Sunday, 16 June 2019 00:00

የጀግናው ርዕሰ መምህር ገድል!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)


                      “በህዝብ መወደድን የመሰለ ፀጋ የለም”
                         
               በብዙ ታዋቂና ታላላቅ ሰዎች ልብ ውስጥ እንደ መዝሙር የሚዘመሩ .. እንደ ችቦ በፍቅር የሚንበለበሉ…የተወደዱ መምህራን አሉ፡፡ በሬድዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅነት ስራዬ፤ ከታላላቅ ሰዎች ጀርባ ድንቅ መምህራን እንዳሉ ተገንዝቤአለሁ፡፡…ዛሬ በጥበቡ አደባባይ የደመቀ፣ በሞያው አንቱ የተሰኘ የጥበብ ሰው፤ የጥንት መምህሩን ሲያገኛት፣ ዝቅ ብሎ ጉልበትዋን እንደሚስም አውግቶኛል፡፡
የዛሬ እንግዳዬ ጋሽ በቀለ አየለ፤ በተማሪዎቹ ልብ ውስጥ በአድናቆትና በክብር ዘውድ የደፋ መምህር ነው፡፡ ለብዙ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን  መፈጠር ድንቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ጋሽ በቀለ አንድ ጊዜ፤ ተማሪው ከነበሩ የቀድሞ የናይጀሪያና የሴኔጋል አምባሳደር፣ ክቡር አቶ ደምረው ዓለሙ ጋር በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ ነበር፡፡ የአምባሳደሩ ምስክርነትና አክብሮትም፣ በብዙዎች ልብ ግርምት ፈጥሮ እንደነበር አይረሳኝም፡፡ … በዚህ ድንቅ መምህር ጥረትና ትጋት፤ በርካታ አምባሳደሮች፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ስፔሻሊስት ዶክተሮች፣ ጋዜጠኞች፣…ወዘተ  ተፈጥረዋል፡፡
ለመሆኑ ጋሽ በቀለ፤  ምን ሰርቶ ነው ትውልድ ያጨበጨበለት!? ጋሽ በቀለን ለከፍተኛ ውጤት ያበቃው ስትራቴጂና ስልት ምን ነበር!?
ርዕሰ መምህር በነበርኩበት ወቅት ትምህርት ቤቱ፣ ተማሪዎችን በማትሪክ ፈተና፣ ለጥሩ ውጤት ለማብቃት የማይፈነቀል ድንጋይ  አልነበረም፡፡ ለምሳሌ ከተለያዩ ቦታዎች በርካታ ሞዴል ፈተናዎች ሰብስቦ በማምጣት፣ ተማሪዎች ደጋግመው እንዲሰሩና እንዲያጠኑ ያደርጋል፤ የማትሪክ ፈተናዎችን በመከለስና ጥያቄዎችን በመስራት፣ በሌሎች ትምህርት ቤቶች የተሰጡ ሞዴል ፈተናዎችን ከየቦታው አምጥቶ  በመፈተን፣ ጎበዝ ተማሪዎች ያላቸውን እውቀት ሳይደብቁ  እንዲያካፍሉ በማግባባት፣ እርስ በርስ እንዲተጋገዙ ያበረታታም  ነበር።
ሁሉም መምህራን፤ በራሳቸው የትምህርት ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን ከመደበኛ ስራቸው በተጨማሪ በትርፍ ሰዓት ሁሉ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ተማሪዎች ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች በሚገባ አጠናቅቀው፣ ለማትሪክ ዝግጅት የሚያግዙዋቸው ክለሳዎችና ተጨማሪ ጥናቶችን እንዲያደርጉ ተመቻችቶላቸው ነበር፡፡ ለዚህ የመምህራን ጥረት ደግሞ ሞራል መጠበቂያ እንዲሆንና የመምህራን ጊዜ እንዳይባክን ለማገዝ፣ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለጥቂቶቹ መኖሪያ ቤት በመስጠት፣ ጥሩ የሥራ ተነሳሽነት መፍጠር ተችሎ ነበር፡፡ በት/ቤቱ ግቢ ውስጥ ካፍቴሪያ ተከፍቶ፣ መምህራን በወር ከ100 ብር የማይበልጥ ገንዘብ እየከፈሉ  ምሳና እራታቸውን እዚያው እንዲመገቡ ማድረግ፣ እንደ ጥሩ ስልት ተወስዶ ውጤት አምጥቷል፡፡
