Sunday, 16 June 2019 00:00

ኦልጐ ሪልስቴት ከደንበኞቹ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 • “በ1 አመት ውስጥ እናስረክባችኋለን የተባልነውን ቤት በ17 አመትም መረከብ አልቻልንም” - ቅሬታ አቅራቢዎች
             - “ከመጠነኛ መዘግየት በቀር ቤቶቹን አስረክቤያለሁ” ኦሎጐ ሪል ስቴት


                     በ1 ዓመት ከ6 ወር ውስጥ “አጠናቀን እናስረክባችኋለን” የተባልነውን መኖሪያ ቤት በ17 ዓመትም መረከብ አልቻልንም ሲሉ ከኦሎጐ ሪል እስቴት ጋር የቤት ግንባታ ውል የገቡ ደንበኞች ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡ ሪልስቴቱ በበኩሉ ቤቶችን ከመጠነኛ መዘግየት በቀር አስረክቤያለሁ፣ አግባብ ያልሆነ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው ብሏል፡፡
ከ40 በላይ የሚሆኑት የሪል እስቴቱ ደንበኞች አብዛኞቹ ከ90 በመቶ በላይ ለግንባታ የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ ቢከፍሉም መኖሪያ ቤታቸውን በውላቸው ላይ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ መረከብ እንዳልቻሉ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
አብዛኞቹ የሪል እስቴቱ ደንበኞች ኑሮአቸውን በውጭ አገር ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ከ3 እስከ 8 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ክፍያ ለሪል ስቴት ኩባንያው መክፈላቸውን ተናግረዋል፡፡
ለቤቶቹ ግንባታ ከሚፈለገው ገንዘብ 90 በመቶ ያህሉን ቢከፍሉም የቤቶቹ ግንባታ በተያዘው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቁን የሚጠቁሙት ደንበኞቹ፤ በዝቅተኛ የጥራት ደረጃ የተሰራውን ቤት እንኳን በውላቸው መሠረት መረከብ ሳይችሉ ለአመታት እየተጉላሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“በጠራራ ፀሐይ መንግስት ባለበት ሀገር ገንዘባችንን ተዘርፈናል” የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ የሪል ስቴቱ ባለቤቱ ካደረሱብን ኪሣራና መጉላላት በተጨማሪ ቤቶቹን ለሌላ አካል ለመሸጥ ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡
ደንበኞቹ ላቀረቡት ቅሬታ ምላሽ እንደሰጡን የጠየቅናቸው የሪል ስቴቱ ባለቤት አቶ ሊዮናርዶ ሲቦና በበኩላቸው ቤቱን ለመሸጥ ምንም አይነት ጥረት እየተደረገ አለመሆኑን ይህም ሀሰተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ደንበኞቻቸው ቅሬታ ላይ ለአዲስ አድማስ ምላሽ የሰጡት የኩባንያው ባለቤት አቶ ሊዮናርዶ 10 ዓመት ቆይቶብናል የሚለው እጅግ የተጋነነ ነው እኛ ስራ የጀመርነው በራሱ በ1997 ዓ.ም ከ13 ዓመት በፊት ነው ይላሉ፡፡
የአንዳንድ ቤቶች ርክክብ በኮንስትራክሽን መሣሪያዎች በገበየ አለመገኘት ምክንያት መዘግየቱን የሚገልፁት አቶ ሊዮናርዶ ቅሬታ አቅራቢዎች 17 አመት ዘገየብን ያሉት ግን የተጋነነ ነው በ4 ወርም ያስረከብናቸው ደንበኞች አሉን ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ድርጅቱ የተለያዩ የመንግስት እዳዎች እንደነበሩበት የጠቀሱት አቶ ሊዮናርዶ በአሁኑ ወቅት እዳዎችን ከፍለው መጨረሳቸውንና አንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለደንበኞቻቸው ካርታ እንደሚያስረክቡ አስታውቀዋል፡፡
መሠረተ ልማትን በተመለከተም ከመንግስት ጋር ተነጋግረው እያሟሉ መሆኑን እንዲሁም የቤቶች ማጠናቀቂያ ስራን ሙሉ ለሙሉ ሰርተው ማስረከባቸውን ነገር ግን የውስጥ ይዘትን ደንበኛው በፈለገው መልኩ መቀየር እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡
በ7.2 ሚሊዮን ብር ከኦሎጉሪል ስቴት ቤት መግዛታቸውንና የቤቱን 90 በመቶ ዋጋ ከ3 ዓመት በፊት አስቀድመው መክፈላቸውን ከሚገልፁት ቅሬታ አቅራቢዎች አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ማርታ አብርሃም፤ ኩባንያው ቤቱን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ለማስረከብ ቃል ገብቶ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ላለፉት ሶስት ዓመታት ቤቱን ገንብቶ አጠናቆ ሊያስረክባቸው ባለመቻሉ በራሣቸው ወጪ ቤቱን አጠናቀው በውስጡ መኖር እንደጀመሩ ተናግረዋል፡፡ ቤቶቹ መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው መሆኑንም ደንበኞች ይጠቁማሉ፡፡
በዚህ መልኩ እየተጉላሉ ከሚገኙት ከ40 በላይ የሚሆኑ የሪል ስቴቱ ደንበኞች መካከል 25 ያህሉ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመው ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የሪል ስቴቱ ባለቤት በዜግነት ኢጣሊያዊ በመሆናቸውና ትክክለኛ የመኖሪያ አድራሻ የሌላቸው በመሆኑ፣ ጉዳያችን እልባት ሳያገኝ ከሀገር እንዳይወጡ ይታገዱልን” ሲሉ አቤቱታ ማቅረባቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡


Read 820 times