Print this page
Sunday, 16 June 2019 00:00

በፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው የፖለቲካ ድርጅት የሰማዕታት ቀን ሰየመ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ባለፉት 26 ዓመታት ጠንካራ የፖለቲካ መሠረቱን በደቡብ ክልል ሃዲያ፣ ከንባታ፣ ጠንባሮ አድርጐ የቆየው በፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ባካሄደው ትግል መስዋዕትነት ለከፈሉ ደጋፊዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የመታሰቢያ ፕሮግራም አካሄደ፡፡
ግንቦት 26 ቀን 2011 ዓ.ም በሃዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ በተዘጋጀው የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ “በ1992 እና በ1997 በተከናወነው ሃገር አቀፍ ምርጫ የድርጅታቸው ደጋፊ ሆነው የህይወት ዋጋ እና የአካል ጉዳት መስዋዕትነት የከፈሉ ሁሉ የትግላችን ሰማዕታት ናቸው ክብራቸውም ሁሌ ሲዘከር ይኖራል” ብለዋል፡፡
በፓርቲው ተመዝግበው የሚታወቁ በትግሉ ህይወታቸውን ያጡ እና ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 53 የትግሉ ተሳታፊዎች እንዳሉ ለአዲስ አድማስ ያብራሩት የፓርቲው ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሉምባ ደምሴ ግንቦት 6 ቀንም በየአመቱ የመታሰቢያቸው ቀን ሆኖ ተሰይሟል ብለዋል፡፡
በእለቱ በተከናወነው መርሃ ግብር ላይም መስዋዕትነት የከፈሉ ደጋፊዎች ዝርዝራቸው ተገልፆ እናንተ የትግላችን ሰማዕታት ናችሁ የሚል እውቅና እና ከብር መሰጠቱንም አቶ ሉምባ አስረድተዋል፡፡
የ1992 ምርጫን ተከትሎ አዲስ ተመራጮች ፓርላማ በገቡበትና የቀድሞ የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ምርጫው ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ የሃዲያ፣ ከንባታ፣ ጠንባሮ ተወላጆች የህሊና ፀሎት ተደርጐ እንደነበርም አቶ ሉምባ አስታውሰዋል፡፡
ፓርቲው ለመጀመሪያ ጊዜ ሰማዕታቱን በከፍተኛ ስነስርዓት የዘከረውና የመታሰቢያ ቀን የሰየመላቸው አሁን አንፃራዊ የፖለቲካ ለውጥ በመምጣቱ መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

Read 5109 times