በትምህርት ቤቱ የትምህርት ይዞታውን በተሻለ ሁኔታ ለማጎልበትና ለውጥ ለማምጣት የተደረገው ሌላው ነገር፤ ለተማሪዎች የተመቻቸ የትምህርት ከባቢ መፍጠር ነበር፡፡ለዚህ መሳካት ደግሞ በቂ የትምህርት መጻህፍት፣ የተመቻቸና የተሟላ ቤተ-መጻሕፍት፣ ላቦራቶሪ፣ ወርክሾፕ ወዘተ እንዲኖር ማድረግ፣ የግድ ነበር።
ትምህርት ቤቱ በዚህ ጥረቱ  ከብሪቲሽ ካውንስልና ከሌሎች እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች፤ የመጻህፍት ሽልማት አግኝቷል፡፡ በየጊዜው ባስመዘገባቸው ከፍተኛ ውጤቶችም፣ ከትምህርት ሚኒስቴር ባገኘው ሽልማት፣ በቂ የላብራቶሪ ቁሳቁሶችን አሟልቷል፡፡ በጊዜው በክፍለ ሀገሩ የትም ሁለተኛ ደረጃ የሌለና ለሁሉም መምህራን በየትምህርት ዘርፉ አገልግሎት የሚውሉ ወደ 13 ያህል  የመምህራን የዝግጅት ክፍል በማሰራት፣ በትምህርት ቤቱ ለውጥ ለማምጣት ረድቷል።
ትምህርት ቤቱ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ የፋይናንስና የቁሳቁስ ችግሮች ሲገጥሙት በራሱ ሰዎች መፍትሄዎችን እያመጣ በስኬት ግስግሶ ነበረ፡፡ ጋሽ በቀለ እንዲህ ይቀጥላል፤
የዲፓርትመንት ክፍሎችን ለማሰራት ትምህርት ቤቱ በቂ ገንዘብ ስላልነበረው፣ አንድ መላ ዘየድን፡፡ ስኳር እንደ ወርቅ የሚቆጠርበት ጊዜ ስለነበር  የቀበሌ ኅብረት ሱቆችን የስኳር እርዳታ በመጠየቅ፣ 60 ኩንታል ስኳር ማግኘት ቻልን:: ስኳሩን በነደደ ዋጋ ሸጠን፣ ያለንን ጨማምረን፣ የቀሩት ክፍሎች ተሰሩ፡፡ የክፍሎቹ መሰራት ለመምህራን የትምህርት ዝግጅት ምን ያህል እንደጠቀማቸው በቃላት መግለጽ ያዳግታል፡፡
ያኔ የቡታጅራ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ በእረፍት ጊዜያቸው እንኳ እንዳይቦዝኑ  ለማድረግ፣ በውጭው የክፍል ግድግዳዎች ላይ ለማስተማሪያ የሚሆኑ የተለያዩ ትምህርት ክፍሎችን የሚያግዙ ስዕሎችም ማሳል ጀምረን ነበር፤ የኛን ትምህርት ቤት አርአያነት በመውሰድም፣ ሁኔታው ወደ ሁሉም ክፍለ ሀገር ተዛመተ፡፡
 በግሌ ጎበዝ ተማሪዎችን በጣም እወዳለሁ፤ የተለየም  ትኩረት ነበረኝ። ጎበዝ ተማሪ ሆነው በተለይ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርት ለማቋረጥ የሚገደዱ ሲኖሩ፣ መምህራንን አስተባብሬ ገንዘብ በማዋጣትና የሽሮ ቤት ኮንትራት በመክፈል፣ እዚያ እየተመገቡ፣ያለ ሃሳብ ትምህርታቸውን እንዲያጠኑና እንዳያቋርጡ ያደረግንባቸው ብዙ ጊዜያት ነበሩ። ለተረጂዎቹ ተማሪዎች ስነልቡናዊ ጥንቃቄ ሲባል፣ እርዳታው የሚደረገው በጥብቅ ምስጢር  ነበር፡፡
