Saturday, 08 June 2019 00:00

የእጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ሐሳብ ላይ የቀረበ ሒሳዊ አስተያየት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(3 votes)

“ሥልጣኔ ማለት አንድ ትልቅ ሕብር (Compositum) ያለው ነገር ነው፤ ብዙ ተናባሪዎች ወይም ዋጋዎች (Values) አሉት፡፡ እነዚህም ዋጋዎች አምስት ሲሆኑ እነሱም፡- ቅድስና፣ ደግነት፣ እውነት፣ ውበትና ጠቃሚነት ናቸው፡፡ “
                
               በክፍል-1 ጽሁፌ፣ ኢትዮጵያን ለማዘመን ከተነሱት ትውልዶች ውስጥ እጓለ ገብረ ዮሐንስ ሁለተኛው ትውልድ ላይ እንደሚገኝ፤ እንዲሁም፣ ሀገራዊውንና የውጭውን እሴት ያጣመረውን የዘመናዊነት እሳቤውንም ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› በሚል ስያሜ ፍልስፍናዊ ማብራሪያ እንደሰጠው ተመልክተናል፡፡ በዛሬው ጽሁፌ ደግሞ፣ እጓለ የአውሮፓንና የኢትዮጵያን ሥልጣኔ የተነተነበትን ሐሳብ እንመለከታለን፡፡
እጓለ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ሲል ጥንታዊ የኢትዮጵያን ሥልጣኔ (እጓለ ‹‹ያሬዳዊ ሥልጣኔ›› ይለዋል) እና የአውሮፓን ሥልጣኔ ጥምረት አስፈላጊነት ለመግለፅ የተጠቀመበት ቃል ነው:: እጓለ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› የሚለውን ፍልስፍናዊ ፕሮጀክት ከማስተዋወቁ በፊት ስለ ተጣማሪዎቹ ሥልጣኔዎች (ያሬዳዊውና አውሮፓዊው ሥልጣኔ) አንዳንድ ባህሪያትን ይዘረዝራል፡፡ እጓለ ወደዚህ ዝርዝር የሚገባው አጠቃላይ የሰው ልጅ ህይወት ሁለት መንገዶች እንዳሉት በመጥቀስ ነው:: እነዚህም መንገዶች የህሊና (የአመክንዮ) እና የመንፈስ (የእምነት) ናቸው፡፡ የሰው ልጅ በህሊናው መሪነት አሊያም በመንፈስ ጎዳና በመሄድ ታላላቅ ሥልጣኔዎችን ሊፈጥር ይችላል፡፡
እጓለ፣ በህሊና (በአመክንዮ) መንገድ ሄደው ታላላቅ ሥልጣኔዎችን ከፈጠሩ ህዝቦች ውስጥ የጥንት ግሪካውያንንና አውሮፓውያንን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል፡፡ በአውሮፓ ሥልጣኔ ውስጥ ማዕከላዊውን ሥፍራ የሚይዘው ‹‹ሰው›› ነው:: በዚህም የተነሳ ሥልጣኔያቸው ‹‹ሰዋዊ (Anthropocentric) ሥልጣኔ›› ተብሎ ይጠራል (ገፅ 64)፡፡
በሌላ በኩል፣ የመንፈስን (የእምነትን) ጎዳና ተከትሎ ከበቀሉ ሃይማኖታዊ ሥልጣኔዎች ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ (ያሬዳዊ) ሥልጣኔ ነው፡፡ በዚህ መንፈሳዊ (Theocentric) ሥልጣኔ ውስጥ ማዕከላዊውን ስፍራ የሚይዘው መለኮት ነው (ገፅ 64)፡፡
እጓለ፣ የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ለምን ‹‹ያሬዳዊ ሥልጣኔ›› ብሎ እንደጠራው ሲያስረዳ እንዲህ ይላል::
ስለ አንድ ሥልጣኔ ለማውራት በሥልጣኔው ውስጥ ስላሉት ስለ እያንዳንዱ ሊቃውንት መናገር ስለማይቻል፣ አብነት፣ አርዓያነትና ምሳሌነት ያለውን አንዱን ትልቁን ሊቅ መርጦ ስለ እሱ መናገር ይሻላል፡፡ በዚህ ረገድ፣ ቅዱስ ያሬድ በዘመናት መካከል ለነበሩት ሁሉ የሀገራችን ሊቃውንት እንደራሴነት ያለው ትልቅ መንፈስ ነው፡፡ ያሬድን ለኢትዮጵያ መንፈስ እንደራሴ ብለን ስንጠራው ለሀገሩ ሥልጣኔ አንድ ጠባይ መስጠታችን ነው፤ ይሄም ሃይማኖታዊነት ነው (ገፅ 62-63)፡፡
እጓለ፣ ስለ ሁለቱ ሥልጣኔዎች መሰረታዊ ባህሪ በዚህ መልኩ ካስረዳ በኋላ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ብሎ የጠራውን ፅንሰ ሐሳብ ወደ ማስተዋወቅ ይገባል፡፡ ይሄንንም ሐሳብ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› ላይ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› በሚለው ምዕራፍ ውስጥ ከገፅ 75-83 ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡
በዚህ ምዕራፍ ውስጥ እጓለ ሦስት ርዕሰ ጉዳዮችን ያነሳል፡-
የመጀመሪያው፤ የባህል ሽግግር ወቅት ላይ ስለሚያጋጥም የመንፈስ ችግር ሲሆን (ከክ.ል.በ. በ6ኛው ክ/ዘ አቴናውያን እና በ16ኛው ክ/ዘ ደግሞ አውሮፓውያን ያጋጠማቸውን ተሞክሮ በመጥቀስ)፣
2ኛው ደግሞ፤ 20ኛው ክ/ዘ አጋማሽ ላይ ኢትዮጵያም የአውሮፓውያኑ ዓይነት የመንፈስ ችግር እንዳጋጠማትና የመውጫ መንገዱም ‹‹በተዋህዶ መክበር›› እንደሆነ የጠቀሰበት ነው፡፡
3ኛው፤ ስለ ትምህርት ምንነት ነው፡፡
ሆኖም ግን፣ እጓለ ፍልስፍናዊ ፕሮጀክቱን በተነተነበት በዚህ ምዕራፍ ላይ ለአንድ ወሳኝ ጥያቄ መልስ ሳይሰጥ ሄዷል፡፡ ይሄም ጥያቄ፤ ‹‹ያሬዳዊውን ሥልጣኔ ከምዕራባዊው ሥልጣኔ ጋር ‹‹ማዋኻሃድ›› ያስፈለገው ለምንድን ነው?›› የሚል ነው፡፡ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ምን ጎድሎት ነው እጓለ የአውሮፓን እገዛ አስፈላጊ አድርጎ ያመጣው?
በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ የእጓለን መልስ የምናገኘው ‹‹ያሬድ ወይም ስለ ኢትዮጵያ ሥልጣኔ-I እና II›› በሚሉት ሌሎች ሁለት ምዕራፎች ውስጥ ነው፤ ከገፅ 59-74፡፡
እጓለ ‹‹ያሬድ ወይም ስለ ኢትዮጵያ ሥልጣኔ-I›› በሚለው ምዕራፍ ውስጥ (ገፅ 59-66) ያሬዳዊውን ሥልጣኔ ከአውሮፓዊው ሥልጣኔ ጋር ከማነፃፀሩ በፊት አጠቃላይ ‹‹ሥልጣኔ›› ስለሚባለው ነገር የሚከተለውን ትርጉም ይሰጣል፡-
ሥልጣኔ ማለት አንድ ትልቅ ሕብር (Compositum) ያለው ነገር ነው፤ ብዙ ተናባሪዎች ወይም ዋጋዎች (Values) አሉት፡፡ እነዚህም ዋጋዎች አምስት ሲሆኑ እነሱም፡- ቅድስና፣ ደግነት፣ እውነት፣ ውበትና ጠቃሚነት ናቸው፡፡
ቅድስና የሃይማኖታዊ ሥልጣኔ መሪ አኃዝ ነው፤
ደግነት የሥነ ምግባር ወይም የሞራል ሥልጣኔ መሪ አኃዝ ነው፤
እውነት የዕውቀት ሥልጣኔ መሪ አኃዝ ነው፤
ውበት የሥነ ጥበብ ወይም የአርት ሥልጣኔ መሪ አኃዝ ነው፤
ጠቃሚነት የሐብት ወይም የኢኮኖሚ ሥልጣኔ መሪ አኃዝ ነው፤ (ገፅ 63፣ 40)፡፡
እንደ እጓለ ትንታኔ፣ አንድ የተሟላለት ሥልጣኔ (የአውሮፓ ዓይነቱ (ገፅ 50-51፣ 57-58)) እነዚህ አምስቱ ዋጋዎች ሊኖሩት ያስፈልጋል፤ ያለበለዚያ ሥልጣኔው ጉድለት ወይም ህፀፅ አለው ማለት ነው (ገፅ 63)፡፡
እጓለ ይሄንን ካለ በኋላ ያሬዳዊውን ሥልጣኔ በዚህ መስፈርት ሲመዝነው ‹‹ከሞላ ጎደል ከእነዚህ የሥልጣኔ ሃብታት (ዋጋዎች) ውስጥ አብዛኛዎቹን ከያዙት ሥልጣኔዎች አንዱ የሀገራችን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ነው›› ይላል (ገፅ 63)፡፡
ሆኖም ግን፣ እጓለ ከዘረዘራቸው አምስት የሥልጣኔ ዋጋዎች ውስጥ የኢትዮጵያው ሥልጣኔ የትኛው እንደሚጎለውና የትኞቹን እንደሚያሟላ ‹‹ያሬድ ወይም ስለ ኢትዮጵያ ሥልጣኔ-I›› በሚለው ምዕራፍ ላይ በግልፅ ያስቀመጠው ነገር የለም:: ቢሆንም ግን፣ ከተጠቀሱት አምስት የሥልጣኔ ዋጋዎች ውስጥ የኢትዮጵያው ሥልጣኔ የሚጎድለው ነገር እንዳለ በግልፅ ተናግሯል፡፡ ሆኖም ግን፣ ያቺ ‹‹ጎደለች›› የተባለችው የሥልጣኔ ፍሬ (እሴት) የትኛዋ ናት?
እጓለ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ››ን እንዲፅፍ ምክንያት የሆነችው ይቺ ‹‹ጎደለች›› የተባለችው መሪ አኃዝ ነች፡፡ የእጓለ አጠቃላይ ጥረትና ድካም ይቺ ‹‹ጎደለች›› የተባለችውን እሴት በእሱ ዘመን ለነበረው ትውልድና ምሁራን ማሳየት ነው፡፡ ይሄንንም ብርቱ ፍላጎቱን ሬዲዮ፣ ጋዜጣና መፅሐፍ በመጠቀም ለማሳካት ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል፡፡
በክፍል-3 ፅሁፌ፣ እጓለ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ ውስጥ ጎድላ ተገኘች›› ያላት እሴት የትኛዋ እንደሆነች እንመለከታለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1062 times