Monday, 10 June 2019 13:19

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)


             “--አለማመን በራሱ “እምነት” ነው ብለው የሚያምኑ ብዙ ናቸው፡፡ ለሃይማኖታዊ ዕምነት የማይጨነቅ አንድ ሰው፤ ስለ መጀመሪያው ምክንያት (First cause) ላለማሰብ ቢሞክር ወይም ሳይንሳዊውን መንገድ (የቢግ - ባንግ ጽንሰ ሃሳብን ጨምሮ) መከተል ቢመርጥ አያስገርምም፡፡--”
          
              ለምን “ኢድ ሙባረክ!” አላልከኝም? እንዳትል፡፡ አትቸኩል፡፡ አንዳንዴ‘ኮ ይከፋሃል፡፡ ሰው አይደለህ?... ሲከፋህ ደግሞ ትራገማለህ፡፡ በደለኝ የምትለውን ሰው፤ ጐረቤትህን፣ ጓደኛህን፣ መንግስትን፣ ጊዜን አምላክህንም ሊሆን ይችላል፡፡
ሃዲስን እየጠቀሰ፣ አብሮ አደጌ ዳውድ ሲያጫውተኝ፤ አንድ ሰው ሆን ብሎ አስቦበትም ሆነ በስሜት ተገፋፍቶ በሚራገምበት ጊዜ፣ እርግማኑ ከአፉ እንዳፈተለከ ቀጥታ ወደ ላይ ነው የሚያሻቅበው፡፡ አየር ላይ ሆኖ ቁልቁል እየተመለከተ ማረፊያውን ይፈልጋል፡፡ ትክክለኛውን ቦታ ካላገኘ ወደ ተራጋሚው ይመለሳል ብሎኝ ነበር --- ቡመሪንግ ኢፌክት እንደሚሉት፡፡
ወዳጄ፡- እርግማን የአላህ ፍትህ እንጂ የሰው አይደለም፡፡ ተራጋሚ በተረጋሚ በኩል ያለውን ዕውነት ሳይረዳ (the other side of the Story) ለመፍረድ ከተቻኮለ ፍትህ ሚዛኗን ትስታለች፡፡ ሰው ራሱን ብቻ ማዕከል ካደረገ (Self Centered)  ስሜት ርቆ  ልብ እንዲገዛ፣ አጓጉል ፍላጐቶቹንና ቀበዝባዛ ምኞቱን እንዲገራና ቆም ብሎ ስለ ሌሎች ግፍዓን በማሰብ፣ ወደ እውነተኛው መንገድ ለመመለስ ውስጡን የሚያፀዳበት ዕድል እንዲያገኝ ይመስለኛል “ቅዱሱ” የሮመዳን ወቅት “ጀባ!” የተባለለት፡፡
“እውነቱን ከሚናገሩት መሃል ከሆንክ ማስረጃህን አቅርብ (Bring your proof, if you are among those who speak truthfully)” ይልሃል፤ቅዱሱ መጽሐፍ (2፡111)
ኢድ ሙባረክ !!
ወዳጄ፡- አለማመን በራሱ “እምነት” ነው ብለው የሚያምኑ ብዙ ናቸው፡፡ ለሃይማኖታዊ ዕምነት የማይጨነቅ (atheist) ሰው፤ ስለ መጀመሪያው ምክንያት (First cause) ላለማሰብ ቢሞክር ወይም ሳይንሳዊውን መንገድ (የቢግ - ባንግ ጽንሰ ሃሳብን ጨምሮ) መከተል ቢመርጥ አያስገርምም፡፡ ለሁሉም ነገር መጀመሪያ አለው፡፡ ነገር ግን ሳይንስ እንደሚያከራከርበት ምክንያት ሳይሆን የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ እግዜር ብቻ ነው ብሎ ለሚያምን ቲዎሎጂስት፤ሃሳቡን ለማስረዳት አስቸጋሪ ሳይሆን አልቀረም፡፡ ምክንያቱም ከእምነት ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች በሎጂክ የተደገፈ፣ አሳማኝ መልስ መስጠት ፈተና ይሆናልና!!
