Saturday, 08 June 2019 00:00

መዓዛ ብሩ ገብረወልድ የህትመትና ሬዲዮ ጋዜጠኛ፣ የሚዲያ ባለቤት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“--የኢትዮጵያ ሴቶች የሚገባቸውን ያህል ዋጋ አልተሰጣቸውም ብዬ አምናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ሴቶች አካላዊ ውበት ላይ የማተኮር አዝማሚያ ይታያል፤ የኢትዮጵያ ሴቶች መለያ ግን አካላዊ ውበታቸው ብቻ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አስደናቂ ጥንካሬና ብርታታቸውም መለያቸው ነው፡፡--”

             በልጅነቴ ሬዲዮ ላይ እሰራለሁ የሚል ሀሳብ ሽው ብሎብኝም አያውቅም ነበር፡፡ ክፍል ውስጥ ከኋላ እንጂ ከፊት መሆንን የማልደፍር፤ በፅሑፍም ሆነ በትወና ችሎታዬ እርግጠኛ ያልሆንኩ ተማሪ ነበርኩ፡፡ በአጋጣሚ በሬዲዮ ድራማ ላይ አንዴ የመስራት ዕድል አገኘሁና የምወደውን ሙያ እንዳገኘሁ አወቅሁ፡፡ ለመስራት ወደምሻው ሙያ የሚያቀርበኝን ስራ ሳፈላልግ ግን ከአስር ዓመት በላይ ፈጀብኝ፡፡ በ1987 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮ 97.1 ኤፍኤም ላይ ጨዋታ ፕሮግራምን በጋራ የማዘጋጀት እድል አገኘሁ፡፡ በ1999 ዓ.ም ደግሞ ከባለቤቱ አበበ ባልቻ እና ከረዥም ጊዜ ጓደኛዬና የሥራ ባልደረባዬ ተፈሪ አለሙ ጋር ሸገር ኤፍኤምን አቋቋምን፡፡ የምወደውን ሙያ የመስራት እድል የከፈቱልኝ እነዚህ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡
የተወለድኩት በ1950 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ወላጆቼ የሐረር ሰዎች ሲሆኑ፤ እስከ 9 ዓመቴ ድረስ በምዕራብ ሐረርጌ በምትገኘው ትንሿ የሂርና ከተማ ነበር ያደግሁት፡፡ ሂርና በሚገርም ሁኔታ የተለያዩ ህዝቦችን በአንድ ላይ ያስተሳሰረች ከተማ ነበረች፡፡ ጎረቤቶቼ የመናውያን፣ ኦሮሞዎች፣ ሐረሪዎችና ሶማሌዎች ነበሩ፡፡ የእነዚህን ሁሉ ህዝቦች የበለፀገ የባህል መስተጋብር እያጣጣምኩ አደግሁ፡፡
ወላጆቹ ነጋዴዎች ነበሩ፡፡ አባቴ ቡናና ሌሎች ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የተዋጣለት ነጋዴ ሲሆን እናቴ ደግሞ የአነስተኛ ግሮሰሪ ባለቤት ነበረች:: ባለፀጋ ቤተሰብ ነበርን፡፡ አንብቦ የማይጠግበው አባቴ፤ ብዙ መጻሕፍትና ጋዜጦችን ወደ ቤት ይዞ ይመጣ ነበር፡፡ ጋዜጦችን እንዳነብ ከማበረታታትም ባሻገር የእጅ ጽሑፌ እንዲሻሻል ከጋዜጣው ላይ በእጄ እንድገለብጥ ያደርግ ነበር፡፡ ሁሌም በእኔ ላይ ትልቅ ተስፋ እንዳለው ይነግረኝና ያበረታታኝ ነበር፡፡ አባቴ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ቢሞትም፣ በራሴ ላይ እምነት ሳጣ እንኳን፣ እሱ በእኔ ላይ የነበረው እምነት ብርታት ይሰጠኛል፡፡
