንደነበር ብዙዎች ተናግረዋል። የአንድን ሰው ፔጆ መኪና ለመውሰድ በፀረ አብዮተኛነት እንዳስገደለም የመሰከሩ አሉ። በዚህ የተነሳ በሌለበት እድሜ ልክ ተፈርዶበታል። የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ፣ አትላንታ እስር ቤት ድረስ ሄዶ ቀልቤሳን ፀረ አብዮተኞችን ስለ መመንጠር ስለ ፃፈው ሲጠይቀው፤ “ያ የወቅቱ አብዮታዊ ቋንቋ” እንደነበር አስረድቷል።
ይሁንና ግን ወንጀሉ አሜሪካ ውስጥ ስላልተፈፀመ የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን የማየት ሥልጣን የላቸውም። ነገሩን ያወሳሰበው ደግሞ ተጠርጣሪው ዜግነት መውሰዱ ነው። አሜሪካ ዜጎቿን አሳልፋ አትሰጥም። የቀልቤሳ ታሪክ የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ አንድሩ ራይስ፤ The Long Interrogation የሚል ርዕስ የተሰጠው ጥልቅ ምርመራ የሰራበት ጉዳይ ነው። ይህ ፅሁፍም ከዚሁ ዘገባ መረጃዎችን ተጠቅሟል።
ቀልቤሳ ከሀገር የወጣው በሐምሌ 1979 ዓ.ም ነው። ደርግ ገና አልወደቀም። እሱ እንደሚለው፤ ራሱ የደርግ ተቃዋሚ በመሆኑ ለዓመታት ታስሯል። ከተፈታ በኋላ ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ሰራተኛ ነበር። ከዚያ በኋላ ነው የተማሪ ቪዛ አግኝቶ በቦሌ በኩል ወደ አሜሪካ ለትምህርት የሄደው። እዚያ በደረሰ በስድስት ወሩ “የደርግ መንግሥት እያሳደደኝ ነው” ብሎ ጥገኝነት ይጠይቃል። የወቅቱ ፖለቲካ አግዞት ጥያቄው በቀላሉ ተቀባይነት ያገኛል። ቀልቤሳ ነገዎ በጆርጂያ ክፍለግዛት ትልቋ ከተማ በሆነችው አትላንታ፣ ኮሎኒ ስኴር በሚገኝ ሸራተን ሆቴል መግቢያ ላይ የእንግዶችን ሻንጣ ይቀበል ነበር። በአንድ ባልታሰበ ቀን ሆቴሉ ውስጥ በሌላ መደብ የምትሰራ ኢትዮጵያዊት፣ ስራዋን ጨርሳ ስትወጣ ሊፍቱ ላይ ተገናኝተው ሰላምታ ይለዋወጣሉ። ከዚያም በየፊናቸው ይሄዳሉ። ሴትየዋ ግን ሰላም ያለችው ሰው፣ ከአእምሮዋ ሊወጣ አልቻለም። እንደምታውቀው እርግጠኛ ናት። ሆኖም ሰውየው ኡዚ ጠመንጃ አንግቶ፣ በሰው ህይወት ላይ ሲፈርድ የነበረው የከፍተኛ ዘጠኝ ሊቀ መንበር ቀልቤሳ ነው ብላ ለማመንም ተቸግራለች። ስለዚህ ጓደኞቿን አምጥታ እሱ መሆኑን እስክታረጋግጥ ድረስ ቸኩላ ነበር፡፡ በመጨረሻም፣ አሜሪካና ካናዳ የሚኖሩ ሌሎች ጓደኞቿን አምጥታ እሱ መሆኑን አረጋገጠች:: እነሆ የ15 ዓመት ሙግት መጀመሪያ።