ሌላው ጐበዝ ተማሪዎችን የምናበረታታት መንገድ፤ የተማሪዎችን ፎቶግራፍ በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ በመለጠፍ ነበር። ይህ ደግሞ በተማሪዎች መካከል ለሚፈጠር ጤናማ ውድድር እጅግ ጠቃሚ አስተዋዕኦ አበርክቷል:: ወደ ኋላ በልምድ ባመጣነው ፈጠራ ደግሞ ተማሪዎች ፈተና በሚቀመጡበት ወቅት አቀማመጣቸውን ቀደም ሲል ባመጡት የክፍል ደረጃ ውጤት  መሰረት እንዲሆን አድርገን ነበር። ለምሳሌ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ የወጡ  (የደረጃ ) ተማሪዎች፤ በአንድ ክፍል ውስጥ መፈተን ተለምዶ ነበር:: በተግባር እንደታየው እነዚህ ተማሪዎች ጨርሶ አይኮራረጁም፤ ይልቁንም፤ ሁሉም ደረጃቸውን ለማሻሻልና ያላቸውን ነጥብ ለማስጠበቅ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡
በተጨማሪም ጎበዝ ተማሪዎች ያላቸውን እውቀት ሳይደብቁ ለሌሎች እንዲያካፍሉ በማግባባት እንዲረዳዱና ምን ጊዜም እንዳይዘናጉ፣ ሁሌ ዝግጁ እንዲሆኑ የአእምሮ ማንቃት ሥራ እንሠራ  ነበር፡፡
የቋንቋን ብቃት ለማሳደግም ተማሪዎች እንግሊዝኛ መጻፍና መናገር እንዲችሉ የትምህርት ቤታችን አስተማሪዎች  በተለይ ደበበ ታፈሰና ደቦጭ ብራቱ የተባሉ ታታሪ መምህራን፣ በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ተማሪዎች ልምምድ እንዲያደርጉ፣ አጫጭር ድራማዎችን እንዲሰሩ፣ ክፍልም ውስጥ ያልገባቸውን ነገር በእንግሊዝኛ እንዲጠይቁ ያበረታቱና ያግዟቸው  ነበር፡፡
ይህ ጥረት የት አደረሳቸው?...ምንስ ፈየደ? ጋሽ በቀለ እንዲህ ይላል፡-
በትምህርት ቤታችን በርካታ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ያገኛሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ከ75% በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች፤ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ሁለትና ከዚያ በላይ ያገኙ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ጥሩ ውጤት አግኝተው ሳለ፣ ዩኒቨርሲቲ ሳይገቡ የሚቀሩት  በቦታ እጥረት ነበር፡፡ እንዳሁኑ ቢሆን ምን ያህል ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆኑ እንደነበረ መገመት ይቻላል:: ከዚህም ሌላ ትምህርት ቤታችን ጎበዝ ሆነው ውጤት ያልመጣላቸው ተማሪዎች፤ በቀጣዩ ዓመት በግል ተፈትነው ውጤታማ እንዲሆኑ ብዙ ሠርቷል፡፡ ለምሳሌ ቤተ መጽሐፍት እንዲጠቀሙ፤ አንዳንዴም ክፍል እየገቡ ክለሳ እንዲወስዱ  በማድረግ፣ ከመደበኛ ተማሪዎች ያላነሰ ድጋፍ ይሰጣቸው  ነበረ፡፡ ሌሎች ጥቂት ተማሪዎች ደግሞ ለማትሪክ የበለጠ ለመዘጋጀት ሲሉ 11ኛ ክፍል የመጨረሻ ፈተና በመፈተንና ተመልሰው በመግባት ለጥሩ ውጤት ይበቁ ነበር:: በዚህ ዓይነት ዳግም አሻሽለው ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች ቁጥር እጅግ ብዙ ነው፡፡ በዚህ ዕድል ተጠቅመው  ህክምና  ለማጥናት ዩኒቨርሲቲ  የገቡ ተማሪዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡
በዚህ ስራው ትምህርት ሚኒስትርና ሌሎች ተቋማት ምን ማበረታቻ ሰጡ?