አባት ከልጁ ጋር ሲወያይ፡-
“ሰው ከየት መጣ?”  ይለዋል፤ልጅ
“ከአዳምና ከሄዋን”
“አዳምና ሔዋን ከየት መጡ?”
“እግዜር ሰራቸው”
“እግዜርን ማን ሰራው?”
“እንደዚህ አይጠየቅም፤እግዜር ደስ ያለውን ማድረግ ይችላል፡፡”
“ጥፋት ቢያጠፋስ?”
“እንደ ጥፋት አይቆጠርም”
“ለምን?”
“ሰው አይደለማ፤ የኛና የሱ አስተሳሰብ ይለያያል”
“አሁን እኔ አስባለሁ?”
“አንተማ ህፃን ነህ፤ አድገህ “ሰው” ስትሆን ነው ማሰብ የምትጀምረው፡፡ ክፉና ደጉን ስትለይ” በማለት መለሰ፤ አባት አለማወቁን እየሸሸ፡፡
 ከወራት በኋላ አንድ ምሽት በመኖሪያቸው ሳሎን፣ ልጁ ከቺሚኒው አጠገብ እሳት እየሞቀ ሲጫወት፣ አባቱ ከስራው ተመለሰ፡፡ ልጁን በፍቅር እየሳመ፤ “ነገ ት/ቤት ትገባለህ” ብሎት ወደ መፀዳጃ ቤት ተጣደፈ፡፡ ልጁ እንደለመደው ቸኮሌት ምናምን ያመጣለት መስሎት፣ ያባቱን ቦርሳ ሲከፍት ያገኘው፤ አባቱ ሰዓት በማለፉ ምክንያት ከሚሰራበት ቦታ ይዞ የመጣው የዕለቱ የስቴዲየም ገቢና ለልጁ ት/ቤት የተበደረው፣ በታሳቢ የሚከፈል፣ የአንድ ዓመት ደሞዝ ነበር፡፡ ህፃኑ እነዚህን የብር ኖቶች እያወጣ ወደ ቺሚኒው እየወረወረ፣ በደስታ ሲፈነድቅ አባትየው ይደርስበታል፡፡ ያየውን ማመን ከበደው፡፡ ጉልበቱ ተሸበረከ፡፡ ላቡ ተንጠባጠበ፡፡
“ምነው ቤቢ? ምነው ምነው” በማለት ጮኸ፤ ራሱን በሁለት እጁ ይዞ፡፡
ቤቢ በአባቱ መደናገጥ ግራ እየተጋባ፡-“እ…እ”  እያለ ሲንተባተብ፤ አባቱ ስሜቱን መቆጣጠር ባለመቻሉ፣ ህፃኑን በጥፊ ደረገመው፡፡ ወዲያው፤ ከህፃኑ ጆሮ ደም ቡልቅ ብሎ እየፈሰሰ፣ ወለሉ ላይ ተዘረረ፡፡ ያለ እናት ባሳደገው ልጁ ላይ ያደረሰውን ጉዳት ሲያይ፣ አባት ኡኡታውን አቀለጠ፡፡
ሆስፒታል ደርሰው አስፈላጊው ህክምና ተደርጐ፣ ህፃኑ ነፍስ ሲዘራ፣ አባትየው እንባውን እየረጨ፤
“ይቅርታ ቤቢ! ሁለተኛ አይለምደኝም፤ ጥፋት ስለሰራህ ተበሳጭቼ ነው” እያለ ሲያባብለው፣ቤቢ ከዋክብት ዓይኖቹን እያንከባለለ፣ በኮልታፋው አንደበቱ አባቱን የጠየቀው በአራት ቃላት ነበር:: ምስኪን አባት፤ የልጁን ጥያቄ ሲሰማ፣ እራሱ በተናገረው ነገር፣ ህፃን ልጁን አጥቶት እንደነበር በማሰብ በእጅጉ አዘነ፡፡ ቤቢ፤ አባቱን ምን ብሎ ይሆን የጠየቀው?