እጅጋየሁ ታዬ ከአትላንታ፥ ኤልሳቤጥ ደምሴ ከሎስ አንጀለስ እንዲሁም ሂሩት አበበ ከካናዳ ሆነው የተለያዩ የህግ ባለሙያዎችን ቢያነጋግሩም ጉዳዩ እንዲህ በቀላሉ በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች የሚታይ አለመሆኑን ተረድተዋል። እንደዚህ አይነት ወንጀል የታየበትን የአርጀንቲና ጉዳይ ከዚያም አልፎ በድሮ ጊዜያት ወጥተው ሊተገበሩ ያልቻሉ የሕግ አንቀፆችንም ተመልክተዋል። አንዱም አስተማማኝ ሊባል በሚችል መልኩ ክስ አቅርቦ ለመርታት የሚያስችል የህግ መሠረት ሊገኝበት አልቻለም።
የነፃ አገልግሎት ለመስጠት የተስማሙት የህግ ባለሙያዎች የመከሩት፤ በድሮ ጊዜ ለባህር ላይ ዘራፊዎች በወጣ ብዙም ጥቅም ላይ ባልዋለ ሕግ ከስሶ፣ የጉዳት ካሳ መቀበል ብቻ ነበር። በዚህ መዝገብ ሶስቱ ተጎጂዎች በጥምረት የ30 ሚሊዮን ዶላር  የካሳ ጥያቄ ክስ ተሟግተው፣ ለእያንዳንዳቸው 500 ሺህ ዶላር በጥቅሉ አንድ ሚሊዮን ተኩል  እንዲከፈላቸው ይወሰናል። ቀልቤሳ ለላይኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢልም ውሳኔው ፀንቶ ገንዘቡን እንዲከፍል ይወሰናል። እርግጥ ያን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ ስላልነበረው፣ በህጉ መሰረት ኪሳራ ያውጅና እጁ ላይ የተገኘውን ወደ 800 ዶላር ገደማ ከፍሎ  ጉዳዩ ይዘጋል። ተበዳዮቹ ያገኙትን ገንዘብ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ችረዋል።
ይሁንና ግን ይህ ክርክር በሚካሄድበት ጊዜ የቨርሞንት ግዛት ተወካይ ሴናተር ፓትሪክ ለሂ፣ በሌላ ሀገር ወንጀል ፈፅመው አሜሪካ የገቡ ሰዎችን ይዞ ወደመጡበት ለመመለስ የሚያስችል ህግ ለማርቀቅ ተነሳሽነቱን ወስዶ ነበር። ሴናተሩ ይህ ህግ እንዲወጣ ግፊት ማድረግ የጀመረው በሚኖርባት ክፍለ ግዛት፣ በዳቦ ጋጋሪነት የሚተዳደር ግለሰብ፣ በ1990ዎቹ በቦስኒያ የዘር ማጥፋት ወንጀል የተሳተፈ መሆኑ ከተጋለጠ በኋላ ሌሎችም ተመሳሳይ ወንጀል ለፈፀሙ ግለሰቦች፣ አሜሪካ መሸሸጊያ መሆን የለባትም በሚል ዕምነት ነው።
ቀልቤሳ አሜሪካ ውስጥ የሚያስጠይቀው ነገር ስለሌለ ኑሮውን ቀጥሏል። አዲስ ትዳርም መስርቷል። ኢትዮጵያ ከነበረችው ባለቤቱ ቢፋታም የሶስት ልጆች አባት ነበር። አሁን እንደገና የአንድ ሴት ልጅ አባት ሆኗል። ተምሮም ከደቭራይ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ ዲግሪውን ይዟል። ከዛም አልፎ ሶስት መኝታ ክፍል ያለው ቤት ገዝቶ ተመቻችቷል። ምን ያደርጋል ታዲያ--- የሴናተሩ ጥረት ተሳክቶ፣ በ2004 አዲሱ ሕግ ወጣ። ህጉ ከወጣ ከወራት በኋላ ጭቅጭቁ ይቀርልኛል በሚል እሳቤ ቀልቤሳ በፈቃዱ ዜግነቱን መለሰ። ከተፋራጆች አንዷ የነበረችው የህግ ባለሙያ ሂሩት አበበ ጅሬ፣ በሸገር ሬዲዮ ቀርባ በሰጠችው ቃለ ምልልስም ሆነ አንድሩ ራይስ ባቀረበው ዘገባ፤ እርምጃው ብልህነት የጎደለው ነበር ብለዋል። ዜግነቱን መመለሱ ጥፋቱን ማመን ነው ያስመሰለበት። የዜግነት ጉዳዮች መሥሪያ ቤት የቀልቤሳን የኋላ ታሪክ ያውቅ ስለነበር፣ አሁን ጉዳዩን ለመመልከት የሚከለክለው ነገር አልነበረም።
