Monday, 10 June 2019 12:38

ስለ ግብረ ሰዶም ህግ እና ሃይማኖቶች ምን ይላሉ?

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)


              መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው “ቶቶ” የተባለ የግብረሰዶማውያን አስጐብኚ ድርጅት ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ከተሰማ ወዲህ ከኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ተቃውሞ ቁጣ ተስተጋብቷል፡፡ ለመሆኑ ስለ ግብረሰዶም ሃይማኖቱን ምን ይላል? ህጉስ? አለፍ አለፍ እያልን እንቃኛቸዋለን፡፡
ግብረ ሰዶም ምንድን ነው?
ግብረሰዶም የሚለው መጠሪያ የተገኘው ከመጽሃፍ ቅዱስ ነው፡፡ የሶዶም ስራ እንደማለት ነው:: ሰዶምና ገሞራ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 19 ላይ የተጠቀሱ የጥንት መንደሮች ናቸው:: በዚያም ጊዜ በእነዚህ መንደሮች ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴትጋር ይዳራ ነበር፡፡
እግዚአብሔርም ይህን አይቶ ከተማዋን በእሳት አጠፋት፡፡ የሎጥ ሚስትም ከተማዋ ስትቃጠል ዞራ በማየቷ እንደ ሐውልት ደርቃ ቀረች፡፡
ግብረ ሠዶም በመጽሐፍ ቅዱስ
ኦሪት ዘፍጥረት 1፥27 -24 እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ… ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠራቸው፤ እግዚብሔርም ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፡- ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት ግዙአትም፡፡
1 ቆርቶስ 6፥9-10
አመፀኞች ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ወንድ ሆነው ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ የእግዚያብሔርን መንግስት እንዳይወርሱ አታውቁምን፣ /ወደ ሮሜ ሰዎች 1፥26-30/ ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሠጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባህሪያቸው የሚገባውን ሥራ ለባህሪያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባህሪያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስህተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ፡፡
እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚብሔርን ህግ እያወሩ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም ይላል፤ መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ክፍሎቹ ስለ ግብረ ሰዶም አፀያፊ ተግባር ሲጠቅስ፡፡
ግብረ ሰዶም በቅዱስ ቁርአን
በቅዱስ ቁርአን ላይ በቅዱስ ቁርአን በሱረቱ አል - ምዕራፍ በአንቀጽ ከ80-84 እንዲሁም በሱረቱ አል - ሒጅር አንቀጽ 72 -76 እንዲህ ብሎ ተመልክቶ ይገኛል፤ ሎጥንም ለህዝቦች ባለ ጊዜ አስታውሶ አስቀያሚ ስራ ትሠራላችሁን? በኤርሳ ከአለማት አንድም አልቀደማችሁም፤ እናንተ ከሴቶች ሌላ ወንዶችን በመከጀል በእርግጥ ትመጡባችኋላችሁ፤ በእውነትም እናንተ ወሰንን አላፊዎች ህዝቦች ናችሁ::
የህዝቦችም መልስ ሎጥንና ተከታዮችም ከከተማችሁ አውጧቸው፤ እነሱ የሚጠራጠሩ ሰዎች ናቸው ማለት እንጂ ሌላ አልነበረም፡፡ እሱንና ቤተሰቦቹንም አዳንናቸው፤ አድነናቸው ሚስቱ ብቻ ስትቀር እሷ ለጥፋት ከቀሩት ሆነች፡፡ በእነሱም ላይ የእሳት ዝናብን አዘነብንባቸው፤ የሀጢያተኞችም መጨረሻ እንዴት እንደሆነ ተመልከቱ ይላል፡፡
የአላህ መልዕክተኛ ሙሐመድ ሰዐወ ግብረ ሰዶምን አስመልክቶ ሲናገሩ እንደዚህ ይላሉ፡-
“ግብረ ሰዶም የሚፈጽም ሰው ከተገኘ በፈፀመውም በተፈፀመበትም ሰው ላይ የሞት ፍርድ ፍረዱበት” ቲርሚዚ ፥ 1456 አቡ ዳውድ 4462 አብን ማጃህ 256 “ግብረ ሰዶም ፈፃሚዎችን አላህ ረግሟቸዋል” አህመድ 2915 በማለት ያስቀምጣል፡፡
የኢትዮጵያ የወንጀል ህግና የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ምን ይላል?
ለህዝብ ሞራል ተቃራኒ ማለት አንዱ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ነው፡፡ በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ጋብቻ ከሚከለክልባቸው ነገሮች አንዱ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ሲሆን ይህም በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ በወንጀል የሚያስቀጣ መሆኑ ተደንግጓል፡፡
በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 629 ማንም ሰው ከእርሱ ጋር አንድ ዓይነት ፆታ ካለው ከሌላ ሰው ጋር ግብረሰዶም ወይም ለንፅህና ክብር ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነውን ሌላ ድርጊት የፈፀመ እንደሆነ በቀላል እስራት ይቀጣል ይላል፡፡
አንቀጽ 630 ላይ ወንጀሉን የሚያከብዱ ነገሮችን ሲዘረዝር ጥፋተኛው የሌላኛው የሌላውን ሰው የገንዘብ ችግር ወይም የህሊና ሀዘን ወይም የዚህ ሰው አዳሪ ሞግዚት፣ ጠባቂ፣ አስተማሪ፣ አሠሪ ወይም ቀጣሪ በመሆኑ ያገኘውን ኃላፊነት ሥልጣን ወይም ችሎታ፣ ወይም በመካከላቸው ያለውን ይህን የመሰለ ሌላ ግንኙነት ያለአግባብ በመጠቀም ድርጊት የፈፀመበት ወይም ይህን ሰው ከእርሱ ጋር የዚህ አይነቱን ድርጊት እንዲፈጽም ያደረገ እንደሆነ ወይም በዚህ ህግ አንቀጽ 82 በተደነገገው መሠረት ድርጊቱን ዋናው አድርጐ የያዘ እንደሆነ በአንድ አመት ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥም ደግሞ ከአስር አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡
የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ከአንቀፅ 629 -630 ድረስ በየደረጃው የግብረ ሰዶም ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦች በወንጀል የሚያስቀጣ መሆኑን ዘርዝሮ አስቀምጧል፡፡      

Read 7703 times