የ9 ዓመት ልጅ ሳለሁ ወላጆቼ አዲስ አበባ ባለው የቅድስት ማርያም አዳሪ ት/ቤት አስገቡኝ፡፡ ሴቶች ብቻ በሚማሩበት በዚህ የካቶሊክ አዳሪ ት/ቤት፤ መነኮሳቱ የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች ወለም ዘለም አያውቁም ነበር፡፡ በሥነ ሥርዓት ጉዳይ ላይ ፈፅሞ የሚደራደሩም አልነበሩም፡፡ ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ማታ ማታ ስራዬ ማልቀስ ብቻ ነበር:: ቀስ በቀስ ግን የአዲስ አበባ ኑሮን ተላመድኩት፤ የሳምንቱን የእረፍት ቀናት አክስቴ ቤት ማሳለፌም አረጋጋኝ፡፡ ንባብ ብቸኝነቴን የማመልጥበት መደበኛ ባልንጀራዬም ሆነ፡፡ ያኔ ልጃገረዶች ወጣ ወጣ ማለት አይፈቀድላቸውም ነበርና በየሳምንቱ መጨረሻ አክስቴ ቤት ስሄድ፣ ሁለትና ሶስት መጻሕፍትን እየያዝኩ ነበር፡፡ ለዚያን ዘመን ልጃገረዶች ያልተለመደ ቢሆንም፣ “አዲስ ዘመን” እና “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጦችንም ማንበብ እወድ ነበር፡፡
የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ በደርግ ወታደራዊ መንግስት የእድገት በሕብረት ዘመቻ፣ በሰሜን ትግራይ ወደምትገኘው ውቅሮ የተባለች የገጠር መንደር ተላኩ፡፡ ለእኔ ነፃ የወጣሁበት ጊዜ ይሄ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ትክክለኛ ኃላፊነት ምን እንደሚመስል የተገነዘብኩበት የመጀመሪያ አጋጣሚዬም ነበር፡፡ ገበሬዎችን የሕብረት ሥራ ማህበራት እንዲመሰርቱ ለማገዝ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር እልም ወዳለ ገጠር ነበር የተላኩት:: ከስድስት ወራት አገልግሎት በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ፡፡ ከዚያም ቅድስት ማሪያም ት/ቤት ተመልሼ በመግባት ያቋረጥኩትን ትምህርት የቀጠልኩ ሲሆን በ1970 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቀቅሁ፡፡ ይህ ጊዜ የደርግ መንግስት አስከፊውን የቀይ ሽብር ዘመቻ ያጧጧፈበት ወቅት ስለነበር፤ በተለይ ለተማሪዎች አስፈሪ ነበር:: አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብገባም የእለት የእለቷን ከመኖር ውጭ ለወደፊት ህይወቴ ምንም ዓይነት ህልም አልነበረኝም፡፡ የተመደብኩበትን የሥነ ልሳን ትምህርት ባልወደውም፣ አብረው ለሚሰጡት የሥነ ጽሑፍ ትምህርቶች ስል ገፋሁበት፡፡
የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለሁ በአጋጣሚ በሬዲዮ ድራማ ላይ የመተወን እድል አገኘሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- አንድ ቀን የትያትር ጥበባት የትምህርት ክፍል ተማሪዎች የነበሩት አስታጥቃቸው ይሁን እና ተፈሪ አለሙ፤ የተማሪዎች መኖሪያ ደባል ጓደኛዬን መንበረ ታደሰን ፍለጋ ወደ ክፍላችን ይመጣሉ፤ መንበረን የፈለጓት አስታጥቄ በፃፈው የሬዲዮ ድራማ ላይ ለመቀረፅ አብራቸው እንድትሄድ ነበር:: እሷ እንደሌለች ስነግራቸው በእሷ ምትክ ካልሰራሽ ብለው ወጥረው ያዙኝ፡፡ መጀመርያ ላይ አሻፈረኝ ብያቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ተስማምቼ፣ በያኔው የታደሰ ሙሉነህ ‹እሁድ ፕሮግራም› የተሰኘ ተወዳጅ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ድራማ ለመቅረፅ አብሬያቸው ሄድኩ፡፡ ያኔ ‹የእሁድ ፕሮግራም› በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከወታደራዊው አገዛዝ አብዮታዊ ፕሮፓጋንዳ የተለየ መዝናኛ የሚያቀርብ ብቸኛ ዝግጅት ነበር:: በቀረፃው ወቅት ታደሰ ሙሉነህ አገር ውስጥ አልነበረም:: እንደተመለሰ ግን “ለሬዲዮ ጥሩ ድምፅ አላችሁ” በሚል እንድናነጋግረው ጠየቀን፡፡ በሬዲዮ ላይ መስራት የጀመርኩት በዚህ መልኩ ነበር፡፡ ታደሰ ሙሉነህ ለሁላችንም የሙያ አባታችን ነበር፡፡ ምንም ልምድ ባልነበረን ጊዜ ተቀብሎ በማሰልጠንና በሬዲዮ እንድንሰራ እድሉን በመስጠት አግዞናል፡፡
ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቅሁኝ በኋላ መንግሥት፤ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መደበኝ፡፡ ያኔ የሚዲያ ዋና ስራው የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት ስለነበረ፣ ሚዲያ ውስጥ የመስራት ጉጉት አልነበረኝም:: መጀመርያ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የፕሬስ መምሪያ ኃላፊ፣ አብሬው እንድሰራ አልፈለገም ነበር:: ለነገሩ በእሱም አይፈረድም፤ ቀድሞ የነበረችው ሰራተኛ የወሊድ ፈቃድ እየወሰደች በቅጡ ስለማትሰራ እኔም እንደሷ እንዳልሆን ሰግቶ ነው:: ከስድስት ወራት የሥራ ጊዜ በኋላ ግን አቅሜንና ችሎታዬን በማረጋገጡ፣ የመርሃ ስፖርት ጋዜጣ፣ የስፖርት ዘጋቢ እንድሆን ተመደብኩ፡፡ እውነቱን ለመናገር የስፖርት ፍላጎት አልነበረኝም፤ ነገር ግን የክልል ውድድሮችን ለመዘገብ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ስለምጓዝ፣ በአጋጣሚው ያገኘሁትን ኢትዮጵያን ተዘዋውሮ የማየት እድል ወድጄው ነበር፡፡ በኋላ ላይ ወደ ባህል ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ ግንኙነት ክፍል ተዛወርኩ፡፡ ጎን ለጎን ግን በኢትዮጵያ ሬዲዮ እሁድ ፕሮግራም ላይ በግል መስራቴን ቀጠልኩ፡፡ በባህል ሚኒስቴር ሥራዬ እርካታ ባይኖረኝም፣ አስደሳች ተመክሮ መቅሰምና ለጋዜጠኝነት የሚቀርብ ሥራ ማፈላለጌን ገፋሁበት:: ከዚያም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተቀጥሬ የባንኩ ወርሃዊ መፅሄት ብሪቱ ዋና አዘጋጅ በመሆን፣ የፋይናንስ ዜናዎችንና አጭር ልብወለዶችን መፃፍ ጀመርኩ፡፡ በመቀጠልም አዲሱ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬስና መረጃ ዋና ዳይሬክተር እንድሆን ጠየቀኝ፡፡ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት፣ በዚህ መ/ቤት ውስጥ ያገለገልኩ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ለስራው እንደማልሆን ተገነዘብኩ:: በሬዲዮ ሥራዬ የሚያውቁኝ አንዳንድ ሰዎች ለቢሮክራሲያዊ ስራ እንደማልሆን ይነግሩኝ ነበር፤ እኔም ትክክል እንደሆኑ አውቅ ነበር፡፡ ለስምንት ዓመታት በግሌ በሬዲዮ ላይ ሰርቻለሁ፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም በሬዲዮ ድራማዎቼ፣ ጭውውቶቼና ጥናታዊ ስራዎቼ ታዋቂነትን አትርፌአለሁ፡፡  