ባለ ውጤት ሆኖ ለመገኘት ባደረኩት ጥረት የወጠንኳቸው እቅዶች ሁሉ ተሳክተውልኝ ትምህርት ቤቱ በቀድሞ ሸዋ ክፍለ ሀገር እንደ ሞዴል ተቆጥሮ፣ በየስብሰባው ወቅት የሁሉም ትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን በተገኙበት፣ የትምህርት ቤቱ ስራና ውጤት ሲነገርና እኔ መድረክ ላይ ወጥቼ ልምዴን ሳካፍል፣ የሚሰማኝን ኩራትና እርካታ ልነግርህ አልችልም።  ቡታጅራ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ በስራ ውጤት የነገሰበት፣ የብዙዎችን ቀልብ የሳበበት፣ ጥሩ የስራ ባህል የዳበረበት ወርቃማ ዘመን ነበር።
በትምህርት ቤታችን ትጋትና ውጤት በተፈጠረው ለውጥ፤ ትምህርት ለመቅሰም በርካታ የትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራንና አስተማሪዎች ጎብኝተውናል፡፡ ልምድ ቀስመዋል:: ትምህርት ቤቱ በነበረው ጠቅላላ እንቅስቃሴና ውጤታማነት በመማረክ፣ ሌሎች ትምህርት ቤቶች  ያስተምሩ የነበሩ መምህራን፤ በዝውውር ወደ ትምህርት ቤታችን ለመምጣት በጣም ይጓጉና ይጠይቁ ነበር፤ ተሳክቶላቸው ከእኛ ጋር የውጤቱ ተቋዳሽ የሆኑም ነበሩ፡፡
በውጤትም ረገድ ትምህርት ሚኒስቴር በጊዜው ያወጣውን ዕቅድ ለመተግበር በተደረገ የሰባት ተከታታይ ዓመታት የሽልማት ዘመን፤ አምስቱን ዘመን የቡታጅራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሸልሞበታል። አንድ የትምህርት ቤቱ መምህር በክፍለ ሀገሩ ብቸኛ፣ ከብሔራዊ ጀግና ተሸላሚዎች አንዱ ሆኖ ልዩ ሽልማትና የወርቅ ሜዳሊያ ሲሸለም፣ አንዲት መምህርትና እኔ፤ የብሄራዊ ወርቅ ተሸላሚ ሆነናል። ሁለት ጊዜ በክፍለ ሀገር ደረጃ፣ ሁለት ጊዜ በአውራጃ ደረጃ፣ ትምህርት ቤቱም እኔም ተሸላሚ ነበርን።
ዘመን አልፎ፣ ከዓመታት በኋላ ተማሪዎቹ፣ ጋሽ በቀለን በምን አስታወሱት?...የዘራውን አጨደ ወይስ ከንቱ ሆነ!...አሜሪካ  በሄደ ጊዜ ያገኛቸውን ተማሪዎቹን ሁሌም አይዘነጋም፡፡ ጋሽ በቀለ ይቀጥላል፡-
 አሜሪካ  በሄድኩበት ወቅት እዚያ ነዋሪ ከሆኑ የቀድሞ ተማሪዎቼ፤ ከ40 ሺ ብር በላይ የሚገመቱ  ሽልማቶችን ተሸልሜያለሁ፡፡ አፕል ሞባይል፤ መጽሐፍት፤ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶች::  ከፍቅራቸው ባሻገር  በእነርሱ እገዛ ወደ ሰባት የሚሆኑ የአሜሪካ ግዛቶችን ጎብኝቻለሁ:: የጊዜ እጥረት ስለነበረብኝ እንጂ በየግዛቱ  የግብዣ ጥሪ ያደረጉልኝ በርካታ ተማሪዎቼ ነበሩ:: ከየአቅጣጫው የነበረውን የስልክ ጥሪ ተወዉ! ብዙዎቹ  በየቤታቸው ድል ባለ ድግስ ጋብዘውኛል፡፡
…ወልዶ መርካት እንዲህ ነው!...ጋሽ በቀለ እዚህም ያሉ ተማሪዎቹ፣ ተመሳሳይ ሽልማት ሸልመውታል፡፡ ለሽልማት የተፈጠረ ያገር ልጅ ነው፡፡ ስራ ውጤት እንደሚያስገኝም በተደጋጋሚ ያሳየ ጀግና ነው፡፡