በ1997 ታህሳስ መጨረሻ፣ አንድ ቀን ማለዳ፣ የቀልቤሳ ቤት ተንኳኳ። ውጪ የሚጠብቁት የዜግነት ጉዳዮች መሥሪያ ቤት ፖሊሶች ነበሩ። ከዛን ቀን ጀምሮ ቤቱ እስር ቤት ሆኗል። አመት ከስድስት ወር ከሀገር የመባረር ሙግት ላይ ነበር። ባለ በሌለ አቅሙ ቢከራከርም፣ የቀረቡበት ማስረጃዎች የሚያፈናፍኑ አልነበሩም። በመጨረሻም ወደመጣበት እንዲመለስ ተፈርዶበት በጥቅምት 1999 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ተላልፎ ተሰጥቷል። በኢትዮጵያም የተፈረደበትን የዕድሜ ልክ እስራት እየፈፀመ ይገኛል። ቀልቤሳ አሜሪካን ውስጥ ከቆየባቸው 20 ዓመታት ውስጥ 17ቱ የወንጀል ደመና እንዳጠላበት ነው ያሳለፈው።
መቶ አለቃ እሸቱ አለሙ
እስካሁን በውጭ ሃገር ከነበሩ የቀይ ሽብር ተጠርጣሪዎች በወንጀሉ ተከሶ የተቀጣው ብቸኛ ሰው መቶ አለቃ እሸቱ አለሙ ነው። እንደ ሌሎቹ ሁሉ መጠለያ ያገኘበትን ሀገር ዜግነት ወስዷል። ለሠላሣ አመት ድምፁን አጥፍቶ የነበረው እሸቱ፤ በጎጃም ክፍለ ሀገር በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን በማስገደል የተከሰሰ ሲሆን “እርምጃ እንዲወሰድ” ከዚያም “እርምጃ መወሰዱን” የፃፈበት ደብዳቤ ሁሉ በማስረጃነት ቀርቦበታል።
“...ስማቸው ከዚህ ጋር ተያይዞ በተላከልዎት ዝርዝር የተገለጹት 80 (ሰማንያ) ፀረ-አብዮተኞች፣ ፀረ-አብዮት ድርጊታቸው በጣም ከፍተኛ በመሆኑ አብዮታዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ሆኖ አፈፃፀሙ እንዲገለፅ ያደርጉ ዘንድ አስታውቃለሁ። 8/12/70 ም/መ/አ እሸቱ ዓለሙ የክፍለሀገሩ ቋሚ የደርግ አባል”
የክፍለ ሀገሩ ወህኒ ቤቶች አስተዳዳሪ፤ ሰባ አንዱ ላይ “አብዮታዊ እርምጃ” መወሰዱን ከእነ ስም ዝርዝራቸው በደብዳቤ አስታውቋል።
የሆላንድ ፍርድ ቤቶች፣ በየትኛውም የዓለም ክፍል በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀልን የማየት ሥልጣን አላቸው። በዚህም የተነሳ እሸቱ የተከሰሰው መረጃን በማጭበርበር ሳይሆን በቀጥታ በቀይ ሽብር ላይ በነበረው ተሳትፎ ነው። ተፋራጆችን ዘሄግ በሚገኘው ፍርድ ቤት የተጋፈጠው መቶ አለቃ፤ ለተፈፀመው ግድያ ይቅርታ ጠይቋል። ነገር ግን በግሉ የፈፀመው ወንጀል ባለመኖሩ ጥፋተኛ አለመሆኑን አስረድቷል። “ለተጎጂዎችና በዛም በኩል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጉልበቴ ተንበርክኬ ይቅርታ እጠይቃለሁ።” ነገር ግን በ1970 ዓ.ም በጎጃም ለተፈፀመው ግርፋትና ግድያ ተጠያቂ አይደለሁም “በቦታው አልነበርኩም” ሲል ተከራክሯል።
