Saturday, 08 June 2019 00:00

… ከሆነ” — ቃላቸው እጥር ምጥን ያለው ስፓርታዎች

Written by  አስረስ አያሌው asrinholeo@gmail.com
Rate this item
(0 votes)


             ሳነብ ያገኘሁት the Laconic Spartan (ቃላቸው እጥር ምጥን ያለው ስፓርታዎች) የሚል ርዕስ ያለው መሳጭ ታሪክ በሰሞነኛው የአገራችን ሁኔታ ዙሪያ አንዳንድ ሀሳቦችን እንድጽፍ አነሳሳኝ። ታሪኩ Parables of Sivananda በሚል ርዕስ Sri Swami Sivananda የተሰኘ ጸሐፊ ባዘጋጀው መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል። ታሪኩን እነሆ፡-
* * *
በጥንቷ ግሪክ፤ ስፓርታ የተባለ ጎሣ ይኖር ነበር። የጎሣው አባላት በጣም ጀግኖች፣ በልማዳቸው ልከኞች እንዲሁም ስለ ራሳቸው ጉራ የማይነዙ ነበሩ። የስፓርታዎች ጀግንነት በአገራቸው እንደ አ ፈታሪክ ይነገራል። አንድ ስፓርታ አንድ ነገር አደርጋለሁ ካለ፣ ሳያደርገው ከሚቀር ሞትን እንደሚመርጥ ሁሉም ሰው ያውቅ ነበር።
ስፓርታዎች የሚኖሩበት ቦታ ላኮንያ ይባል ነበር። ስለዚህ ላኮናዊ ተብለውም ይጠሩ ነበር። መሪያቸው ካወጣላቸው ደንቦች አንዱ እንዲህ ይላል፡- “ንግግራችሁ አጭር፣ ግልጽና እውነተኛ ይሁን። የማይጨበጥ ነገር አትናገሩ፤ ስለማታወቁት ነገር በማውራት አላስፈላጊ ቃላት አትደርድሩ። አንድን ነገር ካላወቃችሁ አናውቅም በሉ። አንድ ነገር ለማድረግ ካሰባችሁ፣ እስክታደርጉት ድረስ ጉራ አትንዙ።”
* * *
መችም ዘንድሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ጉረኛው በዝቷል። ሁሉም ነጻ አውጪ፣ ሁሉም አክቲቪስት፣ ሁሉም ታሪክ ሠሪ፣ ሁሉም የአባቶቹን ታሪክ ደጋሚ ሆኗል። የሕዝብን ድምጽ ያለ ምርጫ ሰርቆ ራሱን ተወካይ የሚያደርገው ተበራክቷል። ለውጡን ያመጣሁት እኔ ነኝ የማይል የለም። ሁለት መንግሥት እንዳለም ተነግሮናል። በቃ  ያልቻሉትን በይቅርታ፣ አገር ቤት ከገቡ በኋላ ትጥቅ እንዲፈቱ ሲጠየቁ ማነው ፈቺ፣ ማነው አስፈቺ ሲባልም ሰምተናል። በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ፤ እስቲ ወንድ ትነኩና ተብሏል። ክልሎች እስካፍንጫቸው ታጥቀው ይዋጣልን ማለት ጀምረዋል። የወረዳ አስተዳደር በነዋሪ ፈርሷል። በመንግሥት የተፈቀደ የፓርቲ ስብሰባ፣ በጉልበተኞች እንዳይካሄድ ተደርጓል። ወጣቶች የክልል ባለስልጣናትን አዳራሽ ገብተው እስከ መደብደብ ደርሰዋል። መንግሥት በበኩሉ፤ ህግና ሥርዓት ማስከበር እንደተሳነው ገሀድ ወጥቶ ሳለ፣ “ኧረ እኔ ምኅዳሩን ላስፋ ብዬ እንጂ ማሰርና መግደል አላቃተኝም” እያለ ያልተጠየቀውን ይዘባርቃል።
