Print this page
Sunday, 16 June 2019 00:00

የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

 - አዲስ አበባ ከጋምቤላ ቀጥሎ በኤችአይቪ ስርጭት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች
        - ባለፈው ዓመት ብቻ 13556 ሰዎች በኤችአይቪ ኤድስ ህይወታቸውን አጥተዋል
        - በአንድ ዓመት ብቻ 13488 በኤችአይቪ የተያዙ አዳዲስ ሰዎች ተመዝግበዋል
        - 610,335 ወገኖች ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ይገኛል
                       
             የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና አዲስ አበባ ከተማ በስርጭት መጠን የጋምቤላ ከተማን ተከትላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ተገለፀ፡፡
ባለፈው ዓመት ብቻ በአገራችን 13556 ሰዎች በበሽታው ህይወታቸውን ማጣታቸውም ታውቋል፡፡
የኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ከትናንት በስቲያ በብሔራዊ ቤተ መንግስት አዘጋጅቶት በነበረው 14ኛው አገር አቀፍ የኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደተገለፀው፤ የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ሄዷል፡፡
የኢትዮጵያ የስነህዝብና ጤና ቅኝት ሪፖርትን ዋቢ በማድረግ በዚሁ ስብሰባ ላይ እንደተገለፀው፤ በጋምቤላ ክልል የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭቱ በከፍተኛ መጠን ጨምሮ 4.8 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማ የስርጭቱ መጠን 3.4% በመሆን በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች:: በተመሳሳይ ሁኔታ፤ ስርጭቱ በድሬዳዋ ከተማ ላይ ጭማሪ በማሳየት 2.5% ላይ የደረሰ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
እንደ ጤና ቅኝቱ ሪፖርት፤ በከተሞች ያለው የስርጭት መጠን ሰባት እጥፍ ያህል ብልጫ አለው፡፡ ጥናቱ እንዳመለከተው፤ በሴቶች ላይ ያለው የስርጭት መጠን የወንዶቹ እጥፍ ያህል ይሆናል፡፡
የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በተካሄደው በዚሁ አገር አቀፍ ጉባዔ ላይ ይፋ እንደተደረገው፤ ባለፈው ዓመት ብቻ 13488 በኤችአይቪ አዳዲስ ሰዎች ተመዝግበዋል፡፡
በዚሁ ዓመትም 13556 የሚሆኑ ወገኖች በዚሁ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን ማጣታቸው ታውቋል፡፡
በአገራችን እስከአሁን ድረስ 610.335 ወገኖች ኤችአይቪ በደማቸው እንደሚገኝ መረጋገጡን የጠቆመው ይኸው መረጃ፤ በየዓመቱም 29ሺ የሚደርሱ ነፍሰጡሮች ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ  ጠቁሟል፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ከሚገኙ ወገኖች መካከል የፀረ ኤችአይቪ ህክምና በመውሰድ ላይ የሚገኙት 458‚480 መሆናቸውንና ህክምናውን የሚወስዱት ህፃናት፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን መረጃው አመላክቷል፡፡
“የላቀ የአመራር ትኩረት ለውጤታማና ዘላቂ የኤችአይቪ ዘርፈ ብዙ ምላሽ” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚሁ አገር አቀፍ ኮንፍረንስ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እንደተናገሩት፤ የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት መባባስ ለበሽታው የሰጠነው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡ በሽታው በተለይም ሴቶችን በእጅጉ እያጠቃ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቷ፤ ይህ አገሪቱ ለምትገኝበት የለውጥና የዕድገት ጐዳና መሰናክል የሚሆንን ችግር ሁላችንም በጋራ ተረባርበን ልናስወግደው ይገባል ብለዋል፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝና ትውልድ ያድን ብለው ህብረተሰቡን ለማስተማር ወደፊት የወጡ ወገኖች እጅግ ሊበረታቱና ሊመሰገኑም እንደሚገባ ገልፀዋል:: መንግስት ለበሽታው ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራም ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል፡፡
የበሽታው ስርጭት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገራችን ክልሎች እየጨመረ መምጣቱ ሁላችንም ሊያሳስበን የሚገባ ጉዳይ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ የጋምቤላ፣ የአፋር፣ የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንቶችና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ለጉዳዩ ለሰጡት ትኩረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በሽታውን ሁሉም አካል በጋራ ተረባርቦ ሊያስወግደው እንደሚገባም የተገለፀ ሲሆን፤ የቃልኪዳን መግባት ስነስርዓትም ተከናውኗል፡፡
ባለፈው ዓመት የወጣው አለምአቀፍ የኤችአይቪ ሪፖርት፤ በአሁኑ ወቅት በአለማችን 36.9 ሚሊዮን ሰዎች ኤችአይቪ በደማቸው እንደሚገኝ መረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡ ባለፈው ዓመት 940ሺ ሰዎች በዚሁ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን ማጣታቸውም ተገልጿል::

Read 783 times