መኖሪያቸው ቡታጅራ ከተማና አዲስ አበባ የሆኑ የቀድሞ ተማሪዎቼ ደግሞ ባላሰብኩት ወቅት ድንገት መኖሪያ ቤቴ ተገኝተው በወቅቱ አባባል surprise አደረጉኝ፡፡ ደነገጥኩና በደስታ ብዛት ማመስገን አቃተኝ፡፡  ሽልማቱ 80ሺ ብር ነበር፡፡ እንደዚሁ አንድ ተማሪዬ ከደቡብ አፍሪካ 50ሺ ብር ሸልማኛለች፡፡ እኒህ ሸላሚዎቼ እኮ በጉርምስና አፍላ ዕድሜያቸው፣ በቁጥጥርና ክትትል አላፈናፍን ብዬ ወጥሬ የያዝኳቸው ነበሩ:: ያኔም ያንን የጉርምስና ዘመን ክትትሌን በአካልና በአእምሮ፣ ሲያድጉና ሲበስሉ፤ ለራሳቸው ሲባል እንደተደረገ ይደርሱበታል የሚል ግምት ነበረኝ፤ ዛሬ በተግባር  ያሰብኩት ሆነ፡፡ በኋላ ላይ በሥራ አጋጣሚ ወርቅቾ፣ ሽመክት፣ ማሩ --- የሚባሉ ተማሪዎቼ፤ በአንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ የበላይ አለቆቼ ነበሩ፡፡ ወርቅቾ የሚባለው ተማሪዬ፤ 12ኛ ክፍል ሳለ የቀጣሁትን እያነሳ፣ ብዙ ጊዜ  ያስቀኝ ነበር፡፡ ይሁንና ዛሬ ተማሪዎቼን ሳስባቸው በጣም እኮራባቸዋለሁ፤ እንደ ጓደኛ፣ እንደ ወንድም ነው የማያቸው፡፡ ሁሉም ‹‹ጋሽ በቀለ›› አንተ ብለው እንደ ወላጅ አባታቸው ሲጠሩኝና ሲያከብሩኝ ያስደስተኛል፡፡
አሁንስ መምህርነት ለጋሽ በቀለ ምንድነው?...ከተማሪዎቹስ ጋር እንዴት ነው?
… አንዳንዶቹ አሁን የቤተሰብ ኃላፊ፣ የልጆች አባት ሆነው እንኳን ቡና ቤት ድንገት ካጋጠሙኝ የሚጠጡትን ቢራ እስከመደበቅ ይደርሳሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው አንድም ለእኔ ያላቸውን ከበሬታ፣ በሌላም በኩል ያ የድሮው አያያዜ በአእምሮዋቸው ተቀርጾ ይመስለኛል፡፡ ተማሪ እያሉ  አልባሌ ቦታ ድንገት ካየኋቸው  በጣም ይፈሩ ነበር ፡፡
  መምህርነት ሰውን በእውቀት፣ በክህሎት፣ በአስተሳሰብ መቅረጽና መገንባት ነው፡፡ መምህርነት ሁል ጊዜ ዝግጁ፣ ጥንቁቅ እንድትሆን ያደርግሀል። ራሱ ፈተና ነው፡፡ በሰዎች አእምሮ ላይ ተቀርጾ የሚቀር እውቀት ለማስጨበጥ ከፍተኛ ጥንቃቄና ችሎታም ይጠይቃል። ካበላሸህ ወይም ካሳሳትክ የማይድን የአእምሮ ቁስለት ነው:: አሁን ሳሰላው ጠቅላላ አገልግሎቴ ሰላሳ ሶስት አመት ከአምስት ወራት ሲሆን በመምህርነት፣ በርእሰ መምህርነትና በወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊነት ሰርቻለሁ።
በስራ ዘመኔ በመምህርነት ያሳለፍኩት ጊዜ አሁንም በትዝታ ወደ ኋላ እየመለሰኝ ነው። በቀድሞ ተማሪዎቼና በህብረተሰቡ ዘንድ የሚሰጠኝ ክብር እንዳለ ነው። አንድ በሹመት ላይ ያለ ሰው፤ በሹመቱ ወቅት የሚሰጠው ክብር ሲሻር አብሮ ይሻራል። እኔ ግን አሁንም የቀድሞው ክብሬ እንዳለ ነው። እውነት ለመናገር በህዝብ መወደድን የመሰለ ፀጋ የለም።
ዕድለኛ ሆኜ ዛሬ ተማሪዎቼን በያጋጣሚው ሳገኛቸው፣ እንደ ጓደኛ አጫውታቸዋለሁ። ሳያቸው የዚያን ጊዜው እንቅስቃሴ ፊት ድቅን ይላል። በርግጥም በስራዬና ክትትሌ ተማሪውም ወላጅም በአጠቃላይ ህብረተሰቡ ይመርቀኝ ነበር። “የማታ እንጀራ ይስጥህ” የሚለው ምርቃት ይኸው ጡረታ ከወጣሁ በኋላ ለጥሩ ስራ አብቅቶኛል፤ ከ16 አመት በላይ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እያገለገልኩ ነው።  በስራ አለም በአጠቃላይ 50 አመት ልደፍን ነው። አሁንም ግን የስራ ሞራሌ ንክች አላለም፡፡

Read 3143 times