***
የእስልምና እምነት ምሰሶዎች የሚባሉ አምስት ህግጋት አሉ፡፡ እነሱም፡- ከአላህ በስተቀር ማንም የለም፣ ሙስሊም በቀን አምስት ጊዜ ፊቱን ወደ መካ አዙሮ መስገድ ይኖርበታል፣ ማንኛውም ሙስሊም ከገቢው ላይ ቀንሶ ለድሆች መመጽወት አለበት (Zakah)፣ ቅዱሱን የረመዳን ወር መፆም (Sawm) እና የሚችል ከሆነ በህይወቱ አንድ ጊዜም ቢሆን መካን መሳለም (Pilgrimage) ይኖርበታል የሚሉ ናቸው… በአጭሩ፡፡
እነዚህን ምሰሶዎች አቅፈው የያዙ አምስት ማዕዘናት ወይም ምሰሶዎቹ የቆሙባቸው አምስት መሰረቶች ደግሞ አሉ፡፡ የመጀመሪያው መሰረት፣ በአንድ አምላክ ማመን የሚለው (Surah 23፡16,117) የመጀመሪያው ምሰሶ የቆመበት ሲሆን ሁለተኛው የመላዕክቶችን መኖር መቀበል ነው (Surah 2፡177) ሶስተኛው አዳምን ጨምሮ አብርሃም፣ ሙሴ፣ እየሱስና የመጨረሻው ነቢይ (the seal of the prophets) ለሚባሉት ለመሐመድ ተገቢውን አክብሮትና ዕውቅና መስጠት ሲሆን አራተኛው በመጨረሻ ጊዜ የፍርድ ቀን እንደሚኖር ማወቅና ሁላችንም እንደየ ስራችን ተፈርዶብን ገነት ወይ ገሃነም እንደምንገባ (Surah 15:35:36) የሚያመለክት ነው:: ከላይ የተጠቀሰውን እንደየ ስራችን የሚለውን ሃረግ ይዘን በተለያዩ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ አወዛጋቢ ትርጉም በመፍጠር አለመሰጣጣትን ወዳስከተለው የመጨረሻው ማዕዘን ስንሄድ፡-
“የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ፣ ማወቅም ሆነ አለማወቅ አላህ ብቻ ነው፡፡ ያለ እሱ ፈቃድ የሚሆን አንዳች ነገር የለም” ይላል (Surah 9:51)፡፡ እዚህ አንቀጽ ላይ ነው ተከራካሪ ወገኖች ጥያቄ የሚያነሱት፡፡ ሁሉም ነገር በሱ ፈቃድ የሚሆን ከሆነ፣ ሰው ለሚሠራው ስራ ኃላፊነቱን መውሰድ አይችልም፤ የጽድቅና የኩነኔ ነገርም “ወሬ” ሆኖ እንዲቀር ያደርገዋል፡፡ ሰው፤ እንደሱ “ሰው” የሆነውን ወንድሙን እየገደለ፣ እየዋሸ፣ ፍርድ እያጓደለ፤ “ያለ አላህ ፈቃድ የሚሆን ምንም ነገር የለም” ማለት፣አላህን እንደ ሰው ኢ-ፍትሃዊ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡ አንተስ፤ ምን ትላለህ ወዳጄ?
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፤ ህፃኑ ቤቢ አባቱን፡- “ባባ ሰው ሆንኩ‘ንዴ?” ብሎ ነበር የጠየቀው፡፡
 በተናገሩ “ይፈሩ” አያሰኝም?
ሠላም!!

Read 379 times