የሕግ ባለሙያውና የካናዳ ነዋሪ የሆነው አቶ ወርቁ ደመና፣ በነሐሴ 1970 እሸቱ በጎጃም እስር ቤት ውስጥ በነበረ ቤተ ክርስቲያን በርካታ እስረኞች እንዲገደሉ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ሌሎቹ እስረኞች ደግሞ ሟቾችን በጅምላ እንዲቀብሩ ማዘዙን መስክሯል። “በእሸቱ ትዕዛዝ በግፍ ለተጨፈጨፉት ሁሉ ፍትህን የማስገኘት ሃላፊነት አለብኝ” ያለው ወርቁ፤ ምክትል መቶ አለቃው ሊገደሉ የነበሩት ሰዎች ስም ዝርዝር ላይ ምልክት እያደረገ ግድያውን ማስፈፀሙን መስክሯል። የጎጃም ክፍለ ሀገር የደርግ ተጠሪ፣ ሆላንድ ውስጥ የተከሰሰው በግርፋት፥ በግድያ፥ እንዲሁም ያለምንም ምክንያት ሰዎችን በማሰር ነው። ለፍርድ ከመቅረቡ በፊትም ሁለት አመት በእስር አሳልፎአል። እሸቱ በአራት መዝገቦች በቀረቡበት ክሶች “ጥፋተኛ አይደለሁም” ብሎ ተከራክሯል። አንድ መቶ ገፅ የሚደርሰው የክሱ መዝገብ እንደሚያስረዳው፤ ተከሳሹ ባብዛኛውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በነበሩ በ321 ሰዎች እስር ግርፋትና ሞት ተጠያቂ ነው። ከእነዚህ ውስጥ 75ቱ በአንድ ምሽት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደተገደሉ በክሱ ተጠቅሷል።
እንደ ቀልቤሳ ሁሉ እሸቱም ከሀገር የወጣው ደርግ ከመውደቁ በፊት ነው። ሌላው ቀልቤሳና እሸቱን የሚያመሳስላቸው ጉዳይ፣ ሁለቱም በተለያዩ ጊዜያት በወቅቱ የሶሻሊዝም አራማጅ ወደነበረችው ቡልጋሪያ መላካቸው ነው። እሸቱ ከቡልጋሪያ አልተመለሰም። ደርግ ሊወድቅ ሁለት ዓመታት ሲቀሩት፣ ጎመን በጤና ብሎ ወደ ሆላንድ ሾልኳል። በ1990 ደግሞ ዜግነት አግኝቷል። ኢትዮጵያ ውስጥ በሌለበት የሞት ቅጣት የተላለፈበት እሸቱ፤ሆላንድ ውስጥ እድሜ ልክ ተፈርዶበታል። በሆላንድ ሕግ ያልተለመደ ቢሆንም “እድሜ ይፍታህ ብቸኛው አማራጭ ነው” ብለዋል፤ የመሀል  ዳኛው።
ከአራቱም የከፋው የመቶ አለቃ እሸቱ ቅጣት ይመስላል። በሃገሪቱ ህግ መሠረት፤ እድሜ ልክ ማለት  እድሜ ልክ ነው። ወለም ዘለም የሌለው። ለንፅፅር ቢረዳ፤ በሴራሊዮን የእርስ በርስ ጦርነት በነበረው ተሳትፎ እዛው ሆላንድ ውስጥ በጦር ወንጀለኝነት የተከሰሰው የቀድሞው የላይቤሪያ መሪ ቻርለስ ቴይለር የተፈረደበት ሃምሳ አመት ነው። ነገሩ እሳት ካየው… ቢሆንም፣ በመርህ ደረጃ ቴይለር የእስር ጊዜውን ቢጨርስ መፈታት ይችላል።
የስጋት ጥላና ከለላ
