Sunday, 16 June 2019 00:00

የእርቅና ብሔራዊ መግባባት መድረክ ለማዘጋጀት ለቀረበው ጥያቄ መንግስት ምላሽ አልሰጠም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ህውሓትን ጨምሮ 89 ፓርቲዎች የመድረኩን መዘጋጀት ደግፈዋል

                  ህውሓትን ጨምሮ 89 ያህል የፖለቲካ ድርጅቶች የደገፉትን የብሔራዊ መግባባት እና እርቅ ጉባኤ ለማካሄድ የመንግስት በጎ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን አዘጋጅ ኮሚቴው አስታወቀ፡፡
በብሔራዊ መግባባት እና እርቅ ጉዳይ በራስ ሆቴል ለሁለት ጊዜያት ያህል ከ60 በላይ የሚሆኑ ፓርቲዎች እርቅና መግባባት እንዴት ይካሄድ? በሚለው ላይ መምከራቸውን ለአዲስ አድማስ ያስረዱት የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ስለሺ ሶስት አጀንዳዎች መመረጣቸውን አስታውቀዋል፡፡
ብሔራዊ እርቅ እና ሃገራዊ መግባባት እንዴት ይፈጠር፣ የለውጥ ሂደቱ በማንና እንዴት እየተመራ ነው? እንዲሁም ህገ መንግስቱ እንዴት ይሻሻል? የሚሉት አጀንዳዎች የብሔራዊ መግባባትና እርቅ መድረኩ ትኩረቶች እንዲሆኑ በፓርቲዎች ስምምነት ተደርሶበታል ብለዋል - አቶ ስለሺ፡፡
በዚህ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ጉባኤ አስፈላጊነቱን አምኖ ለመሳተፍ ፊርማቸውን ካኖሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ህውሓት፣ ደኢህዴንና ኦነግ ተጠቃሽ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን መንግስት ለጉባኤው ድጋፍ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ቢጠየቅም እስካሁን ምላሽ እንዳልተገኘ አቶ ስለሺ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ኮሚቴው ለዘጠኙ የክልል መንግስታት እና ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ብሔራዊ መግባባትና እርቅ መድረክን እንዲደግፉ እና እንዲሳተፉ መጠየቁንና ምላሻቸው እየተጠበቀ መሆኑን አቶ ስላሺ አስረድተዋል፡፡
መንግስት በጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ሂደቱን እንዲደግፍ ጥሪ ያቀረቡት አዘጋጆቹ መንግስት ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ በሰላማዊ ሰልፍ ለመጠየቅ እንገደዳለን ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በዋናነት ንግግር እንዲያደርጉ ጠ/ሚኒስትሩ መመረጣቸውን የገለፁት አቶ ስለሺ ጉባኤውን ለማስኬድ የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የመንግስታቸውን በጎ ምላሽ እየተጠባበቅን ነው ብለዋል፡፡

Read 5604 times