ሦስተኛ ልጄን እርጉዝ ሳለሁ ነበር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የለቀቅሁት፡፡ ለጥቂት ጊዜያት ምን መስራት እንዳለብኝ እያሰላሰልኩ ቆየሁ፡፡ ለትንሽ ጊዜ በፕሬስ አደራጅነት የሰራሁ ሲሆን የሕዝብ ግንኙነት ስራዎችን የሚያከናውን ድርጅትም ከፍቼ ነበር፡፡ በዚህ መሃል ግን የኢትዮጵያ ሬዲዮ ሥራ አስኪያጅ የነበረው ፈቃዱ የምሩ፣ ባለቤቴን በኤፍ ኤም 97.1 የአየር ሰዓት ወስዶ፣ የራሱን ፕሮግራም እንዲያዘጋጅ ጠየቀው፡፡ ባለቤቴ አዘጋጅ ሆኖ፣ እኔና ተፈሪ አለሙ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የሚቀርበውን “ጨዋታ” የተሰኘ ፕሮግራም ማዘጋጀት ጀመርን፡፡ በኋላም ጌታቸው ማንጉዳይ፣ ብርሃኑ ድጋፌ፣ ግሩም ዘነበና ደረጀ ኃይሌ ተቀላቀሉን፡፡ “ጨዋታ” ለስምንት ዓመት ገደማ በአየር ላይ ውሏል፡፡ ፕሮግራሙ የመፅሄት ይዞታ የነበረው ሲሆን የታሪክ ትረካዎች፣ ድራማዎች፣ ቃለ ምልልሶችና ሌሎችንም ያካተተ ነበር፡፡
ከዚያም መንግስት ለሁለት የግል ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ እንደሚሰጥ ይፋ ሲያደርግ ባለቤቴ ማመልከት አለብን አለ፡፡ መጀመርያ ላይ ወደ ኋላ ብዬ ነበር፡፡ ሳልፈልግ ቀርቼ ሳይሆን ገንዘቡም ዝግጅቱም ሳይኖረን፣ ምኑን ከምኑ እናደርገዋለን የሚል ፍራቻ ይዞኝ ነው፡፡ ባለቤቴ ግን ይህን እድል በድጋሚ ላናገኘው እንችላለን ብሎ ተሟገተኝ፡፡ በመጨረሻም የእሱ ሃሳብ አሸነፈና ከተፈሪ አለሙ ጋር አመለከትን:: ረዥም ጊዜ ከፈጀ ሂደት በኋላም የሸገር ኤፍኤምን ፈቃድ በእጃችን አስገባን፡፡ ይኼኔ በፍርሃት ራድኩኝ:: “አሁን ምንድነው የምናደርገው?” ብዬ ግራ ገባኝ:: የምንመዘነው የ90 ዓመት እድሜ ካስቆጠረው ግዙፉ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ድርጅት ጋር ነው፡፡ ሸገር ከዜሮ መጀመር ነበረበት፡፡ ነገሩ በከፍታና በዝቅታ የተሞላ አጓጊ፣ አነቃቂና እልህ አስጨራሽ ነበር:: አንዳንዴ “ለምንድነው እዚህ ውስጥ የገባሁት?” እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር፡፡ የእኔ ጥንካሬ በሬዲዮ ፕሮግራሞችና ይዘቶች ዝግጅት ላይ እንጂ በቴክኒክ፣ በአስተዳደራዊ ወይም በንግድ ጉዳዮች ላይ አልነበረም፡፡ እንደመታደል ሆኖ ግን ከአሜሪካዊው አማካሪዬ ከዴኒስ እስራኤል ጋር ዕድል አገናኘኝ:: እሱ የሬዲዮ ጣቢያ ለማቋቋም አስፈላጊ የሆኑ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ሁሉ ቁጭ አድርጎ አማከረኝ፡፡ በንግዱ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከደጓሚዎች ጋር የመስራት መጠነኛ ልምድ ነበረን፡፡ ባለቤቴም በማስተዋወቅና የንግድ ትልሙን በመንደፍ አገዘን:: በመጨረሻም የግል ሬዲዮ ሥርጭት መስፋፋትን በሚደግፉ በርካታ ባለሙያዎች እገዛ፣ ሸገር 102.1 መስከረም 25 ቀን 1997 ዓ.ም አየር ላይ ዋለ፡፡