ከቀይ ሽብር ጋር በተያያዘ  በውጪ ሀገር ተሸሽገው የሚኖሩ ግለሰቦች መያዛቸው የሚቀጥል ይመስላል፡፡ የቀይ ሽብር ተጎጂዎች ባሉበት ሁሉ ወንጀል ፈጻሚዎቹ በሰላም ይኖራሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ ተፈላጊዎቹ የአረጋዊነት ዕድሜ ላይ እየደረሱ ቢሆንም፣ አሁንም ያለፈው ታሪክ ጥላ እንዳጠላባቸው በስጋት ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ በልዩ አቃቤ ህግ የክስ መዝገብ፤ በሌለበት በእድሜ ልክ እስራት የተቀጣ ግለሰብ ካናዳ ውስጥ እንደሚኖር ተጠቁሟል፡፡ የቀይ ሽብር ሰለባዎችን አስመልክቶ መረጃ የሚያሰባስበውና ከፍትህ አካላት ጋር የሚሰራው “ያ ትውልድ” የተባለው ተቋም፤ ዴንቨር ውስጥ በጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማራ እንዲሁም ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ በመኪና ንግድ የሚተዳደር ግለሰብን ሁኔታ እየተከታተለ መሆኑን በአንድ ወቅት አስታውቆ ነበር። በፍሎሪዳ ግዛት ታምፓ ውስጥም እንዲሁ በቀይ ሽብር ወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ ጉዳይ ፍትህ አካላት ዘንድ ደርሷል።  
በሀገራቸው ውስጥ ወንጀል ፈፅመው ሌላ ቦታ ተሸሽገው ሲኖሩ የነበሩ በተለይም የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ፥ ሩዋንዳ፥ ላይቤሪያና ሌሎች ዜጎች፣ በተለያዩ አገራት መንግስታት ተይዘው ተላልፈው ተሰጥተዋል። በቅርቡ ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ የኡበር ታክሲ ነጂ የነበረው የቀድሞ ሶማሊያ መሪ ሲያድ ባሬ አንጋች ኮሎኔል ዩሱፍ አብዲ፣ በእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የጦር አበጋዝ ሆኖ በፈፀማቸው ተግባራት፣ በፍትሃ ብሔር ተከስሶ ግማሽ ሚሊየን ዶላር እንዲከፍል ተወስኖበታል። በሀገር የመቆየቱ ሁኔታ ያልተዘጋ መዝገብ ነው። ይኸው ግለሰብ ከካናዳ ከመባረሩ በፊት ሲቢሲ የተባለው የሀገሪቱ ቴሌቪዥን የምርመራ ዘገባ ሰርቶበት ነበር።
ከመገናኛ ዘዴዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ አለም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየጠበበች መጥታለች። በዚህ የተነሳ ሳይታወቁ መኖር ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ እየሆነ ነው። በሌሎች አገሮች ወንጀል ፈፅመው የተሸሸጉ ከ150 እስከ 1000 የሚደርሱ ሰዎች በአሜሪካ  እንደሚኖሩ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ይገምታል። በስጋት ጥላ መኖር ከእስር አይተናነስም። ወንጀልና ቅጣት!!


Read 1608 times