Sunday, 16 June 2019 00:00

የቀዳማዊት እመቤት ፕሮጀክቶች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

20 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችን በ4 መቶ ሚሊዮን ብር እያስገነቡ ነው

            መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የአገሪቱ  ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ቀዳማዊት እመቤት ሆነው ታላቁ ቤተ መንግስት የገቡት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው፤ በበጐ ተግባራት ሥራ እረፍት አልባ ህይወት እየመሩ ነው ተብሏል፡፡
ቀዳማዊት እመቤቷ ከቀድሞው ቀዳማዊ እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ የተረከቡትን ጽ/ቤት በማደስ ስራቸውን እንደጀመሩ የገለፁት ምንጮች፤ በወ/ሮ ሮማን የተጀመረውን የዝቅተኛ ቤተሰብ ተማሪ ልጆችን የመመገብ በጐ ተግባር ከማስቀጠል ጐን ለጐን፤ ሙሉ ጊዜያቸውን ለአዳዲስ የበጐ አድራጐት ተግባራት እያዋሉ ይገኛሉ፡፡
ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው በዋናነት ት/ቤቶችን የማስገንባትና ሆስፒታሎችን የመደገፍ እንዲሁም የበጐ አድራጐት ተቋማትን የማጠናከር ተግባራት ላይ አተኩረው እየሰሩ ነው ተብሏል፡፡
 “ለዜጐች ጥራት ያለው ትምህርት፣ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ማድረግ፣ የሃገሪቱን የወደፊት ትውልድ ለማነጽና ለማዘጋጀት ሊፈፀም የሚገባ ቁልፍ ተግባር ነው” የሚሉት ቀዳማዊት እመቤቷ በተለይ በገጠር የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ ትኩረት መደረግ አለበት የሚል እምነት አላቸው፡፡
ይህን እምነታቸውን በተግባር ለማሳየትም የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤትን በተረከቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች 20 የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ግንባታ ተጀምሯል:: በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ክልል ግንባታው ቀደም ብሎ የተጀመረ ሲሆን በቅርቡም በቤኒሻንጉልና በጋምቤላ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡
በግንባታ ሂደት ላይ ከሚገኙ ት/ቤቶች መካከል የደሴ ጦሳ ፈላና ዞን የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የጐንደር ከተማ ሎዛ ማርያም ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ሊበን ጩቃላ ወረዳ ት/ቤቶች ሲሆኑ በአሁን ወቅት ከ40 እስከ 50 በመቶ የግንባታ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
አብዛኞቹን ት/ቤቶች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የታቀደ ሲሆን፤ የእያንዳንዱ ት/ቤት የግንባታ ዋጋም 20 ሚሊዮን ብር፤ በአጠቃላይ የ20ዎቹ ት/ቤቶች የግንባታ ወጪ 4 መቶ ሚሊዮን ብር ይፈጃል ተብሏል፡፡
አብዛኞቹ ት/ቤቶች በአካባቢው መጠሪያ የተሰየሙ ሲሆን በጋምቤላ ክልል የሚገነባውና ግንቦት 1 ቀን 2ዐ11 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት ት/ቤት ግን “የወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው የ2ኛ ደረጃ ት/ቤት” ተብሎ እንዲጠራ ክልሉ መወሰኑ ታውቋል፡፡
ቀዳሚ እመቤቷ እነዚህን ተግባራት እያከናወኑ ያሉት ከአንዲት በጐ አድራጊ የውጭ ሀገር ዜጋ በተገኘ 1 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ነውም ተብሏል፡፡
ቀዳማዊት እመቤቷ የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶችን በማስገንባት ብቻ አልተወሰኑም፡፡ በአዲስ አበባ የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ግንባታም ጀምረዋል::
ይህ ህፃናት ማሳደጊያ በአዲስ አበባ ቁስቋም ይገኛል፡፡ የካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠ ሲሆን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡
ት/ቤቶችን ከማስገንባት ጐን ለጐን፤ ቀዳማዊ እመቤቷ በአንድ አመት ቆይታቸው በርካታ የበጐ አድራጐት ተግባራትንም አከናውነዋል፡፡
በአዲስ አበባ አልፋ መስማት የተሣናቸው ት/ቤት፣ የቀጨኔ ህፃናት ማሳደጊያን የአማኑኤል የአዕምሮ ህሙማን ሆስፒታል፣ የካትሪን ሃምሊን የፌስቱላ ህክምና ማዕከል፣ መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን ማዕከላት ቀዳማዊ እመቤቷ ከጐበኟቸውና የተለያየ ድጋፍ ካደረጉላቸው ተቋማት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የቀድሞዋ ቀዳማዊ እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ የጀመሩትን የት/ቤት ተማሪዎችን የመመገብ ፕሮጀክትንም እየተከታተሉ መሆኑን ከቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የዘመን መለወጫ በአልን ምክንያት በማድረግ መስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተ መንግስት ከተለያዩ የህፃናት ማሳደጊያዎች ለተውጣጡ 400 ህፃናት የምሣ ግብዣ አድርገው የአብሮነት ጊዜ ማሳለፋቸውም ይታወሳል፡፡
ቀዳማዊት እመቤቷ ለሆስፒታሎች የቁሳቁሶች ድጋፍ የሚያደርግ ፕሮጀክትም አላቸው፡፡ ከተለያዩ የውጭ ለጋሽ ተቋማት የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ በስጦታ የሚያበረክቱ ሲሆን፤ እስካሁን ለጐንደር ሆስፒታል፣ በደቡብ ክልል ለሚገኘው ሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና ለአማኑኤል ሆስፒታል ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ለሆስፒታሎቹ ከተለገሱ ቁሳቁሶች መካከል የህፃናት አልጋ፣ የደም ማስቀመጫ ፍሪጅ፣ ICU አልጋ፣ የላብራቶሪ ማሽኖች ወዘተ የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በአጠቃላይም 5 ሚሊዮን 630ሺህ ብር ግምት አላቸው ተብሏል፡፡
በቀጣይ ከኢየሩሣሌም የልማት ድርጅት ጋር በመሆንም በባህርዳር ከተማና አጐራባች ከተሞች የሚገኙ ሴተኛ አዳሪዎችን መልሶ የማቋቋምና አቅምን የመገንባት ስራ ላይ አተኩረው ለመስራት እቅድም ይዘዋል - ቀዳማዊት እመቤቷ፡፡
ለበጐ አድራጐት ተግባራት የሚውል የገንዘብ ምንጭን ለማሳደግም ከቢልጌት ፋውንዴሽን ጋር የነበረው የድጋፍ ውል መታደሱም ተገልጿል፡፡
ቀዳማዊት እመቤቷ ከበርካታ አካላት የአብረን እንስራ የሚል ጥያቄ እየቀረበላቸው መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ከእስራኤል ኤምባሲ፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢትዮጵያ ሣይካትሪ ማህበር፣ ከኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር እና ከኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር አብሮ የመስራት ስምምነቶችን እንደተፈራረሙ አመልክተዋል፡፡    


Read 6056 times