ሸገር በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሌሎች የሬዲዮ ጣቢያዎች ለየት የሚያደርገው የራሱ ልዩ ድምፅና ድባብ እንዲኖረው እንፈልግ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ውጭ ከነበሩ ሁለት አማራጮች አንደኛው ስለነበርን፣ መጀመርያ ላይ ይሄን ማድረግ ከባድ አልነበረም፡፡ ዛሬ ግን ሌሎች ሬዲዮ ጣቢያዎች የአቀራረብ ስልታችንን ያለ ፈቃድ ስለሚወስዱብን፣ ሁልጊዜም አዲስ ነገር መፍጠር ይጠበቅብናል:: በእርግጥ ይሄ ያኮራናል እንጂ አያስቆጨንም:: በየሳምንቱ ቅዳሜ የሚተላለፈውን ‹የጨዋታ እንግዳ› እና የእሁድ ጠዋቱን ‹ሸገር ካፌ› ፕሮግራሞች በመቅረፅ የማሳልፋቸው አራት ሰዓታት ለእኔ ተወዳጅና ተናፋቂዎች ናቸው፡፡
ወደፊት ሸገር ኤፍ.ኤም ወደ ሸገር ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ ቀስ በቀስም ወደ ሸገር ሲኒማ አድጎና ሰፍቶ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ሸገር ኤፍኤም ህብረተሰቡ ሰምቶት የማያውቀውንና የሚማርበትን፣ የሚያዝናናውንና የሚያስቀውን ነገር እንዲያቀርብ እንሻለን፡፡ ሸገር አድማጮቹ ሃሳባቸውን የሚያንሸራሽሩበት ትክክለኛ መድረክና ድምፅ አልባ ለሆኑትም ድምፃቸው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ሴት ሆኖ መኖር ተጨማሪ ፈተና አለው፡፡ በስፖርት ኮሚሽን ሳለሁ ሥራዬን የማከናወን ብቃት እንዳለኝ ለአለቃዬ ለማሳየት የበለጠ መትጋት ነበረብኝ፡፡ አሁንም ሳይቀር በሥራዬ ላይ አንዲትም ክፍተት እንዳይገኝብኝ በከፍተኛ ጥንቃቄ እዘጋጃለሁ፡፡ በቀላሉ ደግሞ ተስፋ አልቆርጥም፡፡ በመንገዴ ላይ መሰናክል ከገጠመኝ መውጪያ መንገድ የምፈልገው በመሰናክሉ ዙሪያ ነው፡፡ በምሰራው ሁሉ መቶ በመቶ እርግጠኝነት ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ አሁንም ወደ ቃለ መጠይቅ ስሄድ፣ ሁሉን ነገር እንደማላውቅ ስለማውቅ መረበሼ አይቀርም፡፡ ግን ደግሞ ሁሉን ነገር አለማወቃችን ነው ህይወትን የሚያጣፍጣት፡፡ ያልተገመቱ ነገሮች እንዲከሰቱም እድል ይሰጣል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች የሚገባቸውን ያህል ዋጋ አልተሰጣቸውም ብዬ አምናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ሴቶች አካላዊ ውበት ላይ የማተኮር አዝማሚያ ይታያል፤ የኢትዮጵያ ሴቶች መለያ ግን አካላዊ  ውበታቸው ብቻ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አስደናቂ ጥንካሬና ብርታታቸውም መለያቸው ነው፡፡ ራሳቸው የኢትዮጵያ ሴቶችም ሆኑ ቀሪው ዓለም ይሄን ጥንካሬያቸውን የሚገነዘቡላቸው ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በትምህርት ቤት ወይም በራሳቸው ንባብ አሊያም ደግሞ እርስ በእርስ በመማማር ሴቶች ራሳቸውን እንዲያስተምሩ እመክራለሁ፡፡ በባል፣ በልማድ፣ በሃይማኖት ወይም በአጠቃላይ በህብረተሰቡ የተቀመጡ መለኪያዎችን ወይም ገደቦችን መቀበል የለባቸውም፡፡ ራሳቸውም ቢሆኑ በራሳቸው ላይ ገደብ ከማስቀመጥ መታቀብ አለባቸው፡፡ ሁሉ ነገር ወዲያውኑ አይሳካምና የሚፈልጉት ነገር ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል መረዳት፤ እንዲሁም ውስጣቸውን ማድመጥ አለባቸው፡፡  
ምንጭ፡- (ተምሳሌት፤ ዕጹብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፤2007)   

Read 670 times