የስፓርታዎች የጎሣ ህግ እኛ ዘንድ አይሠራም። ሁሉም የሚያውቀውንም የማያውቀውንም ይናገራል እንጂ ንግግሩ “አጭር፣ ግልጽና እውነተኛ” አይደለም፤ ቢያንስ ከሦስቱ አንዱ መስፈርት ይጎድለዋል። የሚጨበጥ ነገር መናገር አቅቶናል። ቃላት አላግባብ እየበዙ፣ አላግባባ ብለውናል። ዛቻና ማስፈራሪያ ተለምዷል። ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ግዴለም ተዉአቸው ይናገሩ፤ ብሶት አለባቸው በማለት ይሁንታ ሰጥተው ሲያበቁ መልሰው ደግሞ የፀረ ጥላቻ ንግግር አዋጅ እያረቀቁ ያደናግሩናል። እሳቸውም እንኳ የዛሬ ዓመት ከገቡት ቃል ሸርተት ማለት አብዝተዋል። ቁርጠኝነት አይታይባቸውም።
የብሔር አለቆች የሕዝባቸውን አንገብጋቢ የልማት ጥያቄ የመመለስ ወኔ የላቸውም። ወጣቱ ቤቱ ተቀምጦ ስለነገ ሕይወቱ በጽሞና እንዳያስብ ዘወትር በሰልፍ እያስጠመዱት ውሎው አደባባይ እንዲሆን ይፈልጋሉ። የጤናው ነገር አያሳስባቸውም፤ ከHIV ሊጠብቁት አይሞክሩም። የሚኖርበት መንደር የአቧራ መንገድ ለምን አስፓልት እንዳልሆነ እንዳይጠይቅ ከዘመናዊ መኪኖች ኋላ እየሮጠ “ለጀግኖች” አቀባበል በማድረግ የልማት ጥያቄውን እንዲረሳ ያደነዝዙታል።
እስቲ ወደ ላኮናውያን እንመለስ።
* * *
የላኮንያ ነዋሪዎች በጦር ሜዳ ጀግኖች የሆኑትን ያህል ለመሪያቸውም ታዛዦች ነበሩ። እንደውም አንድ ላኮናዊ ጥያቄ ሲጠየቅ የሚሰጠው መልስ እጥር ምጥን ያለ ከመሆኑ የተነሳ ዛሬም ድረስ አንድ ሀሳብ በጣም ካጠረ “laconic” ይባላል።
ይህን ነጥብ በምሳሌ ለማስረዳት አንድ ታሪክ መጥቀስ ይቻላል። የታላቁ እስክንድር አባት የሆነው ዳግማዊ ፊሊፕ በሰሜናዊ ግሪክ የምትገኘውን መቄዶንያ ይገዛ ነበር። ፊሊፕ መላዋን ግሪክ የመቆጣጠር ፍላጎት ነበረው። በመሆኑም በርካታ ክፍለ ጦሮችን ያቀፈ ሠራዊት አደራጅቶ አጎራባች መንግሥታትን ወረረ። በመቀጠል የላኮንያ ገዢነቱን እንዲቀበል ለስፓርታዎች መሪ ደብዳቤ ላከለት። አክሎም ስፓርታዎች የማይታዘዙ ከሆነ ሠራዊቱ እንደሚያጠፋቸው አስጠነቀቀው።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሥ ፊሊፕ መልስ ደረሰው። የስፓርታዎች መሪ የላከው ደብዳቤ ላይ የሰፈረው “ከሆነ” የሚለው ቃል ብቻ ነበር። ይህም ስፓርታዎች የፊሊፕን ሠራዊት እንደማይፈሩትና ሠራዊቱ ወደ ላኮንያ ገብቶ ጥቃት መሰንዘር የሚችለው ጀግኖቹ ላኮናውያን የሚፈቅዱለት “ከሆነ” ብቻ መሆኑን የሚገልጽ ነው።
* * *
ዛሬ አገራችንን የሚያምሷት እኩያን ብሔርተኞችም አፍራሽ ተልዕኳቸውን መፈጸም የሚችሉት እኛ የምንፈቅድላቸው “ከሆነ” ብቻ መሆኑን ልንነግራቸው ይገባል። በራሳቸው ምንም የማድረግ አቅም የላቸውም። አዎ፣ በኢትዮጵያ ምድር የንጹሐን ደም የሚፈስሰው ዘረኞች ገጀራ ስለውና ጠብመንጃ አቀባብለው ሲሰጡን ተቀብለን በወገናችን ላይ የምንዘምት “ከሆነ” ብቻ ነው። በዚህ የሉላዊነት ዘመን ጎረቤታችን ከተወለደበት ቀዬ መጤ ተብሎ የሚባረረውስ አፈናቃዮችን አበጃችሁ የምንል አልያም በቸልታ የምናልፍ “ከሆነ” እንጂ ሌላ በምን ምክንያት ሊሆን ይችላል? ምስኪኑ ዜጋ ለዓመታት ጠብቆ ያገኘውን ቤት እንዳይረከብ በመከልከል ሰቆቃውን የምናበዛውም የግፈኞች ተባባሪ የምንሆን “ከሆነ” ብቻ ነው።
የገዛ ወንድማችንን ለኑሮ አስፈላጊ ነገሮች እንዳይደርሱት በማድረግ የምንቀጣው፣ ክፉዎች ከዚህ ወደዚያ ምንም እንዳያልፍ መንገድ ዝጉ ሲሉን የታዘዝን “ከሆነ” ብቻ ነው። እንደ አበባ እርሻ የተዋበው ጉራማይሌነታችን የሚደበዝዘውስ ጠባቦች ከብሔራችሁ ውጭ አትጋቡ፣ አትዋለዱ ብለው ሲሰብኩን የምንሰማቸው “ከሆነ” አይደለምን? በማኅበራዊ ድረ ገጾች አክራሪዎች የሚነዙትን የጥላቻና የሐሰት ወሬ የምናምነውስ ማመዛዘን አቁመን እንደ ደራሽ የምንፈስስ፣ እንደ አውሎ ንፋስ የምንነፍስ “ከሆነ” ብቻም አይደል? ሌላው ቀርቶ ገንጣዮች እንደሚፎክሩት የኢትዮጵያ ህልውና እንኳ የሚያከትመው በሕዝበ ውሳኔ መገንጠልን የምንመርጥ “ከሆነ” ብቻ ነው። በእርግጥም ጨካኝ ብሔርተኞች ያለእኛ ትብብር የውኃ ላይ ኩበት ናቸው።
እንግዲህ ከስፓርታዎች ታሪክ ተነስቼ ስለአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ይህን ያህል ካልኩ ይበቃኛል። ሀሳቤን ለመቋጨት የታሪኩን የመደምደሚያ ሁለት አንቀጾች እንዳለ ከማስቀመጥ በቀር የምጨምረው የለኝም።
* * *
ዓለም በጉረኞች የተሞላች ነች። የአሉባልተኛ ሰዎች እጥረት የለባትም። የተግባር ሰዎች መቼም ቢሆን ስለሥራቸው አይጎርሩም።
የሚያወሩት ጥቂት፣ የሚሠሩት ግን ብዙ ነው። ቃል አይገቡም ወይም መሃላ አይፈጽሙም፤ ሆኖም ከእነሱ የሚጠበቀውን ያደርጋሉ።
የሀሰት ወሬ አያሠራጩም፤ የፈጠራ እውነትም አይፈበርኩም። አሉባልተኝነት አይነካካቸውም። ኩራት ምክንያታዊነታቸውን ፈጽሞ አይጋርደውም። ብዙ ባለማውራትና ለሐሜት ጆሮ ባለመስጠት ውዥንብር እንዳይፈጠር ያደርጋሉ።
በመሆኑም የሚወስኑት ውሳኔ ቀጥተኛና የማያወላውል ነው። የጥንቶቹ ላኮናውያን ሁሉም ሰው ሊከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትተው አልፈዋል።


Read 527 times